የቁርአን የመጀመሪያ ምንጮች

ምዕራፍ አራት ክፍል ሁለት

የድንግል ማርያም ታሪክ 

REV. W. ST. CLAIR TISDALL, M.A., D.D

ትርጉምና ቅንብር በአዘጋጁ

የማርያም ታሪክ በቁርአንና በነቢዩ ልማዶች ላይ እንደሚገኘው ሙሉ በሙሉ የተወሰደው ከአፖክሪፋዊ (አዋልዳዊ) ወንጌሎችና ተመሳሳይ ባህርይ ካላቸው  ስራዎች ላይ ነው፡፡ ይሁን እንጂ መሐመድ በውስጡ ሌላ የስህተትን ነገር አስገብቶበታል ይህም ወደ ታሪኩ ከመግባታችን በፊት ማግኘት የሚገባን ምንጭ ነው፡፡

ቁርአን 19.28፣29፣ የተነገረን ጌታን ከወለደች በኋላ ማርያም ወደ ሕዝቧ ስትመለስ እነርሱ ለእርሷ እንደሚከተለው አሏት፡- ‹የሃሩን እህት ሆይ አባትሽ መጥፎ ሰው አልነበረም እናትሽም አመንዝራ አልነበረችም አሉዋት፤ ወደርሱም ጠቀሰች በአንቀልባ ያለን ሕፃን እንዴት እናናግራለን አሉ›፡፡ ከእነዚህ ቃላት እርግጥ የሆነው ነገር በመሐመድ አመለካከት ውስጥ ማርያም ከሙሴና ከአሮን እህት ከማርያም ጋር አንድ መሆኗ ነው፡፡ ይህም በጣም ግልጥ የተደረገው በቁርአን 66.12 ላይ ነው፣ በዚያም ማርያም የቀረበችው ‹የዒምራን ሴት ልጅ› ተደርጋ ነው፣ ኢምራንም የሚለውም የአረብኛ ስም፤ ለሂብሩው ‹አምራም› ለአማርኛው ‹እንበረም› የተሰጠ ነው፡፡ እርሱም በሙሴ መጽሐፍት ውስጥ ‹የአሮን የሙሴና የእህታቸው የማርያም› አባት ነው ዘኁልቁ 26.59፡፡ የአሮን እህት የሚለው መጠሪያ ስም ደግሞ ለማርያም የተሰጠ ስያሜ መሆኑን በዘፀዓት 25.20 ላይ ተጽፎ እናገኘዋለን፣ ስለዚህም ይህንን አባባል መሐመድ የተዋሰው ከዚህ ክፍል ላይ መሆን አለበት፡፡ ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን የወለደችውን ማርያም እርሱ ከመወለዱ ከ1570 በላይ ዓመታት በኋላ ከነበረችው ሴት ማለትም ከብሉይ ኪዳኗ ማርያም ጋር ለማምታት ለመሐመድ ምክንያት የሆነው ነገር በአረብኛ ማርያምና፤ ሚሪያም የሚለው ስም በአንድ መንገድ ብቻ ማርያም ተብሎ ስለሚታወቅ ነው፡፡ የስሞች መለያየት የታሪካዊ ቅደም ተከተል ችግር ይኖረዋል ብሎ የሚለው ሐሳብ ለመሐመድ አልታየውም፡፡ ይህም በሻናሜህ ተረት ውስጥ ያመጣናል፣ በዚያም ፊርዶሲ የነገረን ነገር ጀግናው ፋሪዱን ዳሃክን ባሸነፈበት ጊዜ (በፋርሳውያን ዛሃክ ተብሎ የሚነበበውን)፣ በአምባገነኑ ግንብ ውስጥ የጃምሲድን ሁለት እህቶችን አገኘ፣ እነርሱም እዚያ በእስራት ውስጥ ተቀምጠው ነበር፡፡ የተነገረንም ፋሪዳን በእነርሱ አስደሳችነት (ውበት) ተነካ፡፡ ይህም የታሪኩን ሌላኛ መልክ ሲሆን፣ በሌላ ጎኑ ደግሞ ከግጥሙ የምንረዳው እነዚህ ቆነጃጅት ሴቶች በዳሃክ እስር (ቁጥጥር) ስር ከኋላኛው ግዛት መጀመሪያ ጀምሮ እንደቀጠሉ ነው፣ ይህም ከመሐመድ ስህተት በፊት ከአንድ ሺ ዓመት በፊት መሆኑ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከዚህም በጣም በበለጠ መልኩ፤ ቅደም ተከተሉ እጅግ በጣም ትልቅ ክፍተት አለው፣ ይህም በፍቅር ዓይነት ልብ ወለድ ውስጥ ሊፈቀድ የሚችል ሲሆን በመለኮት መገለጥ ውስጥ ግን ቦታ የለውም፡፡ መሐመዳውያን ተንታኞች ይህንን ታሪካዊ ስህተት ለማስተባበል ከንቱ ሙከራዎችን አድርገዋል፡፡

በመሐመድ ስህተት ላይ ለመጨመር አስፈላጊ ከሆነ፣ ሚሪያምን በተመለከተ በአይሁድ ልማድ ላይ የሚከተለው እንደተጨመረ መመልከት እንደሚቻል ነው፣ ‹የሞት መልአክ በእርሷ ላይ ስልጣን ሊኖረው አልቻለም፣ ነገር ግን በሌላው ጎን እርሷ በ(መለኮት) መሳም ነው የሞተችው፣ ትሎችና ነፍሳት በእርሷ ላይ ምንም ኃይል አልነበራቸውም›፡፡ ቢሆንም ግን አይሁዶች ማርያም እስከ ክርስቶስ ልደት እንደኖረች በፍፁም አልተናገሩም፣ እንዲሁም ከድንግል ማርያም ጋር አላመሳሰሏትም፡፡

