የመለኮታዊ መገለጥ ድንቁርና?

መሐመድየነቢይነትን ፈተናበተደጋጋሚ እንዴት እንደወደቀ

Jochen Katz

ትርጉምና ቅንብር በአዘጋጁ

ቁርዓን መሐመድ ከአይሁዶች ጋር ስላደረገው አንድ ዓይነት ግጭት፣ ክርክራቸውንና አይሁዶች የመሐመድንና የእሱን መልእክት የተቃወሙበትን ነገር ይናገራል፡፡ ለምሳሌም በምዕራፍ 3.181-185 ውስጥ የሚከተለውን ዓረፍተ ነገር እናገኛለን፡-

‹እነዚያ ለማንኛውም መልክተኛ እሳት የምትበላው የኾነን ቁርባን እስከሚያመጣልን ድረስ ላናምን አላህ ወደኛ አዟል ያሉ ናቸው መልክተኞች ከኔ በፊት በታምራትና በዚያም ባላችሁት (ቁርባን) በእርግጥ መጥተውላችኋል እውነተኞች ከኾናችሁ ታዲያ ለምን ገደላችኋቸው? በላቸው፡፡› 3.183፡፡ በእርግጥ ይህ ምስጢራዊ የሆነ አረፍተ ነገር ነው ስለዚህም ምን ማለት እንደሆነ እንዲሁም ለምን ስህተትም እንደሆነ ለመረዳት እኛ ዓረፍተ ነገሩን መበተንና መመልከት ይኖርብናል፡፡

በእርግጥ የተጠቀሰው ይህ እሳት ሰዎች መስዋዕትን (ወይንም ሌላ ምንም ዓይነት ነገርን) ለማቃጠል የሚጠቀሙበት የተለመደው ዓይነት እሳት አይደለም፣ ነገር ግን ተዓምራታዊ እሳት ነው፡፡ ይህም አንድ እውነተኛ ነቢይን እውነተኛ ለመሆኑ አረጋጋጭ የሆነና በእግዚብሔር የሚሰጥ እሳት እንደሆነ ተገምቶ (የቀረበ) ነው፡፡ ማለትም ይህ ጥቅስ የሚገልጠው ወይንም የሚያመለክተው ከሰማይ የሆነን እሳት ነው፡፡ መስዋዕቱን የሚበላውን እሳት የሚሰጠው እራሱ እግዚአብሔር ነው፡፡ የዚህ ዓይነቱም መረዳት በብዙዎቹ የሙስሊም ተርጓሚዎች ትርጉም ውስጥ የተደገፈ ነው፡፡ እኔ እዚህ የሁለቱን ብቻ እጠቅሳለሁኝ፡

እነዚያ:-  ‹በእርግጥ አንድ መልእክተኛ ከሰማይ እሳት መጥታ የምትበላውን መስዋዕት የሚያቀርብ እስካልሆነ ድረስ አናምንም ብለን የገባነውን ቃል ኪዳን አላህ ተቀብሎልናል› ያሉት አይሁዶች የሚሉት ‹በእርግጥ ወደ እናንተ ከእኔ ዘንድ መልእክተኛ መጥቷል በግልጥ ምልክት እንዲያውም እናንተ (እራሳችሁ) በተናገራችሁት(ታዲያ) እውነተኞች ከሆናችሁ ለምን እናንተ ገደላችኋቸው?› በማለት አላ-ሂላሊ እና ካሃን ተርጉመዋል፡፡

እነዚያ እንዲህ ያሉት፡-  ‹በማንኛውም መልእክተኛ እንዳናምን አላህ አዞናል ከሰማይ እሳት ወርዳ የምተበላውን መስዋዕት እስካላመጣ ድረስ ብለው ላሉት እንዲህ በላቸው፡፡ ለእነሱ መልስላቸው፡ እናንተ በተናገራችሁት በዚያ ተዓምራት ከእኔ በፊት ወደ እናንት መልእክተኞች በተዓምራት መጥተውላችሁ ነበር፡፡ እናንተ እውነተኞች ከሆናችሁ ታዲያ ለምን እናንተ ገደላችኋቸው?› ፒክታል፡፡

መሐመድ ስለማን ነው እየተናገረ ያለው?

የትኛው ነቢይ ነው ከሰማይ እሳት ወርዳ የበላችውን መስዋዕት ያቀረበና የተገደለው? ከዚያስ በማን ነው የተገደለው? በጣም ቅርብ የሆነውና የዚህ ጥቅስ ሰፊው ዓውድ የሚያሳየው ነገር መሐመድ ከአንዳንድ አይሁዶች ጋር ያደረገው ክርክር ይህን በተመለከተ እንደሆነ ያሳያል (ይህም አል-ሂላሊ እና ካሃን በትርጉማቸው ላይ እንዳሳዩት ነው)፡፡ ስለዚህም የዚህ ውይይት የማስረጃ ነጥብ መሆን ያለበት የአይሁድ ቅዱስ መጽሐፍ የብሉይ ኪዳን መሆን አለበት፡፡

መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃዎች፡- በነቢያት በመሳፍንት እና በእስራኤል ንጉስ የቀረቡ መስዋዕቶችን የምትበላ እሳትን እግዚአብሔር ከሰማይ በተለያዩ ጊዜያት መላኩ እውነት ነው፤ ለዚህም ማስረጃ የሚሆን (ሌዋውያን 9.23-24፤ መሳፍንት 6.20-22፤ 1ዜና 21.26፤ 2ዜና 7.1-3 እና 1ነገስት 18) ክፍሎች ላይ ይገኛል፡፡ ከዚህም በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሐሰተኛ ነቢያት በመናገር የእስራኤል ልጆች ከእውነተኛዎቹ ነቢያት እንዲለዩአቸው የተለያዩ መለያዎችን እንደሰጣቸው ነው፡፡ በ1ነገስት 18 ላይ እንደተገለፀው ከሰማይ የተላከችው እሳት የነቢዩ ኤልያስ መለኮታዊ ስልጣን ከእግዚአብሔር መሆኑን ምልክት ሆና ለማሳየት፡፡ እንዲሁም የበዓል ነቢያቱ አምላክ - በዓል - ሐሰተኛ መሆኑን ለማሳየት መስዋዕቱን መብላቷ እርግጥ ነው፡፡

