ቁርአንና ታሪክ
በዳንኤል
በሙስሊሞች እምነት መሠረት ቁርኣን ናዚል (ከላይ የወረደ መገለጥ) እንጂ ታሪክ አይደለም፡፡ ሙስሊሞች ቁርኣን ከታሪክ ያለፈ ነው ብለው ያምናሉ፡፡ ይህ ማለት ግን ከታሪክ ጋር የሚገናኝ ምንም አይነት ሐሳብ በውስጡ አይገኝም ማለት አይደለም፡፡ የኖህ እና የጥፋት ውሃ ታሪክ፤ የሙሴ እና የእስራኤላውያን ታሪክ ወዘተ. በውስጡ ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን እነዚህ ታሪኮች ተጽፈው የሚገኙት ቅደም ተከላቸው በተጠበቀ ሁኔታ በታሪካዊ ዘገባ መሠረት አይደለም፡፡ በቁርኣን ውስጥ የሚገኙትን እነዚህን ታሪክ-ጠቀስ ዘገባዎችን ወስደን ስንመዝናቸው በውስጣቸው ብዙ አሳማኝ ያልሆኑ እና በየትኛውም መመዘኛ ሚዛን የማይደፉ እንዲሁም ከተረጋገጡ የታሪክ እውነታዎች ጋር የሚጋጩ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ አንባቢዎች እግዚአብሔር የሰጣቸውን የማመዛዘን ችሎታ ተጠቅመው የቀረቡትን ነጥቦች እንዲመዝኑ በትህትና እየጠየቅን፣ የሚከተሉትን ጥቂት ምሳሌዎች ከቁርአን ውስጥ እናቀርባለን፡
1. ሳምራዊ በሙሴ ዘመን?
ቁርኣን 20.85 “/አላህ/ እኛም ከአንተ በኋላ ሰዎችህን ፈትተን ሳምራዊውም አሳሳታቸው አለው፡፡ ሙሳም ወደ ሰዎቹ የተቆጣ ያዘነ ሆኖ ተመለሠ፡፡”
ታሪክ እንደሚናገረው የእስራኤል መንግሥት በ930 ዓ.ዓ. ለሁለት ተከፍሎ ነበር፡፡ የሰሜኑ መንግሥት “እስራኤል” በመባል ሲጠራ የደቡብ መንግሥት ደግሞ “ይሁዳ” ይባል ነበር፡፡ የሰሜኑ መንግስት ህዝብ ከ722-705 ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ በአሶር ንጉስ በሳርጎን አካዲያን ተማርኮ ተወስዶ ነበር፡፡ በአርኪዎሎጂ የተገኙ መዛግብት እንደሚያስረዱት 27290 የሚያክሉ የዋና ከተማዋ የሰማርያ ነዋሪዎች በምርኮ ወደ አሶር /Assyria/ ፈልሰዋል፡፡ ነገር ግን በዚሁ ጊዜ በሰማርያና በአካባቢዋ ጥቂት ሰዎች ከምርኮ ተርፈው ቀሩ፡፡ እነዚህ ሰዎች ከሌላ ቦታ ከመጡ ሰፋሪዎች ጋር በመጋባትና በመደበላለቅ ሃይማኖታቸውና ባህላቸው ከሌላው ጋር የተቀየጠ ሆነ፡፡ በዚሁም ሳቢያ በተቀሩት አይሁዶች ዘንድ የተገለሉ ሆኑ፡፡ ከዚህ በኋላ ነው እንግዲህ በዋና ከተማዋ በሰማሪያ ስም ሳምራዊያን ተብለው መጠራት የጀመሩት፡፡ www.jewishencyclopedia.com/articles/13059-samaritans ይመልከቱ፡፡ ቁርኣን እንደሚለው በሙሴ ዘመን የወርቁን ጥጃ ሰርተው ያመልኩ ዘንድ ያሳሳታቸው ሳምራዊ ነው፡፡ ሳምራዊ በመባል መጠራት የመጣው ከምርኮው ዘመን በኋላ እንደሆነና ሙሴ ደግሞ ከዚህ ዘመን በብዙ መቶ አመታት ቀድሞ የኖረ መሆኑ ሊካድ የማይችል ሃቅ ነው፡፡ ታዲያ ሳምራዊ በሙሴ ዘመን ከየት ተገኘ? ሙስሊም አስተማሪዎች የትኛውን የታሪክ ምንጭ በመጥቀስ ይሆን ይህንን የመጽሐፋቸውን ስህተት የሚያስተባብሉት?