አሁን ቁርአንና ልማድ ስለ ኋለኛው የሚሉትን ነገር እንመልከታለን፡፡ በቁርአን 3.35-37 ላይ የሚከተለውን እናነባለን፡-

‹የዒምራን ባለቤት (ሐና) ጌታዬ ሆይ እኔ በሆዴ ውስጥ ያለውን (ፅንስ ከሥራ) ነጻ የተደረገ ሲኾን ለአንተ ተሳልኩ ከኔም ተቀበል፤ አንተ ሰሚው ዐዋቂው ነህና ባለች ጊዜ (አስታውስ)፡፡ በወለደቻትም ጊዜ ጌታዬ ሆይ እኔ ሴት ኾና ወለድኳት አላህም የወለደችውን ዐዋቂ ነው ወንድም እንደ ሴት አይደለም እኔም መርየም ብዬ ስም አወጣሁላት እኔም እስዋን ዝርያዋንም ከተረገመው ሰይጣን በአንተ እጠብቃቸዋለሁ አለች፡፡ ጌታዋም በደህና አቀባበል ተቀበላት በመልካም አስተዳደግም አፋፋት ዘከርያም አሳደጋት ዘከርያም በርሷ ቁጥር እርስዋ ዘንድ ሲሳይን አገኘ መርየም ሆይ ይህ ለአንቺ ከየት ነው? አላት እርሱ ከአላህ ዘንድ ነው አላህ ለሚሻው ሰው ሲሳዩን ያለድካም ይሰጣል አለችው፡፡›

ከዚህ በተጨማሪና ይህንን ታሪክ በመግለጥ፣ ባይዳዊ እና ሌሎች ተንታኞች እና ልማዳዊዎች የነገሩን የሚቀጥለውን ል ነገር ነው፡ ‹የዒምራን ሚስት መካን ነበረች በዕድሜዋም አርጅታ ነበር፡፡ አንድ ቀን አንዲት ወፍ ለጫጩቶቿ ምግብን ስትሰጥ ተመልክታ ለልጅ በጣም ናፈቀች፣ ከዚያም እግዚአብሔር ልጅን እንዲሰጣት ለመነችው፡፡ እንዲህም አለች፡ ‹ኦ አምላኬ ሆይ አንተ ልጅን ብትሰጠኝ ወንድ ቢሆን ወይንም ሴት፣ እኔ ለአንተ እንደስጦታ በኢየሩሳሌም በፊትህ እሰጠዋለሁ› አለች፡፡ እግዚአብሔርም ፀሎቷን ሰማና መለሰላት እርሷም ልጅን ፀንሳ ሴት ልጅን ወለደች፣ ማርያንም፡፡ ጃላሉዲን የሚነግረን የማርያም እናት ስም ሐና ነበር በማለት ነው፡፡ እርሷም ማርያምን ወደ ቤተመቅደስ ስታመጣት ለካህናቶቹም አሳልፋ ስትሰጣት፣ ስጦታውን ተቀብለው ዘካርያስ ልጅቷን እንዲጠብቃት መደቡት፡፡ እርሱም በክፍል ውስጥ አስቀመጣት ከእርሱም ሌላ ማንንም አያስገባም ነበር ነገር ግን የዕለት ምግቧን መልአክ ይሰጣት ነበር፡፡

ወደ ቁርአን 3.42-47 ስንመጣ የምናገኘው ነገር ማርያም ትልቅ እንደሆነች ነው፡ ‹መላእክትም ያሉትን (አስታውስ) መርየም ሆይ አላህ በእርግጥ መረጠሸ አነጻሽም በዓለማት ሴቶችም ላይ መረጠሸ፡፡ መርየም ሆይ ለጌታሽ ታዘዢ ስገጂም ከአጎንባሾቹም ጋር አግንብሺ፡፡ ይኽ ወደ አንተ የምናወርደው የኾነ ከሩቅ ወሬዎች ነው፣ መርየምንም ማን እንደሚያሳድግ ብርዖቻቸውን (ለዕጣ) በጣሉ ጊዜ እነሱ ዘንድ አልነበርኩም በሚከራከሩም ጊዜ እነሱ ዘንድ አልነበርክም፡፡ መላእከት ያሉትን (አስታውስ) መርየም ሆይ አላህ ከርሱ በኾነው ቃል ስሙ አልመሲህ ዒሳ የመርየም ልጅ በዚህ ዓለምና በመጨረሻውም ዓለም የተከበረ ከባለሟሎችም በኾነ (ልጅ) ያበስርሻል፤ በሕፃንነቱና በከፈኒሳነቱ ሰዎቹን ያነጋግራል ከመልካሞቹም ነው (አላት) ጌታዬ ሆይ ሰው ያልነካኝ ስኾን ለኔ እንዴት ልጅ ይኖረኛል? አለች፣ ነገሩ እንደዚህሽ ነው አላህ የሚሻውን ይፈጥራል አንዳችን በሻ ጊዜ ለርሱ ኹን ይለዋል ወዲያውኑም ይኾናል አላት፡፡›

ብርዖቻቸውን ወይንም እስኪሪብቶቻቸው ለዕጣ ጣሉ የሚለውን በተመለከተ ባይዳዊ እና ጃላሉዲን ያሉት ዘካርያስ እና ሃያስድስት ሌሎች ቄሶች ማርያምን ለመጠበቅ በመፈለግ ተፎካክረው ነበር፡፡ እነርሱም ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ፈፋ ሄደው ወደ ውሃው ውስጥ ብርዖቻቸውን ጣሉ ነገር ግን ከዘካርያስ ብርዕ በስተቀር ሁሉም ሰጠሙ ከዚህም የተነሳ ዘካርያስ ማርያምን እንዲጠብቅ ተሰጠው፡፡

