የቁርአን የመጀመሪያ ምንጮች
ምዕራፍ ስድስት ክፍል ሁለት
በአዳጊው እስልምና ላይ የሃኒፎችና የእነሱ ተፅዕኖ፣ መደምደሚያ
በREV. W. ST. CLAIR TISDALL, M.A., D.D
ትርጉምና ቅንብር በአዘጋጁ
በእስልምና ምንጭ ላይ ያደረግነውን ምርመራ በትግስት የተከታተለ ሰው ምናልባት አንድ ተቃውሞ ሊኖረው ይችል ይሆናል፡፡ ምናልባትም እንደሚከተለው፡ “ይህ ሁሉ ከሐምሌት ተውኔት፤ ማለትም የዴንማርክ ልዑል ከተወው ተውኔታ ጋር ተመሳሳይ ነው” ሊል ይችላል፡፡ በጽሑፉ ውስጥ እንድታዩ የተደረገው ነገር እስልምና ሃይማኖት ሙሉ ለሙሉ በፊት ከነበሩት ስርዓቶች የተወሰደ መሆኑን ነው በመሆኑም በመሐመድ በራሱ የተደረጉ ምንም ነገሮችን መሐመድ አላስቀረም (ወይንም አላስቀመጠልንም)፡፡ ስለዚህም ተቃውሞው፡ “መሐመዳዊኒዝምን ያለ መሐመድ ማስቀረት እንግዳ ነገር አይሆንምን?” የሚል የተቃውሞ ጥያቄ ነው፡፡ ለዚህ የተቃውሞ ጥያቄ የሚሆነውን መልስ ለማግኘት በጣም ከባድ አይሆንም፡፡ ልክ እንደ ድሮው የእስልምና መግለጫ አሁንም ያለው መግለጫ የሚያሳየው በሙስሊሞች የሃይማኖት ስርዓት ውስጥ መሐመድ የተጫወተውን በጣም ጠቃሚ ክፍልን ነው፡፡ ምክንያቱም “ጊቦን” በሚገባ እንዳለው ዘላለማዊ እውነታንና በጣም ጠቃሚና፡ “ሌላ አምላክ የለም አላህ ብቻ ነው፣ መሐመድም የአላህ ሐዋርያ ነው” የሚለውን ልብ ወለድ ይዟልና፡፡፡ በክርስትያኖች ዘንድ ክርስቶስ ኢየሱስ እንደያዘው ቦታ ሁሉ መሐመድ በተከታዮቹ አዕምሮ ጠቃሚ ቦታን መያዙ ከመነገር ያለፈ ነገር ነው፡፡ ለዘለቄታው ሁሉ የሆነው የእርሱ የምሳሌነት ተፅዕኖ፣ ወይንም በመሐመዳውያን ዓለም ውስጥ ሁሉ በጣም ጥቂት በሆነው ጉዳይ ላይ እንኳን የእርሱ አሉታዊ ተፅዕኖ አሉበት፤ በእርግጥ ከእስልምና መስራች በቀር በሰው ልጅ የሃይማኖት የሞራልና የፖለቲካዊ ታሪክ ውስጥ ትልቅ አስተዋፅዖ በማድረግ የተጠቀሱት በጣም ጥቂት ሰዎች ብቻ ናቸው፡፡
መሐመድ ለራሱ እራሱ የሰጠውን ቦታ ይዞ፣ መሐመድ የራሱን ልዩ የሆነ ማንነቱን በእምነቱ ላይ ሳይጥል ትቷል ማለት በጭራሽ የማይቻል ነገር ነው፡፡ አንድ ግንበኛ የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ ከተለያዩ ቦታዎች ይሰበስባል ነገር ግን የእርሱ አደረጃጀት እና አያያዝ ግን የእርሱን ችሎታ (ክህሎት) ይጠይቃል፡፡ የአርክቴክቱ ዕቅድ (ንድፍ) የሚታየው በፕላኑ መሰረት በተገነባው በግንቡ ላይ ነው፡፡ ልክ በተመሳሳይ መንገድ መሐመድ ሐሳቦችን፣ አፈታሪኮችን፣ የሃይማኖት ስርዓቶችን ከሌሎች ብዙ ቦታዎች ቢሰበስብና ቢወስድም እንኳን የእስላም ሃይማኖት በራሱ የተገነባ መስሏል፣ ይህም በብዙ ሁኔታዎች ከሌሎች ማንኛውም ዓይነት እምነቶች ሲወዳደር የሚለው የራሱ ነገር አለው፡፡
