የቁርአን የመጀመሪያ ምንጮች

ምዕራፍ አራት ክፍል አንድ

የክርስትናና የክርስትያናዊ አፖክሪፋዊ መጽሐፍት ተፅዕኖዎች

REV. W. ST. CLAIR TISDALL, M.A., D.D

ትርጉምና ቅንብር በአዘጋጁ

 

መሐመድ በተነሳበት ጊዜ ክርስትና በአረቦች አካባቢ ይህ ነው የሚባል ተጨባጭ ተቀባይነትን አላገኘም ነበር፡፡ ‹ከአምስት መቶ ዓመታት የክርስትና ስልጣኔ በኋላ፣ እዚህና እዚያ የተበታተኑትንና ወደክርስትና የተለወጡትን ማመልከት እንችላለን፡ የናጅራን ባኑ ሓሪዝ፣ የያማማ ሐኒፋ፣ አንዳንዶቹ በታይማ የነበሩት ባኑ ታይ እንጂ ሌላ ምንም አልነበረም› መሐመድ በልጅነቱ የናጅራን ፓስተር የቁስን ስብከት እንደሰማ፣ እንዲሁም ብዙ መነኩሴዎችንና ክርስትያን ነን የሚሉ ሰዎችን  እንደ ነጋዴ ነቢይ ነኝ ከማለቱ በፊት ሶርያ በሄድ ጊዜ እንደተገናኘ ተነግሮናል፡፡ ነገር ግን ስለ ክርስትና ያየውና የሰማው ነገር በሕይወቱ ላይ ዘላቂ ለውጥን አላመጣም ነበር፡፡ በዚህም ልንደነቅ አይገባንም፡፡ ‹የመሐመድና የካሊፋቶቹ ሰይፍ የሚቀድላቸውን መንገድ በሁሉም አቅጣጫ ማግኘታቸው ነበር›፡፡ ይስሐቅ ቴይለር የተናገረው ነገር ይህንን ነው፡፡ ቆየት ባለውም ጊዜ በቃላት ሲናገር የመሐመድን የመጀመሪያ ልምምድ በተመለከተ እንዲህ ነበር ያለው፣ ‹አሰቃቂ ባዕድ አምልኮ ነበር፣ ጉልህ የሆነ አሳፋሪ የጣዖት አምልኮ ነበር፣ የቤተክርስትያን አስተምህሮ በጣም ድንቁርና የሞላበት፣ የቤተክርስትያን ልምምድ በጣም የተዋረደ እና ህፃናዊ ነበር፣ ስለዚህም ጠንካራ አዕምሮ የነበራቸው አረቦቹ፤ የእግዚአብሔር መልክተኛ እነዚህን የዓለም ስህተቶችን ሲነቅፍና የተሳሳተውን ክርስትና ዓለም ከእግዚአብሔር ተልኮ ለመቅጣት ሲነቅፍ ሲያገኙት እራሳቸው አዲስ መገለጥን እንዳገኙ ተሰማቸው›፡፡