2. አይሁዶች ዑዘይር (ዕዝራ) የአላህ ልጅ ነው አሉ?
ቁርኣን 9.30 “አይሁድ ዑዘይር የአላህ ልጅ ነው አለች፤ ክርስቲያኖችም አልመሲህ የአላህ ልጅ ነው አሉ”
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደሚታወቀው ዕዝራ ካህንና የህግ መምህር ሲሆን ከነህምያ ጋር በመሆን ከባቢሎን ምርኮ በኋላ ኢየሩሳሌምን እንደገና ለመገንባት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥም በስሙ “መጽሐፈ ዕዝራ” በመባል የሚታወቅ አንድ መጽሐፍ ጽፏል፡፡ በአይሁድ ህግና ልማድ መሠረት ክርስቲያኖች ጌታ ኢየሱስን “የእግዚአብሔር ልጅ” በሚሉት አጠራር ዓይነት አንድን ሰው “የእግዚአብሔር ልጅ” በማለት መጥራት እንደ ክህደት ይቆጠራል፡፡ የጌታ ኢየሱስንም የእግዚአብሔር ልጅነት እስከዛሬ ድረስ ለመቀበል የተቸገሩበት አንዱ ምክንያት ይህ ቢሆንም ብሉይ ኪዳን ግን መሲሁ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን በግልፅ ያውጃል (መዝሙር 2.7፤ ሆሴዕ 11.1 ከማቴዎስ 2.15 ጋር ያወዳድሩ)፡፡ አይሁዶች ዕዝራን በየትኛውም የታሪክ አጋጣሚ የእግዚአብሔር ልጅ ብለው እንደጠሩት የሚጠቁም ፍንጭ እንኳ የለም፡፡ በዚህ ተግባር የቁርኣን ክስ አይሁድን ሁሉ በጅምላ እንጂ ከአይሁድ መካከል አንዳንዶቹን ብቻ ስላልሆነ ምናልባት በአረቢያ ይኖሩ ከነበሩት አይሁድ መካከል ጥቂቶቹ ዕዝራ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ያምኑ ይሆናል የሚል ግምት የሚያስኬድ አይሆንም፡፡ ለምሳሌ እኔ የማውቃቸው መጠጥ የሚጠጡና የሚሰክሩ የተወሰኑ ሙስሊሞች አሉ፡፡ እነዚህን ጥቂት ሰዎች ብቻ በመመልከት “ሙስሊሞች ጠጪዎችና ሰካራሞች ናቸው” ብዬ ሙስሊሙን ህብረተሰብ በጅምላ በመንቀፍ መጽሐፍ ብጽፍ ትልቅ ስህተት አይሆንምን? ያለጥርጥር ይህ አይነቱ የጅምላ ክስ እውቀት የጎደለውና አግባብነት የሌለው ነው፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ጥቂት ሰዎች መላውን የእስልምና እምነት ተከታይ ህዝብ የማይወክሉ ናቸውና፡፡ በመሐመድ ዘመን ዕዝራ የአላህ ልጅ እንደሆነ የሚያምኑ ጥቂት አይሁድ በአረቢያ ነበሩ ብለን ብንቀበል እንኳ እነዚህን ጥቂት ሰዎች ብቻ በመመልከት አይሁድ ዕዝራ የአላህ ልጅ ነው ብለው እንደሚያምኑ በመናገርና በመጻፍ የአይሁድን ህዝብ በጅምላ መንቀፍ ከፍተኛ የሆነ ስም ማጥፋት ነው፡፡ ዳሩ ግን ከአይሁድ መካከል አንዱ እንኳ ዕዝራን የአላህ ልጅ ብሎ መጥራቱን የሚጠቁም ታሪካዊ ዘገባ ባለመኖሩ ይህ የቁርኣን ጥቅስ ታሪክንና የአይሁድን ሃይማኖት ትምህርት ያላገናዘበ ነው፡፡ እናም በግልፅ የሚታይ ታሪክን እና ሃይማኖታዊ እውነታዎችን ያፈረሰ ስህተት አለበት፡፡
3. ሩቁ መስጊድ?