ይሁን እንጂ ‹መስዋዕትን የሚበላ እሳት ከሰማይ ማምጣት› ነቢይ ነኝ ከሚል ሁሉ አይሁዳውያኑ የሚጠይቁት የመለያ መስፈርት ሆኖ በእስራኤላውያን በፍፁም ተቀምጦ አያውቅም ነበር፡፡ እንደዚህም ዓይነት የሆነ ትዕዛዝ በፍፁም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የለም፡፡ እንዲህም ዓይነት ቃል ኪዳን በፍፁም የለም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በእግዚአብሔር ተልከው የነበሩት እጅግ በጣም ብዙዎቹ እውነተኛ ነቢያት ይህን አንድ ዓይነት ተዓምር ብቻ በፍፁም ተለማምደውት አያውቁም፡፡ ስለዚህም እኛ እዚህ ላይ አንድ ጥያቄን መጠየቅ ይኖርብናል ጥያቄውም ‹ማነው የዋሸው?› የሚል ነው፡፡

አንደኛ፡- ‹ለማንኛውም መልእክተኛ እሳት የምትበላው የኾነን ቁርባን እስከሚያመጣልን ድረስ ላናምን አላህ ወደኛ አዟል› የሚለው ዓረፍተ ነገር በእነዚህ አይሁዶች የተነገረ ውሸት ነበር፤ ወይንም ይህንን ስህተት የሆነ ዓረፍተ ነገር በአይሁዶች አንደበት ውስጥ በማስቀመጥ እነሱ ምንም እንኳን በፍፁም ባይናገሩትም (እንደተናገሩት በማስመሰል) በቁርዓን ጸሐፊው በመሐመድ የተነገረ ውሸት ነበር ማለት ነው፡፡

በሁለተኛው በኩል መሐመድ በአይሁዶች አንደበት ይህንን ነገር በማስቀመጥ እራሱ የፈጠረው የውሸት ክርክር ከሆነ፣ እሱ ውሸታም ነው የሚሆነው፡፡ ስለዚህም እሱ ለእግዚአብሔር ነቢይነት አይበቃም፡፡ የቁርአን ጸሐፊ ስለ አይሁዶች የውሸት ዓረፍተ ነገርን ፈጥሮ ከሆነ (ለነገሩ ስለማንም ሰው ቢሆን) ቁርአን የሚጋለጠው እንደርካሽ የሃይማኖት መከራከሪያ መሳሪያ ሆኖ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህም እውነት ከሆነው ከእግዚአብሔር ሊመጣ አይችልም ማለት ነው፡፡

በመጀመሪያው በኩል ከሆነ ደግሞ መሐመድ በእግዚአብሔር መገለጥ የተላከ መሆኑን ለማሳየትና እና አይሁዶችን ለማጋለጥ እጅግ ፍፁም የሆነ አጋጣሚ ነበረው ማለት ነው፡፡ ስለዚህም በቀላሉ እሱ እንደሚከተለው ማለት ይችል ነበር፡ ‹እግዚአብሔር እናንተ እንደምትዋሹ ነግሮኛል፡፡ ይህን የታዘዛችሁበትን ከቅዱስ መጽሐፋችሁ ውስጥ አሳዩኝ!› ማለት ይችል ነበር፡፡ እነሱም ይህንን ለማሳየት አይችሉም ነበር፡፡ የእሱ ተቃዋሚዎችም አፋቸውን ይዘጉ ነበር መሐመድም ተቀባይነት ያገኝ ነበር፡፡

ከዋናው ሐሳብ ወጣ ያለ አመለካከት፡

መሐመድ በተደጋጋሚ ምንም ተዓምራትን ለማድረግ ባለመቻሉ የተነሳ በአዕምሮ ሐሳብ ላይ መታገል ነበረበት፡፡ ከእሱ በፊት የተላኩትን ነቢያት ከላከው ከአንዱ አምላክ እንደተላከ ተናግሯል፡፡ በአንድ በኩል ከእሱ በፊት ስለመጡት ነቢያት ታሪክና በእነሱም ስለተደረጉ ብዙ ተዓምራት በመልእክቱ ውስጥ ጨምሯል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በአዳማጮቹ እንደ አንድ ሌላ ነቢይ ተቀባይነትን እንዲያገኝ እየጠየቀ ነው፤ ይሁን እንጂ ከመለኮት ለመሆኑ ምንም መለኮታዊ የሆነ ማረጋገጫን አላሳየም፡፡

ስለዚህም መሐመድ በተደጋጋሚ በተጠራጣሪዎች ጥያቄ ይጠየቅ የነበረ መሆኑ ምንም አያስደንቅም፡ ‹ከጌታ ዘንድ ምልክት ወይንም ተዓምራት ለእሱ ለምን አይመጣለትም?› ወይንም ተመሳሳይ የሆነ አንዳንድ ነገር፡፡ እንደዚህ ዓይነት ጥያቄዎች በቁርአን 2.118፣ 6.37፤ 10.20፤ 11.12፤ 13.7፤ 20.133፤ 29.50 ላይ ይገኛሉ፡፡ መሐመድ የቁርአኑ ጸሐፊ እንደዚህ ዓይነት ጥያቄዎችን የሚመልስባቸው እጅግ ብዙ የተለያዩ መንገዶች ነበሩት፡፡ እጅግ ብዙ ጊዜ ተደጋግሞ ይሰጥ የነበረው መልስ እግዚአብሔር እንዲህ ዓይነትን ተዓምራትም እንኳን ቢያደርግ እነሱ እንደማያምኑ መናገር ነበር ይህም በ2.145፤ 17.59፤ 28.48፤ 37.14-15 ጥቅሶች ላይ ተገልጧል፡፡ ማለትም ተዓምራትን መስጠት ምንም አስፈላጊ አይደለም ነው፡፡ (መሐመድና ተዓምር የሚለውን ዝርዝር የቁርአን አንቀፆችን በተመለከተ ወደፊት እናቀርባለን)፡፡

ስለዚህም 3.183 የሚካተተው ከእነዚህ ዓይነት የጥቅስ ቡድኖች ውስጥ ነው፡፡ ማለትም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የመሐመድን ተዓምራት ያለመስራትን ችግር ሰዎች እንዳይመለከቱ ትኩረታቸውን በመቀየርና ተዓምራትንም መስጠት ምንም ጥቅም እንደሌለው ማሳየት ነው፡፡ የአይሁዶች ጥያቄ እዚህ ጋ በተለይም በውስጠ ታዋቂ መልስ አዘል ጥያቄ መንገድ ሲመለስ እንመለከታለን ይህም -  የተለያየ ተዓምራትን ያሳዩአችሁን ማለትም አሁን እኔን አሳየኝ ብላችሁ የምትጠይቁኝን ዓይነት ተዓምራትን ያሳዩአችሁን የቀደሙትን ነቢያት ገድላችሁ እያለ አሁን ከእኔ ተዓምራትን ለምን ትጠይቁኛላችሁ? የሚል ነው፡፡