የፐርሺያውን አትናቴዎስን ሰማዕትነት ሞት ታሪክ የጻፈው የግሪኩ መነኩሴ በፓለስታይን ሕዝብ ላይ በፐርሺያውያን እጅ ተጥሎ የነበረውን ጥቂት የመከራ ጊዜ በመሐመድ ጊዜ ሲናገር፣ በዚያ ስለነበሩት ክርስትያኖች ክፉነት አስፈሪ ስዕልን አስቀምጦ ነበር፣ ከዚያም ለዞሮአስተርያውያን አሳዳጆች እግዚአብሔር አሳልፎ እንደሰጣቸው ለመናገር ምንም አላመነታም፡፡ በራዕይ መጽሐፍ 9.20፣21 ላይ የሚገኘው የጣዖት አምልኮና ሌሎች ኃጢአቶች በዚህ መነኩሴ እንደተጠቀሱት ዓይነቶች ናቸው፤ እነዚህም መሐመዳውያን የምስራቅን ቤተክርስትያናት እንዲጨቁኑ ኃይል እንዲያገኙ አድርገዋቸዋል፡፡ በዚያው ጊዜ የነበረው ሞሼይም እንዳለው ‹እውነተኛ ሃይማኖት በዚያን ጊዜ በባዕድ አምልኮ የስሜት አልባ ብዛት ውስጥ ተቀብራ ነበር፣ እራሷንም ቀና ለማድረግ አልቻለችም ነበር፡፡ የቀደሙት ክርስትያኖች  እግዚአብሔርንና ልጁን ብቻ ነበር ያመለኩት፡፡ በነዚህ መቶ ዘመን ግን ክርስትያን ተብለው ተጠርተው የነበሩት የእንጨት መስቀልን፣ የቅዱሳን ሰዎችን ምስልና ምንጫቸው የማይታወቁ አፅሞችን ሁሉ ያመልኩ ነበር፡፡ የጥንት ክርስትያኖች መንግስተ ሰማይንና ሲዖልን በሰዎች ፊት ያቀርቡ ነበር፣ እነዚህም የኋለኞቹ ይናገሩ የነበረው ግን የነፍስን ፍፁም አለመሆንና የሚያጠራ የሆነ ዓይነት እሳት ስለመዘጋጀቱ ብቻ ነበር፡፡ የመጀመሪያዎቹ ያስተማሩት ክርስቶስ በሞቱና በደሙ ለሰዎች ኃጢአት ማስተሰርያን አድርጓል በማለት ሲሆን፣ የኋለኞቹ ግን ያስተምሩ የነበረው ካህናቱን በስጦታዎቻቸውና በምድራዊ ነገር ባላበለፀጉት ላይ የመንግስተ ሰማይ በር እንደሚዘጋባቸው ነው፡፡ የመጀመሪያዎቹ ቅዱስና ቀላል ኑሮን በመኖር በእምነታቸው ነገር የምር፣ እንዲሁም ንፁህና እግዚአብሔራዊ ነበሩ፣ የኋለኞቹ ግን የሃይማኖትን ነገር በውጫዊ ስርዓቶች ላይና በአካላዊ ልምምድ ላይ አድርገውት ነበር፡፡ ቁርአን የሚያቀርብልን የክርስትና ስዕል መሐመድ ስለ ክርስትና የወሰደውን የጥቂት ልምምዱን ፅንሰ ሐሳብ ነው፡፡ ስለ እምነቱ የነበረው የእርሱ እውቀት በዚያን ጊዜ ‹ኦርቶዶክስ› ቡድን በሚባለው ትምህርት ቢያንስ በጣም ተፅዕኖ ተደርጎበት ነበር፡፡ እነርሱም ያቀረቡት ማርያምን ‹የእግዚአብሔር እናት› በማለት የነበረ ሲሆን፤  ቃሉንም አላግባብ በመጠቀም በቀላሉ ትክክለኛውን ግንዛቤ በመሳት፣ በታላቁ እግዚአብሔር ምትክ የአይሁድን ሴት ለማምለክ መንገድን የከፈቱ ነበሩ፡፡ የዚህም ስህተት ውጤት በግልጥ የተጠቆመው በኢብን ኢሻክ ነው፤ የናጅራን ክርስትያን መልእክተኞች፣ ‹ለገዢው እምነት ለሆኑት› ለመሐመድ በመዲና በ632 ዓ.ም የተናገሩትን ነው፡፡ እርሱም የነገረን መልእክተኞቹ እንደ ሁሉም ክርስትያኖች፡ ‹ኢየሱስ እግዚአብሔር ነው፣ የእግዚአብሔር ልጅ ነው፣ ከሦስቱ ማለትም ከእግዚአብሔር ከክርስቶስ እና ከማርያም አንዱ ነው› ብለዋል በማለት ነው፡፡

በእርግጥ ይሄ በዚያ አገልግሎት ላይ ለዋለው ቋንቋ እውነተኛ መረጃ አይደለም፣ ይሁን እንጂ መሐመድ በእነዚህ ክርስትያኖች ዘንድ አለ የሚለውን ዶክትሪንና የተረዳውን ነገር በትክክል ያቀርባል፡፡ ይህም በጣም ግልጥ የሚሆነው በሚከተሉት የቁርአን ጥቅሶች ላይ ነው ‹እላንተ የመጽሐፉ ባለቤቶች ሆይ! በሃይማኖችሁ ከውነት ሌላ የኾነን (ማለፍ) ወሰንን አትለፉ በፊትም በእርግጥ የተሳሳቱትንና ብዙዎችን ያሳሳቱትን ከቀጥተኛው መንገድም (አሁን) የተሳሳቱን ሕዝቦች ከንቱ ዝንባሌዎች አትከተሉ በላቸው› ቁርአን 5.77፡፡ በተጨማሪም ‹አላህም የመርየም ልጅ ዒሳ ሆይ አንተ ለሰዎቹ እኔንና እናቴን ከአላህ ሌላ ሁለት አምላኮች አድርጋችሁ ያዙ ብለሃልን? በሚለው ጊዜ (አስታውስ) ጥራት ይገባህ ለኔ ተገቢዬ ያልኾነን ነገር ማለት ለኔ አይገባኝም፤ ብዬው እንደ ኾነም በእርግጥ ዐውቀኸዋል በነፍሴ ውስጥ ያለውን ሁሉ ታውቃለህ ግን አንተ ዘንድ ያለውን አላውቅም አንተ ሩቆችን ሁሉ በጣም ዐዋቂ አንተ ብቻ ነህና ይላል› ቁርአን 5.116፡፡

