በቁርአንና በሙስሊሞች ዘንድ ችግር የፈጠረ እውነታ! ጉንዳኖች ይናገራሉን?

አዘጋጁ

የሙስሊሞች መጽሐፍ ቁርአን በምዕራፍ 27 ላይ ጉንዳኖች እንደተናገሩ ንግግራቸውንም የአይሁዱ ንጉስ ንጉሱ ሰሎሞን ሰምቶት እንደነበረ ያቀርባል፡፡ ቃሉም ከቁርአን ላይ ቃል በቃል እንደሚከተለው፡ “በጉንዳንም ሸለቆ በመጡ ጊዜ አንዲት ጉንዳን እላንተ ጉንዳኖች ሆይ! ወደ መኖሪያዎቻችሁ ግቡ ሱለይማንና ሰራዊቱ እነርሱ የማያውቁ ሲኾኑ አይሰባብሩዋችሁ አለች፡፡ ከንግግርዋም እየሳቀ ጥርሱን ፈገግ አደረገ ጌታዬ ሆይ! ያቺን በኔና በወላጆቼ ላይ የለገስካትን ጸጋህን እንዳመሰግን የምትወደውንም በጎ ሥራ እንድሠራ ምራኝ በችሮታህም በመልካሞቹ ባሮችህ ውስጥ አግባኝ አለ፡፡” 27.18-19 ይላል፡፡ በምዕራፉ ላይ ቁጥር 16 ሰለሞን፤ ማለትም በቁርአን ሱለይማን የበራሪ ወፎችን ቋንቋ እንደተማረ፣ ከቁጥር 20 ጀምሮ ደግሞ ከወፍ ጋር፤ በተለይም “ሁድሁድ” ከሚባል የወፍ ዝርያ ጋር እንደተነጋገረ ያቀርባል፡፡
 
በዚህ በቁርአን 27 ላይ ከሱለይማን (ከሰለሞን) ጋር በተያያዘ መልኩ የሰፈሩት ነገሮች በሙሉ አስገራሚ ብቻ ሳይሆኑ ቁርአንን በከፍተኛ ጥያቄ ውስጥ የሚጥሉት ናቸው፡፡ ከነዚህም ውስጥ የሰለሞን ሰራዊቶች ሰዎች፣ ጋኔኖች እና በራሪ ወፎች የነበሩ መሆናቸው ናቸው፡፡ ሰለሞን ከሦስቱም ጋር ንግግርን አድርጓል ከጉንዳን ጋር በቁጥር 18-19፣ ከወፉ ጋር ከቁጥር 20 ጀምሮ ከጋኔኖች ጋር ደግሞ በቁጥር 30 ላይ ናቸው፡፡ ስለእነዚህ ሦስቱም ነገሮች በአሁኑ ጽሑፍ ላይ ማቅረብ ሀኔታው አይፈቅድልንም ስለዚህም የጉንዳኖቹን ብቻ እንመለከታለን፡፡

የጆኬን ካዝ ጽሑፍ

ጆኬን ካዝ ጉንዳኖች ሊናገሩ አይችሉም በሚል ርዕስ ያቀረበው አጭር ጽሑፍ በሙስሊሞች ዘንድ ትልቅ ድንጋጤን አስከትሎ ብዙ የሙስሊም ሊቃውንት ምላሾችን ለመስጠት ሙከራዎችን አድርገዋል፡፡ ከነዚህም ውስጥ Randy Desmond, Moiz Amjad, Amer Yousafzai, Shibli Zaman ይገኙበታል፡፡

የጆኬን ካዝ ምልከታ እንደሚከተለው ነበር፡ “በቁርአን 27.18-19 ላይ ጉንዳኖች ተናገሩ ተብሏል፤ ነገር ግን  ንጉሱ ሰለሞን ከጉንዳኖች ምንም የሰማው ነገር አልነበረውም ምክንያቱም ጉንዳኖች አይናገሩምና፡፡” ጆኬን በመቀጠል ያቀረበው “ከዚህም በተጨማሪ መታወቅ የሚኖርበት ነገር ጉንዳኖች ተናግረው ነበር በማለት ቁርአን እንዳስቀመጠው ብናስብ እንኳን እንዲህ ዓይነትና ለአንድ ፍጡር ብቻ ማለትም ለሰው በተሰጠው የመናገር ችሎታ ጉንዳኖች ተጠቀሙ ብለን ብንል ቁርአንን የምናደርገው ከሳይንሳዊ መጽሐፍ ይልቅ የልብ ወለድ ተረትን የሚናገር መጽሐፍ ነው፡፡”

