የቁርአን የመጀመሪያ ምንጮች

ምዕራፍ ሦስት ክፍል ሦስ

የሳቢያንና የአይሁዶች ሐሳቦችና ልማዶች ተፅዕኖዎች 

REV. W. ST. CLAIR TISDALL, M.A., D.D

ትርጉምና ቅንብር በአዘጋጁ

3. የንግስተ ሳባ ታሪክ

በቁርአን ውስጥ የሚገኘውን የንግስተ ሳባን የታሪክ ምንጭ በተመለከተ ቅንጣት የምታክል ጥርጥር አይኖርም፡፡ በቀጥታ የተወሰደውም ‹በአስቴር› ላይ ከተጻፈውና ‹በሚክሮት ጌሎሎት› ከታተመው ከሁለተኛው ታርገም ላይ ሲሆን በጣም ጥቂት ለውጦች ተደርገውበታል፡፡ መሐመድ ያለምንም ጥርጥር ያመነው የአይሁድ ቅዱስ መጽሐፍ አንድ ክፍል አድርጎ ነበር፡፡ የመሐመድ ሞኝነቶች እጅግ በጣም ብዙ ነበሩ ለእርሱና ለአረቦች ልማዳዊ ደስታ ሰጪ ተረቶች የሆኑትን እነዚህን በቁርአን ውስጥ አካተታቸው፡፡ ‹ለሱለይማንም ሰራዊቶቹ ከጋኔን ከሰውም ከበራሪም የኾኑት ተሰበሰቡ እነሱም ይከመከማሉ› ቁርአን 27.17 እና ‹በራሪዎቹንም ተመለከተ አለም፡ ሁድሁድን ለምን አላየውም! በውነቱ ከራቁት ነበርን? ብርቱን ቅጣት በእርግጥ እቀጣዋለሁ ወይም በእርግጥ ዐርደዋለሁ ወይም ግልጽ በኾነ አስረጅ ይመጣኛል አለ፡፡ (ወፉ) ዕሩቅ ያልኾነንም ጊዜ ቆዬ አለም፡- ያላወቅከውን ነገር አወቅኩ ከሰበእም እርግጠኛን ወሬ አመጣሁልህ፤ እኔ የምትገዛቸው የኾነችን ሴት ከነገሩም ሁሉ የተሰጠችን አገኘሁ ለርሷም ታላቅ ዙፋን አላት፣ እርሷንም ሕዝቦቿንም ከአላህ ሌላ ለፀሐይ ሲሰግዱ አገኘኋቸው ሰይጣንም ለነሱ ሥራዎቻቸውን ሸልሞላቸዋል ከውነተኛውም መንገድ አግዷቸዋል ስለዚህ እነሱ (ወደ እውነት) አይመሩም፡፡ ለዚያ በሰማያትና በምድር የተደበቀውን ለሚያወጣው የምትሸሽጉትንና የምትገልፁትንም ሁሉ ለሚያውቀው አላህ እንዳይሰግዱ (ሰይን አግዷቸዋል) አላህ ከርሱ ሌላ አምላክ የለም የታላቁ ዐርሽ (ዙፋን) ጌታ ነው፡፡ (ሱለማይንም) አለ፡- እውነት እንደ ተናገርህ ወይም ከውሸታሞቹ እንደ ኾንክ ወደ ፊት እናያለን፤ ይህንን ደብዳቤዬን ይዘህ ኺድ ወደነርሱም ጣለው ከዚያም ከነሱ ዘወር በል ምን እንደሚመልሱም ተመልከት፡፡ እርሷም በደረሳት ጊዜ አለች እላንተ መማክርቶች ሆይ እኔ ክብር ያለው ጽሑፍ ወደ እኔ ተጣለ፤ እርሱ ከሱለይማን ነው እርሱም በአላህ ስም እጅግ በጣም ርኁሩህ በጣም አዛኝ በኾነው፤ በኔ ላይ አትኩሩ ታዛዦችም ኾናችሁ ወደኔ ኑ (የሚል ነው)፡፡ እላንተ መማክርቶች ሆይ በነገሬ (የሚበጀውን) ንገሩኝ እስከምገኙልኝ ድረስ አንድንም ነገር ቆራጭ አይደለሁምና አለች፡፡›