ወደዚህ ጽሑፍ ዋና ርዕስ እንመለስ፡፡ ቁርአን ምዕራፍ 3.183 የሚያቀርበው የተሳሳተ ዓረፍተ ነገርን ነው፡፡ ይህም የመሐመድን ነቢይነት የሚናገረውን ነገር ስለተቃወሙ አንዳንድ አይሁዶች እንደተናገሩት ተደርጎ የተጨመረ ነው፡፡ እነዚህ የተለዩ አይሁዶች በዚህ ‹መለኮታዊ መስፈርት› መሐመድን ለመፈተን ወይንም ለማታለል መሞከር አለመሞከራቸውን ላናውቅ እንችላለን፣ ይሁን እንጂ ቁርአን ግን በቀጥታ መዝግቦታል ወይንም መሐመድ ስለ አይሁዶች መዋሸቱን ቁልጭ አድርጎ አቅርቦታል፡፡

ይህ እንዳለ ሆኖ እዚህ ላይ የሚመጣው ጥያቄ - ስለቀደመው የእግዚአብሔር መገለጥ የውሸት ጥያቄ ሲመጣ - አንድ እግዚአብሔር መገለጥን ሰጥቶኛል የሚል ነቢይ መመለስ ያለበት እንዴት ነው? የሚል ነው፡፡ ምንም እንኳን መሐመድ ተዓምራትን ማድረግን ባይችልም እሱ የእነሱን የውሸት ጥያቄ ቢያጋልጠው ኖሮ እሱ በራሱ ተቀባይነት በኩል የሆነ እድገትን ማሳየት ይችል ነበር፡፡

ይሁን እንጂ የእነሱን ጥያቄ እንደ ውሸት ከማሳየትና ፈጠራ መሆኑን ከማሳየት ይልቅ እሱ የጠያቂዎቹን እውነተኛነትንና ትህትናቸውንም ሲያጠቃ ነው የሚታየው፡፡ እነሱ ለነቢይነት ከሰጡት የመለያ መስፈርት ጋር ከመደራደር ይልቅ እሱ የተጠቀመው የእሱን ደስ የማያሰኝ የራሱን ተቀባይነት ለማስወገድ ሲል ስሜታዊ የሆነ አቀራረብን ነው፡፡

እነዚህ አይሁዶች በመሐመድ ፊት የነቢይነትን መለያ መስፈርት አስቀምጠዋል ይህም እሱ ሊያሟላው የማይችለው ነበር፡፡ እነሱን ማጥቃት እንደራሱ የተለየ መከላከያ መንገድ በመቁጠር መሐመድ በአፀፋው የእነሱን እውነተኛነት ጥያቄ ውስጥ አስገባው፡፡ ውንጀላና መደምደሚያ ሆኖ በውስጡ ምላሽን ያዘለ አነጋገር ተሰጠው ይህም፡- በተዓምራት ወደ እናንተ የተላኩትን ነቢያትን ስለገደላችሁ እናንተ እውነተኞች አይደላችሁም ስለዚህም እኔን ለመጠየቅ ምንም መብት የላችሁም የሚል ነው፡፡ ጥያቄውም - ለእውነተኛ ነቢይ መለያ መስፈርቱ ምንድነው? ከሚለውና መሐመድም ያንን መስፈርት ያሟላል ወይ? ከሚለው ውስጥ በድንገት ወጥቶ አሁን አነጋጋሪ እየሆነ የመጣው ነገር መሐመድን የጠየቁት ሰዎች እውነተኝነት ወይንም ሐቀኝነት ሆኖ መጣ፡፡

መሐመድ እውነተኛ የእግዚአብሔር ነቢይነቱን ጥያቄ በምንም የተዓምራት ስራ ለማረጋገጥ ያለመቻሉ እውነታ እንዳለ ሆኖ እያለ አሁን ሊያደርግ የሚችለው የተሻለው ነገር ምናልባትም ይህ ብቻ ነው፡፡ በአንድም መንገድ ይህ እጅግ የብልጥነት እንቅስቃሴ ነው፡፡ እጅግም መጥፎ የሆነው ነገር ደግሞ ቁርአን መሐመድ ላደረገው የመቀልበስ (አቅጣጫ የመቀየር) ዘዴ አይሁዶች ለሰጡት አስተያየት ምንም ክፍተትና ቦታን አልሰጠም፡፡ ይሁን እንጂ እነዚያ ተጠራጣሪ አይሁዶች ለመሐመድ እውነተኛነት የማያቋርጥ ጥያቄዎች ነበሩ፡፡ ስለዚህም እሱ የነቢይነቱን ደረጃ በተደጋጋሚ ጥያቄ ውስጥ ሲገባ በመመልከት ለመታገስ ፈቃደኛ አልነበረም፡፡ ስለዚህም መሐመድ እነሱን ለማስወገድ (ለማጥፋት) ወሰነ ስለዚህም በመዲና ውስጥ ይኖሩ የነበሩትን አይሁዶች በሙሉ አስወጣቸው ወይንም ገደላቸው ይህንንም ያደረገው ችግሩን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድ ነበር ይንንም እውነት የበለጠ ለመገንዘብ (መሐመድና አይሁዶች የሚለውን በቅርቡ የሚወጣውን ጽሑፍ ይመልከቱ)፡፡

ፍፁም ካልሆነ ሰው እንደመጣ አድርገን የመሐመድን የግል ምላሽ ብንመለከተው ሁሉን ነገር እንረዳዋለን፡፡ ይሁን እንጂ እስላም እኛን እንድናምን የሚጠብቀን ቁርአንን የመሐመድ ቃል ሳይሆን የእግዚአብሔር ቃል እንደሆነ አድርገን ነው፡፡ ለአይሁዶቹ የተሰጠው የመሐመድ መልስ የመሐመድ ሐሳብ ሳይሆን እግዚአብሔር እንዲመልስ የነገረው መልስ እንደሆነ ነው፡፡ ይህም ደግሞ እጅግ በጣም ብዙ ችግሮችን ያስከትላል፡፡