አሁን ወደ ቁርአን 19.16-34 ስንመጣ የሚከተለውን የክርስቶስን አወላለድ ታሪክ ነገር እናገኛለን፡

‹በመጽሐፉ ውስጥ መርየምንም ከቤተሰቧ ወደ ምስራቃዊ ስፍራ በተለየች ጊዜ (የኾነውን ታሪኳን) አውሳ፡፡ ከነርሱም መጋረጃን አደረገች፣ መንፈሳችንንም (ጂብሪልን) ወደርሷ ላክን ለርሷም ትክክለኛ ሰው ሆኖ ተመሰለላት፡፡ እኔ ከአንተ በአልረሕማን እጠበቃለሁ ጌታህን ፈሪ እንደ ኾንክ (አትቅረበኝ) አለች፡፡ እኔ ንፁህን ልጅ ለአንቺ ልሰጥሽ የጌታሽ መልክተኛ ነኝ አላት፡፡ (በጋብቻ) ሰው ያልነካኝ ኾኜ አመንዝራም ሳልኾን ለኔ እንዴት ልጅ ይኖረኛል አለች፡፡ አላት (ነገሩ) እንደዚህሽ ነው ጌታሽ እርሱ በእኔ ላይ ገር ነው ለሰዎችም ታምር ከኛም ችሮታልናደርገው (ይህንን ሠራን) የተፈረደም ነገር ነው አለ (ነፋባትም)፡፡ ወዲያውኑም አረገዘችው በርሱም (በሆድዋ ይዛው) ወደ ሩቅ ስፍራ ገለል አለች፡፡ ምጡም ወደ ዘንባባይቱ ግንድ አስጠጋት ዋ ምኞቴ ምነው ከዚህ በፊት በሞትኩ ተረስቼም የቀረሁ በኾንኩ አለች፡፡ ከበታቿም እንዲህ ሲል ጠራት - አትዘኝ ጌታሽ ከበታችሽ ትንሽን ወንዝ በእርግጥ አድርጓል፡፡ የዘምባባይቱንም ግንድ ወዳንቺ ወዝውዣት ባንቺ ላይ የበለስን የተምር እሸት ታረግፍልሻለችና፡፡ ብይም ጠጭም ተደሰችም ከሰዎችም አንድን ብታይ እኔ ለአልረህማን ዝምታን በፍጹም አላነጋግርም በይ፡፡ በርሱም የተሸከመቺው ኾና ወደ ዘመዶችዋ መጣች መርይም ሆይ ከባድን ነገር በእርግጥ ሠራሽ አሏት፡፡ የሃሩን እህት ሆይ! አባትሽ መጥፎ ሰው አልነበረም፣ እናትሽም አመንዝራ አልነበረችም አሉዋት፡፡ ወደርሱም ጠቀሰች በአንቀልባ ያለን ኽፃን እንዴት እናናግራለን አሉ፡፡ (ሕፃኑም) አለ፡ እኔ የአላህ ባሪያ ነኝ መጽሐፍን ሰጥቶኛል ነቢይም አድርጎኛል፡፡ በየትም ስፍራ ብኾን ብሩክ አድርጎኛል በሕይወትም እስከ አለሁ ሶላትን በመስገድ ዘካንም በመስጠት አዞኛል፡፡ ለእናቴም ታዛዥ (አድርጎኛል) ትዕቢተኛም እምቢተኛም አላደረገኝም፡፡ ሰላምም በኔ ላይ ነው በተወለድሁ ቀን በምሞትበትም ቀን ሕያው ኾኜ በምቀሰቀስበትም ቀን፣ ይህ የመርያም ልጅ ዒሳ ነው ያ በርሱ የሚጠራጠሩበት እውነተኛ ቃል ነው፡፡›

እዚህ የተጠቀሱትን እያንዳቸውን ነገሮች ከአፖክሪፋል ምንጮች ከዚህ ቀጥሎ በምንጠቅሰው ምዕራፍ ግልጥ እንደሚሆነው ሁሉ ውስጥ ለማግኘት እንችላለን፡-

በትንሹ ጀምስ ፕሮቶኢቫንጀሊየም (ቅድመወንጌል)፣ የማርያምን አወላለድ በተመለከተ እንደሚከተለው እናነባለን፡- (39)

ዓይኗን ወደ ሰማይ ትኩር አድርጋ እየተመለከተች እያለ ሐና በሄይ ዛፍ ላይ የስፓሮው ወፍ ጎጆን አየች እናም ለእራሷ የሐዘን እንጉርጉሮን አደረገች እንደዚህም  ‹ወዮልኝ ለእኔ ወዬው ለእኔ እኔን ማን ነው የወለደኝ? ወዮው እኔ፤ እኔ ማንን ነው የምመስለው? እኔ የሰማይን ወፎች አልመስልም፣ የሰማይ ወፎችም እንኳን በፊትህ ፍሬያማዎች ናቸው፣ ኦ ጌታ ሆይ› አለች፡፡ እነሆም የጌታ መልአክ አጠገቧ ቆሞ ነበር ለእርሷም እንዲህ አላት ‹ሐና፣ ሐና ጌታ እግዚአብሔር የልመናሽን ድምፅ ሰምቷል አንቺም ትፀንሻለሽ ትወልጃለሽም የአንቺም ዘር በዓለም ሁሉ የሚነገርለት ይሆናል› ነገር ግን ሐና አለች ‹ጌታዬ ሕያው እግዚአብሔርን፤ ወንድ ወይንም ሴት ብወልድ ለጌታዬ እግዚአብሔር ስጦታ አድርጌ እስጠዋለሁኝ እርሱም በሕይወቱ ዘመን ሁሉ የአንተን አገልግሎት ያገለግላል›፡፡ ነገር ግን ወራቶቿ ተፈፅመው ነበር በዘጠነኛውም ወር ሐና ወለደች ለልጇም ጡቷን ሰጠች እና ስሟንም ማርያም አለቻት›፡፡    