በመቀጠልም “ነገር ግን በሳይንስ የተረጋገጠው እና አሁንም እየተጠና እና እየተገኘ ያለው ነገር ጉንዳኖች ግንኙነት የሚያደርጉት ወይንም መረጃዎችን እርስ በእርሳቸው የሚለዋወጡት በኬሚካላዊ ምልክት አሰጣጥ ብቻ ነው፣ ይሁን እንጂ አንዳንድ የጉንዳን ዝርያዎች የተወሰነ የድምፅ ምልክት አሰጣጥን ያደርጋሉ፡፡ ነገር ግን የሚያወጡት ድምፅ ምን ያህል ረቂቅነትና ትርጉም ያለው ነው?” የሚለው ሊመለስ የሚገባው ነው በማለት አስቀምጧል፡፡

እንደ እውነቱ ከሆነ  Amazing Facts About Ants የሚለውን ሳይንሳዊ ጥናታዊ መረጃ ላይ ስለጉንዳኖች ያሉትን መረጃዎች ማየት እንደሚቻል ጆኬን ጠቅሷል፡፡ በሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የታተመውን The Ants መጽሐፍ በመጥቀስም ጆኬን ያስቀመጠው፡ “በጉንዳኖች የእንቅስቃሴ ምልክት መረጃ ማስተላለፍ ከኬሚካላዊው ጋር ሲወዳደር በጣም ደካማ ነው ይሁን እንጂ የሁለት ዓይነት ድምፅ ፈጠራዎች ታይተዋል፡፡ እነዚህም ሰውነትን ከበታች ካለው ምድር ጋር መምታት እና እንደ ፌንጣዎች ዓይነት ሰውነትን በመጨቆን (በማሸት) የሚፈጠሩ ድምፆች ናቸው፡፡ ሁለተኛው ዓይነት በትክክል ለመልእክት ማስተላለፍ የተፈጠረ ነው፡፡ (ከዚህ በታች ከተጠቀሰው መጽሐፍ ገፅ 255) ይሁን እንጂ ለሳይንሳዊ ምርምሮች ምስጋና ይድረሳቸውና ለረጅም ጊዜ የታወቀው ነገር ጉንዳኖች በአጠቃላይ በአየር መርገብገብ አማካኝነት የሚተላለፉ ድምፆችን እንደማይሰሙ ነው፤ ሆኖም ግን ከምድር አካል ውስጥ ለሚተላለፉ መርገብገቦች ግን እጅግ በጣም ንቁዎች ናቸው፡፡ (ከዚህ በታች ከተጠቀሰው መጽሐፍ ገፅ 257፡፡)

በሳይንሳዊው ጽሑፉ መረጃ ላይ እንደተጠቀሰው የበረሮዎች ዓይነት የ”ጭርታ” ድምፆችን ደረጃ የሰጠውና ከአንድ ዓይነት ብቻ ድምፅ ያሳለፈው ምንም ማስረጃ ጨርሶ አይገኝም፡፡ በሌላ ቃል ጉንዳኖች በጭራሽ አይናገሩም፤ በድምፅ ፈጠራና መልክት ባለው በድምፅ ማስተላለፍ የመነጋገሪያ መንገድ ማንኛውም ዓይነት የጉንዳን ዘር በፍፁም አይነጋገሩም፡፡ የበረሮዎቹ ዓይነት ጉንዳኖች ድምፅ ማለትም “የጭርታ” ድምፅ አንድ ዓይነት ብቻ የሆነ ድምፅ ነው (ከዚህ በታች ከተጠቀሰው መጽሐፍ 257፡፡) የምልክት አሰጣጡ ስርዓትም የምላሽ እንቅስቃሴን ከመስጠት ጋር አይገናኝም፡፡ ማለትም ወደ ጎጆአቸው የሚመጣውን የአደጋ ዓይነት በመለየት የተለየ የማስጠንቀቂያ ምልክትን አይሰጡም ገፅ 256፡፡ ከዚህ በላይ ያሉትን በሙሉ ጆኬን ካዝ የጠቀሳቸው ከሚከተለው መጽሐፍ ላይ ነው፡፡

