ለቃላቱ ለዋጭ የለም! 

“ከጌታህም መጽሐፍ ወደ አንተ የተወረደውን አንብብ፣
ለቃላቶቹም ለዋጭ የላቸውም ከርሱም በቀር መጠጊያን በፍጹም አታገኝም”
ቁርአን  18፡27

በ ዳንኤል

 

ቁርኣን በበርካታ ቦታዎች ላይ መጽሐፍ ቅዱስ እውነተኛ የአላህ ቃል መሆኑን ይናገራል፡፡ ሱራ 5፡44-48, 29:46, 10:37, 46:12, 6:91, 35:31, 2:40-42, 2:89, 3:3, 21:7, 2:285, 3፡93, 4፡47, 5፡68-69, 5፡6, 5፡15 ወዘተ፡፡

ነገር ግን በሁለቱ መጽሐፍቶች መካከል በሚገኙ ፍፁም ሊታረቁ በማይችሉ ተቃርኖዎች ሳቢያ ሙስሊሞች “መጽሐፍ ቅዱስ ከቀድሞ ይዘቱ ተለውጧል” ወደሚል ድምዳሜ ለመድረስ ተገደዋል፡፡ ይህንን እምነታቸውን ለማጠናከር ብዙ ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛሉ ብለው ስለገመቷቸውና “ግጭቶችና” “ብረዛዎች” ናቸው ስለሚሏቸው ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡ ይሁን እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛሉ ብለው ስለገመቷቸው “ስህተቶች” ከመናገርና ከመጻፍ ውጭ መጽሐፍ ቅዱስ መቼ፣ በማን እና የት ሀገር እንደተበረዘ ለመጻፍም ሆነ ለመናገር የደፈረ ይህንንም እምነቱን ማስረጃ ጠቅሶ ለማረጋገጥ የቻለ አንድም የሙስሊም ሊቅ አልተገኘም፡፡ ቀደም ሲል የተጠቀሱት የቁርኣን ጥቅሶች መጽሐፍ ቅዱስ በመሐመድ ዘመን በቀድሞ ይዘቱ መኖሩን አረጋጋጭ ናቸው፡፡ በመሐመድ ዘመንም ሆነ ከእርሱ በፊት በብዙ የአለም ቋንቋዎች ተተርጉሞ በተለያዩ የአለም ክፍሎች ተበትኖ እና በብዙ ሺህ ቅጅዎች ተጽፎ የተቀመጠ መጽሐፍ ተበርዟል ብሎ ማሰብ በራሱ የማይታመን ነው፡፡

ከሀገራችን ውጭ የሚገኙ ዛኪር ናይክን የመሳሰሉ ግለሰቦች እና በሀገራችን ውስጥ የሚገኙ የሃይማኖት ንጽጽር ትምህርት ተማሪዎች ነን ባዮች ቁርኣን ከመጽሐፍ ቅዱስ ይልቅ የጠራ እና ተአማኒ መሆኑን የማሣየት ከፍተኛ ጉጉት ስላላቸው በእነርሱ አባባል “የመጽሐፍ ቅዱስን ብረዛዎች ለማጋለጥ” የማይፈነቅሉት ድንጋይ የማይቧጥጡት ተራራ የለም፡፡ እነዚህ ወገኖች አንድ ያልተረዱት ነገር ግን ለእነርሱ እጅግ አደገኛ የሆነ እውነታ አለ፡፡ ይኸውም የመጽሐፍ ቅዱስን “ብረዛዎች ለማጋለጥ” ጥረት ሲያደርጉ በተዘዋዋሪ ደግሞ ቁርኣን እራሱ መሳሳቱን እያረጋገጡ መሆናቸውን ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እንደተለወጠ ለማሳየት በደከሙ ቁጥር የራሳቸውን መቀበሪያ ጉድጓድ አርቀው እየቆፈሩ መሆናቸውን አለማስተዋላቸው የገዛ መጽሐፋቸው እንኳ ምን እንደሚል በውል አለማወቃቸውን ያመለክታል፡፡