ተረቱም እንዴት እንደነበረ በመናገር ይቀጥላል ልጅቷም ዕድሜዋ በደረሰ ጊዜ በሐና በቃል ኪዳኗ መሰረት እናቷን ለመተው ወደ ቤተመቅደስ ተወሰደቸ፡፡ ከዚያም ታሪኩ እንደሚከተለው ይቀጥላል፡- ‹ቄሱ ተቀበላት፤ ሳማትና ባረካት እናም እንደሚከተለው ተናገረ፡ ‹‹ጌታ እግዚአብሔር ያንቺን ስም በምድር ትውልድ ሁሉ መካከል ከፍ አድርጎታል፣ በመጨረሻዎቹም ቀናት ባንቺ ላይ ጌታ እግዚአብሔር ለእስራኤል ልጆች ማዳንን ይገልጣል›› ነገር ግን ማርያም ግን እንደ እርግብ በጌታ መቅደስ ውስጥ እያደገች ነበር፣ እርሷም ከመልአክ እጅ ምግብን ትቀበል ነበር፡፡ ነገር ግን አስራ ሁለት ዓመት ሲሞላት የካህናት ስብሰባ ተደረገና ካህኑ እንደሚከተለው ተናገረ፡ ‹እነሆ ማርያም በጌታ ቤተመቅደስ ውስጥ አስራ ሁለት ዓመት ቆየች፣ ስለዚህ አሁን እሷን ምን እናድርጋት? እነሆም የእግዚአብሔር መልአክ በአጠገቡ ቆመ እንዲህም አለ፡ ‹ዘካሪያ ዘካሪያ ሄድና የሕዝቡን መበለቶች ሰብስብ እያንዳንዳቸውም በትርን ያምጡ ጌታ እግዚአብሔር ምልክት ላሳየው ለእርሱ እርሷ ሚስት ትሆናለች ከዚያም ወሬው ለይሁዳ አገር ሁሉ ወጣ የጌታም መለከት አስተጋባ ከዚያም ሁሉም ሮጡ፡፡ ነገር ግን ዮሴፍ መጥረቢያውን ጥሎ እራሱ ብቻውን ወደ ምኩራቡ ሮጠ፡፡ እዚያም ሁሉም ተሰብስበው ወደ ቄሱ ሄዱ፡፡ ቄሱም የሁሉንም በትሮች ወስዶ ወደ ቤተመቅደስ ገባና ፀለየ፡፡ ፀሎቱንም ጨርሶ ወጣና ለእያንዳንዱ በትሮቻቸውን መለሰላቸው በእነርሱም ላይ ምንም ምልክት አልነበረም፡፡ ነገር ግን ዮሴፍ የመጨረሻውን በትር ተቀበለ፡፡ እነሆም እርግብ ከዮሴፍ በትር ውስጥ ወጥታ ወደ ዮሴፍ እራስ ላይ በረረች፡፡ ከዚያም ቄሱ ለእርሱ እንዲህ አለው ‹አንተ የጌታን ድንግል በዕጣ አግኝተሃል እርሷንም በራስህ ዘንድ ለመጠበቅ ተቀበላት› ዮሴፍም ፈርቶ እርሷን ለመጠበቅ ተቀበላት፡፡ ማርያም ግን የውሃ መቅጃ ማሰሮ ወስዳ ውሃ ልትሞላው ሄደች፡፡ እነሆም ድምፅ አላት፡ ‹ሰላም ማርያም ፀጋ ያገኘሽ ሆይ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው አንቺም ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ› እርሷም ወደ ግራና ቀኝ ድምፁ ከየት እንደመጣ ለማየት ዙሪያዋን ተመለከተች፡፡ ደንግጣም ወደ ቤቷ ተመለሰች የውሃውንም ገንቦ አስቀምጣ በመቀመጫዋ ላይ ተቀመጠች እነሆም የጌታ መልአክ በአጠገቧ ቆመ ለእርሷም እንዲህ አላት ‹ማርያም ሆይ አትፍሪ በእግዚአብሔር ፊት ሞገስን አግኝተሻልና ከእርሱም ቃል ትፀንሻለሽ ነገር ግን ማርያም ሰምታ በልቧ አስባ እንዲህ አለች፡ ‹እኔ እንማንኛውም ሴት እንደሚፀንሰው ነውን የምፀንሰው? አለች፡፡ መልአኩም ለእርሷ እንዲህ አላት ‹ማርያም እንደዚያ አይደለም፣ የልዑል ኃይል በአንቺ ላይ ይከልልሻልና ስለዚህም ደግሞ ቅዱሱ ነገር ይወለዳል እርሱም የልዑል ልጅ ይባላል አንቺም ስሙን ኢየሱስ ብለሽ ትጠሪዋለሽ አላት፡፡›

ማርያም በቤተመቅደስ አደገች የሚለው አፈታሪክ እዚህ እኛ ከጠቀስነው በተጨማሪ በብዙ የአፖክሪፋ መጽሐፍት ስራ ውስጥ ይገኛል፡፡ ለምሳሌም ያህል በኮፕቲክ ቤተክርስትያን ‹የድንግል ማርያም ታሪክ ውስጥ፡› እንደሚከተለው እናነባለን፡- እርሷ በቤተ መቅደስ ውስጥ እንደርግቦች ተመግባለች፣ ምግብም በእግዚአብሔር መላእክት በኩል ከሰማይ ወደ እርሷ ይመጣላት ነበር፡፡ በቤተመቅደስም ውስጥ እንድታገለግል ተደርጋ ነበር፣ የእግዚአብሔርም መልአክ እርሷን ያገለግላት ነበር፡፡ ነገር ግን ብዙውን ጊዜ በደስታ እንድትበላቸው ከሕይወት ዛፍ ላይ ፍሬዎችን ያመጡላት ነበር›፡፡ በሌላ ‹የዮሴፍ ሞት ታሪክ› በሚል ርዕስ በተዘጋጀው የኮፕቲክ ጽሑፍ ደግሞ የሚከተለው አንቀፅ ይታይበታል፡- ‹ማርያም በቤተመቅደስ ውስጥ ትኖር ነበር እዚያም በቅድስና ታመልክ ነበር እርሷም እስከ አስራ ሁለት ዓመቷ ድረስ አደገች፡፡ በወላጆቿም ቤት ውስጥ ለሦስት ዓመታት ያህል ቆየች፣ ከዚያም በጌታ ቤተመቅደስ ውስጥ ደግሞ ለዘጠኝ ዓመታት ያህል ቆየች፡፡ ከዚያም ቄሶቹ እርሷ ድንግል ሆና በንፅህና እንደኖረች ካዩ በኋላ እናም በጌታ ፍርሃት እርስ በእርሳቸው ተነጋገሩ ‹አንድ ጥሩ ሰው እንፈልግና እናሳጫት እስከ ጋብቻ ድግሱ ድረስ› አሉ፡፡ ከዚያም የይሁዳን ነገድ ሰበሰቡና በእስራኤል ልጆች ነገዶች ስም መሰረት ከእነርሱ ውስጥ አስራ ሁለት ሰዎችን መረጡ፡፡ ዕጣውም በጥሩው ሰው በዮሴፍ ላይ ወደቀ›፡፡

ወደ ፕሮቶእቫንጀሊየን ስንመለስ ደግሞ የተነገረን ነገር ማርያም የመፅነሷ እውነታ በታወቀበት ጊዜ ዮሴፍና እርሷ በቀሳውስቱ ፊት ለፍርድ እንዲቀርቡ ተደረገ፡፡ ታሪኩም እንደሚከተለው ይቀጥላል፡- ‹ቄሱም አለ፡ ‹ማርያም ሆይ ይህንን ለምን አደረገሽ ነፍስሽን አዋረድሽ?› አላት፡፡ አምላክሽን ጌታ እግዚአብሔርን ረስተሻል፣ በቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ አድገሽ ከመላእክትም እጅ ምግብን ተመግበሽ፣ እንዲሁም ዝማሬን ሰምተሸ ይህን ለምን አደረግሽ?› ነገር ግን እርሷ በጣም አምርራ አለቀሰች እንዲህም አለች፡ ‹ጌታ በሕያው እግዚአብሔር፤ በእርሱ ፊት እኔ ንፁህ ነኝ እናም ወንድ አላወቅሁም› አለች፡፡

ከዚህ በኋላ የተነገረን ነገር ዮሴፍና ማርያም ከናዝሬት ወደ ቤተልሔም መሄዳቸው ነው፡፡ በእንግዶች ማረፊያ ቤት ማደሪያ ቦታንም በማጣት በመጨረሻ በዋሻ ውስጥ ለማደር ሄዱ፤ እዚያም ጌታ ኢየሱስ ተወለደ፡፡ የመጀመሪያው ቃል ከአሁኑ ዓላማችን ጋር የማይገኛኘውን ነገር በሙሉ በመዝለል እንደሚከተለው ሊተረጎም ይችላል፡-

‹እርሱም ዋሻን አገኘና ወደዚያ ውስጥ አስገባት፤ ነገር ግን እኔ ዮሴፍ ወደ ሰማይ ተመለክትሁና የሰማይን ጣራ የማይነቃነቅ ሆኖ አየሁት የአየርም ወፎች ሲንቀጠቀጡ አየሁ፡፡ ወደ ምድርም ተመለከትሁ ሳህን ተዘርግቶ ሰራተኞችም ተቀምጠው አየሁ፣ የእነሱም እጅ በሳህኑ ላይ ነበር እነርሱም ምግቡን ወደ ከንፈራቸው ያነሱ የነበሩት አያነሱትም ነበር፣ ወደ አፋቸውም ውስጥ ያገቡት የነበሩት አያገቡትም ነበር፣ ነገር ግን የሁሉም ፊቶች ወደ ላይ ይመለከት ነበር፡፡ እኔም በግ አየሁኝ፣ እየተነዳና በጉም ሳይንቀሳቀስ ቆሞ ነበር ነገር ግን እረኛው እነርሱን ሊመታበት ማገጃውን አነሳ  እጁም እንደተዘረጋ ቀረ፡፡ እኔም ወደ ውሃው ማዕበል አየሁና ልጆችን ተመለከትሁ፣ አፋቸውም በውሃው ላይ ነበር ነገር ግን አይጠጡም ነበር፣ ሁሉም ነገር አስደናቂ ነበር›፡፡

በቁራን 19.23-26 ላይ ያለው የማርያምና የተምር ዛፉ ክስተት ከዚህ በላይ እንደገለፀው የተወሰደው ‹የማርያም መውለድና የአዳኙ የሕፃንነት ታሪክ› ከሚለው የአፖክሪፋ ስራ ላይ ነው፡፡ ቢሆንም እንደምናየው ሁሉ ሁለቱንም ትረካዎች ወደ አንድ ጥንታዊ ምንጭ ልናዛምዳቸው እንችላለን፡፡ አሁን በጠቀስነው መጽሐፍ ውስጥ ክስተቱ የተዛመደው ወደ ግብፅ በመሄድ ላይ ነው፡፡ ታሪኩም የዘገበው ቅዱሱ ቤተሰብ ጉዞውን እንዴት እንደጀመሩና ለሁለት ቀናትም በፀጥታ እንደተጓዙ ነው፡፡ ከዚያም ታሪኩ እንደሚከተለው ይቀጥላል፡-

‹ነገር ግን በሦስተኛው ቀን ጉዞ ከጀመሩ በኋላ ማርያም በምድረበዳው ፀሐይ ከባድነት የተነሳ በጣም ደከመች፡፡ እርሷም ዛፍን ባየች ጊዜ ለዮሴፍ እንዲህ አለችው፣ ‹ለትንሽ ጊዜ ያህል በዚህች ዛፍ ጥላ ስር እንረፍ አለችው› ዮሴፍም ፈጠን ብሎ ወደ ተምር ዛፏ አመጣት ከተቀመጠችበትም እንሰሳ አወረዳት፡፡ ማርያምም በተቀመጠችበት ጊዜ ወደ ተምሩ ዛፍ አናት ወደ ላይ ተመለከተች በፍሬም የተሞላ መሆኑን ካየች በኋላ ለዮሴፍ እንዲህ አለችው ‹የሚቻል ከሆነ ከዚህ የተምር ዛፍ ፍሬ ለመብላት እፈልጋለሁ› አለች፡፡ ዮሴፍም ለእርሷ እንዲህ አላት ‹ዛፉ እጅግ ትልቅ ሆኖ እያለ ይህንን በመናገርሽ እደነቃለሁ፡፡ ነገር ግን እኔ በጣም የጓጓሁት ስለ ውሃ ነው የአቁማዳው ውሃችን አሁን አልቋልና እርሱንም ለመሙላትና ጥማችንንም ለመቁረጥ የምንችልበት ምንም ቦታ የለንም አላት›፡፡ ከዚያም ኢየሱስ ለእርሱ (ለዛፉ) እንዲህ አለው፡ ‹የዘንባባ ዛፍ ሆይ ተነስና ደስ ይበልህ እንዲሁም በአባቴ ገነት ውስጥ ካሉት ዛፎች እንደ አንዱ ሁን፡፡ ነገር ግን በስሮችህ በመሬቱ ውስጥ የተደበቀውን ምንጭ ክፈተው እናም ውሃ ከዚያ እንዲመነጭ አድርግ እኛም ጥማታችንን እናረካዋለን› የዘንባባውም ዛፍ ተነስቶ ቀጥ ብሎ ቆመ፣ ከዚያም ንፁህ፣ ቀዝቃዛ እና በጣም ጣፋጭ ውሃ ከስሩ መካከል መንጭቶ ፈለቀ፡፡ እነሱም እነዚህን የውሃ ምንጮች ሲመለከቱ እጅግ በጣም ተደሰቱ ከተከታዮቻቸው እና ከአራት እግር እንስሳቶቻቸው ጋር ጠጥተው በመርካት እግዚአብሔርን አመሰገኑ›፡፡