መሐመድ እንዲያስብበት የቀረበለትን ክርስትና አልፈልግም ብሎታል ብለን ለማሰብ በጣም እንቸገራለን፡፡ ‹እርሱ የክርስትናን ንፁህ ትምህርትና ስርዓት ቢመሰክር ኖሮ፣ እንዲሁም አዲስ ሕይወት የሚሰጠውንና የሚያድሰውን ተፅዕኖ ብዙ ቢያይ ኖሮ፣ በቅንነት እውነትን ይፈልግ በነበረበት በመጀመሪያዎቹ አካባቢዎች የክርስቶስን እምነት ተቀብሎ በእምነት ሊፀና ይችል ነበር፡፡ በእርግጥ በሚያሳዝን ሁኔታ የሚታየው በቤተክህነት ሰዎችና በሶሪያ መነኩሴዎች አማካኝነት የተገለጠው ክርስትና ዝቅተኛ ዓይነት ነበረ፣ እንዲሁም የተቀየረና የተዛባ ነበረ፡፡ በጣም ቀላል የሆነውን ክቡር ወንጌል - እግዚአብሔር እራሱን ከዓለም ጋር በልጁ በኩል የማስታረቁ መገለጥን ከማቅረብ ይልቅ፤ የስላሴን ቅዱስ ዶግማ አስተምህሮ በተጓዦች ላይ ይጫን ነበር፡፡ ይህም አሰናካይ ከነበረው የአውጣኬያውያንና ያቆባውያን ደጋፊነት ጋርና የማርያም አምልኮ ጥቅልል በነበረ መልኩ በመሐመድ አዕምሮ ውስጥ እርሷ እንደ ሴት አምላክ ተወስዳለች የሚልን ተፅዕኖን ፈጥሮ ነበር፡፡ ይህም አመለካከት እርሷን እንደ ሦስተኛ የስላሴ አካልና የመለኮት ተጓዳኝ ናት እስከሚል ድረስ ሄዷል፡፡ መሐመድ ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው የሚለውን እውነተኛ አስተምህሮ የተቃወመው በዚህ በጣም በተጋነነና ስድበ እግዚአብሔር በመሰለው ትምህርት ምክንያት መሆን አለበት፡፡ ስለዚሀም በቁርአን ውስጥ ‹ኢየሱስ የማርያም ልጅ› በማለት ብቻ ጌታ ኢየሱስን ለመጥራት ተገዷል፡፡

ስለዚህም አሁንም መርሳት የሌለብን ነገር መሐመድ ንፁህ ከሆነው የወንጌል ክርስትና ጋር ለመገናኘት እንዳልመጣ ነው፡፡ እናም በአጠቃላይ መናገር የሚቻለው መሐመድ መረጃዎቹን ያገኘው በአብዛኛው ከሐሰት ክርስትና ጋር ነበር፡፡ እነዚህንም በመቃወም  በወንጌሎች ውስጥ ያለውን እውነት መሐመድ በእርግጥ እንዳይፈልግና ፀረ ክርስትያን የሆነ አዲስ ሃይማኖትን እንዲመሰረት አስገደደው፤ ይህ እውነታ ነው የእስልምናን መነሳት ገሃድ እንዲሆን ያደረገው፡፡

በመሐመድም ጊዜ አዲስ ኪዳን በአረብኛ መኖሩን የሚያሳይ ምንም አጥጋቢ የሆነ ማስረጃ የሌለን ይመስላል፡፡ በጤናማ በሚመስሉ ቤተክርስትያንም እንኳን ወንጌል በቅዱሳን አፈታሪክ አማካኝነት ተዘንግቶ ነበር፡፡ አብዛኛዎችም የሚፈልጉት ድንቅ ነገርን መስማት ብቻ ነበር፡፡ አረቢያም ለተለያዩ ብዙ የስህተት ቡድኖች መጠለያ ነበረች ከቁርንም ውስጥ በግልጥ እንደምናየው በጽሑፍ ይሁን ወይንም አይሁን፣ በጣም ብዙዎቹ የአፈታሪክ ምትሃተዊ ታሪኮች፤ በስህተት ወንጌሎች ውስጥና በሌሎች ስራዎች ውስጥ፤ በአንዳንድ ዋና ሐሳቦች ላይ አተኩረው ከነበሩ ብዙ የኑፋቄ አመለካከቶች ጋር ወደ መሐመድ ደርሰው ነበር፡፡ እርሱም እነዚህን ሁሉ እንደ እውነቶች ተቀብሏቸው እንደነበረ ነው፡፡ እርሱም እነርሱ የወንጌልን ክፍል እንደሰሩ አድርጎ አምኖ ነበር፡፡ ይህም በቁርአን ላይ ብዙ ጊዜ መጠቀሱ በጣም የሚያስደንቅ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የእርሱ መረጃ አቀባዮች እውነተኛና በሚገባ ያልተማሩ ክርስትያኖች የነበሩ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ እውነታ ነው፡፡ እንዲሁም ደግሞ ከክርስትና መልእክት ይልቅ ታልሙዲክ በሆነው አይሁዲነት ላይ ትኩረትን ማድረግ መርጧል ነበር፡፡ ሙሉ የሆነ ነገርን በፍፁም የማያቀርቡት እነዚያ የቁርአን አንቀፆች፤ ማለትም መሐመድ የክርስትና አስተምህሮ ነው ብሎ የገመታቸው ሁሉ፤ የእርሱ ስርዓት ከተመሰረተ፤ በብዙ ቦታዎች ላይ ከተሰራጨና ከበሰለ ጀምሮ ያሉት ክርስትያናዊ መረጃዎች በጣም ብቁ ያልሆኑ፣ ተረቶች እና ያልተጣሩ መረጃዎች ነበሩ፡፡ ስለዚህም በእስልምና ውስጥ ካሉት ስርዓቶች ወይንም ትምህርቶች መካከል ከታወቁት የክርስትና ክፍሎች የተዘጋጁ ወይንም የተያያዙ አናገኝም፡፡ በተፃራሪው ግን አይሁዳዊነት ለመላው የእስልምና ስርዓት አጠቃላይ መልክን ሰጥቶታል፡፡ እንዲሁም ለእርሱ ቅርፅና ሁኔታ ብዙ ነገሮችን አበድሯል ብዙዎቹ ስርዓቶች እራሳቸው እንዳሉ ባይገኙም፡፡