“መጽሐፍ ቅዱስ ቀድሞ የእግዚአብሔር ቃል ነበር አሁን ግን ተለውጧል” የሚሉት እነዚህ ወገኖች በተዘዋዋሪ ደግሞ የሚከተሉት የቁርኣን ጥቅሶች ውሸት መሆናቸውን እያረጋገጡ ነው፡-

      6፡34 “የአላህን ንግግሮች ለዋጭ የለም”

      6፡115 “ለቃላቱ ለዋጭ የለም”

      10፡64 “የአላህ ቃል መለወጥ የላትም”

      18፡27 “ለቃላቱ ለዋጭ የላቸውም”

      33፡62 “ለአላህ ድንጋጌ ፈጽሞ መለወጥን አታገኝም”

መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል ከነበረ፤ የእግዚአብሔርን ቃል ደግሞ መለወጥ የሚችል ከሌለ፤ መጽሐፍ ቅዱስ አልተለወጠም ማለት ነው፡፡ አለበለዚያ የአላህን ቃል ማንም መለወጥ እንማይችልና ቃሉ እንደማይለወጥ የሚናገሩት ከላይ የተጠቀሱት ጥቅሶች በሙሉ ውሸት ናቸው ማለት ይሆናል፡፡ ሙስሊም ሐያስያን መጽሐፍ ቅዱስን ለመተቸት ብዕሮቻቸውን ሲያነሱ የራሳቸው የሃይማኖት መጽሐፍ ውድቅ የሚሆንበትን መንገድ እየከፈቱ መሆናቸውን ማስተዋል ነበረባቸው፡፡ ሙስሊም ወገኖች መጽሐፍ ቅዱስ እንደተበረዘ መናገራቸው ቃሉን የመጠበቅ አቅም ከሌለው አምላክ ጋር የሚተዋቸው ሲሆን በተዘዋዋሪ ደግሞ ከላይ የተጠቀሱት የቁርኣን ጥቅሶች ስህተት ናቸው ወደሚል ድምዳሜ ያመራል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እና ቁርኣን ትክክለኛ መገለጦች መሆናቸውን በአንድ ጊዜ (በአንድ ላይ) መቀበል በምድር ወገብ ላይ ቆሞ በቀኝና በግራ እጅ የሰሜንና የደቡብ ዋልታዎችን በአንድ ጊዜ ለመንካት የመሞከር ያህል የማይታሰብ ነው፡፡ ስለዚህ ሙስሊሞች ያላቸው አማራጭ ሁለት ብቻ ነው የሚሆነው እነዚህም፡

1.      መጽሐፍ ቅዱስ እውነተኛ መገለጥ መሆኑን በመቀበል ቁርኣንን መጣል፡፡ ቁርኣን በአንድ ወገን መጽሐፍ ቅዱስ እውተኛ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን ካረጋገጠ በኋላ፣ በውስጡ በያዛቸው ትምህርቶች መጽፍ ቅዱስን መልሶ ስለሚቃረነው ተቀባይነት የሚኖረው ድምዳሜ የቁርኣን ጸሐፊ የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርቶችን ጠንቅቆ የማያውቅ ሰው ነበረ የሚል ነው፡፡ ስለዚህ የቁርኣን ጸሐፊ ሀሰተኛ መሆኑና ቁርኣንም የፈጣሪ ቃል ባለመሆኑ ቁርአንን አለመቀበል ነው፡፡

2.      መጽሐፍ ቅዱስም ቁርኣንም እውነተኛ መገለጦች እንዳልሆኑ ደምድሞ ሁለቱንም መጣል፡፡ ቁርአንን ብቻ እንደ እውነተኛ መገለጥ ተቀብሎ መጽሐፍ ቅዱስን አለመቀበል፤ ከላይ እንደተመለከትነው መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን በማረጋረጥ የእግዚአብሔር ቃል ፈጽሞ ሊለወጥ እንደማይችል በአጽንኦት በሚናገሩ የቁርኣን ጥቅሶች እና ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር በሚጋጩ የቁርኣን ትምህርቶች መካከል ባለው ውጥረት ሳቢያ የማይታሰብ ነው፡፡ በቁርኣን ውስጥ የሚገኙ መጽሐፍ ቅዱስ እውነተኛ የእግዚአብሔር ቃል እንደሆነ እና የእግዚአብሔርን ቃል ማንም መለወጥ አንደማይችል የሚናገሩት ጥቅሶች እውነት ናቸው ብለን ከተቀበልን፤ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚጋጩት የቁርኣን ትምህርቶች ስህተት ናቸው ማለት ነው፡፡ ነገሩ ሁሉ በጣም ግልፅ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ከተለወጠ የአላህ ቃል እንደማይለወጥ የሚናገሩት የቁርኣን ጥቅሶች ውሸት ይሆናሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ተለውጧል የሚለው የሙስሊሞች ክስ ውሸት ከሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚጋጩት የቁርኣን ክፍሎች ውሸት ይሆናሉ፡፡ በሁለቱም አቅጣጫዎች ቁርኣን አደገኛ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል፡፡ 