‹እኛ የኃይል ባለቤቶች የብርቱ ጦርም ባቤቶች ነን ግን ትእዛዙ ወደ አንቺ ነው ምን እንደምታዢም አስተውሊ አሏት፡፡ (እርሷም) አለች፡- ንጉሦች ከተማን (በኃይል) በገቡባት ጊዜ ያበላሹዋታል የተከበሩ ሰዎችንም ወራዶች ያደርጋሉ እንደዚሁም (እነዚህ) ይሠራሉ፤ እኔም ወደነርሱ ገጸ በረከትን የምልክና መልክተኞቹ በምን እንደሚመለሱ የምጠባበቅ ነኝ፡፡ (መልክተኛው) ሱለማይንንም በመጣው ጊዜ አለ፡- በገንዘብ ትረዱኛላችሁን? አላም የሰጠኝ ከሰጣችሁ የበለጠ ነው፣ ይልቁንም እናንተ በገጸ በረከታችሁ ትደሰታላችሁ፡፡ ወደ እነርሱ ተመለስ ለነሱም በርሷ ችሎታ በሌላቸው ሰራዊት እንመጣባቸዋለን ከርሷም እነርሱ የተዋረዱ ኾነው በእርግጥ እናወጣቸዋለን (አለ)፡፡›

‹እናንተ መኳንንቶች ሆይ ሙስሊሞች ኾነው ሳይመጡኝ በፊት ዙፋንዋን የሚያመጣልኝ ማንኛችሁ ነው? አለ፡፡ ከጋኔን ኃይለኛው ከችሎትህ ከመነሳትህ በፊት እኔ እርሱን አመጣልሃለሁ እኔም በእርሱ ላይ ብርቱ ታማኝ ነኝ አለ፡፡ ያ እርሱ ዘንድ ከመጽሐፉ ዕውቀት ያለው ሰው (የተገለጸው) ዓይንህ ወደ አንተ ከመመለሱ በፊት እኔ እርሱን አመጣልሃለሁ አለ፤ (እንደዚሁም አደረገ) እርሱ ዘንድ ረግቶ ባየውም ጊዜ ይህ ከጌታዬ ችሮታ ነው የማመሰግን ወይም የምክድ መኾኔን (ቸረልኝ) ያመሰገነም ሰው የሚያመሰግነው ለራሱ ነው የካደም ሰው ጌታዬ ከርሱ ተብቃቂ ቸር ነው አለ፡፡ ዙፋንዋን ለርሷ አሳሳቱ ታውቀው እንደ ኾነ ወይም ከነዚያ ከማያውቁት ትኾን እንደ ኾነ እናያለን አላቸው፡፡ በመጣችም ጊዜ፡- ዙፋንሽ እንደዚህ ነውን? ተባለች እርሱ ልክ እርሱ ነው መሰለኝ አለች (ሱለይማን) ከርሷ በፊትም ዕውቀትን ተሰጠን ሙስሊሞችም ነበርን (አለ)፡፡›

‹ከአላህ ሌላ ትገዛ የነበረችውንም ከለከላት እርሷ ከከሐዲዎች ሕዝቦች ነበረችና፡፡ ሕንጻውን ግቢ ተባለች ባየቺውም ጊዜ ባሕር ነው ብላ ጠረጠረችው ከባቶችዋም ገለጠች እርሱ ከመስተዋት የተለሰለሰ ሕንጻ ነው አላት ጌታዬ ሆይ እኔ ነፍሴን በደልኩ ከሱለማይንም ጋር ሆኜ ለዓለማት ጌታ ለአላህ ታዘዝኩ አለች› 20-44፡፡

ይህ በቁርአን ላይ ያለው የንግስተ ሳባ ታሪክ በታርገም ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንድ ዝርዝር ነገሮችን ዘሏቸዋል በአንዳንድ ቦታዎች ላይም ከኋኛው ይለያል፡፡ ታርገም የሚተርከው ዙፋኑ የሰሎሞን ዙፋን ነው፣ ሃያ አራት ንስሮችም ከዙፋኑ በላይ ተቀምጠዋል፡፡ ንጉሱ በዙፋኑ ላይ ሲቀመጥ ወፎቹ በእራሱ ላይ ጥላቸውን ያጠሉለታል፡፡ ሰሎሞንም ወደ አንድ ቦታ ለመሄድ በፈለገ ጊዜ እነዚህ ንስሮች እርሱንና ዙፋኑን በመሸከም ያጓጉዙት ነበር፡፡ ስለዚህም በታርገም ውስጥ የምናየው ንስሮች የዙፋን ተሸካሚዎች ሆነው ነው፣ ቁርአን ያቀረበው ‹ኢፍሪት› ግን ለሰሎሞን እንደዚህ ዓይነት አገልግሎትን አንድ ጊዜ ብቻ እንዳደረገለትና፣ ከዚያም በኋላ የቀጠለው ዙፋኑ ባዶ በሚሆንበት ጊዜ ብቻ ነው፡፡