ቁርአን በተለያየ ቦታ ላይ አለው የሚባለው የስነ-ጽሑፍ ውበቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ አድናቆት አግኝቷል፣ እንዲሁም የጸሐፊውን ችሎታ በማያጠራጥር መንገድ አስመስክሯል፡፡ የቁርአን የአደረጃጀትና የስምምነት ጉድለቱ ከእርሱ ላይሆን ይችላል ነገር ግን በአጠቃላይ ስራው የሚያንፀባርቀው የመሐመድን የእውቀት ችሎታ ውሱንነት ነው፡፡ እርሱ የነበረው እውነተኛ የእውቀት መጠንና ትምህርትም በጣም መጠነኛ የነበረ መሆኑን ያሳያል፡፡ የእርሱ ያልተወሰነ (መጠነ ሰፊ) ግልብነት (ሞኝነት) እንዲሁም የነገሮችን አበጥሮ አለማየት ችሎታ፣ እንዲሁም የእርሱን የባህርይና የሞራል ችግር ሁሉ በግልጥ ያሳያል፡፡ አሰባሰቡ፤ በቅድም ተከተል የአደረጃጀቱ ሁኔታ በሚጠናበት ጊዜ ግን ቁርአን የሚያመለክተው በየጊዜው የመርሆ ለውጥን ሲያካሂድ ነው፡፡ ይህም አብሮ የሚሄደው መሐመድ በጊዜያዊ ሁኔታዎች ላይ ተነስቶ ስላደረጋቸው የራሱ የአቋም ለውጦች ጭምር ነው፡፡ የእርሱ አንዳንድ ክፍሎች በመሐመዳን ተንታኞችም እንኳን ዘንድ የሚገለጡት ከተወሰኑ የሕይወቱ ገጠመኝ ክስተቶች ጠቀሜታ አኳያ ብቻ ነው፡፡ ያ የተወሰነው የቁርአን ቁጥር የሚታየው መገለጡ ከመጣበት የተለየ ሁኔታ አንፃር ብቻ ነው፡፡ ይህንን ለማሳየት ለመጥቀስ ብቁ የሚሆነው፡ በመጀመሪያ መሐመድ እስልምናን ለማስፋፋት ጦርን ስለመጠቀም የነበረው አመለካከት እንዲሁም በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ፡ በጋብቻ ግንኙነቶቹ ሁኔታው ላይ የሰጠውን አንድ ክስተት መጥቀስ በቂ ይሆናል፡፡
መካን ከመልቀቁና በመዲና ጥገኝነት ከማግኘቱ በፊት በ622 ዓ.ም መሐመድ ምንም ጊዜያዊም እንኳን ስልጣን እንዳልነበረው በሚገባ የታወቀ ነገር ነው፡፡ በመካ ያሉት የእርሱ ተከታዮች በጥቂት አስሮች የሚቆጠሩ ነበሩ ስለዚህም በሁለት ሁኔታዎች በ615 እና እንደገና በ616 ጥገኝነትንና ጥበቃን ለማግኘት ወደ አቢሲኒያ ተሰደዱ፡፡ በመሆኑም በእነዚያ ጥቅሶችና ምዕራፎች ከሂጂራ በፊት በተቀናበሩት ውስጥ እምነቱን ለማስፋፋት ጦር ስለማንሳት ምንም የተጠቀሰ ነገር የለም፡፡ ነገር ግን ከሂጂራ በኋላ የመዲና ሕዝቦች ብዙዎቹ የእርሱ ረዳቶች ከሆኑ በኋላ እርሱ በመጀመሪያ ደረጃ ለእርሱ ጓደኞች ለራሳቸው ሕይወት ጥበቃ እንዲዋጉ ትዕዛዝን ሰጣቸው፡፡ ኢብን ሒሻም ይህ ፈቃድ በመጀመሪያ ደረጃ የተሰጠው በእነዚህ ጥቅሶች እንደሆነ ጠቀሰ “ለነዚያ ለሚገደሉት (ምእመናን) እነርሱ የተበደሉ በመኾናቸው (መጋደል) ተፈቀደላቸው አላህም እነርሱን በመርዳት ላይ በእርግጥ ቻይ ነው፡፡ ለነዚያ ጌታችን አላህ ነው ከማለታቸው በስተቀር ያለ አግባብ ከአገራቸው የተባረሩ ለኾኑት (ተፈቀደ) አላህ ሰዎችን ከፊላቸውን በከፊሉ መገፍተሩ ባልነበረ ኖሮ ገዳማት ቤተክርስትያኖችም ምኩራቦችም በውስጣቸው የአላህ ስም በብዛት የሚወሳባቸው መስጊዶችም በተፈረሱ ነበር አላህም ሃይማኖቱን የሚረዳውን ሰው በእርግጥ ይረዳዋል አላህ ብርቱ አሸናፊ ነውና፡፡” ቁርአን 22.39 እና 40፡፡ ከጊዜ በኋላ ግን የመሐመድ ክንድ በብዙ የዝርፊያዎች ዘመቻዎች ድሎችን ባገኘበት ጊዜያት በቁራይሽ ነጋዴዎች የንግድ ጭነቶች ላይ ይህ ፈቃድ ወደ ትዕዛዝ ተለወጠ፡፡ ከዚህም የተነሳ በቁርአን 2.216 እና 217 ላይ የሚከተለውን ጥቅሶች እናነባለን “(ከሐዲዎችን) መጋደል እርሱ ለእናንተ የተጠላ ሲኾን በናንተ ላይ ተጻፈ አንዳች ነገርን እርሱ ለናንተ የበለጠ ሲኾን የምትጠሉት መኾናችሁ ተረጋገጠ አንዳችንም ነገር እርሱ ለናንተ መጥፎ ሲኾን የምትወዱት መኾናችሁ ተረጋገጠ አላህም (የሚሻላችሁን) ያውቃል ግን እናንተ አታውቁም፡፡ ከተከበረው ወር (ከረጀብ) በርሱ ውስጥ ከመጋደል ይጠይቁሃል፤ በላቸው፡- በርሱ ውስጥ መጋደል ታላቅ (ኃጢአት) ነው፤ ግን ከአላህ መንገድ (ሰዎችን) መከልከል በርሱም መካድ ከተከበረውም መስጊድ (ማገድ) ባለቤቶቹንም ከርሱ ማውጣት አላህ ዘንድ ይበልጥ ታላቅ (ወንጀል) ነው፤ ፈተናም (ማጋራት) ከመግደል ይበልጥ ከባድ ነው፤ (ከሐዲዎች) ቢችሉ ከሃይማኖታችሁ እስከሚመልሳችሁ ድረስ የሚዋጉዋችሁ ከመኾን አይቦዝኑም ከናንተ ውስጥም ከሃይማኖቱ የሚመለስና እርሱም ከሐዲ ሆኖ የሚሞት ሰው እነዚያ (በጎ) ሥራቸው በቅርቢቱም በመጨረሻይቱም አገር ተበላሸች እነዚያ የእሳት ጓደኞች ናቸው እነርሱ በርሷ ውስጥ ዘውታሪዎች ናቸው” ይህም ማለት ሙስሊሞች እንዲዋጉ ተደርገዋል ማለት ነው፡፡ ይህም ባልተጻፈው በአረቦች ሕግ መሰረት ጦርነት በተከለከለበትም ጊዜ እንኳን ነበር እንደዚሁም ጠላቶቻቸውን ወደ ከአባ እንዳይገቡ መፍቀድ በሌለባቸውም ጊዜ እንኳን ነበር፡፡ በሦስተኛ ደረጃ የምንመለከተው በሂጂራ በስድስተኛው ዓመት ላይ ሙስሞሊሞች ያሸነፉት (ድል ያደረጉት) የባኑ ቁራይዳሃንና ሌሎችንም አይሁድ ጎሳዎችን ነበር የቅዱስ ጦርነት ላይ መካፈል የሚለው ትዕዛዝ ወይንም ጂሃድ አሁንም ጥብቅ ነበር ምክንያቱም በቁርአን 5 ቁጥር 33 እንደሚከተለው ተጽፏል “የነዚያ አላህንና መልክተኛውን የሚዋጉ በምድርም ላይ ለማጥፋት የሚተጉ ሰዎች ቅጣት (1) መገደል ወይም (2) መሰቀል ወይም (3) እጆቻቸውንና እግሮቻቸውን በማፈራረቅ (4) መቆረጥ ወይም (5) ከአገር መባረር (1) ነው፡፡ ይህ ለነሱ በቅርቢቱ ዓለም ውርደት ነው በመጨረሻይቱም ለነርሱ ከባድ ቅጣት አላቸው፡፡” ሊታይ የሚገባው ነገር ተንታኞች ይህንን መግለጫ የሚገልጡት ለጣዖት አምላኪዎች ላይ እንደተጣለ ቅጣት እንደሆነ አድርገው ነው እንጂ በአይሁድና በክርስትያኖች ላይ እንደተጣለ አድርገው ላይሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ሙስሊሞች በመጽሐፉ ሰዎች ላይ የሚያሳዩት ባህርይ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ነው የተገለፀው መሐመድ ከመሞቱ ከጥቂት ዓመታት በፊት በሂጂራ አስራ አንደኛው ዓመት ላይ ነው፡፡ ከዚያም አራተኛው ደረጃ ደረሰ በቁርአን 9.5 እና 29 ላይ ምናልባትም ከቁርአን ምዕራፎችና ቁጥሮች ሁሉ የመጨረሻው በዚያም የታዘዘው ነገር የዓመቱ አራተኛው ቅዱስ ወር ከተጠናቀቀ በኋላ ሙስሊሞች ጦርነቱን መቀጠል አለባቸው፡፡ በእነዚህም ጥቅሶች ውስጥ ያሉት ትዕዛዛት እንደሚከተለው ናቸው “የተከበሩትም ወሮች ባለቁ ጊዜ አጋሪዎቹን በአገኛችሁባቸው ስፍራ ግደሉዋቸው ያዙዋቸውም ክበቡዋቸውም ለነሱም (መጠባበቅ) በየመንገዱ ተቀመጡ ቢጸጸቱም ሶላትንም በደንቡ ቢሰግዱ ግዴታ ምጽዋትንም ቢሰጡ መንገዳቸውን ልቀቁላቸው አላህ መሐሪ አዛኝ ነውና (5)፡፡ ከነዚያ መጽሐፍን ከተሰጡት ሰዎች እነዚያን በአላህና በመጨረሻው ቀን የማያምኑትን አላህንና መልክተኛውን እርም ያደረጉትንም እርም የማያደርጉትንና እውነተኛውንም ሃይማኖት የማይቀበሉትን እነርሱ የተዋረዱ ኾነው ግብርን በእጆቻቸው እስከሚሰጡ ድረስ ተዋጉዋቸው”፡፡ ስለዚህም በቁርአን ውስጥ እንደተገለፀው ሁሉ የእግዚአብሔር ሕግ ይታይ የነበረው በመሐመድ ጦር ስኬት መሰረት እንደነበረ ነው፡፡ ይህንንም ለማረጋገጥ እንደ ሕግ አድርጎ አንዳንድ ጥቅሶች በሌሎች ቆየት ብለው በተገለፁ በተባሉ ተበልጠውና ተሽረው ነበር ይህም በቁርአን 2.106 በተባለው መሰረት ነው “ከአንቀፅ ብንለውጥ ወይም እሷን ብናስረሳህ ከርሷ የሚበልጥን ወይም ቢጤዋን እናመጣለን አላህ በነገሩ ሁሉ ላይ ከሃሊ (ቻይ) መኾኑን አታውቅምን?” ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ መሐመዳውያን ዳኞችና የሕግ ሰዎች የትኞቹ ጥቅሶች እንደተሰረዙና የትኞቹ ቦታቸውን እንደያዙ መወሰን እና ማረጋገጥ አልቻሉም ምንም እንኳን 225 የሚሆኑት በኋላ በተገለጡ ጥቅሶች እንደተሸሩ ቢናገሩም ነው፡፡
መሐመድ ነቢይነቱን ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በአይሁዳውያንና በክርስትያኖች ላይ ያመጣውን የአመለካከት ለውጥ በተመሳሳይ መንገድ ልንደርስበት እንችላለን፡፡ እርሱም (አይሁዳውያንንና ክርስትያኖችን) ወደ እራሱ ሊስባቸው ተስፋ አድርጎ ነበረ፤ ነገር ግን ይህ ጥበቃው ወይንም ተስፋው ያልተሳካለት ሆኖ እራሱን ሲያገኘው እርሱ የወሰደው እርምጃ በእነርሱ ላይ ጦርን መምዘዝ ነበር፡፡ ከዚህ ተመሳሳይ ከሆኑ ምርመራዎች ሁሉ ልናገኝ የምንችለው ነገር ተመሳሳይ ትምህርትን ብቻ ነው፡፡ እንደዚሁም መሐመድ በጊዜው አስፈላጊ ሆኖ ባገኘው ነገር፣ ወይንም አስፈላጊ ነው የሚለውን ነገር ለማስተላለፍ ሲፈልግ ነገሩን በተመለከተ ሙሉ ለሙሉ መገለጥ የመጣለት አድርጎ ማቅረብን ተያይዞት እንደነበር ነው፡፡
በሱራ አል-አሕዛብ ማለትም በቁርአን 33 ውስጥ ከምናገኘውና ከዘይነብ ጋር ባደረገው የጋብቻ ጉዳይም ላይ ተመሳሳይ እውነታን እናገኛለን በዚህም ምክንያት የጉዲፈቻ ልጁ ዛይድ ሚስቱን ዘይነብን ፈትቷታል፡፡ ጉዳዩን በጥልቅ ለመመልከት ለእኛ ምንም የማይጥም ነው ነገር ግን ቁርአን እራሱ በዚህ ጉዳይ ላይ የተናገረው ማገናዘቢያ በቁርአን 33.37 ላይ ከተንታኞችና ልማድ ዘገባ ጋር ተጠናቅሮ ማንበብ ይቻላል፡፡ ይህም የመሐመድን የራሱን ባህርይና አመለካከት በቁርአን በራሱ ላይና በእስልምና የሞራል ሕግ ላይ የራሳቸውን ማህተም አስቀምጠዋል (ስለመሐመድ)፡፡ በቁርአን ውስጥ ለሌላው ሙስሊም በአንድ ጊዜ ከተፈቀደለት ከአራት ሕጋዊ ሚስቶች ጋብቻ በላይ እርሱ እንዲያገባ ለእርሱ ብቻ የተሰጠው ፈቃድ ሌላው ተመሳሳይ ማስረጃ የሚሆን ነገር ነው፣ ይህም እጅግ አስደሳች ባልሆነ ልማድ ውስጥ የእርሱ የተለየ ባህሪ በአይሻ ተገልጧል፡፡