እግዚአብሔር በአይሁዶቹ የተቀመጠው (የተሰነዘረው) መስፈርት ትክክል እንዳልሆነ በትክክል ያውቃል፡፡ እግዚአብሔር እንዲህ ዓይነት ትዕዛዝ በፍፁም ሰጥቶ አያውቅም እንዲሁም እሱ የቀደሙትን መገለጦቹን በፍፁም የሚረሳም አይደለም፡፡ እግዚአብሔርም እነሱ የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ የፈጠሩ መሆናቸውን የሚያጋልጥና ወሳኝ የሆነን መልስ ይሰጣቸው ነበር፡፡

መሐመድ በሌላው በኩል ደግሞ በጉዳዩ ላይ ምንም የማያውቅ ነበር፡፡ እሱ ምናልባትም እነዚህ አይሁዶች ሊያታልሉት እንደሚሞክሩ ተጠራጥሮ ሊሆን ይችላል ነገር ግን ያስቀመጡት መስፈርት ከቅዱስ መጽሐፋቸው ላይም ለመወሰዱ ምንም እርግጠኛ አልነበረም፡፡ በዚህም ነጥብ በተለየ ጉዳይ ላይ እነሱን አሳስታችኋል በማለት በቀጥታ ሊከሳቸው አልቻለም፡፡ ስለዚህም ለመልሱ እንዲህ ያለ መደምደሚያ ላይ ደረሰ፡ ‹እናንተ እውነተኞች ብትሆኑ› ይህም የእሱ የአፀፋ ጥቃት ብቻ ሳይሆን የራሱንም አለማወቅ (ድንቁርና) መቀበሉም ጭምር ነበር፡፡ ይህ ነው እንግዲህ መልሱ ከእግዚአብሔር ሳይሆን ከራሱ ከመሐመድ የመጣ ለመሆኑ የመጀመሪያው ማስረጃ፡፡

በተጨማሪም ደግሞ ይህ ምላሽ የሚጠቁመው የጸሐፊውን እርግጠኛ አለመሆን ብቻ ሳይሆን ግልጥ የሆነ ስህተትንም እንደያዘ ነው ስለዚህም እሱ ስለ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምንም እውቀት እንደሌለውም የሚያረጋግጥና የሚያጋልጥ ነው፡፡ መሐመድ ስለ እነዚህ አይሁዶች ቅንነት ወይንም እውነተኝነት ብቻ አይደለም የሚጠይቀው ነገር ግን ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ሊታይና ሊረጋገጥ የሚችልን አዎንታዊ ዓረፍተ ነገርንም ነው ያስቀመጠው፡፡ መልሱም ‹ከእኔ በፊት ወደ እናንተ መልእከተኞች መጥተውላችሁ ነበር በግልጥ ምልክት እናንተ አሁን በምትናገሩበትም እንኳን ታዲያ ለምን ገደላችኋቸው …› የሚለው አነጋገር ሦስት ነገሮችን እውነት እንደሆኑ አድርጎ ያቀርባል፡-

1. ከእግዚአብሔር የመጡ መልእክተኞች ወደ አይሁዶች በግልጥ ምልክቶች ማለትም በተዓምራት መጥተው ነበር፡፡

2. ቢያንስ አንዳንዶቹ እነዚህ ነቢያት እራሳቸው ያዘጋጁትን መስዋዕት የሚበላን እሳት ከሰማይ በማምጣት በግልጥ ምልክት መጥተው ነበር፡፡

3. አይሁድ እነዚህን መልእክተኞች ገደሏቸው፡፡

መሐመድ የሚናገረው ስለማነው? የእነዚያ መልእከተኞች ስም ማነው? እንደገናም መሐመድ ስለ ዝርዝር ሁኔታውም እርግጠኛ አይደለም፡፡ ስለዚህም ዓረፍተ ነገሩ (እራሱ) የተምታታ ሆኖ ነው የቀረው፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ሐሳብ በቀርሜሎስ ተራራ ላይ ከበዓል ነቢያት ጋር ከተገዳደረው ከኤልያስ ታሪክ ላይ የተወሰደ ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም 1ነገስት 18 ይህም በጣም የታወቀው የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ንብረት ነው፡፡ (ቢያንስ 1 ነገስትን 18.25-39 ላይ ያለውን አንብቡ)፡፡ ታሪኩን የማታውቁት ከሆነ ደግሞ ከ1ነገስት 16.29 ጀምሮ ብታነቡት ጠቅላላ ሐሳቡን ለማግኘት ትችላላችሁ፡፡

ስለዚህም

የመጀመሪያው ዓረፍተ ነገር ትክክል ነው፡ እግዚአብሔር መልእክተኞችን/ነቢያትን ወደ እስራኤላውያን ልኮ ነበር አንዳንዶቹም ደግሞ ተዓምራትን አድርገው ነበር፡፡

ሁለተኛው አረፍተነገር አጠያያቂ ነው፡- ቁርዓን የሚናገር የሚመስለው በአደባባይ መስዋዕትን ያዘጋጁ መልእክተኞችን እና እግዚአብሔር መስዋዕታቸውን ከሰማይ እሳት ልኮ እንድትበላ ያደረጋላቸው መኖራቸውን ነው፡፡ ይህም የእውነተኛ ነቢይነታቸው ማረጋገጫ እንደሆነ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ዓይነት ተዓምራት ተሰጥቶት የነበረው ነቢይ ኤልያስ ብቻ ነበር ይህም ተጠራጣሪ በነበረ ተመልካች ፊት ሕዝቡ የኤልያስ አምላክ እውነተኛ አምላክ መሆኑን እንዲያዩ ነበር እንዲሁም ኤልያስ በእውነት በእግዚአብሔር የተላከ መሆኑንም ጭምር እንዲያዩ ነበር፡፡