ቁርኣን 17.1 “ ያ ባርያውን ከተከበረው መስጊድ ወደዚያ ዙርያውን ወደባረክነው ወደ ሩቁ መስጊድ በሌሊት ውስጥ ያስሄደው /ጌታ/ ጥራት ይገባው፤ ከታምራታችን ልናሳየው /አስሄድነው/፤ እነሆ እርሱ /አላህ/ ሰሚው ተመልካቺው ነው፡፡”
ይህ ጥቅስ በራሱ ‘ያ ባሪያ ማነው?’ ‘ሩቁ መስጊድ የት ነው?’ ‘ያ ባርያ በምንና እንዴት ወደዚያ ሄደ?’ ‘ሄዶስ ምን ሰራ?’ ወዘተ. ለሚሉት ጥያቄዎች መልስ አይሰጠንም፡፡ ለነዚህ ጥያቄዎች መልስ ማግኘተ የምንችለው የተለያዩ ተፍሲሮችን (ማብራራያዎችን) እና ሐዲቶችን እንዲሁም የሙሐመድን የታሪክ መጽሐፍት በመመልክት ነው፡፡ ይህም ደግሞ ሁሉንም ነገር በውስጡ አሟልቶ እንደያዘና ግልፅ እንደሆነ በሙስሊሞች ዘንዱ የሚታመንበት ቁርኣን በራሱ ሙሉ አለመሆኑን የሚገልጥ እና ራሱን ችሎ በመቆም ለጥያቄዎቻችን በሙሉ መልስ የመስጠት ብቃት እንደሌለው የሚያሳይ ነው፡፡ እንግዲህ የተለያዩ የሙስሊም መጽሐፍት እንደሚናገሩት ከላይ የተቀመጠው ጥቅስ የሚያመለክተው መሐመድ በሌሊት ወደ ኢየሩሳሌም የተጓዘበትን ታሪክ ነው፡፡ በዚህ መሰረት መሐመድ ቡራቅ በተባለ ባለ ክንፍ በቅሎ መሳይ እንስሳ ከመካ ተነስቶ ወደ ኢየሩሳሌም እንደሄደና በመሰላል ወደ ሰባቱ ሰማያት እንደወጣ ከዚያም ነቢያት ሁሉ ከሞት ተነስተው በእርሱ መሪነት በኢየሩሳሌም በሚገኘው የሰለሞን ቤተመቅደስ ውስጥ ሶላት እንደሰገዱ ሙስሊም ጸሐፍት ያስነብቡናል፡፡ (Abdullah Yusuf Ali, the Qur’an Commentary pp. 691-693 እንዲሁም እስልምናና የታላቁ ነቢይ የሙሐመድ ታሪክ በሐጂ ሙሐመድ ሳኒ ሐቢብ ገፅ 62-64)
በዚህ ታሪክ ላይ ሩቁ መስጊድ የተባለው የሰለሞን ቤተመቅደስ (አሁን የአል-አክሳ መስጊድ ያለበት) ነው፡፡ ነገር ግን መሐመድ ወደዚያ ስፍራ ሄደ በተባለበት በዚያ ጊዜ የሰለሞን ቤተመቅደስ ከፈረሰ ብዙ ዘመናት አልፈዋል፡፡ ከዚያ በኋላም ቢሆን ሄሮድስ ያሰራው ቤተመቅደስ ቲቶ (Titus) በተባለ ሮማዊ ጄነራል በ 70 ዓ.ም. ፈርሷል፡፡ በዚያ ስፍራ ላይ እስከዛሬ ድረስ ቆሞ የሚታየው የአል-አክሳ መስጊድም ቢሆን ከመሐመድ ሞት በኋላ ብዙ አመታት ዘግይቶ በኻሊፋ አብድ አል-ማሊክ የተሰራ ስለሆነ በመሐመድ ዘመን ምንም አይነት መስጊድም ሆነ ቤተመቅደስ በስፍራው ላይ አልነበረም፡፡ ታድያ ቁርኣንና ሙስሊም ጸሐፍት መሐመድ ወደ ሩቁ መስጊድ ሄደ የሚሉን ይህንን እውነታ እንዴት ቢመለከቱት ነው?