Bert Hölldobler and Edward O. Wilson
The Ants
Cambridge, Mass., Belknap Press of Harvard University Press, 1990. xii, 732 p.,
ISBN 0674040759, Library Call Number: QL568 .F7 H57 1990

በመጽሐፉ ምዕራፍ 7 ገፅ 227-2297 ላይ የሚናገረው ጉንዳኖች የተለያየ ዓይነት መረጃ ማስተላለፍ ዘዴ እንዳላቸው ነው፡፡ ገፅ 228 በጉንዳኖች መካከል ያለውን የተለያየ ዓይነት ግንኙነት የሚያሳይ ሰንጠረዥ ይዟል፡፡ ከተመዘገቡትም 17 ዓይነት ምልክቶች ውስጥ 14 የሚሆኑት የኬሚካል ሲሆኑ 2 ደግሞ የንክኪ ዓይነት ናቸው ቀሪው አንድ ግን የኬሚካልና የንክኪ ድብልቅ ነው፡፡ በጉንዳኖች ላይ በተደረጉት ጥልቅ ጥናቶች ሁሉ ውስጥ “ንግግር” (በድምፅ የሚተላለፍ ትርጉም ያለው) ዓይነት የመረጃ ማስተላለፍ በፍፁም አልተገኘም፡፡

በሕይወት ያለ አንድ ጉንዳን በሞቱ ጉንዳኖች የሚመነጭ ኬሚካል ሲያጋጥመው ማለትም ይህ ጉንዳን የሞተ መሆኑን የሚያሳይ መልእክት ከሆነ ወዲያውኑ የሞተው ጉንዳን በሌሎቹ ተነስቶ ወደ ቆሻሻ መጣያ ይወሰዳል፡፡ ስለዚህም በጉንዳን ሕይወት ውስጥ ኬሚካሎች ከማንኛውም ነገር ይልቅ ቅድሚያ አላቸው ማለት ነው፡፡ በእርግጠኝነት በቁርአን 27 ውስጥ እንደተቀመጠው ዓይነት ምንም እውቀትን ያካተተ ንግግር በፍፁም በጉንዳኖች ዘንድ አልተገኘም፡፡ የጉንዳኖች ድርጊቶች ሁሉ ለኬሚካል መልእክቶች የሚሰጡ የእውርነት ምላሾች ናቸው፡፡

ጆኬን ሲያጠቃልል የተናገረው ስለ ጉንዳኖች የሚናገረው ብቸኛ የቁርአን ጥቅስ ይህ ሲሆን በቁርአን ውስጥ የሚያስተላልፈው መልእክት ግን ከጥሩነቱ ይልቅ መጥፎነቱን ነው፡፡ ነገር ግን አስተዋይ ሙስሊም ሁሉ እንደሚገነዘበው የጉንዳን ንግግር በቁርአን ላይ መገኘቱ ከእውነትነቱ ይልቅ ሙሉ ለሙሉ ስህተት መሆኑ እንዲሁም እምነቱን ከሚገነባው ይልቅ እምነቱን አፍራሽ መሆኑን ያስተውላል፡፡ ከዚህም በላይ የእምነቱ መሰረት ቁርአንን ቁልጭ አድርጎ የሚያቀርበው የፈጣሪ ቃል ከመሆኑና እንደፈጣሪ ቃል ተቀባይንት እንዲኖረው ሳይሆን ከሌሎችና በዘመኑና ከዘመኑም በፊት ከነበሩት የልብ ወለዳዊ አፈታሪኮች ጋር ደረጃው ዝቅ ያለ ጽሑፍ ወደ መሆን ነው፡፡