ነገር ግን በዚያው ጊዜ መሐመድ ክርስትያኖችንና አይሁዶችን ወደ እምነቱ ለመማረክ እጅግ በጣም ተመኝቶ ነበር፡፡ ክርስትያኖች በአረቢያ ከአይሁዶቹ ይልቅ በቁጥርና በኃይል ጥቂት ቢሆኑም ኖሮ፣ በታላቋ ባዛንታይን የተመሰረተው የክርስትና ሃይማኖት የሆነ ጠቀሜታ ያለው መሆኑ በመሐመድ ዓይን ግምት አስገኝቶ ነበር፡፡ ምክንያቱም በተለይ የአረቢያ ክርስትያኖች ካላመኑ የፖለቲካ ምስቅልቅል ሊነሳ ይችላል የሚል ስጋት ነበር፡፡ የዚህ የኋለኛው ስሜት በመሐመድ ላይ ያደረገው ተፅዕኖ እስከምን ድረስ ነበር የሚለውን ለመናገር አይቻልም፡፡ ለማንኛውም እራሱ ከመለኮት ተልእኮ የተቀበለ መሆኑን ለማስረዳት ወንጌልን ይጠቅስ ነበር፡፡ ክርስቶስ የእርሱን መምጣት ትንቢት እንደተናገረ፣ እስከመናገርም ድረስ ሄደ፡ ‹የመርየም ልጅ ዒሳም፡ የእስራኤል ልጆች ሆይ እኔ ከተውራት በፊት ያለውን የማረጋግጥና ከኔ በኋላ በሚመጣው መልክተኛ ስሙ አሕመድ በኾነው የማበስር ስኾን ወደናንተ (የተላክሁ) የአላህ መልክተኛ ነኝ ባል ጊዜ (አስታውስ) በግልጥ ታምራቶች በመጣቸውም ጊዜ ይህ ግልፅ ድግምት ነው አሉ› ቁርአን 61.6፡፡ በቁርአን 3.45 ላይም ‹መላእክት ያሉትን አስታውስ መርየም ሆይ አላህ ከርሱ በኾነው ቃል ስሙ አልመሲሕ ዒሳ የመርየም ልጅ በዚህ ዓለምና በመጨረሻውም ዓለም የተከበረ ከባለሟሎችም በኾነ (ልጅ) ያበስርሻል› እንዲሁም በቁርአን 4.171 በማለት፤ ክርስቶስም የእግዚአብሔር ቃል እንደነበረ ተናገረ ነገር ግን የእርሱን መለኮትነትና መሰቀል ካደና የወንጌልን እውነተኛ መልእክት ምንም እንደማያውቅ በግልጥ አሳየ፡፡ ነገር ግን በብዙ የመጽሐፉ ክፍሎች ላይ፤ ወንጌል የመለኮት ምንጭነት ያለው መሆኑን አክብሮ ተናግሯል፤ ይህንም ሲናገር ወንጌል በኢየሱስ ላይ ከሰማይ እንደወረደ፣ ቁርአንም የወረደው እርሱን ለማረጋገጥና ለመጠበቅ እንደሆነ ተናገረ ቁርአን 5.48 ‹ወደ አንተም መጽሐፉን ከበፊቱ ያለውን መጽሐፍ አረጋጋጭና በርሱ ላይ ተጠባባቂ ሲሆን በውነት አወረድን›፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የክርስቶስን ከድንግል መወለድ መዝግቧል እንዲሁም አንዳንድ የእርሱን ተዓምራቶችንም ጠቅሷል፣ ነገር ግን እዚህም ውስጥ እንኳን የተረትነቱ ድምፅ ከፍ በማለት ይጮኻል፡፡ ስለዚህም መሐመድ ስለ ጌታችንና ስለ ደቀመዛምርቱ ካልታመነ ምንጭ በጣም ጥቂት የተማረ ይመስላል፡፡ ቁርአን በእነዚያ ነገሮች ላይ ያዛመዳቸው ነገሮች ከኑፋቄ ክርስትያናዊ አፖክሪፋዎች ጋር በዝርዝር እንደሚስማሙ እናያለን ይህም በጣም አስገራሚ ነው፡፡ እዚህ እንደገና መሐመድ እውነትን ላለመቀበልና ውሸትን ብቻ ለመቀበል አስገራሚ የሆነ ችሎታ የነበረው መሆኑን እናስተውላለን፡፡ ይህም ከዚህ በላይ በነበረው ምዕራፍ ተጠቅሰው እንዳየናቸው እንደ አይሁዶቹ ልማድ ነው፡፡

