የቁርአን የመጀመሪያ ምንጮች

ምዕራፍ አምስት ክፍል ሦስት

በቁርአንና በእስልምና ልማድ ውስጥ የዞሮአስተሪያን ነገሮች

REV. W. ST. CLAIR TISDALL, M.A., D.D

ትርጉምና ቅንብር በአዘጋጁ

5. የመሐመድ ብርሃን አፈታሪኮች

በመሐመድ ግንባር ላይ የበራው ብርሃን ታሪክ በቁርአን ውስጥ ባይጠቀስም አፈታሪኩ እርሱ ከመፈጠሩ በፊት የመኖሩ ነገር በልማዶች ውስጥ እጅግ በጣም ጠቃሚ ቦታን ይዟል፡፡ እንደ ሮዳቱል አህባብ ዓይነት መጽሐፎች ውስጥ እንደዚህ ዓይነት ልማዶች በየአንቀፆቹ ሁሉ ውስጥ ተሰግስገዋል፡፡ በእነዚያም ውስጥ የምናነበው ነገር ‹አዳም በተፈጠረበት ሰዓት እግዚአብሔር በግንባሩ ላይ ያንን ብርሃን አስቀመጠና እንደሚከተለው አለው፡ ‹ኦ አዳም ሆይ ይህ ብርሃን በግንባርህ ላይ ያስቀመጥኩት እጅግ በጣም የከበረውና በጣም ጥሩ የሆነው የወንድ ልጅህ ብርሃን ነው፣ እርሱም የሚላከው ነቢይ ያም የነቢያት ሁሉ ዋነኛው ብርሃን ነው›፡፡ ከዚያም ታሪኩ እንዲህ በማለት ይቀጥላል ብርሃኑ ከአዳም ወደ ሴት ተላለፈ ከሴትም በእያንዳንዱ ትውልድ ውስጥ ወዳሉት የከበሩ ልጆች ተላለፈ ይህም እስከ አብዱላህ ኢብን አል ሙታላብ ላይ እስከሚደርስ ነበር፡፡ ከእርሱም በኋላ አሚናህ መሐመድን በፀነሰችበት ጊዜ ወደ እርሷ ተላለፈ፡፡ መሐመዳን ይህንን የመሐመድን ብርሃን ዘገባ ያቀዱበት ምክንያት በዮሐንስ 1.4ና 5 ላይ እንዲሁም በዮሐንስ 12.41 ላይ ስለ ጌታ ኢየሱስ ከተጻፉት እውነቶች ጋር ጌታቸውን በማነፃፀር ከፍ ለማድረግ አስበው ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚህም በላይ በዘፍጥረት 1.3 ከተጻፈው ጋር በአዕምሯቸው ውስጥ መምታታት በመኖሩም ጭምር ነው፡፡ ይህም አሁን ከዚህ ቀጥሎ በዝርዝር ከምንጠቅሳቸው አንቀፆች ውስጥ መታየት ይችላል፤ ይህም ታላቅ ማጋነን ወይንም ፈጠራ በዋና ውጥናቸው (ዕቅዳቸው) ውስጥ ቢኖሩም እንኳን በሙሉ የተወሰዱት በዝርዝር እንደምንጠቅሰው ከዞሮአስተሪያን አፈታሪኮች (ተረቶች) ውስጥ ነው፡፡

በፓላቪ ውስጥ ሚኑኪራድ በቀደመው የፐርሺያ ንጉስ ሳሳኒያን ጊዜ ተቀናብሮ የነበረው፣ ያነበብነው ዖርማዝድ ይህንን ዓለምና በውስጧ ያሉትን ፍጥረታት፣ እንዲሁም የመላእክትን አለቆችና የሰማያዊ ምክንያትን ከእራሱ ልዩ የሆነ ብርሃን እንደፈጠረ፣ ይህም ከዛርቫን ኢ አካራና ወይንም ‹ወሰን የሌለው ጊዜ› ጋር እንደነበረ ነው፡፡ ነገር ግን ከዚህም ጊዜ በፊት በጣም በጥንት ጊዜ የብርሃን ተረት በፐርሺያ ውስጥ ነበረ፡፡ በአቨስታ፤ በታላቁ ይማ ካሺየታ ውስጥ ወይንም ይማ ‹በጣም ብልሁ› የሚለውን ስሙን ካመጣበት ጋር ተያይዞ ተጠቅሷል፣ ከዚያም በኋላ በዘመናዊ የፐርሺያንስ ጃምሲድ ተበክሏል፡፡ እርሱም ከሳንስክሪት ያማ ጋር ተመሳሳይ ነው፤ ይህም ‹በሪግ ቭዳ› ታሪክ የመጀመሪያው ወንድ ሲሆን በመንታ እህቱም በ‹ያሚ› በከንቱ እንደተፈተነ እንዲሁም ከሞት በኋላ የሟቾችን ጥላ የሚገዛ ተደርጎ ተነግሮለታል፡፡ ይማ በፐርሺያ ልማድ ውስጥ በሌላ ጎኑ የፐርሺያውያን ስልጣኔ መስራች ነው፡፡ የአባቱም ስም ‹ቨናቫት› በሕንዶች አፈታሪክ ውስጥ ካለው ከ‹ቪቫስቫት› ጋር ተመሳሳይ ነው፣ እርሱም ፀሐይ ሲሆን የእርሱም አባት ‹ያማ› ነው፡፡ በይማ ቅንድብ ላይ የ‹ካቪም ቫርኖ› ወይንም ‹የንጉሳዊ ብሩህነት› ያበራል፣ እርሱም ከመለኮታዊ ክብር ውስጥ የሚወጣው ሲሆን በኃጢአት ምክንያት እርሱ አጥቶታል፡፡ ስለዚህም በአቨስታ ውስጥ የሚከተለው ገለጣ ተሰጥቷል፡