ይህንን ሐሳብ ስናጠቃልል ሙስሊሞች መጽሐፍ ቅዱስ ተበርዟል የሚለው ክሳቸው ተራ የመንደር አሉባልታ አለመሆኑን ለማረጋገጥ የሚከተሉትን ጥያቄዎች በበቂ ሁኔታ መመለስ ይጠበቅባቸዋል፡፡

1.      መጽሐፍ ቅዱስ መቼ በማን እና የት ሀገር ተበረዘ?

2.      የፈጣሪ ቃል ፈጽሞ ሊለወጥ እንደማይችል የሚናገሩትን የቁርኣን ጥቅሶች መጽሐፍ ቅዱስ ተለውጧል ከሚለው ሐሳብ ጋር እንዴት ማስታረቅ ይቻላል?

3.      እግዚአብሔር ቅዱስ ቃሉ የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ይለወጥ ዘንድ እንዴት እና ለምን ፈቀደ?

4.      መጽሐፍ ቅዱስ የተለወጠው ከመሐመድ ዘመን በፊት ወይንስ ከእርሱ በኋላ?

ሀ. ከእርሱ በፊት ከሆነ በእርሱ ዘመን መጽሐፍ ቅዱስ በቀድሞ ይዘቱ መኖሩን የሚናገሩት የቁርኣን ጥቅሶች እንዴት ይተረጐማሉ? (ለምሳሌ ሱራ 5፡43,  4፡47,  2፡89,  21፡7,  29፡46,  ወዘተ.)

ለ. ከእርሱ በኋላ ከሆነ በመሐመድ ዘመንና ከእርሱ በፊት የነበሩ እጅግ ጥንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ቀዳማውያን ጽሑፎች ተገኝተውና በተለያዩ ቤተ-መዘክሮች ውስጥ ተቀምጠዋል፡፡ ይዘታቸውም ሲመረመር አሁን ካለው መጽሐፍ ቅዱስ ጋር ፍፁም አንድ ነው፡፡ ይህንንስ ሀቅ ሙስሊሞች እንዴት ይመለከቱታል?

አንድ ከእስልምና ወደ ክርስትና የተመለሰ ግብፃዊ ክርስቲያን እንደተናገረው፡- “እውነተኛ የገንዘብ ኖት ከሀሰተኛ የገንዘብ ኖት ይቀድማል፡፡ ሐሰተኛ የገንዘብ ኖት ግን ከእውነተኛው ጋር ተመሳስሎ ኋላ ላይ ይሰራል፡፡” ፊተኛው መገለጥ የኋለኛውን ይመረምረዋል እንጂ የኋለኛው እንዴት የፊተኛውን ሊመረምር ይችላል? የኋለኛው ከፊተኛው ጋር የሚጋጭ ከሆነ ግልፅ የሆነው ድምዳሜ የኋለኛው ሀሰት መሆኑ ነው፡፡ የቁርኣን ጸሐፊ በአንድ ወገን መጽሐፍ ቅዱስ እውነተኛ የአምላክ ቃል መሆኑን ከመሰከረ በኋላ መልሶ ደግሞ በሌላ ወገን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚጋጩ መገለጦችን በማምጣቱ ሳቢያ የመጽሐፍ ቅዱስን ይዘት በቅጡ ያልተረዳ አላዋቂ ሰው መሆኑን በራሱ ላይ አስመስክሯል፡፡