ይህንን ለማረጋገጥ የምንቀጥለው በቁርአን ውስጥ የክርስትያን ነገሮችን በሚናገሩትና እነርሱም የተወሰዱበትን ምንጭ በመጠቆም ነው፡፡

ሀ. ዋሻው ውስጥ የቆዩት ወጣቶች ተረት

በመጀመሪያም የምናየው በዋሻው ውስጥ የቆዩትን ወጣት ተገጓዦችን ተረት ነው ይህም በቁርአን 18.9-26 ላይ እንደሚከተለው ተገልጧል፡፡

‹የዋሻውና የሰሌዳው ባለቤቶች ከታምራቶቻችን ሲኾኑ ግሩም መሆናቸውን አሰብክን? ጎበዞቹ ወደ ዋሻው በተጠጉና ጌታችን ሆይ ከአንተ ዘንድ እዝነትን ስጠን ለኛም ከነገራችን ቅንን አዘጋጅልን ባሉ ጊዜ (አስታውስ)፡፡ በዋሻውም ውስጥ የተቆጠሩን ዓመታት በጆሮቻቸው ላይ መታንባቸው፡፡ ከዚያም ከሁለቱ ክፍሎች ለቆዩት ጊዜ ልክ ያረጋገጠው ማንኛው መኾኑን ልናውቅ አስነሳናቸው፡፡ እኛ ወሬያቸውን በአንተ ላይ በውነት እንተርካለን እነሱ በጌታቸው ያመኑ ጎበዞች ናቸው መመራትንም ጨመርንላቸው፡፡ (በንጉሳቸው ፊት) በቆሙና ጌታችን የሰማያትና የምድር ጌታ ነው ከርሱ ሌላ አምላክን አንገዛም ያን ጊዜ (ሌላን ብናመልክ) ወሰን ያለፈን (ንግግር) በእርግጥ ተናገርን ባሉ ጊዜ ልቦቻቸውን አጠነከርን፡፡ እነዚህ ሕዝቦቻችን ከርሱ ሌላ አማልክትን ያዙ (እውነተኞች ከኾኑ) በነርሱ ላይ ግልጽ ማስረጃን ለምን አያመጡም በአላህም ላይ ውሸትን ከሚቀጣጥፍ ይበልጥ በዳይ ማነው? (አሉ)፡፡ እነርሱንና ያንን ከአላህ ሌላ የሚገግገዙትን በተለያችሁ ጊዜ ወደ ዋሻው ተጠጉ ጌታችሁ ለናንተ ከችሮታው ይዘረጋላችኋልና ከነገራችሁም ለናንተ መጠቃቀሚያን ያዘጋጅላችኋል (ተባባሉ)፡፡ ፀሐይንም በወጣች ጊዜ ከዋሻቸው ወደ ቀኝ ጎን ስታዘነብል ታያለህ በገባችም ጊዜ እነርሱ ከርሱ በሰፊው ስፍራ ውስጥ ኾነው ሳሉ ወደ ግራ በኩል ትተዋቸዋለች ይህ ከአላህ ታምራቶች ነው አላህ የሚያቀናው ሰው ቅኑ እርሱ ብቻ ነው የሚያጠምመውም ሰው ለርሱ አቅኝን ረዳት አታገኝለትም፡፡ እነሱም የተኙ ኾነው ሳሉ (ዓይኖቻቸው በመከፈታቸው) ንቁዎች ናቸው ብለህ ታስባቸዋለህ ወደ ቀኝ ጎንና ወደ ግራ ጎንም እናገላብጣቸዋለን ውሸቸውም ሁለት ክንዶቹን በዋሻው በር ላይ ዘርግቷል በነሱ ላይ ዘልቀህ ብታይ ኖሮ የምትሸሽ ኾነህ በዞርክ ነበር ከነሱም በእርግጥ ፍርሃትን በተመላህ ነበር፡፡ እንዲሁም በመካከላቸው እንዲጠያየቁ ቀሰቀስናቸው ከነሱ አንድ ተናጋሪ ምን ያክል ቆያችሁ? አለ አንድን ቀን ወይም የቀንን ከፊል ቆየን አሉ፡፡ ጌታችሁ የቆያችሁትን ጊዜ ልክ ዐዋቂ ነው ከዚችም ብራችሁ ጋር አንዳችሁን ወደ ከተማይቱ ላኩ ከምግቦችዋ የጥኛው ንጹህ መኾንዋንም ይመልከት ከርሱም (ከንጹሑ) ምግብን ያምጣላችሁ ቀስም ይበል በናንተም አንድንም ሰው አያሳውቅ አሉ፡፡ እነሱ በናንተ ላይ ቢዘልቁ ይቀጠቅጧችኋልና ወይም ወደ ሃይማኖታቸው ይመልሷችኋል ያን ጊዜም በፍጹም ፍላጎታችሁን አታገኙም (ተባባሉ)፡፡ እንደዚሁም የአላህ ቀጠሮ እርግጠኛ መኾኑን ሰዓቲቱም በርሷ ጥርጣሬ የሌለ መኾኑን ያውቁ ዘንድ በነርሱ ላይ (ሰዎችን) አሳወቅን (አማኞቹና ከሓዲዎቹ) ነገራቸውን በመካከላቸው ሲከራከሩ (የኾነውን አስታውስ ከሐዲዎቹ) በነሱ ላይም ግንብን ገነቡ አሉ፤ ጌታቸው በነሱ ይበልጥ ዐዋቂ ነው እነዚያ በነገራቸው ላይ ያሸነፉት (ምእመናን) በነሱ ላይ በእርግጥ መስጊድን እንሠራለን አሉ፡፡ በሩቅ ወርዋሪዎች ኾነው (በጥርጣሬ) ሦስት ናቸው፣ አራተኛው ውሻቸው ነው ይላሉ አምስት ናቸው ስድስተኛው ውሻቸው ነውም ይላሉ ሰባት ናቸው ስምንተኛው ውሻቸው ነው ይላሉም ጌታዬ ቁጥራቸውን ዐዋቂ ነው ጥቂት (ሰው) እንጂ አያውቃቸውም በላቸው በነሱም ነገር ግልጽን ክርክር እንጂ (ጠልቀህ) አትከራከር በነሱም ጉዳይ ከነሱ (ከመጽሐፉ ሰዎች) አንድንም አትጠይቅ፡፡ ለማንኛውም ነገር እኔ ይህንን ነገ ሠሪ ነኝም አትበል፡፡ አላህ የሻ እንደሆነ (እሠራዋለሁ ብትል) እንጂ በረሳህም ጊዜ ጌታህን አውሳ ጌታዬም ከዚህ ይበልጥ ለቀጥታ የቀረበን ሊመራኝ ይከጅላል በላቸው፡፡ በዋሻቸውም ውስጥ ሦስት መቶ ዓመታትን ቆዩ ዘጠኝንም ጨመሩ፡፡ አለህ የቆዩትን ልክ ዐዋቂ ነው በላቸው የሰማያትና የምድር ምስጢር የሱ ብቻ ነው እርሱ ምን ያይ ምን ይሰማም ለነርሱ ከርሱ በቀር ምንም ረዳት የላቸውም በፍርዱም አንድንም አያጋራም›፡፡