ንጉሱ ሰሎሞን በወፉ አማካኝነት ለንግስት ሳባ የላከላትን ደብዳቤ በተመለከተ በሁለቱ መጽሐፎች (በቁርአንና በታርገም) መካከል አስደናቂ የሆነ መመሳሰል ይገኛል፡፡ የታርገሙ ጽሑፍ ወፉን ሆፔ (የበረሃ አውራ ዶሮ) በማለት ከሚጠራው በስተቀር ጽሑፉ አንድ አይነት ነው፡፡ አንባቢ የታርገሙን አንቀፅ ትርጉም ከአረብኛው ጋር ለማናፀፀር እንዲችል ከዚህ በታች አቅርበነዋል፡፡

‹እንደገናም የንጉሱ ሰለሞን ልብ በወይን ጠጅ ደስ በተሰኘ ጊዜ፣ የምድርን አራዊት፣ የሰማይን አዕዋፍ፣ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትን ሁሉ ጂኒዎችንና መናፍስትን፣ የጨለማ ተርመስማሾችን፣ በፊቱ ለሚሰግዱት ነገስታት የእርሱን ታላቅነት ለማሳየት በፊቱ መጥተው እንዲደንሱ፣ የንጉሱ ጸሐፍት በየስሞቻቸው አቀረቧቸው እነሱም ሁሉም ተሰብስበው ወደ እርሱ መጡ፡፡ ይህም ከእስረኞች፣ ከምርኮኞች፣ በነሱ ላይ አዛዦች ከሆኑት ሰዎች በስተቀር ነው፡፡ በዚያን ጊዜም የምድረ በዳው አውራ ዶሮ በወፎች መካከል እራሱን ያስደስት ነበርና አልቀረበም፡፡ ንጉሱም በኃይል አስገድደው ያቀርቡት ዘንድ አዘዘ እንዲሁም ሊያጠፋው ፈለገ፡፡ የምድረ በዳውም አውራ ዶሮ ወደ ንጉሱ ሰሎሞን ተመልሶ ለንጉሱ እንዲህ አለው፤ ‹የምድር ንጉስ ጌታዬ ስማ፣ ጆሮህንም አዘንብል እና ቃሌን ስማኝ፡፡ በልቤ ውስጥ ካሰብኩና ጥብቅ ውሳኔን ከወሰንሁ ሦስት ወር አይሆንምን? ዓለምን ሁሉ ሳላይና በዙሪያውም ሳልበርር (ሳልንሳፈፍ) ምንም ላልበላና ምንም ላልጠጣ በራሴ ላይ ከወሰንሁ? እኔም ለጌታዬ ለንጉሱ የማይታዘዘው የትኛው መንግስትና ግዛት ነው? አልኩኝ፡፡ ዓይኔንም ከፈትኩና በምስራቅ አገር የተከበበችን ከተማ አየሁኝ፣ ስሟም ኪቶር የሚባል ነው፤ አፈሯ በወርቅ የከበደ ነው፣ በመንዱም ላይ ብር እንደ ጭቃ ነው፡፡ በዚያም ዛፎች ከመጀመሪያው ጀምሮ ተተክለዋል ከኤድን ገነትም ውሃን ይጠጣሉ፡፡ በራሶቻቸው ላይ የአበባ ጌጥ ያላቸው ብዙ ሕዝቦች አሉ፡፡ ለኤድን ገነት በጣም ቅርብ ስለሆነ ከዚያ አትክልቶች አሉበት፡፡ በቀስት በተኮስ ይዋጋሉ ነገር ግን በቀስት አይወጉም፡፡ በእነሱም ላይ የምትገዛው አንዲት ሴት ናት ስሟም ‹ንግስተ ሳባ› ይባላል፡፡ አሁን አንተን የሚያስደስትህ ከሆነ ጌታዬና ንጉሴ ሆይ፣ ይህ ሰው፤ የኔን መታጠቂያ ይታጠቅ እኔም ወደ ላይ ወጥቼ ወደ ሳባ ከተማ ወደ ኪቶር ግንብ እበራለሁኝ፣ እኔም ‹ነገስታቶቻቸውን በሰንሰለት መሳፍንቶቻቸውንም በብረት ማሰሪያ አስራለሁኝ› እንዲሁም ወደ ጌታዬ ወደ ንጉሰ ዘንድ አመጣቸዋለሁኝ፡፡