ሙስሊም አንባቢዎች ሆይ! እስኪ ለአፍታ ያህል ቆም ብላችሁ ያሉትን ማስረጃዎች ለማገናዘብ ሞክሩ፡፡  በአንዳንድ አላዋቂዎች አሉባልታ ምክንያት የጣላችሁትን የፈጣሪያችሁን ቅዱስ ቃል ለማንበብ እና ለመመርመር ጊዜ ስጡ፡፡ ጌታ ለእናንተ ያለው ፍቅር ምን ያህል የጠለቀ እንደሆነ ትረዳላችሁ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስም ማን እንደሆነ በትክክል ታውቃላችሁ፡፡ ህይወታችሁም ይለወጣል፡፡ ለደህንነታችሁም ዋስትና ታገኛላችሁ፡፡ ልባችሁ በፀጋው ቃል ሲሞላ፤ ከጌታ ምርጦች ጋር ስትቀላቀሉ፤ ከገሃነም ፍርሃት ነፃ ስትወጡ፤ ቅዱስ መንፈሱ ልባችሁን በደስታ ሲሞላ፤ ያኔ እንዲህ በማለት የመዝሙረኛውን የዳዊትን ቅኔ መቀኘት ትችላላችሁ፡-

 “አቤቱ ቃልህ በሰማይ ለዘላለም ይኖራል
እውነትህ ለልጅ ልጅ ናት
ምድርን መሠረትሃት እርሷም ትኖራለች
ሁሉም ባርያዎችህ ናቸውና
ቀኑ በትዕዛዝህ ይኖራል
ህግህ ተድላዬ ባይሆን
ቀድሞ በጉስቁልናዬ በጠፋሁ ነበር
በእርሱ ህያው አድርገኸኛልና
ፍርድህን ለዘላለም አልረሳም፡፡” መዝ. 118፡89-96፡፡

የአዘጋጁ ማሳሰቢያ

መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ እግዚአብሔር ደግሞ የሰማይና የምድር ፈጣሪ ነው፣ ቃሉን ለመጠበቅና ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማስተላለፍ ስልጣንም ችሎታም ያለው አምላክ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ አልተለወጠም ማንም ሊለውጠውም አይችልም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ላለመለወጡ ብዙ ማስረጃዎች ይገኛሉ ታሪክንና የአርኪዎሎጂ ማስረጃዎችን የሚመለከት ሰው ይህንን በትክክል መረዳት ይችላል፡፡

ከዚህ በላይ የቀረበውን ጽሑፍ በጥንቃቄ ያነበባችሁ አንባቢዎች ሁሉ አንድ ነገርን እንድታደርጉ በእግዚአብሔር ፍቅር እንጋብዛችኋለን፣ ይህም መጽሐፍ ቅዱስን አግኝታችሁ እራሳችሁ እንድታነቡት ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን በጥንቃቄ ያነበቡ ሰዎች ያገኙትና በሕይወታቸው ከሚመሰከሩት የጋራ ነገሮች ውስጥ የሚከተሉት አሉበት፡

1.      መጽሐፍ ቅዱስ ለሰው ልጆች ነፍስ፣ ማለትም ለልባቸው የሚናገር ተናጋሪ መጽሐፍ መሆኑ፤

2.      መጽሐፍ ቅዱስ ለሰዎች ልጆች የውስጣቸውን አውጥቶ የሚያሳይ የውስጥ መስታዎት፣ ማለትም ሀሳብን፣ ስሜትን፣ ፍላጎትን ሁሉ የሚያሳይ የረቀቀ ማሳያ መሆኑን ነው፡፡

እንደዚህ ዓይነት መጽሐፍ አግኝቶ ማንበብ ጠቃሚ ብቻ ሳይሆን ወሳኝ ነው፡፡ ስለዚህም መጽሐፍ ቅዱስን አግኝታችሁ እንድታነቡትና የሚናገራችሁን እንድትሰሙት የሚያሳያችሁንም እንድታዩት እንጋብዛችኋለን እግዚአብሔር ይርዳችሁ አሜን፡፡

ለእስልምና መልስ አማርኛ  ዋናው ገጽ