‹ታላቁ ንጉሳዊ ብርሃንነት ለረጅም ጊዜያት የተያያዘው ከጃምሺድ ጋር ነው፣ የመልካሙ መንጋ ጌታ፣ በሰባተኛዋ በተባለችው ምድር ውስጥ በዲቭስና ሰዎች ላይ፣ በአስማተኞችና በፓሪስ ላይ፣ በክፉ መናፍስትና በሟርተኞች ላይ እና በጠንቋዮች ላይ ይገዛ በነበረበት ጊዜ፣ ከዚያም እርሱ ያንን ውሸታምና ምንም ጥቅም የሌለውን ዓለም ይገዛ በነበረበት ጊዜ፣ ይታይ የነበረው ብርሃንነት ከእርሱ ተለየ በወፍ መልክ --- እርሱ ጃምሺድ፣ የመልካሙ መንጋ ገዢ፣ ጃም፣ ከዚያ በኋላ ያንን ብሩህነት ማየት አልቻለም፣ እርሱም ሃዘንተኛና በጣምም ችግረኛ ሆኖ በምድር ላይ ጠላትነትን ማምጣት ጀመረ፡፡ ያ ብርሃንነት በተለየው በመጀመሪያው ጊዜ፣ ያ ብርሃንነት ከጃምሺድ ላይ ሲለይ፣ ያ ብርሃንነት ከጃምም ተለየ፣ እርሱም የቪቫናቫት ወንድ ልጅ ነው፤ እንደ በራሪ ወፍ ሆኖ .. ‹ምትራም› ደግሞ ያንን ብርሃንነት ወሰደ፡፡ ያ ብርሃንነት ለሁለተኛ ጊዜ  ከጃምሺድ ላይ ሲለይ፣ ያ ብርሃንነት የቪቫናቫት ወንድ ልጅ ከሆነው ከጃምም ላይ ተለየ፡፡ እርሱም ከእርሱ ላይ እንደ በራሪ ወፍ ሆኖ ሄደ፣ ‹ፋሪዱን›፣ የ‹አትዊያኒ› ጎሳ የጀግናው ጎሳ ልጅ ያንን ብርሃንነት ወሰደ ምክንያቱም እርሱ ከድል አድራጊ ሰዎች መካከል ዋናው ድል አድርጊ ሰው ነበርና በሦስተኛውም ጊዜ ያ ብርሃንነት ከጃምሺድ ሲለይ ያ ብርሃንነት ከጃምም ተለየ የ‹ቪቫንቫት› ወንድ ልጅ እንደ በራሪ ወፍ .. ‹ኬቴሳስፓ› ያንን ብርሃንነት የወሰደው ወንድ ነው ምክንያቱም እርሱ ከኃይለኞች መካከል ኃይለኛው ነበርና፡፡›

እዚህ ላይ የምናየው ነገር ልክ እንደ መሐመዳውያን አፈታሪክ ብርሃኑ ከትውልድ ወደ ትውልድ መተላለፉን ሲሆን በሁለቱም ውስጥ በጣም ጠቃሚ ወደ ሆኑት ሰዎች ተላልፏል፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ የፀሐይ ልጅ ያንን ብርሃን የመውሰዱ ነገር ተፈጥሮአዊና መተላለፉም የተደረገው በልዑሉ አማካኝነት ነው፡፡ በዚህም ላይ በአፈ ታሪኩ ውስጥ ከአዳም ወደ መሐመድ የመተላለፉ ነገር መሐመድን በድሮዎቹ የፐርሺያ ጀግኖች አይን መሰረት አይቶ ለማክበር ካልሆነ በስተቀር ምንም ልዩ የሆነ አግባብነት አይታይበትም፡፡