እነዚህ ሁሉ ነገሮች ከታዩ በኋላ ግልፅ የሚሆነው ነገር መሐመድ ምንም እንኳን የሃይማኖትን ልምምዶች፣ እምነቶችና አፈታሪኮች ከሌሎች የተለያዩ ምንጮች የወሰደ ቢሆንም እንኳን እርሱ እነርሱን በአንድ ላይ አንድ በሆነ መንገድ ወደ አንድ ወይንም እምብዛም ወጥ ወዳልሆነ አንድነት አምጥቷቸዋል ከዚያም የእስልምናን ሃይማኖት ሰርቶታል (አፍርቷል)፡፡ የዚህም አንዳንድ ክፍሎቹ ጥሩ ናቸው እናም እስልምና ከሌሎች የሃይማኖት ስርዓቶች የወሰዳቸው አንዳንድ ታላላቅ እውነቶችን ይዟል እነዚህም እውነቶች በተወሰነ መጠን እምነቱ በዓለም ላይ እንዲቀጥል ረድተውታል፡፡ ነገር ግን እስልምና አዲስ ወይንም ከሌላው የተለየና ከፍ ያለ የሃይማኖት ፅንሰ ሐሳብን አላመጣም፡፡ ስለዚህም የእርሱ አጠቃላይ ድምፅ ታማኝ በሆነ መልክ የመስራቹ ስሜታዊና ስጋዊ ባህርይ ታማኝ ነፀብራቅ ነው፡፡ ምናልባትም የሩቅ ምስራቅን ምሳሌ መጠቀም ይህንን እጅግ በጣም አካባቢያዊና ሩቅ ምስራቃዊ ሃይማኖት ማለትም መሐመዳኒዝምን ለመግለጥ ተገቢ ላይሆን ይችላል፡፡ ስለዚህም እስልምና በብቁ ሁኔታ ሊነፃፀር የሚችለው ከሚከተለው ሐሳብ ጋር ነው፤ ማለትም፡
“ሶዶምና ገሞራው ከተቃጠሉበት ከዚያ የእቶን እሳት ጋር ነው”
ይህም በእቅፉ ውስጥ የብዙ ምንጮችን ውሃ ተቀብሎና አቀላቅሎ የእነርሱ መገናኛ የሆነ ቅርፅንና መልክን የያዘ መስሎ ወደ ትልቅና መጠነ ሰፊ ወደሆነ የሞት ባህር ውስጥ እንደሚለውጣቸው ነው፡፡ ከእነርሱም ወደቦች ላይ በእነርሱ ሊደረስ በሚችል ርቀት ላይ ላሉ ለማንኛም ሕይወት ላላቸው ነገሮች ሁሉ ገዳይ (መርዝ) የሆነ ትንፋሽ የሚወጣባቸው ሆነው ይለወጣሉ፡፡ እስልምና ማለት እንደዚህ ነው፡፡ ከተለያዩ ምንጮች ጀምሮ በውስጡም የተወሰኑ እውነቶችን ተቀብሎ የራሱን ቅርፅ የመሰለው በመሐመድ ባህርይና ፀባይ ሆኖ በውስጡ ያለው መልካም (የሚመስለው) ነገር የሚያገለግለው ክፉውን ለመደገፍና ለመጠበቅ ሲሆን፤ እራሱንም የሐሰትና አታላይ እምነት አድርጎታል፡፡ በመሆኑም ለሰዎች እርግማን እንጂ በረከት አይደለም - እንዲሁም እጅግ በጣም ለም የሆኑትን የምድር ቦታዎች ወደ ምድረበዳ የቀየረ፤ በእኛም ጊዜያት እንኳን እጅግ ብዙ ምድሮችን (አገሮችን) ንፁህ ደም የሚጎርፍባቸው ቦታዎች ያደረገ፤ እንዲሁም በእርሱ የብረት ቀንበር ስር ወድቀው የሚሰቃዩትን እና ያለምንም ምህረት የሚቃትቱትን የወደቁትን ማናቸውንም አገሮች ሁሉ በስነምግባር፣ በእውቀት እና በመንፈሳዊ መቅሰፍት ውስጥ የጣለ እምነት ነው፡፡
የአዘጋጁ ማሳሰቢያ፡