የዘንባባውን ዛፍ እና ከስሩ የፈለቀውን ውሃ ምንጭ ወደ ግብፅ ከተደረገው ስደት ጋር ከማያያዝ ይልቅ፤ እንደምናየው ቁርአን በጣም ያቀራረባቸው ከክርስቶስ ልደት ጋር ነው፡፡ እንዲሁም ቁርአን ክርስቶስን የወከለው በዛፉ ስር እንደተወለደ አድርጎ ነው፡፡ በዚያን ጊዜ (በአንድ ገለጣ መሠረት)  ማርያም ፍሬውን እንድትበላ ዛፉ ዘንበል እንዲል በማድረግና ምንጭም መፍሱን ለእሷ በመንገር ነው፡፡ ከዚህ አንፃር በቁርአን ላይ ያለው የዚህ ቃል አቀራረብ ገብርኤል ተናገረ ከሚለው በተሻለ መልኩ ከአፖክሪፋ ወንጌል አካሄድ ጋር ተመሳሳይነት አለው፡፡

ነገር ግን እኛ አሁን መጠየቅ ያለብን ቁርአን ክርስቶስ በዛፍ ስር ተወልዷል የሚለውን ሐሳብ ከየት ምንጭ አመጣው የሚለውን ጥያቄ ነው፣ እንዲሁም እናትና ልጇ ከፍሬው እንዲበሉ የዘንባባው ዛፍ ጎንበስ አለላቸው የሚለው ተረትስ ምንጩ ምንድነው? የሚለውን ነው፡፡ ከእነዚህ ከሁለቱም አረፍተ ነገሮች ውስጥ አንዳቸውም ቢሆኑ ቅንጣት ታክል ማስረጃ እንደሌላቸው መናገር እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ የእነዚህ የሁለቱም ክስተቶች ምንጭ የሚገኘው በቡዲስት ፓሊ የካኖን መጽሐፍ ውስጥ ነው፣ እንደተነገረን ከሆነ በሞሐ ቫምሶ ውስጥ ይገኛል፡፡ በጽሑፍም እንዲቀመጥ የተደረገው በሲሎኑ ንጉስ ቫታጋማኒ ዘመን በ80 ዓ.ዓ ሲሆን ይህ የቅርብ ጊዜው ግምት ነው፡፡ ሆኖም ግን እነዚህ ፓሊ መጽሐፍት ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት ተጠናቅረው ሊሆን ይችላል፡፡ በእነርሱ ውስጥ የነበሩት አፈ ታሪኮች በኋለኞቹም ሆነ በቀደሙት ዓመታት በብዙ ቦታ ላይ በጣም ተስፋፍተው ነበር፡፡ በሕንድና በሲሎን (የአሁኗ ስሪላንካ) ብቻ ሳይሆን በመካከለኛው ኤሺያና በቻይና በትቤት እና በሌሎችም አገሮች ሁሉ ተሰራጭተዋል፡፡ የቡዲስት ሚሽነሪዎች በየሺት 13 ቁጥር 16 ላይ ከክርስቶስ ልደት በፊት በሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በፐርሺያ እንደነበሩ ተጠቅሰዋል፡፡ በምዕራብ፣ በምስራቅ በመካከለኛው በደቡብ ኤሺያ ውስጥ  ቡድሂዝም ያሳደረው የሐሳብ ተፅዕኖ ይህ ነው የሚባል አይደለም፡፡ ማንኪያኒዝም፣ ኖስቲሲዝም እና ሌሎች ኑፋቄዎች እንዲሁም የገዳም ሕይወት እንቅስቃሴዎች ሁሉ በአብዛኛው የመጡት ከዚህ የተነሳ ነው፡፡ በአፖክሪፋል ወንጌሎች ውስጥ የሚገኙት ብዙ አንቀፆች የዚያ የቡዲዝም ምንጭነት በጸሐፊዎቹ አዕምሮ ውስጥ ቦታ ያገኘ መሆኑን የሐሰት ስራዎቹ ሁሉ የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ይህም እነዚህ ሰዎች የጻፏቸው ነገሮች ትክክለኛ ምንጭ ምን መሆኑን በትክክል ባያውቁም እንኳን ነው፡፡  በተመሳሳይ መንገድ ለመሐመድም ለመሳሳት በጣም ቀላል ነበር፣ ስለዚህም እኛ ለተመሳሳይ አንቀፆች ማለትም ስለዛፉ ማጎንበስ አፈ-ታሪክ ጥንታዊውን የተረት ምንጭ ለማሳየት የፓሊን መጽሐፍት ልንጠቁም እንችላለን፡፡

ከእነዚህም አንዱ የሚገኘው በኒዳናካታ ጃታካም (ምዕራፍ 1 ገፅ 50-53) ውስጥ ነው፡፡ በዚያም እኛ የተነገረን ነገር ‹ማያ› የጎታሞ ቡድሃ እናት የነበረችው ልጅ ስታረግዝና መውለጃዋ እንደደረሰ ስታውቅ የባሏን የሱዶዳኖን ፈቃድ ትይዝና በዚያን አገር ባህል መሰረት ለመውለድ ወደ ቤተሰቦቿ ትመለሳለች፡፡ ወደ ቤትም በምታደርገው ጉዞ እርሷና የሴት ሰራተኛዋ ወደ አንድ ውብ ጫካ ውስጥ ይገባሉ በዚያም ልዕልት ማያ በአንዳንድ ዛፎች ላይ የነበሩትን አስደናቂ ውብ አበቦች ታደንቃለች፡፡ እኛ በምንጠቅሰው በአንቀፁ ቃላት ውስጥ ታሪኩ እንደሚከተለው ተዘግቧል፡- ‹እርሷም ጥንቆላ ጉድጓድ ሳል ዛፍ ስር ሄዳ የሳል ዛፍን ቅርንጫፎች ለመጨበጥ በጣም ፍላጎት አደረባት፡፡ የሳል ዛፍም ቅርንጫፎች አጎንብሰው እንደ ልምጭ የለስላሳ ጫፍ ግንድ ወደ ልዕልቲቱ እጅ ለመጨበጥ ቀረቡ፡፡ እርሷም የሳል ዛፍን ቅርንጫፍ እንደጨበጠችና ቅርንጫፉን ይዛ እንደቆመች የልጅ ምጥ መጣባት፡፡›