ከዚህም በላይ የምናስተውለው ጃምሺድ ‹በዲቭስና በሰዎች ላይ፣ በአስማተኞችና በፓሪስ፣ በክፉ መናፍስት፣ በሟርተኞችና በጠንቋዮች ላይ እንደገዛ ነው› ይህም ልክ የአይሁድና የመሐመዳን አፈታሪኮች ሰሎሞን አደረገ በማለት ካቀረቡት ጋር ይመሳሰላል፡፡ ያለምንም ጥርጥር አይሁዶች ታሪኩን የተዋሱት ከዞሮ አስተሪያውያን ነው እነርሱም በምዕራፍ 3 ውስጥ እንዳየነው ለሙስሊሞች አስተላልፈውታል፡፡

በሙስሊሞች ልማድ ውስጥ የሚገኘው ‹የመሐመድን ብርሃን› የማስተላለፍ አፈ ታሪክ፡ በፐርሺያን ጥንታዊና ‹ዳዛቲር ኢ ሰስማኒ› በተባለው መጽሐፍ ውስጥ በልዩ ልዩ ክፍሎች ሌሎች ነገሮች ከእርሱ የተፈጠሩበት ስለተባለውና ስለ ዞሮአስተር ከተጻፈው ጋር በጣም ተመሳሳይነት አለው፡፡ በተለይም ተመሳሳዩ ሐሳብ ከዚህ በላይ ‹በሚኑኪራድ› ውስጥ ተገኝቶ እንደጠቀሰው ሁሉ በጥንታዊ የዞሮ አስተር ጽሐፎች ውስጥ ይገኛል፡፡

6. የሙታን ድልድይ

ይህ ‹የሙታን ድልድይ› በመሐመዳውያን ልማድ ዘንድ ‹አስ-ሲራት› ወይንም ‹መንገዱ› በመባል ይታወቃል፡፡ ስለዚህ አስደናቂ ድልድይ እጅግ በጣም ብዙ ዝርዝሮች በመሐመዳውያን ተሰጥቷል፣ እርሱም ከፀጉር በጣም የቀጠነና ከሰይፍ ደግሞ የሳለ ተብሏል፡፡ ድልድዩም በሲዖል ጥልቅ ላይ አልፎ ይሄዳል፣ እናም በፍርድ ቀን ከምድር ወደ ሰማይ መሸጋገሪያው ብቸኛ መንገድ እርሱ ብቻ ነው፡፡ ሁሉም በእርሱ ላይ እንዲያቋርጡ ይታዘዛሉ፡፡ የተሰጠም ሙስሊምም በመላእክት ተመርቶ ያለምንም ችግር ድልድዩን ያቋርጠዋል ነገር ግን የማያምኑት መሻገር አይችሉም እናም በሲዖል እሳት ውስጥ በጭንቅላቸው ተዘቅዝቀው ይወድቃሉ፡፡

ምንም እንኳን ሲራት የሚለው ቃል በቁርአን ውስጥ በምሳሌያዊ ስሜት መንገድ ለሚለው ሐሳብ የሚያገለግል ቢሆንም በሐረጉ ውስጥ ‹አስ ሲራቱል ሙስታኪም› (‹ቀጥተኛው መንገድ› ምዕራፍ አንድ ላይ እንዳለው)፣ ነገር ግን በቀጥተኛ መልኩ በፍፁም የአረብኛ ቃል አይደለም፡፡ የቃሉም ምንጭ የዚያ ድልድይ ስም አፈታሪክ ከየት እንደመጣ ያሳያል፡፡ ቃሉም የመጣው በእርግጥ ከአረባዊ ወይንም ሴሜቲካዊ ስረ መሰረት አይደለም ነገር ግን ፐርሺያዊ ነው፡፡ ‹ቺንቫት› የሚለው ቃል በአረብኛው ቋንቋ አያስኬድም፣ ምክንያቱም የአረብኛ ቋንቋ ‹ቸ› የሚለውን ቃል የሚወክል ምንም ፊደል የለውምና፣ ስለዚህም ‹ቸ› በ‹ሲራት› የመጀመሪያ ፊደል ‹ሲ› ተብሎ ተተክቷል፡፡ በፐርሺያም ቋንቋ ‹ቺንቫት› ማለት ሰብሳቢ ወይንም የሚደምር ወይንም የሚሰበስብ ማለት ነው፣ ወይንም ዘገባን የሚወስድ ማለት ነው፡፡ ስለዚህም የአረብኛው ሲራት የተገኘው ሁለቱን በማደባለቅ ብቻ ነው፣ ምክንያቱም አቨስታ ስለ ቺንቫት ምንም አይናገርምና፡፡ ይሁን እንጂ በአቨስታ ላይ የምናገኘው ስለ ‹ቺንቫቶ ፕርቱስ› ብቻ ነው፡፡ ‹የእርሱም ድልድይ ያ የሚቆጥረው›፣ መልካምንና ክፉ ስራዎችን፡፡ ይህም ድልድይ የሚዘረጋው ‹ከአልበርዝ› ተራራ እስከ ‹ቻካት ዳይቲህ› ድረስ ከሲዖል በላይ ድረስ ነው፡፡ የሞተው የእያንዳንዱ ሰው ነፍስ የሆነ ዓይነት የቀብር ስርዓት ከተከናወነ በኋላ ወዲያውኑ ነፍሱ ድልድዩ ጋ ይደርሳል እንዲሁም መንግስተ ሰማያት ለመድረስ በእርሱ ላይ ማለፍ አለበት፡፡ ድልድዩንም ባቋረጠበት ጊዜ በ‹ሚትራ፣ በራሹና እና ስራዖሻ› ፍርድ ይሰጥበታል ይህም መልካም ወይንም መጥፎ በሆነው ስራው ዘገባ መሰረት ነው፡፡