የሙስሊም ሊቃውንቱ መልስና ምልልሶች

ለዚህ ለጆኬን ካዝ ጽሑፍ ምላሽን ለመስጠትና ቁርአንን ለመመከት ከዚህ በላይ የተጠቀሱት የሙስሊም ሊቃውንት ምላሽን ሰጥተዋል፡፡ መልስ ከሰጡት ውስጥ አንዱ ራንዲ ዴዝሞንድ በአፅንዖት ያቀረበው የጉንዳኗ ንግግር ለሰለሞን የተሰጠ የተዓምር ምልክት እንደነበረና ይህም አላህ ለባሪያዎቹ ምልክትን በመስጠት ይሰራ እንደነበረ ጠቅሷል፡፡ ይህንንም ለማብራራት በቁርአን ውስጥ ለጉንዳን የተሰጠውን ስያሜ ከንግግሩ ጋር ለማቀራረብ ጥረትን አድርጓል፣ በዚህም ይህ እራሱ ቁርአን የኣላህ ቃል ለመሆኑ ማረጋገጫ ነው ለማለትም ሞክሯል፡፡

ለዚህ ራንዲ ዴዝሞንድ ጆኬን በመመለስ ያሳየው ይህ ቁርአን የአላህ ቃል መሆኑን ሊያሳይ እንደማይችል ነው፡፡ ለዚህም ማስረጃ ሲሰጥ እንደሚከተለው ብሏል፡ “ይህ ከሆነ ዮሴጵ የሚባለው ትንታዊ የቻይና ጸሐፊ እንሰሳት እንደሚናገሩ አድርጎ የጻፈው የልብ ወለድ ጽሑፍ (ጉንዳንንና ፌንጣንም ጨምሮ) ነቢይ ነው ሊያሰኘውና ጽሑፉ ተዓምር ነው ሊባል፤ ወይንም ከአምላክ የመጣ ነው ሊያሰኘው ይችላል ወይ? በማለት መልሶ ይህ ትርጉም ሊሰጥ እንደማይችልና በአምላክ ቃል ውስጥ መኖር እንደሌለበት፣ ለጉንዳ የተሰጠውም ቃል በጥንት አረቦች ባህል ውስጥ የነበረና ቁርአን ከጥንታዊ አረቦች የተዋሰው እንጂ የአምላክ መገለጥ ምስክር ሊሆን እንደማይችልም አስረድቷል፡፡ ጆኬን ለራንዲ መልስ ማጠቃለያ ሲሰጥ እስከ አሁን ድረስ እስልምና እምነቱ እራሱ አሳማኝ እንደሆነ ሎጂካል በሆነ መንገድ አንድም የሙስሊም ሊቅ እንዳላቀረበ ጠቅሷል፡፡

ሁለተኛው የሙስሊም ተከራካሪ ሺቢል ዛማን ነው፡፡ እርሱም ማንኛውም ሙስሊም ተከራካሪ እንደሚያደርገው ሁሉ የዘለፋ ቃላትን ካቀረበ በኋላ በመጀመሪያ የክርክሩ አካሄድ ትክክል እንዳይደለ፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ክርክሩ የቀረበው ከእንግሊዝኛው ቁርአን ላይ ተወስዶ ስለሆነ ተቀባይነት ሊኖረው እንደማይችል እና የአረብኛውን ቁርአን ቃላት መጥቀስ አስፈላጊ መሆኑን አቅርቧል፡፡ እንዲሁም ትችቱ የመነጨው በተሳሳተ ግምት ጉንዳኖች አይናገሩም ከሚል የተነሳ እንደሆነም ጠቅሷል፡፡ ስለዚህም ቃሉ ጉንዳን የሚለው በድምፅ መልእክትን የሚያስተላልፉትን ምስጦችን ማለትም ሊሆን እንደሚችል እና የጉንዳን መሰል ጥናቶችን ጸሐፊው ሌሎችንም አማራጮች ማሰስ እንደነበረበት አቃሎ ለማስቀመጥ ሞክሯል፡፡ በመቀጠልም ወደ መጽሐፍ ቅዱስ አባባሎች በመጥቀስ በትንቢተ ዳንኤል ላይ የተገለጠውን ተናጋሪ ቀንድ፣ እንዲሁም በዘኅልቁ መጽሐፍ ላይ የተገለጠውን የአህያውን ለነቢዩ መናገር ጠቅሶ፡፡ ቀንድ ከሚናገር ይልቅ ጉንዳን አይሻልም ወይ የአህያስ መናገር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መኖር ለወንጌላውያን ክርስትያኖች አሳፋሪ አይደለም ወይ በማለት አቅርቧል፡፡