በቁርአን ውስጥ ያለው የክርስቶስ ልደት እና የዚህ ከዚህ በላይ ያለው አንቀፅ ልዩነት በጣም ጥቂት ነው፡፡ መሐመድ የጠቀሰው በአረብ ዓለም ውስጥ ከዛፎች ሁሉ በጣም የታወቀውን የተምርን ዛፍ፡፡ ይህንንም ያደረገው የሕንድ የሳል ዛፍ በአረቢያ ስለማያድግ ብቻ በቡድሃ መጽሐፍ ላይ በተጠቀሰው በአበቦች ዛፎች ምትክ ነው፡፡ በሌሎች ተመሳሳይ ተረቶች ላይ እንደሆነው ሁሉ ተረቱ ሲተላለፍ ያለምንም ጥርጥር በዚህ መንገድ ተቀይሯል፡፡ የሕንዱ አፈታሪክ የሚያሳየው ከበላዩዋ ባለው ቅርንጫፍ ላይ ያደጉትን የአበቦችን ቅርንጫፍ ለመያዝ በቡድሃ እናት  የተደረገው ጥረት ሳይጠበቅ የልጅ መውለድን አስከትሏል፡፡ ቁራን ግን በተምር ዛፎች ስር የተደረገውን መውለድ ምንም ግልጥ ምክንያት ሳያቀርብ እንዲሁ ትቶታል፡፡ ነገር ግን ታሪኮቹ በእርግጥ አንድና ተመሳሳይ ናቸው፡፡ እዚህ እኛ የምናየው ነገር በቁርአኑ ውስጥ እንዳለው ሁሉ ማያ አበቦችን እንድትቀጥፍ ለማስቻል ዛፏ ቅርንጫፎቿን ወደ ታች እንዳጎነበሰች ነው፡፡ ቁርአን እንደያዘው ደግሞ የበሰሉ የተምር ፍሬዎችን በማርያም ላይ እንዲወርዱ አድርጓል፡፡

ሌላው ታሪክ የዚህ የኋለኛው ክስተት በአፖክሪፋል ወንጌሎች ላይ የሚገኘውና ጌታችን ህፃን በበረበት ጊዜ ወደ ግብፅ ከተደረገው ጉዞ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ይህም በካሪያ ፒታካም ምዕራፍ (1 ግጥም 9) ውስጥ ከምናነበው ጋር ትይዩያዊ ነው፡፡ በዚያም ውስጥ እኛ የተነገረን ነገር በቀደመው ውልደት ቡድሃ ልዑል እንደበረና ቬሳንታሮ ተብሎ እንደተጠራ፤ የራሱን ሕዝብ በማሳዘን ከመንግስቱ እንደ ጠፋ፣ ይህም ከሚስቱና ከሁለት ትንንሽ ልጆቹ ጋር እንደነበር ነው፡፡ እነርሱም ወደሩቅ ተራሮች እየተንከራተቱ ጥገኝነት ለማግኘት በሚፈልጉበት ቦታ ልጆቹ በጣም ተራቡ፡፡ ከዚያም የቡዲስቶች ታሪክ እንደሚከተለው ይነግረናል፡- ‹ልጆች በተራራው ሌላ ጎን ላይ ፍሬ የሚሰጡ ዛፎችን ሲያዩ ለፍሬዎቹ ያለቅሳሉ፡፡ ልጆቹ እንደሚያለቅሱ አይተው፣ ትልልቆቹ ዛፎች እራሳቸውን ዝቅ በማድረግ አጎንብሰው ልጆቹን ቀረቧቸው›፡፡

ሁለቱም ቁርአንና የአፖክሪፋዊው ‹ማርያም መውለድ ታሪክ› ጽሑፍ ጸሐፊዎች ይህንን የተለየ ክስተት ሳያስተውሉት የተበደሩት ከቡዲስት ምንጭ ነው፡፡ ይህ እውነታ በእርግጥ የታሪኩን ሐሰትነት ያሳያል፡፡ ያንን ለማሳየት ማስረጃ በሚፈለግበት ቦታ ሁሉ በመሐመድም ጊዜ እንኳን የቡዲስት አፈታሪክ በምዕራባዊ ኤሺያ ውስጥ በጣም ተስፋፍቶና እንደ ክርስትያን ታሪክ ተቀባይነትን አግኝቶ ነበር፣ እርሱም ‹ባርላም እና ዮሳፋጥ› በሚባለው ተረት መኖር ሊረጋገጥ ይችላል፡፡ ይህ አፈታሪክ በግሪክ በክርስትያኖች ዘመን በስድስተኛው መቶ ዘመን ተጽፎ ነበር፣ ሆኖም ግን እርሱ በአጠቃላይ ተጽፏል ተብሎ የሚነገርለት በጆሃንስ ዳማሲነስ ነበር፡፡ ጸሐፊውም በ753-74 ድረስ በነበረው በካሊፋ አልማንሱር ዘመን ቤተመንግስት ውስጥ ታዋቂ ነበር፡፡  በመጽሐፉ ላይ የተጠቀሰው ክርስትያኑ ልዑል ጆሳፋት፣ ያለምንም ጥርጥር ቡድሃ እራሱ ነው፣ ያም ‹የቦዲስታቫ› የተባለው የእርሱ ስም የተበላሸ አጠራር ነው፣ ይህም ከቡድሃ የማዕረግ ስሞች አንዱ ነው፡፡  የተረቱም ዋና ምንጭ የሳንስክሪት የቡድሃ አፈታሪክ ሲሆን የሚታወቀውም ላሊታ ቪስታራ በመባል ነው፡፡ ነገር ግን ጆሳፋት በግሪክም በሮማንም ቤተክርስትያናት ውስጥ ቅዱስ ተብሎ ይጠራል፡፡ በግሪክ ቤተክርስትያን ውስጥ ነሐሴ 26 ቀን በሮማውያኑ ደግሞ ሕዳር 27 ለእርሱ የተለየ ቅዱስ ቀን ተደርጎ ይከበራል፡፡