የገነት በሮች እርሱን ለማስገባት ክፍት የሚሆኑት መልካሙ ስራው ከክፉዎቹ ከበለጠ ብቻ ነው፡፡ እርሱ ወደ ሲዖል ውስጥ የሚጣለው ደግሞ ክፉ ስራዎቹ ከመልካሙ ጋር ሲነፃፀሩ ክፉ ከሆኑ ብቻ ነው፣ ነገር ግን ክፉዎቹ ከመልካሞቹ ጋር እኩል ከሆኑ የሟቹ መንፈስ መጠበቅ አለበት የመጨረሻውን ፍርድ (ቩላይታይ)፣ የሚሆነው በመጨረሻው ነው ወይንም የመጨረሻው ትግል በዖርማዝድ በአሪማን መካከል፡፡

‹ሲራት› የሚለውን የመሐመዳንን ዶክትሪን ቃል ምንጭ ብቻ ለማሳየት ሳይሆን ‹ዲንካርት› ከሚባለው ከፓላቪ መጽሐፍ ላይ የሚከተለውን አጭር አንቀፅ መተርጎም በቂ ነው ‹እኔም ከብዙ ኃጢአት ሸሸሁኝ፣ እኔም የራሴን ፀባይ ንፁህ አድርጌ ጠበቅሁኝ ይህም ስድስቱን የሕይወትን ንፁህ ባህርያትን ድርጊት፣ ንግግርና ሐሳብ እንዲሁም እውቀትና አዕምሮ እንዲሁም ግንዛቤን ነው በአንተ ፍላጎት በመጠበቅ ነው፣ ኦ ኃያሉ የመልካም ስራዎች ምክንያት፡፡ በፍትህ እኔ አድርጌዋለሁኝ ማለትም ያንተ አምልኮ በጥሩ ሐሳብ፤ ንግግርና ስራ ይህም እኔ በብሩህ መንገድ ላይ እንድቀጥል ነው ስለዚህም በከባዱ የሲዖል ቅጣት ውስጥ እንዳልደርስ ነው ነገር ግን በቺንቫት ላይ እንድሻገር እናም ያንን የተባረከ መኖሪያን እንድኖርበት በሽቶ የተሞላውን ሙሉ ለሙሉ አስደሳች የሆነውን ሁልጊዜ መልካም የሆነውን መኖሪያ እንድደርስበት ነው›፡፡ በአቨስታ ውስጥ እንዲሁም እኛ የምናገኘው ነገር ከተመሳሳዩ እምነት ጋር የሚሄዱ እጅግ በጣም ብዙ እንደዚህ ዓይነት ማገናዘቢያዎች አሉ፡፡ ከሌሎቹም መካከል መልካም ወንዶችና መልካም ሴቶች በሚለው አንቀፅ ውስጥ ‹ማንን ነው እኔ ልመራ የሚገባኝ በፀሎት ውስጥ እንደዚህ እንደ አንተ ከበረከት ሁሉ ጋር እኔ በቺንቫት ድልድይ ላይ ልመራቸው ይገባኛል›፡፡