ሺብል ዛማን በማጠቃለያው ላይ ቁርአን በአሁኑ ጊዜ ገብቶ ያልተገኘበት የሳይንስ መስክ በጭራሽ ላለመኖሩ ይህ ማረጋገጫ እንደሆነና ይህም ቁርአን ሳይንሳዊ ለመሆኑ ሌላው ማስረጃ ነው በማለት ደምድሟል፡፡

ለእነዚህ በዛማን ለቀረቡት ሀሳቦች ሁሉ ጆኬን የሰጠው መልስ አጥጋቢ ነው፡፡

የዛማን ክርክር ምንም ሳይንሳዊ  መሰረት የሌለውና በአረብኛም ቋንቋ ቃላት አጠቃቀም ተመስርቶ ያቀረበውና ምስጦች ይናገራሉ ያለው ነገር የራሱን ማስረጃ እራሱ በራሱ እንዲያፈርሰው አድርጎታል ብሏል፡፡ ምክንያቱም በእነዚህ እንሰሳት ጥናት ላይ ምስጦች ከጉንዳኖች ጋር በአንድ መሰል የእንሰሳት ቡድንነት ላይ አይፈረጁምና፡፡

ከዚህም ባሻገር ጆኬን ያቀረበው ሐሳብ ዛማን እነዚህ ሁሉ እንደማያዋጡት ቢያውቅም በንዴትና በቁጣ ስሜት በመሆን የክርስትያኖች መጽሐፍ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ አለ ብሎ በሚያስበው ችግር ጠቁሞ ለማለፍ ጥረትን አድርጓል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የቀንድ መናገርንና የአህያዋንም በትክክል አስቀምጧቸዋል፡፡ እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ አባባሎች ለምን እንደተቀመጡ ትክክለኛና ሎጂካዊ መልስ ያላቸው መሆናቸውን ዘማን አላስተዋለም፡፡ በመሆኑም የቁርአንን ችግር በእነርሱ ላይ ተደግፎ ለማምለጥ ሙከራን ማድረግ አልነበረበትም፡፡ እያንዳንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላስቀመጠው ነገር ሎጂካል መልስን ለመስጠት እራሱ መጽሐፍ ቅዱስ የሚችል እንደሆነው ሁሉ ቁርአንም እራሱን ችሎ በራሱ ላይ ቆሞ መልስን ለመስጠት መዘጋጀት ይኖርበታል፤ ይህ የሚሆነውና የሚቻለው ግን የአምላክ ቃል ከሆነ ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን እነዚህ ችሎታ ማጣቶች ቁርአንን የፈጣሪ አምላክ ቃል መሆኑን ጥርጥር ውስጥ እያስጣሉት ናቸው፡፡ ስለዚህም ዛማን ያልበሰለና ችኩል የሆነ ቁርአንን የመመከት ስራ በመስራቱ ከሰጠው ጥቅም ይልቅ ጉዳቱ አመዝኗል፡፡ ጆኬን ይህን በተመለከተ ያቀረበው መደምደሚያ ዛማን በዚህ የምር የሆነ ጉዳይ ላይ የምር የሆነ ስራ እንዳልሰራ ነው፡፡

መቋጫው ምንድነው?

ይህንን በቁርአን ላይ ያሉትን የተናጋሪ ጉንዳኖችን አስመልክቶ በቁርአን ውስጥ ያለውን መሰረታዊ ችግር በተመለከተ በቁርአንና ሳይንስ ስር እንዲሁም በቁርአን ስር በተከታታይ የምናቀርባቸውን ቁርአናዊ አፈታሪኮች ተረቶችና የጥንት ልብ ወለዶች ክፍልን እንድትከታተሉ እናሳስባለን፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አንባቢዎች ሁሉ  የሚከተሉትን እንድታስተውሉልን እንፈልጋለን፡፡

  • በቅድሚያ በቁርአን ላይ ያለው የጉንዳን ንግግር ከአምላክ ቃል ውስጥ ገብተው መገኘት ከማይገባቸው ነገሮች ውስጥ አንዱና ለራሱ ለቁርአን ሐፍረት ነው፡፡
  • ሁለተኛው ደግሞ በቁርአን ውስጥ ያለው የጉንዳን ንግግር የተጻፈበት ምንም ዓላማ እንደሌለው ነው፡፡ የጉንዳን መናገር ለምን ዓላማ ተዘገበ?