ይህን ማመንታት ያለበትን ዘገባ ለመረዳት፣ አንዳንዶቹ አሕዛብ የመካ አረቦች መሐመድ የዋሻዎቹን ተጓዥ ወጣቶችን ታሪክ የሚችል ከሆነ እንዲነግራቸው ተፈታትነውት እንደነበረ ተንታኞቹ እንደሚነግሩን ማስታዎስ አለብን፡፡ ይህም መገለጥ አግኝቻለሁ የሚለውን ሰው አነጋገሩን ለመፈተን ብለው ነበር፡፡ ታሪኩም በእነርሱ መካከል በሆነ መልክ በጊዜው በጣም ታዋቂ የነበረ ነው፣ ምናልባትም ከአንድ በላይ በሆነ መንገድ፡፡ ወደ ዋሻው ውስጥ የገቡት ሰዎችን ቁጥርም በተመለከተ ክርክር ስለነበር፣ በዚህም ጉዳይ ላይ የተለያዩ አመለካከቶች ተሰጥተዋል፡፡ መሐመድ በቁጥር 22 እና 23 ላይ እኛ እዚህ የዘለልነው፣ ስለ ጉዳዩ አንድ ሌላ ሰውን ለመጠየቅ በማቀድበ ሚቀጥለው ቀን መልስ እንደሚሰጥ ቃል ገብቶ ነበር፡፡ ነገር ግን እርግጠኛ የሆነ መረጃ ማግኘትን አልቻለም፣ ስለዚህም የወጣቶቹን ቁጥር በተመለከተ ያለምንም ምላሽ ትቶታል፣ እርሱም ከችግሩ ውስጥ ለመውጣት ያደረገው ሙከራ ያልተሳካ ነበር፡፡ እንዲሁም ደግሞ ሁኔታው የት እንደተከሰተ ወይንም መቼ እንደተከሰተ ለመናገር አልቻለም፡፡ ይሁን እንጂ ሞክሮ የነበረው፣ በዋሻው ውስጥ ያለፈው ጊዜ 309 ዓመታት መሆኑን የመናገር እውነታ ነበር፡፡ የሆነው ሆኖ እንደምናያው ሁሉ በዚህም እንኳን እርሱ ተሳሳቶ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በታሪኩ ላይ የተመዘገው ክስተት ተከናውኖ እንደነበረ ምንም ጥርጥር አልነበረውም፡፡ ከአንቀፁ አጠቃላይ አቀራረብ የምንረዳው መሐመድ ምንም የጽሑፍ ማስረጃ እንዲሁም የሁኔታውን ትክክለኛ ዝርዝር የሚሰጠው ታማኝ የሆነ አረጋጋጭ (መረጃ አቅራቢ) በቅርቡ እንዳልነበረው ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከመሐመድ ጊዜ በፊት የተጻፈ የዚህ አፈ ታሪክ ብዙ ገፅታዎች አሉን፡፡ እንዲሁም በመለኮት ተገለጡ ላላቸው ነገሮች ብቻ ሳይሆን በቃል በቁርአን ለተነገሩት ዓይነት ታሪኮችም መሐመድ ሃላፊነት አለበት፡፡ የሲሪያክ ጸሐፊ፣ በ521 ዓ.