የዚህ እምነት የአሪያን ምንጭነት ተጨማሪው ማረጋገጫ የሚገኘው በጥንታዊ የስካንዲናቪያን አፈታሪክ ውስጥ በመገኘቱ እውነታ ነው እርሱም በ‹ቢፍሮስት› ውስጥ የሚገኘው ነው በአጠቃላይም የሚመስለው ‹የአማልክት ድልድይ ነው› በእርሱም ላይ እነርሱ ከ‹አስጋርድ› (በሰማይ) መኖሪያ ወደ መሬት የሚሻገሩበት ነው፡፡ እርሱም ቀስተ ዳመና ነው፡፡ ይህም በአንድ ጊዜ የሚገልጠው ነገር የድልድዩ አፈታሪክ የተመሰረተበትን የመጀመሪያ መሰረት ነው፣ እንዲሁም ምንያህል ጥንታዊ መሆኑን ያሳያል ምክንያቱም ስካንዲናቪያኖች ሐሳቡን ወደ ዩሮፕ ሲያመጡት፡፡ ይህም ደግሞ ለእነርሱና ለፐርሺያውያኖች በጣም በጥንት ጊዜ በጣም የታወቀ ነበር፡፡ በግሪክ የቀስተ ደመና የአማልክት መልእክተኛ ነበር (የኢሪስ) በኢሊያድ ውስጥ እንደተቀመጠው፤ ነገር ግን መሬትንና ሰማይን የሚያገናኝ ድልድይ ሐሳብ ግን ጠፍቶ የነበረ ይመስላል፡፡

7. ከፐርሺያ የተወሰዱ ሌሎች ሐሳቦች

የፐርሺያ ሐሳቦች በእስልምና ላይ በጣም ተፅዕኖ ያደረጉባቸው ሌሎች ብዙ ጉዳዮች የሚገኙ መሆናቸው ምንም ጥርጥር ባይኖረውም እስካሁን የተነገሩት ለእኛ በጣም ብቁዎች ናቸው፡፡ ቢሆንም የዚህን ክፍል ጥያቄ እዚህ ላይ ማጠቃለል የለብንም፤ ስለዚህም ጥቂት ጠቀሜታ ያላቸውን  ሌሎች ሁለት ነጥቦችን መጥቀስ ይኖርብናል፡፡

አንደኛው፡ እያንዳንዱ ነቢይ ከመሞቱ በፊት እርሱን ተከትሎ ስለሚመጣው ነቢይ ማስታወቂያ ይናገራል የሚለው የሙስሊሞች እምነት ነው፡፡ ይህ ሐሳብ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ምንም ድጋፍ የለውም፡፡ የመሲሁን መምጣት የተናገሩ ትንቢቶችን በምናገኝበት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለዚህ ለመሐመዳውያን ፅንሰ ሐሳብ የሚሰጠው ምንም ፍንጭ የለም፡፡ ምናልባትም ሐሳቡ የመጣው ከዞሮአስተሪያን ‹ዳሳቲር ኢ አስማኒ› ከሚለው ስራ ላይ ነው፡፡ ይህ ስራ የሚናገረው እራሱ ትልቅ ጥንታዊነት እንዳለው ነው እንዲሁም (ከመጀመሪያው ክፍል ውስጥ ትርጉም ሰጪ ነገርን ለማውጣት ችግር ያለው መሆኑን ምንም ሳንጠራጠር) በዘመናዊዎቹ ፓርሲስ የሚታመነው ‹በሰማያዊ ቋንቋ ተቀናብሯል› በማለት ነው፡፡ ወደ ጥንታዊ የፐርሺያን ዲያሌክት ‹ዳሪ› የተደረገ ቃል በቃል ትርጉም ቢሆንም ክፍሉን አብሮት ይገኛል፣ ይህም ባለፈው ምዕተ ዓመት መጀመሪያ ላይ በፐርሺያ የተገኘ ነው ይባላል እርሱም በቦምቤዩ ሙላ ፊሩዝ ኤዲት ተደርጓል፡፡ እርሱም አስራ አምስት ትራክቶችን የያዘ ሲሆን እነርሱም ለአስራ አምስት ተከታታይ ነቢያት የተገለጡ ናቸው ይባላል፡፡ የመጀመሪያውም የተመሳሰለው ከማሃባድ የመጨረሻው ደግሞ ከሳሳን ጋር ነው፣ ይህም ከሳሳኒያን ስርወ መንግስት እራሳቸውን እንደመጡ የሚገምቱበት ነው፡፡ የዳሪ ትርጉም በ‹ኩሳሩ ፓርቪዝ› (580-5 ዓ.ም) ዘመን ጊዜ እንደነበረ ይነገራል ስለዚህም የመጀመሪያው ትንታዊነት ያለው ነው፡፡ በእያንዳንዱም ትራክት መደምደሚያ አቅራቢያ ነገር ግን በመጨረሻው ላይ ስለሚከተለው የሚመጣ ነቢይ ትንቢት የሚመስል ነገር ይገኛል፡፡ የዚህም ዓላማ በጣም ግልጥ ነው፡፡ ብዙ ፓረሲሶች ይህንን መጽሐፍ አይቀበሉትም፣ ሙስሎሞችን ግን ሐሳቡ በጣም ያስደሰታቸው ይመስላል ምክንያቱም በዚህ ውስጥ ለእነርሱ እምነት መግቢያ ቀዳዳን አግኝተዋልና፡፡

ሁለተኛው፡ የእነዚህ የአስራ አምስቱም ትራክቶች ሁለተኛው ቁጥር እንደሚከተለው የሚል መሆኑንም ማስተዋል በጣም ጠቃሚ ነው፡ ‹በእግዚአብሔር ስም፣ በሰጪው፣ በመሐሪው፣ በይቅር ባዩ በፃድቁ›፡፡ ከዘጠነኛው የቁርአን ምዕራፍ በስተቀር በቁርአን ውስጥ ያሉት ምዕራፎች የመጀመሪያ አረፍተ ነገሮች ከእነዚህ ጋር በጣም የተመሳሰሉ ለመሆናቸው በጣም ግልጥ ነው፡፡ ‹በአላህ ስም እጅግ በጣም ርኅሩኅና አዛኝ በኾነው›፡፡ ቁርአን ምናልባትም ይህንን ከዞሮአስተሪያን መጽሐፍ ላይ ተውሶት ሊሆን ይችላል፣ ምክንያቱም ‹ቡንዳሂሸኒህ› ላይም የሚከተለው ‹በኦርማዝድ ስም በፈጠሪው› የሚለው ተመሳሳይ ሐረግ ይገኛልና፡፡ ሌሎች ደግሞ የሚያስቡት በቁርአን ላይ ያለው ሐረግ ከአይሁድ የመነጨ ነው በማለት ነው፡፡ በሚቀጥለው ምዕራፍ ውስጥ እንደምንመለከተው ልማድ የሚለው ከሐኒፎች አንዱ፣ ‹ዑሚያህ›፣ ከታይፍ የሆነው ገጣሚ፣ ለ‹ቁራይሾች› ይህንን ሐረግ አስተምሮአቸዋል በማለት ነው፣ ይህም እርሱ ወደ ሶሪያና ወደ ሌላ ቦታ እንደ ነጋዴ ጉዞ ባደረገበት ጊዜ ከክርስትያኖችና ከአይሁዶች ጋር ካደረገው ንግግር ተምሮታል፡፡ መሐመድ በዚህ መንገድ ሰምቶት ከሆነና ከወሰደው ያለምንም ጥርጥር በተወሰነ ሁኔታ ቀይሮታል፣ ይህ ደግሞ በወሰደውን በማንኛውም ነገር ላይ ሁልጊዜ ያደርገው የነበረ ነው፡፡ ነገር ግን እነዚህ ሐሳቦች በጣም በአመዛኙ የሚመስሉት የዞሮ አስተሪያን ምንጭነት ያላቸው እንጂ ከአይሁድ የመጡ አለመሆናቸው ነው፣ እናም ‹ዑሚያ› በንግድ ጉዞው ወቅት ከፐርሺያኖች የተማረው መሆን አለበት፡፡