የቁርአን የመጀመሪያ ምንጮች የሚለውን አስገራሚ መጽሐፍ አሁን እያጠቃለልን ነው፡፡ በተከታታይ እንዳየነው ሁሉ የቁርአን ምንጮች በጣም ግልጥ ሆነውልናል፡፡ ብዙ ሙስሊሞች የቁርአን ምንጩ ምን እንደሆነ በጭራሽ አያውቁም፣ አንፈርድባቸውም ምክንያቱም ስለሚከተሉት እምነት ስርና አመጣጥ እንዲረዱና እንዲጠይቁም አይገፋፉምና ነው፡፡ አንዳንዶችም ቁርአንንም በቃል ሊያውቁት ይችላሉ ትርጉሙ ግን ሊገባቸው እንደማይቻል ያውቃሉ፣ መምህራኖቻቸውም እንኳን የተወሰኑ ሊቃውንቶቻቸው የሰጡትን ትንተና ወይንም ልማድን ሳያገናዝቡ የሚያነቡትን ክፍለ-ሐሳብ በመረዳት የሚሰጡት ማብራሪያ የተወሰነ ነው፣ አይኖርምም ማለት ይቻላል፡፡
ይሁን እንጂ የምንከተለውን ሃይማኖት አመጣጥ ማወቅ በጣም ጠቃሚ ነገር ነው፡፡ የምንከተለው ሃይማኖት ላይ የተሰጡትን ትምህርቶች መረዳት መቻላችን እንዲሁም የምንከተለው ሃይማኖት በትክክል ከእግዚአብሔር የመጣ ወይም ያልመጣ መሆኑን ማወቃችን በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ሃይማኖታችን ከእግዚአብሔር የመጣና ከእግዚአብሔር ጋር የምንታረቅበትን የሚያሳየን ከሆነ ያለነው በትክክለኛው መንገድ ላይ ሲሆን ከእግዚአብሔር ካልመጣ ግን አደጋ ላይ ነን ማለት ነው፡፡ አደጋው በቀላሉ የሚታይና ጊዜያዊ አለመሆኑ ደግሞ ጉዳዩን በጣም አስፈሪና አስደንጋጭ ያደርገዋል፡፡ ጉዳዩ ጥልቅ ነው ዘላለማዊ ሕይወትን የት እንደምናሳልፍ የሚጠቁም ነው፡፡
እኛ አዘጋጆቹ እንደምንገምተው ሁሉ የዚህ ገፅ ተከታታዮችና አንባቢዎች ሁሉ ስለ መንግስተ ሰማይና (ፓራዳይዝና) ስለ ሲዖል መጠነኛ ግንዛቤ እንዳላቸው ነው፡፡ የምንከተለው እምነት ከእግዚአብሔር ካልመጣ መጨረሻችን ሊሆን የሚችለው ለዘላለም ሲዖል ውስጥ መውደቅ ነው፡፡ የምንከተለው እምነት ከእግዚአብሔር ካልሆነ በአጭሩ ያለነው ከፍተኛ ኪሳራ ውስጥና ውዥንብር ውስጥ መሆኑ ነው፡፡
እነዚህን የምንለው ሙስሊሞች የሚከተሉት መጽሐፍ ማለትም ቁርአን ከእግዚአብሔር ያልመጣ መሆኑን ነገር ግን ምንጩ በየምዕራፉ ላይ እንደተገለጠው የሚከተሉት መሆናቸውን ነው፡-
አንደኛ፡ የጥንት አረቦች እምነትና ልምምድ
ሁለተኛ፡ የጥንት ሳቢያንስ እና አይሁዶች ሐሳቦችና ልምምዶች
ሦስተኛ፡ የክርስትና ልማድና የክርስትያን ነክ አፖክሪፋዊ መጽሐፍት ተፅዕኖዎች
አራተኛ፡ የፋርሱ የዞሮ አስተርያን እምነቶችና የእስልምና ልማዶች
አምስተኛ፡ የሐኒፋውያን ተፅዕኖዎች ናቸው፡፡