4. ስለ ሰለሞን ተረት ተረት ወይስ እውነተኛ ታሪክ?
በቁርኣን መሠረት ሰለሞን:-
- ነፋስ ይታዘዝለት ነበር፡፡ ቁርኣን 21.81
- ሰይጣናት ሉልን ያወጡለት ነበር ሥራም ይሠሩለት ነበር፡፡ ቁርኣን 21.82
- የወፍ ቋንቋ ይችል ነበር፡፡ ቁርአን 27.16 እንዲያውም ከዝናብ ወፍ ጋር ይነጋገር ነበር፡፡ ቁርኣን 27.20-28
- ሰራዊቶቹ ከጋኔን ከሰውም ከወፎችም ነበሩ፡፡ ቁርኣን 27.17
- ጉንዳን ስትናገር መስማት ይችል ነበር፡፡ ቁርአን 27.18-19
- የንግስተ ሳባን ዙፋን ከጋኔን ሀይለኛው ሰርቆ አምጥቶለታል፡፡ ቁርኣን 27.38-40
- ጋኔኖችም ምኩራቦችን፣ ምስሎችን፣ ገንዳዎችንና ድስቶችን ይሠሩለት ነበር፡፡ ቁርኣን 34.12-13፤ ቁርኣን 38.36-37
የሰለሞንን አሟሟት በተመለከተ ቁርኣን 34.14 ላይ እንዲህ ይላል፡- “በእርሱም ላይ ሞትን በፈፀምንበት ጊዜ መሞቱን በትሩን የምትበላ ተንቀሳቃሽ ምስጥ እንጂ ሌላ አላመለከታቸውም፡፡ በወደቀ ጊዜም ጋኔኖች ሩቅን ሚስጢር የሚያውቁ በሆነ ኖሮ በአዋራጅ ስቃይ ውስጥ የማይቆዩ እንደነበሩ ተረዱ፡፡”
እዚህ ጋ ልብ በሉ እንግዲህ ሰለሞን በትሩ ላይ ተደግፎ ቆሞ ለእርሱ ይሰሩ የነበሩትን ጋኔኖች ሲቆጣጠር ሳለ ድንገት በቆመበት ሞተ፡፡ ጋኔኖቹ እርሱ እየተመለከታቸው በሕይወት ያለ መስሏቸው ይሠራሉ፡፡ ነገር ግን አንዲት ምስጥ የተደገፈበትን በትር በላችና ወደቀ፡፡ በዚህ ጊዜ ጋኔኖቹ የእርሱን መሞት ተረዱ፡፡ ቁርኣንና ሙስሊም ምሁራን የሚነግሩን ይህንን ነው፡፡ ለመሆኑ የት ሀገር ነው ንጉስ በቆመበት ስፍራ እስኪሞት እና ምስጥ የተደገፈበትን በትር በልታ እስኪወድቅ ድረስ ብቻውን የሚሆነው? ለመሆኑ ሰለሞን ከሞተ በኋላ የመሬት ስበት ህግ በርሱ ላይ ስለማይሠራ ይሆን ደርቆ የቆመው?