መደምደሚያ

በመሐመድ ጊዜ የፐርሺያ ተፅዕኖ በአረቢያ ላይ ምን ያህል መጠነ ሰፊ እንደነበረ አይተናል፣ ስለዚህም በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ያሉትን ከክስተቶቹ ሁሉ ውስጥ የሚመጣውን መደምደሚያ ላለመቀበል የሚያደርግ ምንም ቅድሚያ ችግር አይኖርም ማለትም ዞሮአስተሪያን ሐሳቦችና አፈታሪኮች እስልምና በቁርአንና በልማዱ ውስጥ ላስቀመጣቸው አንዳንድ ክፍሎች ምንጮች ናቸው፡፡ ልማድ እራሱ የዚህን ምናልባትነት ያረጋግጣል ምክንያቱም ‹ሮዳቱል አባብ› የሚነግረን በእነርሱ ቋንቋ ጥቂት ቃላትን መናገር የመሐመድ ልማድ እንደነበር ነው፡፡ ከተለያዩ አገሮች ውስጥ ወደ እርሱ ለሚመጡት ለእንደዚህ ዓይነት ጎብኝዎች በአንድና በሁለት ክስተቶች ውስጥ እርሱ የፐርሺያን ቋንቋ ተናግሯል፣ ስለዚህም በዚህ መንገድ ጥቂት የፐርሺያ ቃላት በአረብኛ ቋንቋ ውስጥ የመግቢያን በር አግኝተዋል ማለት ነው፡፡ በእርግጥ በዚህ አረፍተ ነገር ውስጥ እጅግ በጣም ብዙ አፈታሪኮች አሉ፤ ነገር ግን በራሱ መንገድ እራሱ ጠቃሚ ነው፤ ከሌላ አገር ቋንቋ ጋር መሐመድ ግንኙነት ባይኖረውም በጣም በግልፅ ቢያንስ ጥቂት የሆነ የፐርሺያን ግንኙነት እንደበረው ያሳያል፡፡ እንደገናም በሌሎች  የፐርሺያ የተለወጡ መካከል የኢብን ኢሻክ እና ኢብን ሂሻም ‹ሲራቱል ራሱል› እንደነገረን እዚያ ሳልማን የሚባል ትምህርትና ችሎታ የነበረው አንድ ሰው ነበር፡፡ ቁራይሾችና አባሪዎቻቸው መዲናን በህዳር 627 ዓ.ም ሲያጠቁ መሐመድ ከተማዋን የተከላከለው በተከበረው የጉድጓድ የምሽግ ዘዴ ነበር ይህም አረቦቹ ከዚያ በፊት ተጠቅመውበት የማያውቁት የነበረ ሲሆን ከሳልማን ወታደራዊ ልምድና ምክር የመጣ እንደነበረ ተናግረዋል፡፡ በጣይፍ ላይ መሐመድ ዘመቻን ባደረገበት ጊዜ (በ630 ዓ.ም) በሳልማንስ ምክር ወንጭፍን ተጠቅሞ ነበር፡፡ አንዳንዶች የሚሉት ሳልማን ምንም እንኳን ሁልጊዜ እንደ ‹ፐርሺያን› የታወቀ ቢሆንም በመጀመሪያ ከሜሶፖቶሚያ የተማረከ ክርስትያን ነበር፡፡ ምንም እንኳን የተሰጠው ስም ይህንን ባይደግፍም ይህ እውነት ሊሆንም ላይሆንም ይችላል፡፡ ይህ እውነት ካልሆነ ምናልባትም እርሱ በመሐመድ ጠላቶች መሐመድን ሲከሱት በአንዳንድ የቁርአን ክፍል ውስጥ የተጻፈውን ነገር በማቀናበር በኩል ይረዳዋል ያሉት ሳይሆን አይቀርም ምክንያቱም በቁርአን 26.103 ‹እነርሱም እርሱን (ቁርአንን) የሚያስተምረው ሰው ብቻ ነው ማለታቸውን በእርግጥ እናውቃለን የዚያ ወደሱ የሚያስጠጉበት ሰው ቋንቋ ዐጀም ነው ይህ (ቁርአን) ግን ግልፅ ዐረብኛ ቋንቋ ነው፡፡› ሳልማን የፐርሺያ ሰው ባይሆን እንኳን በመሐመድ ቡድን ውስጥ የነበረና በቁርአን ውስጥ የተጨመሩ አንዳንድ ክፍሎችን ለመሐመድ ያስተምራል ተብሎ ይታመንበት የነበረ አንድ ፐርሺያዊ ሰው በመካከላቸው የነበረ መሆኑን ጥቅሱ ለማስረዳት በጣም በቂ ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ ውስጥ የምናየው ነገር የፐርሺያ አፈታሪኮች በሚገባ የታወቁ የነበሩ መሆናቸውንና ቢያንስ፤ ቢያንስ በአረቦች የሚታወቁት የፐርሺያ አፈታሪኮች  የመለኮት ቃል ነው ተብሎ በሚጠራው ‹በቁርአን› ውስጥ አብረው ተቀምጠዋል፡፡ መሐመድም እራሱ ለዚህ ክስ ብቁ መልስንም ለመስጠት አልቻለም ነበር፤ ምክንያቱም የውጭ አገር ሰው የአረብኛ ቋንቋውን አቀራረብ እንዲያሻሽል ያስተምረዋል ብሎ ማንም አይገምትም ነበርና፡፡ ክሱ የጎዳው ነገሮችን ነው እንጂ የቁርአንን ቋንቋ አይደለም፡፡ ከዚህም በላይ እንዳረጋገጥነው መሐመድ ከአህዛብ አረቦችና ከአይሁዶች አፈታሪኮች ውስጥ ብዙ ነገሮችን ወስዷል ስለዚህም ከዞሮአስተሪያን ምንጮች ለመውሰድ ፈቃደኛ የማይሆንበትና ዝግጁ የማይሆንበት ምንም ምክንያት አልነበረውም፡፡ በእርግጥ በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ያቀረብናቸው ክስተቶች በጥሩ ሁኔታ የሚያረጋግጡት እርሱ እንዳደረገው ነው ስለዚህም እነዚህ የፐርሺያ አፈታሪኮች በጣም ብዙዎቹ ለፐርሺያዎች በጣም የታወቁ የነበሩት ከሌሎች የአርያን ቤተሰብ (ዘር) አገሮች ቅርንጫፍ ጋር የሰጡት የእስልምናን ሌላውን የመጀመሪያ ምንጭን ነው፡፡