መስዋዕት ከእግዚአብሔር በተላከ እሳት የተበላበት ሌሎችም ተጨማሪ ሁኔታዎች አሉ ነገር ግን በማናቸውም በነዚህ ሁኔታዎች የእሳቱ መላክ ነቢዩን ከእግዚአብሔር ለመላኩ ማረጋገጫ እንደሆነ የሚያሳይ ምንም ዓላማ የለባቸውም፡፡ በሌዋውያን 9.23-24 ላይ በሙሴ ትዕዛዝ መሠረት በአሮን የተዘጋጀውን መስዋዕት ከእግዚአብሔር ዘንድ የመጣች እሳት በልታዋለች፡፡ ይሁን እንጂ ሙሴ እጅግ ብዙ ተዓምራትን አድርጓል ሕዝቡም አንዴም የእሱን የመለኮት ስልጣን አልተጠራጠሩም፡፡ እሳቱ ሙሴ ነቢይ መሆኑን ለማረጋገጥ አልመጣም፡፡ ሁኔታውም የአሮንን እና የልጆቹን የክህነት አገልግሎት መርቆ መጀመር ነበር፡፡ በመሳፍንት 6.20-22 ላይ ደግሞ የጌዲዮን መስዋዕት በእግዚአብሔር እሳት ሲበላ እንመለከታለን ነገር ግን ሁኔታው ለጌዲዮን የሚናገረው ነገር ሊጠቀምበት የጠራው እርሱ እግዚአብሔር እንደሆነ የሚያረጋግጥ ምልክት ነበር፡፡ ይህም ጌዲዮን ወደ ሕዝቡ የሚያመጣው የነበረ ምልክት አልነበረም፡፡ በዚያም ቦታ ማንም ሰው አልነበረም፡፡ በ1ዜና 21.26 ላይ ደግሞ ዳዊት የንስሐ ፀሎትን ከፀለየ በኋላ እግዚአብሔር በመስዋዕቱ ላይ እሳትን ላከ ይህም እግዚአብሔር የዳዊትን ንስሐ ለመቀበሉ እንደምልክት ሆኖ ነበር፡፡ ዳዊት የእስራኤል ንጉስ ነበር ስልጣኑን ጥያቄ ውስጥ ያስገባው አንድም ሰው አልነበረም፡፡ እሳቱም የተላከው ዳዊትን እንደ ንጉስና እንደ ነቢይም ተቀባይነትን እንዲያገኝ ምልክት ሆኖ አልነበረም ነገር ግን የእሱ ንስሐና መስዋዕት በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት እንዳገኘ ለማሳየት ብቻ ነበር፡፡ በመጨረሻም በ2ዜና 7.1-3 ላይ እግዚአብሔር የቤተ መቅደሱ ምረቃ ጊዜ ሰለሞን ፀሎትን ሲፀልይ እግዚአብሔር እሳትን ከሰማይ ልኮ ነበር፡፡ እዚህም ጋ አሁንም አንደገና ስለ ሰለሞን ስልጣን ምንም ጥያቄ አልነበረም፡፡ እሱ ንጉስ ነበር እግዚብሔርም ይህንን እሳት የላከው ቤተመቅደሱን እንደ ራሱ ማደሪያ ቦታ የተቀበለው መሆኑን ምልክት እንዲሆን ለመግለጥ ነበር፡፡

ስለዚህም በመስዋዕት ላይ እሳትን በመላክ በሕዝብ ፊት ነቢይን ነቢይ ለመሆኑ ማረጋገጫ ተሰጥቶ የነበረው አንድ ጊዜ ብቻ ነበር ያም በኤልያስና በበዓል ነቢያት ፊት በነበረው ተግዳሮት ጊዜ በቀርሜሎስ ተራራ ላይ ነበረ 1ነገስት 18፡፡ ስለዚህም ሁለተኛው ዓረፍተ ነገር ማለትም እግዚአብሔር ብዙዎቹን ነቢያት ለማረጋገጥ ያዘጋጁትን መስዋዕት እሳት በመላክ ይበላ ነበር የሚለው ስህተት ነው፡፡

ሦስተኛው ዓረፍተ ነገር ሙሉ በሙሉ ስህተት ነው፡፡ እኛ ከዚህ በላይ ስማቸው የተጠቀሱትን ሰዎች መስዋዕታቸውን እግዚአብሔር እሳትን ልኮ ሲበላ ያዩትን ሰዎች ልምድ (ሙሴን፣ አሮንን ጌዲዮንን ዳዊትን ሰሎሞንን እና ኤልያስን) ሁሉ ብንፈቅድም ከእነሱ መካከል አንድም ሰው በአይሁዶች አልተገደለም፡፡ የሚገርመው ለዚህ ምልክት የሆነው ብቸኛው ነቢይ ኤልያስ ደግሞ ብንወስድ እሱ በዚህ ምድር ላይ ሞትን በጭራሽ አልቀመሰም፡፡ ነገር ግን በእግዚአብሔር ወደ ሰማይ ተወስዷል 2ነገስት 2.11፡፡ በእርግጥ ኤልያስን ለመግደል እቅዶች ነበሩ፤ ነገር ግን እሱን ለመግደል ያቀዱት አይሁዶች አልነበሩም፡፡ አካአብ የእስራኤሉ ንጉስ ኤልዛቤልን አግብቶ የነበረው የሌላ አገር ሴትና የአሕዛብን የጣዖት አምልኮ ከእራስዋ ጋር ወደ እስራኤል አምጥታ የነበረችው ነበረች፡፡ እሷ ኤልያስን ለመግደል ትፈልግ ነበር ይህም እሱ የሐሰት ነቢያቱን ከረታና ከገደላቸው በኋላ ነበር 1ነገስት 19.1-2፡፡ ይሁን እንጂ ኤልያስን እግዚአብሔር ጠበቀው እናም በስተመጨረሻ ላይ ሳይሞት ወደ ሰማይ ተወሰደ 2 ነገስት 2.11፡፡

ብዙ ጊዜ እንደሆነው ሁሉ የቁርዓን ጸሐፊ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን ያምታታቸዋል፡፡ ወደ አይሁድ ተልከው የነበሩ ብዙ ነቢያት ተሰደዋል እንዲሁም ተገድለዋል ይህ እውነት ነው፡፡ እንዲሁም ደግሞ ከእግዚአብሔ የመጣች እሳት ያዘጋጁትን መስዋዕት የበላችላቸው ሰዎች መኖራቸው እውነት ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከእነዚህ ሰዎች ማለትም ‹እሳት ከሰማይ የመጣችላቸው› አንዳቸውም በአይሁድ አልተገደሉም፡፡ ይህንንም እግዚአብሔር በእርግጥ ያውቃል፡፡ ነገር ግን መሐመድ ዝርዝሮቹን አያውቅም ስለዚህም ብዙውን ጊዜ መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆኑትን ታሪኮች ያምታታቸዋል፡፡ ይህም ስህተት እጅግ በጣም ጠንካራ የሆነ ማስረጃ ነው፡፡ ቁርአን የመሐመድ ፈጠራ ለመሆኑ እና በእሱ ለመጻፉ ማስረጃ ነው፡፡ ስለዚህም ለአይሁዶች የሰጠው መልስ እግዚአብሔር የሰጠው ምላሽ አልነበረም የራሱ የፈጠራ መልስ ነበር እንጂ፡፡