ም የሞተው የሳሩግ ጃኮብ፣ በአክታ ሳንክቶሪየም ላይ በታተመ ስብከት፣ የዚህን አፈታሪክ በረጅሙ ሰጥቷል፡፡ ሌላው የቀደመው የሲሪያክ ጽሑፍ የሰጠው የታሪኩ መልኮች የታወቁ ናቸው፡፡ ብዙዎቹ መረጃዎች የሚሉት ‹ሰባት ሰዎች ተኝተው እንደነበር ነው› ስለዚህም በዮሮፕ ውስጥ በአጠቃላይ በዚህ ስም ነው የሚታወቀው፣ ነገር ግን በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በነበረ በአንድ ሲሪያክ ኤምኤስ፣ በብሪቲሽ ሚዚየው ውስጥ የሚናገረው እነርሱ ስምንት ናቸው በማለት ነው፡፡ መሐመዳውያን ተንታኞች በቁርአን ውስጥ ያለውን ያገናኙት ከልማዶች ጋር ነው፡፡ አንዳንዶቹም ሰባት ነበሩ የሚሉ ናቸው ሌሎች ደግሞ የሚያረጋግጡት ስምንት ናቸው በማለት ነው፡፡ ይህም በቁርአን ላይ መሐመድ በተግባር ለመወሰን ያልቻለው ነገር ነበር፡፡ እስከምናውቀው ድረስ ይህንን አፈታሪክ ለማዛመድ የጀመረው የመጀመሪያው የዩሮፕ ጸሐፊ የቱረሱ ግሪጎሪ ነበር፡፡ እርሱም የሚነግረን በንጉስ ዲሲየስ የግዛት ዘመን (249-51 ዓ.ም) ሰባት የሆኑ የከበሩ ወጣት ክርስትያኖች ከኤፌሶን ስደት ሸሽተው ከከተማው ርቆ በሚገኝ ዋሻ ውስጥ ተጠለሉ፡፡ ከጊዜም በኋላ ጠላቶቻቸው የት እንዳሉ አወቁና በረሃብ እንዲሞቱ የዋሻውን በር ከውጭ ዘጉባቸው፡፡ ከ196 ዓመታት በኋላ ዳግማዊ ቴዎዶሲየስ ዙፋን ሲይዝ አንድ የከብቶች ጠባቂ ዋሻውን አግኝቶ ከፈተው፡፡ ከዚያም ሰባቱ አንቀላፊዎች በእነዚህ ዘመናት ሁሉ ከነበሩበት ከእንቅልፋቸው ውስጥ ነቁ፡፡ (ልክ ቁርአንም እንደሚለው ማለት ነው) ከመካከላቸው አንዱን ወደ ከተማ ሄዶ የሚያስፈልጋቸውን እንዲገዛ ላኩት፡፡ እርሱም ክርስትናን በሁሉም ቦታ ላይ ተስፋፍቶ አገኘውና እጅግ በጣም ተደነቀ፡፡ ጥቂት ምግብን ሊገዛበት ባለውም ሱቅ ውስጥ የዲሲየስን ገንዘብ አውጥቶ ለመክፈል ሰጠ፡፡ በዚያንም ጊዜ የተደበቀ ንብረት ያገኘ ሰው ተብሎም በመወንጀሉ የራሱንና የጓደኞቹን ታሪክ ተናገረ፡፡ ወደ ዋሻውም መንገድን እየመራ እያለ የጓደኞቹ መልክ ገና ወጣት፣ እንደ ሰማያዊ ብርሃን የሚያበራ ነበርና፣ የተናገረውን የታሪኩን እውነታነት አረጋገጠው፡፡ ንጉሱም ይህንን ወዲያውኑ ሰማ ወደ ዋሻውም እራሱ በአካል ሄደ ከእንቅልፍ የተነሱት ሰዎች እነርሱን እግዚአብሔር ይህንን ያህል የጠበቃቸው ለእርሱ የነፍስን ሕያውነት (አለመሞት) ለማረጋገጥ እንደሆነ ነገሩት፡፡ መልእክታቸውንም ካስተላለፉ በኋላም ተሰወሩ፡፡