የአዘጋጁ ማሳሰቢያ፡

ከዚህ በላይ በቅደም ተከተል የቀረቡት ነጥቦች የሚያመለክቱን ጭብጥ የቁርአንን ትክክለኛ ገፅታ ነው፡፡ እነዚህን ጽሑፎች ከተመለከተ በኋላ ቁርአንን የሚያነብ ማንኛውም ሰው የቁርአን ምንጩ የሰማይና የምድሩ ፈጣሪ እግዚአብሔር ሊሆን ከቶ እንደማይችል ይገነዘባል፡፡

ቁርአን ምንጩ እግዚአብሔ ካልሆነ ደግሞ ሙስሊሞች ከቅዱስ እግዚአብሔር ጋር ህብረት ለማድረግ እርሱንም ለማምለክ ወደ እርሱም መንግስት ለመግባት የሚኖራቸውን ተስፋ በሙሉ የሚያጨልም ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ በጣም ግልፅ ነው፣ እውነተኛው እግዚአብሔር በውሸትና ከእርሱ ባልመጣ ቃል መሠረት ሊመለክ ወደ መንግስቱም ለመግባት አይቻልም፡፡

የመጽሐፍ ቅዱሱ እግዚአብሔር በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተናገራቸው ነገሮች ሁሉ ትክክለኛ የሆኑና በሕዝቡ ታሪክም ውስጥ ተፈትነው ያለፉ ናቸው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሰጡት ሐሳቦች አንዳቸውም ከሌላ ሃይማኖት አልተኮረጁም ወይንም አልተቀዱም፡፡ የሆነው ሆኖ የእስልምና ልማድና ቁርአንም እራሱ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አሳስተው የወሰዷቸው ነገሮች እጅግ ብዙ ናቸው፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ በቀደምትነቱ፣ በእውነተኛነቱ፣ ታሪኩና በውስጡ ያለው ነገር ለአንባቢ ያለምንም ችግር በግልጥ የሚገባ በመሆኑ ሊከበርና ሊታመን ይገባዋል፡፡ ከሁሉ በላይ በጣም ግልጥ በሆነ መንገድ ኃጢአተኛው ሰው ከቅዱሱ እግዚአብሔር ጋር የሚታረቅበትን የፀጋ መንገድ ያቀርባል፡፡ የዚህ ገፅ አዘጋጆች ትልቅ ትኩረት አንባቢዎች መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ማንበብ እንዲመለሱና የዘላለም ሕይወት የሚገኝበትን መንገድ ለራሳቸው እንዲረዱ ነው፡፡

አንባቢዎች ሆይ! ቆም ብላችሁ የግል ሕይወታችሁን መርምሩ፣ የሃይማኖታችሁን እውነታ ተረዱ ከዚያም ስለ ዘላለም ሕይወት ትክክለኛ ምላሽ የሚሰጣችሁን መንገድ እግዚአብሔር እንዲመራችሁ ጠይቁት እርሱም አዳኙን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስንና እርሱ ለእናንተ የሰራውን ስራ ያሳያችኋል፡፡ ከዚያ በኋላ የናንተ ድርሻ ወደ ጌታ ኢየሱስ የማዳን ስራ መቅረብና ከእርሱ የዘላለም ይቅርታን ለመቀበል በትህትናና በንስሐ መምጣት ነው፡፡ እርሱ እንዲህ የሚል ቃል ኪዳንን ገብቶላችኋል፤ ‹ወደ እኔ የሚመጣውን ከቶ ወደ ውጪ አላወጣውም›፣ ጌታ ኢየሱስ ይህንን ለማድረግ ኃይልም ብቃትም አለው ስለዚህ ወደ ጌታ ኢየሱስ አሁኑኑ ኑ፣ ጌታም በፀጋው ይርዳችሁ! አሜን፡፡

የትርጉም ምንጭ: THE ORIGINAL SOURCES OF THE QUR'AN 

ሙሉ መጽሐፉ በአማርኛ:  የቁርአን የመጀመሪያ ምንጮች

ለእስልምና መልስ አማርኛ  ዋናው ገጽ