አሁንም ለአይሁዶች የተሰጠው ምላሽ በመሐመድ የተፈጠረ ነበር በውስጡም ያለው ስህተት የሚያጋልጠው ነገር ቢኖር የጸሐፊውን አለማወቅ ነው (ድንቁርና ነው)፡፡ ይህ በቁርአን ውስጥ ያለ የስህተት ጥያቄ ነው፡፡ ይህም የተቀናበረው በመሐመድ በራሱ ለመሆኑና ጠንካራ - እሱ ከመለኮት መገለጥ የተቀበልኩት ነው - ለሚለው ስህተትነት ጠንካራው ማስረጃ ነው፡፡ ከእነዚህ እውነቶች ስንነሳ እግዚአብሔር የቁርአን ጸሐፊ ነው ብሎ ማለት ለእግዚአብሔር ሊሆን የሚችለው - ስድብ ነው - ምክንያቱም እግዘኢብሔርን ምንም የማያውቅ ሲያደርገው በቁርዓን ውስጥ ላሉት ስህተቶች እንዲወቀስ ያጋልጠዋልና፡፡

ያለምንም ጥያቄ ነቢይነትን የመፈተን ጉዳይ እጅግ በጣም ጠቃሚ ጉዳይ ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እግዚአብሔር ስለጉዳዩ ብዙ ጊዜ ተናግሯል ይህም እውነተኛ ነቢያትን ከሐሰተኞ እንዴት ልንለይ እንደምንችል ነው፡፡ መሐመድን ይህ ጥያቄ እጅግ በጣም ብዙ ጊዜ አጋጥሞታል፡፡ ነገር ግን ይህ አቢይ የሆነ ጉዳይ በቁርአን ጸሐፊ ብዙ ጊዜ ወደ ጎን ተጥሏል፡፡ አይሁዶች በመስፈርት መጡ፡፡ ለምንደነው አላህ የእነሱን የተሳሳተ መስፈርት አርሞ በትክክለኛው መስፈርት ያላስተካከለው? ነገር ግን መሐመድ ነገሩን በቀላሉ አድበስብሶ ጥያቄ ያቀረቡትን ሰዎች በስሜት ገንፍሎ አጠቃቸው፡፡ ከእግዚአብሔር እኔ የምጠብቀው ነገር ያንን አይደለም፡፡ ይህ ለእግዚአብሔር የማይገባ ነገር ነው፡፡ የጥቅሱ ፈጣሪ በመሆኑ - ያም ምርመራ እንደዚሁ የሚጠቁመው ወደ መሐመድም ጭምር ነው፡፡ መሐመድ ለዚህ ነገር ምንም መልስ የለውም ነበር፡፡

ይህን በተመለከተ ሊኖር የሚችል የሙስሊሞች ተቃውሞ

አንዳንድ ሙስሊሞች በዚህ ጥቅስ መሠረት ለመሐመድ የቀረበውን ክስ ለማስወገድ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ ይህንንም ሲያደርጉ የሚጠቀሙት መጽሐፍ ቅዱስን ወይንም ኤልያስን ተሳስተዋል በማለት ነው ወይንም ደግሞ ይህ ክፍል ስለ ኤልያስ አይናገርም የሚናገረው የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ታሪክ ስላልመዘገባቸው ስለሌሎች ነቢያት ነው ይላሉ፡፡

እንደዚህ ዓይነቱ ገለፃ አይሰራም፡፡ ለማንኛውም የመሐመድ የአፀፋ ጥቃት በአይሁዶች ላይ የተደረገው እሱ ስለምን እንደሚናገር ካወቁ - የእነሱን አፍ ለማዘጋት ብቻ የተደረገ ነው፡፡ ማለትም እነሱ ከሰማይ እሳትን ያመጣና በአይሁድ የተገደለ ነቢይ አለ የሚለውን ካወቁ የመሐመድ መልስ እነሱን ሊያሳምናቸው በፍፁም አይችልም ነገር ግን ምንም የማያውቅ መሆኑ የሚያስቃቸው ብቻ ነበር የሚሆነው፡፡ አይሁዶች ስለነቢያቶቻቸው ሊያውቁ የሚገባቸው ነገር ሁሉ በቅዱስ መጽሐፍቶቻቸው ውስጥ ይገኛል፡፡ ምላሹም በቅድሚያ የሚጠቁመን ይህ በአይሁዶች ዘንድ የታወቀ እውነት ነው የሚለውን ነገር ነው፡፡ ነገር ግን መሐመድ በዚህ ቅድመ ሐሳብ መሠረት ስህተት ነበር፡፡ እንደገናም ደግሞ እነዚህ አይሁዶች በምላሹ ሊሉ የሚችሉትን ነገር መስማትን እንወድ ነበር ይህም ለመሐመድ በቀጥታ ምላሽን በመስጠት ወይንም ደግሞ በራሳቸውም መካከል በመነጋገርም እንኳን ቢሆን ነገር ግን ቁርአን ይህንን በፍፁም አልዘገበውም፡፡

የውስጥ ቅራኔ

እስካሁን የተመለከትነው በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ሦስተኛው ዓረፍተ ነገር ስህተት መሆኑን ነው፡፡ ይሁን እንጂ ነገሩ ከዚያም በላይ የከፋ ነው የሚሆነው፡፡ የቁርአን ፀሐፊ ያንን ብቻ አልተናገረም የሚከተለውን ተመልከቱ ‹አንዳንድ አይሁዶች (ባለፉት ጊዜያት) እነዚያን መልእክተኞችን› ገድለዋል፡፡ ነገር ግን ‹ለምን እናንተ ገደላችኋቸው› የሚለው ጥያቄ በቀጥታ የሚናገረው ጠያቂዎቹን ነው፡፡ ይህ ደግሞ የተሳሳተ ማስረጃ ብቻ መሆኑ ሳይሆን ቁርአን በሌላ ክፍሎች ላይ ያስተማረውንም ነገር የሚቃረን ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

በእስልምና መሠረት የተፈጥሮ ኃጢአተኝነት የሚባል ነገር የለም ስለዚህም ማንም ሰው ወላጆቹ ስላደረጉት ነገር አይከሰስም ወይንም ሊቀጣ አይችልም፡፡ በመሐመድ ጊዜ ወደ አይሁዶች የተላኩ ነቢያት እንዳልነበሩ እናውቃለን፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ ጥቅስ መሠረት መሐመድ በእሱ ጊዜ የነበሩትን አይሁዶች እየከሰሳቸው ያለው በፊት ነቢያትን ስለገደሉት አይሁዶች ነው፡፡ ይህ ደግሞ የሚሆነው የእሱን የራሱን ቲዎሎጂና ትምህርት የሚቃረን ነው፡፡ ይህንን የበለጠ ለመረዳት አይሁዶች የትኛውን ነቢይ ነው የገደሉት? የሚለውን ሌላ ጽሑፍ ያንብቡ፡፡

መሐመድ የነቢይነትን ፈተና በብዙ መንገድ እንዴት ወደቀው?