በቁርአን ላይ ለቀረበው ለዚህ በጣም የጅልነት ተረት ላይ አስተያየት መስጠት አስፈላጊ አይደለም፡፡ በማንኛውም መልኩ የፈጠራ ታሪክ የሆነውንና በአገሮች ሁሉ ውስጥ ባልተማሩ ክርስትያኖች አማካኝነት የተስፋፋውን ይህን ተረት መሐመድ እንደእውነት ቢቀበለውም እንደ ከክርስትያኖቹ በላይ ሊወቀስ አይገባውም፡፡ ታሪኩም በቅድሚያ ምሳሌያዊ ተረት ወይንም ምናልባት ሃይማኖታዊ የጀብዱ ልብወለድ ሳይሆን አይቀርም፡፡ የክርስትና እምነት በምን ያህል ፍጥነት በድንቅ እንደተስፋፋ ለማሳየት ታቅዶ የተቀናበረና በብዙ ታማኞች አማኞቹ ድፍረት በብዙ ቦታ እምነቱ እንደተስፋፋ ለማሳየት ሳይሆን አይቀርም፡፡ ይህ እንዲህ ሆኖ ከመሐመድ ጊዜ ብዙ ዓመታት በፊት የሆነ መሆኑ ምንም ጥርጥር ባይኖረውም ተረቱ ግን በምስራቅ በብዙ ቦታዎች ላይ ተቀባይነትን አግኝቶ ነበር፡፡ በመሐመድ ጊዜም በመካም እንኳን ሳይቀር ታማኝነት ነበረው፡፡ የመሐመድ ስህተት የሚገኘው እርሱ በመለኮት መገለጥ እንደተቀበለው አድርጎ ማስመሰሉ ነበር፣ ሆኖም ግን በቅዱስ ጊዮርጊስና በዘንዶው ላይ እንደተተረተው ዓይነት ተረት ትንሽ አመኔታ የነበረው ነበር፡፡ በግሪኮች መካከል እንዳለው እንደ ሲንዴሬላና የመስታዎት ጫማዋ ወይንም በተለያዩ አገሮች ውስጥ እንዳሉ አስደናቂ ነገር ግን እውነት እንዳልሆኑ ተረቶች ነበር፡፡

የአዘጋጁ ማሳሰቢያ፡

በቁርአን ውስጥ ከሚገኙት ተረቶች አንዱና ከዚህ በላይ የተገለጠው የመጽሐፉን ምንነት እንድንረዳ ዓይኖቻችን ከሚከፍቱት ነገሮች መካከል አንዱ ነው፡፡ ከእግዚአብሔር መጡ በሚባሉ፣ ነገር ግን ከእግዚአብሔር ባልሆኑ የውሸት መገለጦች ሰዎች ምን ያህል እንደሚሳሳቱም ግልጥ በሆነ መንገድ ያስረዳል፡፡ የዚህ ገፅ አዘጋጆች ዓላማ ሙስሊሞች እነዚህን እውነቶች እንዲያወቁና ስለዘላለማዊ ሕይወት በጥልቅ እንዲያስቡ ለመርዳት ነው፡፡ ስለዚህም የዚህ ገፅ አንባቢዎች መጽሐፍ ቅዱስን እንድታነቡና ከእርሱ ውስጥ ያለውን የእግዚአብሔርን መልእክት እንድትገነዘቡ በእግዚአብሔር ፍቅር አሁንም እንጋብዛችኋለን፡፡ እግዚአብሔር በቸርነቱና በምህረቱ ይርዳችሁ፡፡

 

የትርጉም ምንጭ: THE ORIGINAL SOURCES OF THE QUR'AN 

ሙሉ መጽሐፉ በአማርኛ:  የቁርአን የመጀመሪያ ምንጮች

ለእስልምና መልስ አማርኛ  ዋናው ገጽ