ጸሐፊው ካደረገው ከዚህ አስገራሚ ምርምር የምንገነዘበው ነገር ቁርአንና እስልምና ምንጫቸው የሰማዩና የምድሩ ፈጣሪ እግዚአብሔር ሳይሆን ከዚህ በላይ የተጠቀሱት ልዩ፤ ልዩ ሐሳቦች እምነቶች እና ልማዶች ናቸው፡፡ ብዙዎቹ የሰው ሐሳቦችና የጣዖት አምልኮ የውሸት የሰው ፈጠራ እምነቶች ናቸው፡፡ ከክርስትና የመጣውም ምንጭ ከእውነተኛው ክርስትና ሳይሆን በወቅቱ ከተወገዙ ከስህተት እና በእውነተኛ ክርስትያኖች ዘንድ ተቀባይነት ከሌላቸው ጽሑፎች ውስጥ ነው፡፡
በዚህ መጽሐፍ መረጃ መሰረት ክፍት በሆነ አዕምሮ ነገሮቹን የሚያገናዝብ ሰው ሊረዳ የሚችለው የእስልምናን እምነት የሚከተል ማንም ሰው ከእግዚአብሔር እውነተኛ የመገለጥ እምነት ውጪና በከፍተኛ አደጋ ላይ መሆኑን ነው፡፡
የዚህ ገፅ አዘጋጆች ለአንባቢዎች ግልፅ እንዲሆን የሚፈልጉት አንድ ዋና ቁም ነገር ከዚህ የሚከተለው ነው፡፡ ክርስትያኖች የሚከተሉት መጽሐፍ ቅዱስ በጣም የተለየና በትክክል ከእግዚአብሔር የመጣ መሆኑን ነው፡፡ ይህንን እንዴት ለማወቅ ይቻላል ለሚል ጥያቄ መልሱ በአጭሩ አንብቦ ማየት ብቻ ነው የሚል ነው፡፡ እኛ ቁርአንን እንደምናነበው ሁሉ ሙስሊሞችም መጽሐፍ ቅዱስን የማንበብ መብት ሊኖራቸው ይገባል፡፡
ተደጋጋሚው ጥሪያችን ሲነበብ በጣም ግልፅና የሚገባውን መጽሐፍ ቅዱስን አግታችሁ እንድታነቡ ነው፡፡ አንብቡት ስለ ሰው ባህሪ፣ ስለ እግዚአብሔር ማንነትና ከእርሱ ጋር እንዴት መታረቅና በእርሱም ፀጋ በኩል አዲስ ሕይወትን ስለማግኘት እጅግ በጣም አስደናቂ ትምህርቶችን ታገኛላችሁ፡፡
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከምትሰሟቸው ጥሪዎች አንዱ ንስሐ ስለመግባት ነው፡፡ ጥሪውን ተቀብላችሁ ንስሐ ብትገቡ በእውነት ይቅር ሊላችሁ እንደሚችል የተገቡ መለኮታዊ ቃል ኪዳኖችን ታያላችሁ፡፡ ይቅርታው የሚሰጠውም በቀራኒዮ መስቀል ላይ ለኃጢአተኞች ምትክ ሆኖ በሞተው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ብቻ ነው፡፡ ኦ ይህን ጥሪ ሰምተው ወደ እርሱ የመጡ ሁሉ ተጠቅመዋል የዘላለም መንግስተ ወራሾች ተደርገዋል እናንተም ኑ ንስሐ ግቡ ጌታ ኢየሱስ በመስቀል ላይ በሰራላችሁ ስራ በኩል እግዚአብሔር ይቅር እንዲላችሁና እንዲለውጣችሁ ጠይቁት፤ በራሳችሁ፣ በሕይወታችሁ ውስጥ አዲስ ነገርን ታያላቸሁ እግዚአብሔር በምህረቱ ይርዳችሁ አሜን፡፡
የትርጉም ምንጭ: THE ORIGINAL SOURCES OF THE QUR'AN
ሙሉ መጽሐፉ በአማርኛ: የቁርአን የመጀመሪያ ምንጮች
ለእስልምና መልስ አማርኛ ዋናው ገጽ