አንዳንድ አይሁዶች ወደ መሐመድ በመምጣት ነቢይነቱን ለማረጋገጥ ፈተናን አቀረቡ፡፡ ይህ ይሁን ብቻ የምንለው ነው ምክንያቱም መሐመድ እነሱ እንደ ነቢይ ነው ብለው እንዲቀበሉት ጠይቋልና መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ እኔ ነቢይ ነኝ የሚልን ማንኛውንም ሰው እንድንፈትነው ይናገረናል፡፡ ይህ ግጭት ወይንም ሁኔታ ለመሐመድ በብዙ መልኩ የቀረበ ፈተና ነው መሐመድም በሁሉም መንገድ ፈተናውን ወድቋል፡፡

በመጀመሪያ ደረጃ፡- መሐመድ ከእሱ በፊት የመጡት ነቢያት ከእግዚአብሔር ለመላካቸው ማረጋገጫ እንዲሆን ያደርጉ የነበረውን የሚታይ ተዓምራት ምንም ባለማድረጉ የእግዚአብሔር ነቢይ ከመሆን ወድቋል፡፡ አይሁዶች ‹መስዋዕትን የምትበላ እሳት ከሰማይ› የሚልን መስፈርት ብቻ አቅርበው ከሆነ አይሁዶች ትክክል አይደሉም ነበር፡፡ ነገር ግን የእነሱ ቅዱስ መጽሐፍ የሚናገረው ነገር እግዚአብሔር እውነተኛ መልእክተኞችን እንዴት በተዓምራት እንደሚያረጋግጥ ነው፡፡ አይሁዶች እውነተኛ የሆነ የእግዚአብሔር ነቢይ ተዓምራታዊ የሆነ የማረጋገጫ ተዓምር ያደርጋል ብለው በመጠበቃቸው አይሁዶቹ ሙሉ በሙሉ ትክክል ናቸው፡፡

መሐመድ ከእሱ በፊት እንደመጡት ነቢያት ዓይነት የሆነን አንድም ተዓምር እንኳን፤ እሳት ከሰማይ ማምጣት ወይንም ሌላ ምንም ዓይነት የሆነ ሰማያዊ ተዓምራት ማድረግን አልቻለም ነበር፡፡

በሁለተኛ ደረጃ፡- አይሁዶች ያቀረቡት ጥያቄ ማለትም የእግዚአብሔር መፈተኛ የሆነው ነገር እሳትን ከሰማይ መላክ ነው የሚለው ስህተትም ቢሆን እንኳን፣ በሐሰት ጥያቄ መቀረብ እራሱ ፈተና ነው የሚሆነው፡፡ ምናልባትም ይህ ሆነ ተብሎ የቀረበ ሊሆን ይችላል ማለትም አይሁዶች ያቀረቡት ፈተና እነሱ በፊት ለፊት ያቀረቡት ፈተና አይደለምና፣ እነሱም በእርግጥ ሰማያዊ የሆነን እሳት ለማየት አልፈለጉም ነገር ግን እነሱ ለማየት የፈለጉት መሐመድ ለእነሱ ዘዴ መልስን መመለስ ይችል እንደሆነና ያም መልስ መለኮታዊ የሆነን አንድ ነገር ሊያሳይ የሚችል መሆኑን ለማየት ብቻ ነበር፡፡ አውቆትም ይሁን ሳያውቀው መሐመድ ይህንን ፈተና አላለፈውም ‹ፈተና ከፈተና በስተጀርባ› ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም መስፈርቱ እውነተኛ ይሁን አይሁን እሱ ሊያውቀው አልቻለም ነበር፡፡

በሦስተኛ ደረጃ፡- የመሐመድ ዓረፍተ ነገር ምንም የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት የሌለው መሆኑን የሚያጋልጥ የሆነውን - የተሳሳተ ማስረጃ ያለበት ዓረፍተ ነገር ስለመለሰ መሐመድ ፈተናውን ወድቋል፡፡ አይሁዶች መስዋዕትን ለመብላት ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ እሳትን ያመጣ ማንንም (አንድንም) ነቢይ አልገደሉም፡፡ ስለዚህም የተሳሳተውን መልሱን (እግዚአብሔር እንደተናገረው አድርጎ) ለእግዚአብሔር መስጠቱ ለመሐመድ ምንም ጥቅምን አላመጣለትም፡፡ በአንፃሩ ግን ይህንን በማድረጉ እሱ እራሱ የሐሰት ነቢይ መሆኑን አጋልጧል፡፡