የመጽሐፍ ቅዱሱ የቀንድ ንግግር ምሳሌያዊ መሆኑን ከክፍሉ በትክክል መረዳት የሚቻል ሲሆን የአህያዋ ንግግር ደግሞ በተዓምርና በዓላማ የተደረገ ሲሆን የዓላማውም ውጤት በግልጥ እንደተጻፈ ነው፡፡ የአህያዋ መናገር በትክክል ለታቀደ ዓላማ ተደርጎ የነበረ መሆኑን በአዲስ ኪዳንም ላይ ተደግሞ ተጠቅሶ ተነግሯል፡ “ቃል የሌለው አህያ በሰው ቃል ተናግሮ የነቢዩን እብድነት አገደ።” 2 ጴጥሮስ 2.16፡፡  የጉንዳኑ ግን ስለምን ዓላማ ተጻፈ? የጉንዳን ንግግር ባለበት በምዕራፍ 27 ላይ የሚገኘው የወፉ ንግግር የተወሰደው ከአይሁድ ልማዳዊ ጽሑፍ ቢሆንም ጥቂት ዓላማ ይታይበታል ማለት ያስኬድ ይሆናል፡፡ ይሁን እንጂ የወፉንና የአጋንንትን ከሰለሞን ጋር መነጋገርና አጠቃላይ የቁርአን ምዕራፍ 27 ትዕይንት ለቁርአን የሚያሰጠው ግምት ለሙስሊም ሊቃውንት ከፍተኛ የራስ ምታት ነው፡፡ ምክንያቱም ቁርአንን ወደ ልብ ወለድ የጽሑፍ ደረጃ ዝቅ የማድረግ ውስጣዊ መልእክትና ባህርያት አላቸውና፡፡

ወደ ማጠቃለያ ስንመጣ ልንመለከት የምንችላቸው አንዳንድ ዋና ዋና ነገሮች ይኖራሉ፡፡ የፈጣሪ እግዚአብሔር ቃል አላማው ለሰዎች ሕይወት ሁለት ዋና ዋና መሰረታዊ ነገሮችን ማመልከት ነው፡፡

  • አንደኛው የሰው ልጅ መሰረታዊ ችግር ምን እንደሆነ፣ በተለይም ከፈጣሪው ጋር ያለውን ግንኙነት አስመልክቶ ያለውን ሁኔታ መግለጥ፡፡ ሰው በኃጢአት የወደቀ በመሆኑ አሁን የሰው ዘር ውስጥ ላሉት እና ለምናዝንባቸው ውጣ ውረዶችና ችግሮች ሁሉ ምክንያት ነው፡፡
  • ሁለተኛው ደግሞ የእውነተኛው ፈጣሪ ባህርያት ምንድናቸው የሚለውን ማሳየት ነው፡፡ እውነተኛው ፈጣሪ ቅዱስ ነው፣ ከሰዎች የተለየ ነው፣ እርሱ ፃድቅ ፈራጅ ነው፤ በፍርድም በፍፁም አያዳላም፡፡ ስለዚህም ኃጢአትን መቅጣት አለበት፡፡

ከነዚህ እውነቶች የተነሳ መሰረታዊ የኃጢአት ችግር ያለበት ሰው እንዴት ወደ ቅዱስ እግዚአብሔር ፊት ይቀርባል? ለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ መፍትሔ አድርጎ የሚያቀርበው መልእክቱ ከእነዚህ ሁለት ሀሳቦች አኳያ ሰው ከፈጣሪው ጋር የሚታረቅበትን ተስፋና መንገድን ማሳየት ነው፡፡ ቁርአን ግን ይህንን እውነታ ለማንም ሊያሳይ አይችልም መልእክቱ ከዚህ በላይ እንደተመለከትነው በውስጡ እንደተጻፈው ነውና፡፡

አንባቢዎች ሆይ! መጽሐፍ ቅዱስን በማግኘት በቅን አዕምሮ ሆናችሁ እንድታነቡትና ከእርሱም እንድትማሩ ጥሪያችንን እናቀርብላችኋለን፡፡ ጌታ እግዚአብሔር በምህረቱ ይርዳችሁ አሜን፡፡

 

ለእስልምና መልስ አማርኛ  ዋናው ገጽ