የአዘጋጁ ማሳሰቢያ

ማርያም የሃሩን እህት ተብላ በቁርአን 19.28 ላይ መጠቀሷ ለሙስሊም ተንታኞች ሁሉ አስቸጋሪ የራስ ምታት ነው፡፡ የሃሩን እህት፤ የሃሩን ወንድም የሙሴ እህት አይደለችም በማለት ለማስተባበል ብዙ ጥረት ተደርጓል፡፡ የዚህም አንድ ማስረጃ በአማርኛው ቁርአን ሁለተኛው እትም ሚያዝያ 1997 ገፅ 210 በምዕራፍ 19 ቁጥር 28 ላይ በተሰጠው የግርጌ ማስታዎሻ ላይ ግልጥ ነው፡፡ የአማርኛው ተርጓሚዎች ይህን ከፍተኛ ችግር ለማስተባበል ሃሩን የተባለው ሰው የማርያም የአባቷ ልጅ እንጂ የሙሳ ወንድም ሃሩን አይደለም ይላል፡፡ መልካም ሙከራ ነው ሆኖም ግን ሌሎች የቁርአን ክፍሎች ማለትም ቁርአን 3.35ና ቁርአን 66.12 ይህንን ሐሳባቸውን ውድቅ ያደርጉታል፡፡

ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን የወለደችው የቅድስት ማርያም ታሪክ በቁርአን ምዕራፍ 19፣ 3፣ 66 ላይ ይገኛል፡፡ በቁርአን ውስጥ ያለው ታሪክ ከመጽሐፍ ቅዱስ የተለየ ነው፣ ለምን ልዩ ሆነ፤ ለመሆኑ የነዚህ የቁርአኑ ታሪኮች ምንጫቸው ምንድነው? ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ የተለዩ በመሆናቸው ምንጫቸው ሌላ መሆኑን በማስረጃ አይተናል፡፡ ምንጫቸውም በአረቢያና በአካባቢው በደንብ ይታወቁና ይዘዋወሩ የነበሩት የስህተት ወንጌሎችና የሕንድ ቡድሃ እምነት ምንጮች ናቸው፡፡ እነዚህም ምንጮች መገኘታቸው ቁርአንን ትልቅ ጥያቄ ውስጥ ጥሎታል፡፡ ስለዚህም የማንም ሰው የመደምደሚያ ሐሳብ የሚሆነው፤ ቁርአን የተረት መጽሐፍ እንጂ ከእግዚአብሔር የመጣ የእርሱ ቃል ሊሆን እንደማይችል ነው፡፡

እንደዚህ ዓይነት እውነቶች ግልጥ በሆነ መንገድ ሲገለጡ አንድ አንባቢ ቆም ብሎ ማሰብና መንገዱንም፣ አመለካከቱንም መመርመር አለበት፡፡ የዘላለም ሕይወቱም መጨረሻ ሊያሳስበው ይገባል ምክንያቱም ከምንም ነገር የበለጠ ነውና፡፡ የዘላለምን ሕይወት በተረት ተረት ላይ መመስረትና በተረት መታመን ይቻላልን ደግሞስ ያዋጣልን? የማርያም ታሪክ ምንጩ እየታወቀ በእግዚአብሔር መገለጥ መጣ ከተባለ ሌሎቹንስ ከእግዚአብሔር ነው የመጡት በማለት እንዴት አምናቸዋለሁ?

የዚህ ገፅ አዘጋጆች ዋና ዓላማ ሙስሊሞች እውነትን እንዲያዩና ክቡር የሆነው ዘላለማዊ ሕይወታቸው ለዘላለም ከእግዚአብሔር ጋር የሚኖርበትን መንገድ ማሳየት ነው፡፡ ይህም ሊገኝ የሚችለው መድሃኒትና ጌታ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ብቻ ነው፡፡ ጌታ ኢየሱስ ፍፁም አምላክ ሲሆን የሰውን ስጋ ለብሶ ወደ ምድር የመጣው ኃጢአተኞች ከቅዱስና ፍፁም እግዚአብሔር ጋር የሚታረቁበትን መንገድ ለመክፈት ነው፡፡ ይህንንም መንገድ ለኃጢአተኞች በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ዋጋን በመክፈል ከፍቶታል፡፡ በእርሱም የሚያምኑትን የዘላለም ሕይወት ወራሾች ለማድረግ በወንጌሉ መልእክት ይጣራል፡፡ እኛ እራሳችን ያንን ትልቅ ክብር እና ምህረት ስላገኘን አዲስንም ሕይወት ከእርሱ ስለተቀበልን እንደ እኛ አዲስ ሕይወትን እንድታገኙ ወደ ጌታ እንድትመጡ እንጋብዛችኋለን፡፡ እርሱ ጌታችን ኢየሱስ ይወዳችኋል ወደ እርሱ ብትመጡ ይቅር ሊላችሁና የዘላለም ሕይወትን ዋስትና ሊሰጣችሁ ቃል ገብቷል ስለዚህም ወደእርሱ ኑ ኃጢአታችሁን ተናዘዙ በትህትናም ይቅር በለኝ ብላችሁ ከልባችሁ ጠይቁት ምህረቱን ይሰጣችኋል ይቀበላችኋልም እግዚአብሔር ይርዳችሁ አሜን፡፡

 

የትርጉም ምንጭ: THE ORIGINAL SOURCES OF THE QUR'AN 

ሙሉ መጽሐፉ በአማርኛ:  የቁርአን የመጀመሪያ ምንጮች

ለእስልምና መልስ አማርኛ  ዋናው ገጽ