የመጀመሪያዎቹ ሁለት ውድቀቶች ለዚህ ግጭት የተለየ ሊሆን ይችላል፣ ነገር ግን በሦስተኛው ውስጥ ደግመን፣ ደግመን በቁርአን ውስጥ የምንመለከተው መሐመድ ከእግዚአብሔር ያልሆነ ነቢይ እንደሆነ ነው፡፡ ምክንያቱም እሱ ከእግዚአብሔር ናቸው የሚላቸው መገለጦች ሁሉ እጅግ ብዙ የስህተት ዓረፍተ ነገሮች ያሉባቸው ናቸው፡፡ እነዚህም ከትንሽ የቁጥር ስህተቶች ለምሳሌ ያህል የኖህ እድሜ ጀምሮ እጅግ በጣም ግዙፍ የሆኑ ስህተቶች እንደ እስራኤላውያን ታሪክ እና የአይሁድ ነቢያት (በዚህ ጽሑፍ ውስጥ እንዳየነው ዓይነት) የክርስትናን እምነት ዋና ዶክትሪኖችን አጣሞ እስከ-ማቅረብ ያሉ እጅግ ዋና፣ ዋና ስህተቶችን እንደ ክርስቶስ መሰቀል፤ የእግዚአብሔር ልጅነቱን እና የሥላሴ ዶክትሪን የመሳሰሉትን አሳስቶ ማቅረብን ሁሉ ያጠቃልላል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ የመሐመድ የሥነ ምግባር ሕይወትም እጅግ አጠያያቂ ነው (ትናንሽ ሕፃናትን እንዲያገቡ መፍቀድ እና እራሱም ከዘጠኝ ዓመት ሴት ልጅ ጋር የግብረ ስጋ ግንኙነት ማድረጉ፤ የሚተቹትን ሰዎች መግደሉ ወ.ዘ.ተ ይገኙበታል) እንዲሁም እሱ እራሱ በአስማት ስር መውደቁ መሐመድ በሚለው ርዕስ ስር የተዘረዘሩትን ጽሑፎች ሁሉ ተመልከቱ፡፡

ማስታዎሻዎች፡-

1. መሐመድ መገለጦችን እንደፈጠረ እና እግዚአብሔር ያልተናገረውን ቃላት እንደተናገረው አድረጎ መናገሩን ከተረዳን፣ የምናስተውለው ሁሉንም ነገር አስመስሎ አቅርቦ ሊሆንም ይችላል ብለንም ነው፡፡ ስለዚህም አይሁዶች ያላሉትን ነገር እንዳሉት አድርጎ ተናግሯል ይህም እነሱ በፍፁም ባይናገሩትም እንኳን ነው፡፡ ይሁን እንጂ ይህ የሚሆነው ተጨማሪ ማስታዎሻ ብቻ ነው፣ መሐመድ በሁለቱም አኳያ የእውነተኛ ነቢይነትን ፈተና ወድቋል፡፡ ስለዚህም የዚህ ጥቅስ ዋና ዓላማ የሚሆነው በእርግጥ ሌላ ነገር ነው፡፡ ጥቅሱ ከተመሳሳይ ሌላ ጥቅሶች ቡድን ጋር አብሮ የሚሄድ ነው፡፡ እሱም መሐመድ አይሁዶችን ካጠቃበት ከብዙ ማጥቂያዎች መካከል አንዱ ሆኖ ነው፡፡

2. በእርግጥ የሐሰት ነቢያት ነገር ከቁርዓን ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ጠፍቷል፡፡ መሐመድ ችግርን ላለማምጣት መርጧል፡፡ እሱ የነቢይነትን መመዘኛ መስፈርትን ከሰጠ፣ ነቢያት በቀላሉ ሊታመኑ እንደማይገባቸው ነገር ግን እግዚአብሔር ነቢያት ነን በማለት የሚመጡትን እንዲፈትኑ አማኞችን እንደሚጠብቅባቸው ከተናገረ፣ ሰዎች ለእውነታው ሊነቁ ይችላሉና ነው፡፡ ለነቢይነት የሚቀርቡ ጥያቄዎች ሁሉ መጠየቅና በጥንቃቄም መመርመር ይኖርባቸዋል፡፡ መሐመድ ያንን ለራሱ አደገኛ የሆነውን ነገር ማድረግ አይችልም፡፡ የእግዚአብሔር እውነተኛ ነቢያቶች እንደዚህ ዓይነት ጥያቄዎችን በፍፁም ፈርተው አያውቁም ነበር፡፡ ይህን በተመለከተ ሊፈሩ የሚገባቸው የሐሰት ነቢያት ብቻ ናቸው፡፡ ስለዚህም መሐመድ ያቀረበውን የነቢይነት ጥያቄ ግልፅ በሆኑ መስፈርቶች ሰዎች እንዲመዝኑት የማድረግን ሐሳብ መሐመድ እንዳልወደደው በጣም ግልጥ ነው፡፡

የአዘጋጁ ማሳሰቢያ፡

አንባቢ ሆይ ከዚህ ጽሑፍ ለግል ሕይወትህ የሚሆንን እውነት እንደተገነዘብህ እናስባለን፡፡ የምታምነውን እምነት ምንነት መረዳትና መገንዘብ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ ሃይማኖትህ እውነተኛ ሆኖ የዘላለም ሕይወትን የማያስገኝልህ ከሆነ ምን ይጠቅምሃል? ስለዚህም እውነተኛ ስለሆነው የእግዚአብሔር መንገድ የምታስብበት ሰዓት እና ጊዜ አሁን ነው፡፡ ለምን መጽሐፍ ቅዱስን አግኝተህ ማንበብ አትጀምርም? አትዘግይ ከታሰርክበት የኃጢአት እስራት ውስጥ ሊያወጣህና ይቅር ሊልህ ወደሚችለው ወደ እውነተኛው ጌታ ኢየሱስ እና እሱ በመስቀል ላይ ስለኃጢአትህ ስለከፈለው ውድና ክቡር ዋጋ እውነተኛ መረዳትን ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ታገኛለህ፡፡

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉትና የተገለጡት እውነቶች አይቃረኑም የእውነተኛው እግዚአብሔር መገለጦች እና እውነቶች ናቸው፡፡ የሰው ልጅ በኃጢአት መውደቁንና ከኃጢአት የዘላለም ፍርድ ሊድንና ከእግዚአብሔር ጋር ሊታረቅ የሚችለው በአንድ መንገድ በአዳኙ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ መሆኑን ነው የሚናገሩት፡፡ ይህ እውነት የሚገባህ በረጋ መንፈስ ልብህን አስፍተህ እውነትን ለመረዳት በፀጥታ ሆነህ መጽሐፍ ቅዱስን ስታነበው ነው፡፡ እራሱ እግዚአብሔር ለአንተ በቅዱስ ቃሉ ውስጥ እንደተገለጠው ስለሰራልህ ስራ አንብብ፣ በፊቱም ንስሐን ግባ ይቅርታንም ጠይቀው እውነተኛ ይቅርታንና የዘላለም ሕይወትንም ተስፋ እርግጠኝነት በእውነት ይሰጥሃል፡፡ ጌታ ኢየሱስ ይርዳህ አሜን፡፡

 

የትርጉም ምንጭ: Divinely Inspired Ignorance? How Muhammad failed the "test of a prophet" again and again

ለእስልምና መልስ አማርኛ  ዋናው ገጽ