በዚህ የሰለሞን ታሪክ ውስጥ ልክ እንደሰው የሚታዩ እና በሁለት እግራቸው ቆመው የሚሄዱ ጋኔኖችን፤ የሚናገሩ ወፎችንና የሚናገሩ ጉንዳኖች እናገኛለን፡፡ ለመሆኑ ከመቼ ወዲህ ነው ወፎችና ጉንዳኖች ልክ እንደሰው እንዲያውም የወደፊቱን አውቀው መናገር የጀመሩት? ከወፎች መካከል በቀቀን /Parrot/ ከብዙ ልምምድ በኋላ የሰውን ንግግር አስመስላ መናገር እንደምትችል ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ትርጉሙን አውቃ ሳይሆን በደመነፍስ የምትፈፅመው ነገር ነው፡፡ ቁርአን ባስቀመጠው በሰለሞን ታሪክ ውስጥ ደግሞ እንደሚናገር የተነገረን የዝናብ ወፍ ነው፡፡ ጉንደኖችም መረጃም የሚለዋወጡት ፈፅሞ ሰዎች አይተውም ሆነ ሰምተው ሊረዱት በማይችሉት መንገድ ነው፡፡ የሚገርመው ነገር በቁርኣን ውስጥ እንደተናገረች የተጠቀሰችው ጉንዳን
- የሰለሞንን ስም አውቃለች
- ሰለሞን ሰራዊቶች እንዳሉት አውቃለች
- የሰለሞን ሰራዊቶች ወደዚያ ስፍራ እንደሚመጡ አውቃለች
- የሰለሞን ሰራዊቶች ሳያውቁ ከረጋገጧቸው ጉንዳኖቹን እንደሚሰባብሯቸው አውቃለች (ቁርኣን 27.18)
አንባቢዎች ሆይ ለፈጣሪ የሚሳነው ነገር የለም በሚል ሽፋን እንዲህ አይነት ታሪኮች ተቀባይነት ማግኘት ይገባቸዋልን?
ይህ የሰለሞን ታሪክ ከእውነተኛ ታሪክ ይልቅ በተረታ ተረቶች ውስጥ የሚነገር አይነት የአስማትና የምትሃት አለም ይመስላል፡፡ ሙስሊም የሆኑት ሰዎች ሰለሞን ነቢይ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ በብዙ ሙስሊሞች እምነት መሠረትም ነቢያት ንፁሀንና ፃድቃን ናቸው፡፡ ቁርኣን ይህ የሰለሞን ተግባር ስህተት እንደሆነ ሳይሆን እንዲያውም የአላህ ችሮታ እንደሆነ ይናገራል፡፡ ክርስቲያኖች ግን ከአጋንንትና ከሰይጣናት ጋር ተባብሮ የሚሰራ ነቢይ አያውቁም፡፡ እንዲህ ከአጋንንትና ከሰይጣናት ጋር የሚሰራ ሰው ሊሆን የሚችለው ጠንቋይና አስማተኛ እንጂ ነቢይ አይደለም፡፡ እውነተኛ ነቢይ የተባለ ሰው እንዲህ አይነት ተግባር ሲፈፅም ከተገኘ የነቢይነት ፀጋው ከርሱ ላይ ተወስዶ የሰይጣን ወዳጅ ሆኗል ማለት ነው፡፡ ምንም እንኳ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት የሰለሞን ፍፃሜ እንደ ጅማሬው ያማረ ባይሆንም ነገር ግን ከጌታ አምላክ ጋር ተስማምቶ በኖረበት ዘመን በቁርኣን ውስጥ በተጠቀሰው አይነት ሁኔታ ከአጋንንትና ከሰይጣናት ጋር ተባብሮ የኖረበት ጊዜ አልነበረም፡፡ አባቱ ዳዊት በገና በሚደረድርበት ጊዜ ክፉ መንፈስ ከሳኦል ይርቅ እንደነበር ተጽፏል /1ሳሙኤል 16.14-23/፡፡ የእግዚአብሔር ነቢያት ባህሪም ይሄው ነው፡፡ መቼም ሙስሊም መገኖቻችን ክርስቲያኖች ሰለሞን ነቢይ ሆኖ ሳለ ከአጋንንቶችና ከሰይጣናት የተዋቀረ ሠራዊት አለቃ ሆኖ ይኖር አንደነበረ የሚናገረውን የቁርኣን ቃል እንደ ፈጣሪ ቃል ባለመቀበላቸው ቅር ሊላቸው አይገባም፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ ሰለሞንን በተመለከተ የሚከተለውን ቃል ይናገራል፡- 1ነገስት 4.29-34፡ “እግዚአብሔርም ለሰሎሞን እጅግ ብዙ ጥበብና ማስተዋል በባሕርም ዳር እንዳለ አሸዋ የልብ ስፋት ሰጠው። የሰሎሞንም ጥበብ በምሥራቅ ካሉ ሰዎች ሁሉ ጥበብና ከግብጽ ጥበብ ሁሉ በለጠ። ከሰውም ሁሉ ይልቅ ከኢይዝራኤላዊው ከኤታንና ከማሖል ልጆች ከሄማንና ከከልቀድ ከደራልም ይልቅ ጥበበኛ ነበረ። በዙሪያውም ባሉ አሕዛብ ሁሉ ዝናው ወጣ። እርሱም ሦስት ሺህ ምሳሌዎች ተናገረ፤ መኃልዩም ሺህ አምስት ነበረ። ስለ ዛፍም ከሊባኖስ ዝግባ ጀምሮ በቅጥር ግንብ ላይ እስከሚበቅለው እስከ ሂሶጵ ድረስ ይናገር ነበር፤ ደግሞም ስለ አውሬዎችና ስለ ወፎች ሰለተንቀሳቃሾችና ስለ ዓሣዎች ይናገር ነበር። ከአሕዛብም ሁሉ፥ ጥበቡንም ሰምተው ከነበሩ ከምድር ነገሥታት ሁሉ የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ሰዎች ይመጡ ነበር።”
ከሁለቱ ታሪኮች የትኛው ትክክለኛና አሳማኝ እንደሆነ አንባቢው ለመለየት ይቸገራል ብለን አናምንም፡፡ በቁርኣኑ የሰለሞን ታሪክ ላይ ሊነሱ የሚችሉ ብዙ ጥያቄዎች ቢኖሩም ነገር ግን ከጊዜና ከቦታ አንፃር ታልፈዋል፡፡ አንባቢው ግን በጥልቀት በመመርመር ሊመዝነው ይችላል፡፡
5. የፀሐይ መውጫና መግቢያ ጋ መድረስ የቻለ ሰው?
ዙልቀርናይን የተባለ ልዩ የሆነ ሰው ወደ ፀሐይ መግቢያ ቦታ ደርሶ ጥቁር ጭቃ ባላት ምንጭ ውስጥ ስትጠልቅ እንዳገኛትና እዚያ የሚገኙ ሰዎችን በኃይል እንደገዛቸው እንዲሁም ወደ ፀሐይ መውጫ ቦታ ደርሶ እዚያ አካባቢ የሚገኙ ሰዎች ከሙቀቷ የሚጠለሉበት ነገር እንደሌላቸው እንደተመለከተ ቁርኣን ይነግረናል (ቁርኣን 18.86)፡፡ በተጨማሪም ይህ ታላቅ ተፈጥሮ ያለው ሰው (super human) ከብረት ቁርጥራጮች ትልቅ ግድብ በመስራት ነሃስ አቅልጦ በማፍሰስ እንደሸፈነው እና ይህ ግድብ ግዙፍ ከመሆኑ የተነሳ በሁለት ተራሮች መካከል የሚገኝ ክፍተት መድፈን ችሎ እንደነበር እናነባለን፡፡ ቁርኣን የዚህን ግድብ ጠቀሜታ ሲያብራራ እጁጅ እና ማእጁጅ (ጎግ እና ማጎግ) የተባሉ አመፀኛ ህዝቦች ጥፋት እንዳያስከትሉ ለመከላከል እንደሆነና ይህም ግድብ በፍርድ ቀን እንደሚፈርስ ይናገራል፡፡ ለመሆኑ ዙልቀርናይን ማነው? ዙልቀርናይን የሚለው ስም ትርጉሙ “ባለሁለት ቀንድ” ማለት እንደሆነ የአማርኛው ቁርአን ግርጌ ማስታወሻ ገፅ 206 ላይ ይናገራል፡፡ አንዳንድ ሙስሊም ምሁራን ይህንን ሰው ታላቁ እስክንድር (Alexander the Great) እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን እስክንድር ጣኦት አምላኪ መሆኑ በታሪክ ስለሚታወቅ እና በተፃራሪው ደግሞ ቁርኣን ውስጥ የተጠቀሰው ሰው በአላህ አጥብቆ እንደሚያምን የተገለፀ በመሆኑ ይህ ማብራርያ ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም፡፡ ዙልቀርናይን እንደሰራው የተነገረን ግድብ እስከ ፍርድ ቀን ድረስ የሚቆይ ከሆነ አሁንም አለ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ሙስሊም ወገኖቻችን ይህ ግድብ የት ሀገር እንደሚገኝ ሊነግሩን ይችላሉን? በተጨማሪም ዙልቀርናይን በእርግጠኝነት ማን እንደሆነና የተባለውም ሰው ታላቁን የብረት ግድብ መስራቱን ታሪካዊ ማስረጃ በመጥቀስ ሊያብራሩልን ይችላሉን? መቼም እንዲህ አይነት ታላቅ ሥራ የሠራ ሰው በምድር ላይ ኖሮ ከሆነ ከታሪክ ሊሰወር አይችልም፡፡ እርሱ የሰራው ማንም ሊያልፈው የማይችለው ታላቅ ግድብ በዚህች ኘላኔት ላይ የሚገኝ ከሆነ የት እንዳለ መታወቁ አይቀርም፡፡
የአዘጋጁ አስተያየት፡
ከዚህ በላይ በአምስት ነጥቦች ዙሪያ የቀረቡትና በቁርአን ውስጥ የሚገኙት ሃሳቦች አስገራሚዎች ከመሆናቸውም በላይ በቅንነት ለሚመለከታቸው ሁሉ የሚከተሉትን ዓይነት ጥያቄዎች የሚጭሩ ናቸው፡
እነዚህ ነገሮች በእውነት የሆኑ እውነተኛ ታሪኮች ናቸውን?
እነዚህ የተጻፉት ምን ዓይነት ትምህርትን ለማስተላለፍ ነው፣ የመጻፋቸው ዓላማ ምንድነው? በቁርአን ውስጥ ስለ ሰሎሞን የተጻፉትን ሃሳቦች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለምን አላገኘናቸውም?
እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት አምስት ሐሳቦች ስለቁርአን የሚሰጡት ምስክርነት ምንድነው? ቁርአን ከሰማይ የመጣ የአምላክ መጽሐፍ ነው በማለት አንድ ሰው እንዲቀበለው ያደርጋሉን?
ከፈጣሪ የመጣ መጽሐፍ ሁሉ በውስጡ ማስፈር ያለበት አንድ ሰው ከፈጣሪው ጋር እንዴት ሊታረቅ እንደሚችል የሚገልፁ ትምህርቶችን መሆን ይገባዋል፡፡ ይህም መሆን ያለበት የሰማይና የምድሩ ፈጣሪ፣ ቅዱስና ሕያው እንዲሁም አፍቃሪ አምላክ በመሆኑ ለሰዎች ልጆች ነፍስ እጅግ በጣም ስለሚያስብ ነው፡፡ ስለዚህም ለሰዎች ልጆች ነፍስ መዳን የሚሆነውን የራሱን መንገድ እጅግ በጣም አስደናቂ በሆነ መንገድ ገልጦታል ይህም መገለጥ አንድና መሻሻል የማያስፈልገው በመሆኑ እስከዛሬ ድረስ ድንቅ በሆነ ኃይሉ ተጠብቆ ተቀምጧል፡፡ ይህንንም የእርሱን የራሱን መንገድ ለማወቅና ለመገንዘብ የሚቻለው መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ ሲነበብና ሲሰበክም በመስማት ብቻ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በሰው አዕምሮ በተፈጠሩ ተረቶችና ለሰው የዘላለም ሕይወት ምንም ጥቅም በማይሰጡ ለምክንያታዊ ሎጂካል አስተሳሰብም በማይመቹ የልዩ ልዩ ሃይማኖታዊ መልእክቶች የሰዎች ነፍስ ከሚመጣው ፍርድ መዳን አይችልም፡፡
የዚህ ድረ ገፅ አዘጋጆች ከላይ ያሉትን አምስት ነጥቦች ላነበቡ ሰዎች የምንጠይቀው መሰረታዊ ጥያቄ፤ ሕያው ስለሆነው ስለ ነፍሳቸው በጥልቅ እንዲያስቡ ነው፡፡ እኛ የሰዎች ልጆች ስለ ነፍሳችን የምናስብባቸቸው ዋና ዋናዎቹ ምክንያቶች የሚከተሉት ናቸው፡
አንደኛ፡ የሁላችንም ምድራዊ ሕይወት ወደ ሩቅ አገር የሚደረግ ዓይነት ጉዞ ነው፣ ጉዞውም ወደ ሞት ነው፣ በመሆኑም ሁላችንም በዚያ ጉዞ ላይ ነን ማነው ከዚያ ጉዞ አይቀርም፡፡
ሁለተኛ፡ ሁላችንም የሰው ልጆች ከኃጢአታችን የተነሳ በቅዱስ ንፁህና ፍፁም በሆነው በእግዚአብሔር ፊት የሚያቀርበን ምንም ነገር የለንም ነገር ግን በፍርድ ቀን በፊቱ መቅረባችን አይቀርም፡፡
ሦስተኛ፡ ሁላችንም በቅዱስ እግዚአብሔር በፍርድ ፊት ስንቀርብ ሃይማኖታችን ወይንም አለን ብለን የምናስበው ጥሩነታችን ሁሉ በፍፁም አያዋጣንም፡፡ ስለዚህም ምንም ተስፋ የሌለን ፍርድ የሚገባን የገሃነም እሳት የዘለላም ቅጣትን ከመቀበል አንቀርም፡፡
አራተኛ፡ ነገር ግን፣ ይህ ታላቁ “ነገር ግን” ነው፤ እግዚአብሔር ለእኛ የራሱን መፍትሔ አዘጋጅቷል አንድ ልጁን ጌታ ኢየሱስን በመስቀል ላይ ተሰቅሎ የእኛን የኃጢአት ቅጣት እንዲወስድ ሰጥቶናል፡፡ በእርሱም በኩል ብቻ ከቀረብን እዚህ ምድር ላይ እያለን ሰላምና አዲስ ልብ መቀበል የምንችል ሲሆን በሚመጣው ዓለም ደግሞ የዘላለምን መንግስት መውረስ እንችላለን፡፡ ማለትም በፍርድ ቀን ሊፈረድብን የሚገባው ፍርድ በጌታ በኢየሱስ ስለተወሰደ በእርሱ ስራ በኩል ወደ መንግስተ ሰማይ መግባት እንችላለን፡፡
ከዚህ የበለጠ ለነፍስ የሚሆን ምን ዓይነት የምስራች ዜና ይኖራል? ይህንን አስደናቂ ዜና ከመጀመሪያ እስከመጨረሻ የሚነግረን መጽሐፍና ምንም እንከን የሌለበት የእግዚአብሔር ቃል መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው፡፡
አብባቢዎች ሆይ ይህንን መጽሐፍ አግኝታችሁ እንድታነቡ በእግዚአብሔር ፍቅር እንጠይቃችኋለን እግዚአብሔርም በፍቅሩና በኃይሉ ይርዳችሁ፡፡
ለእስልምና መልስ አማርኛ ዋናው ገጽ