ነገሩም ንጉሱን ደስ አሰኝቶት ነበር፣ የንጉሱም ጸሐፊዎች ተጠሩና ደብዳቤን ጽፈው በበረሃው ወፍ ክንፍ ላይ አሰሩት፡፡ እርሱም ተነሳና ወደ ሰማይ ወጣ የራሱንም ጥምጥም አሰረና በጣም ጠንካራ ሆነ በወፎችም መካከል በረረ፡፡ አነሱም እርሱን ተከትለውት በረሩ፡፡ ከዚያም ወደ ሳባ ከተማ ወደ ኪቶር ግንብ ሄዱ፡፡

እንዲህም ሆነ ንግስት ሳባ በማለዳ ጊዜ ወደ ባህሩ ዳር ለማምለክ ሄደች፡፡ ወፎቹም ፀሐይን አጨለሟት እርሷም እጇን በቀሚሶቿ ላይ አድርጋ ቀደደቻቸው እርሷም ተደነቀች ተረበሸችም፡፡ በምትረበሽበትም ጊዜ የምድረበዳው ወፍ ወደ እርሷ ወረደ እርሷም አየች እነሆም በክንፉ ላይ ደብዳቤ ታስሮ ነበር፡፡ ደብዳቤውንም ከፈተችውና አነበበችው፡፡ በእርሱም ላይ ተጽፎ የነበረው ነገር የሚከተለው ነበር፣ ‹ከእኔ ከንጉስ ሰለሞን፡፡ ሰላም ለአንቺ ይሁን፣ ሰላም ለመሳፍንቶችሽ ይሁን እንደምታውቂው ሁሉ ቅዱሱ እርሱ የተባረከ ይሁን! ለምድር እንሰሳት ሁሉ ንጉስ እንድሆን አድርጎኛል፣ ለሰማይ አዕዋፍም ላይ፣ እንዲሁም በጂኒዎች ላይ በመሳፍንቶች ላይ በጨለማም በሚዘዋወሩት ሁሉ ላይ እንዲሁም የሰሜን የደቡብ የምስራቅና የምዕራብ ነገስታት ሁሉ ወደ እኔ ይመጣሉ ስለ ጤንነቴና (ሰላሜንም) ይጠይቃሉ  አሁንም አንቺ ፈቃደኛ ብትሆኚና ደህንነቴን ብትጠይቂ ደህና በፊቴ ከሚሰግዱትም ነገስታት ሁሉ በላይ ታላቅ አድርግሻለሁኝ፡፡ ነገር ግን ፈቃደኛ ካልሆንሽ፣ የማትመጪ ከሆነና ስለደህንነቴ የማትጠይቂ ከሆነ ግን ነገስታትን ሰራዊትን እና ፈረሰኞችን በአንቺ ላይ እልካለሁኝ፡፡ አንቺም ‹የምን ዓይነት ነገስታት ሰራዊትና ፈረሰኞች?› የምትዬ ከሆነ የምድር አራዊት ነገስታት ሰራዊትና ፈረሰኞች ናቸው፡፡ አንቺም ‹የምን ፈረሰኞች?› የምትዪ ከሆነ የሰማይ አዕዋፍ ፈረሰኞች ናቸው የኔም ሰራዊት መናፍስት እና ጂኒዎች፣ የሌሊት ተርመስማሾች ሰራዊቶች ናቸው በመኝታሽ ላይ እንዳለሽ በቤትሽ ውስጥ የሚያንቁሽ የምድረ በዳዎቹም አራዊት በውጪ ያርዱሻል የሰማይም አዕዋፍ ከአንቺ ላይ ስጋሽን ይበሉታል፡፡› ንግስተ ሳባም የደብዳቤውን ቃል በሰማች ጊዜ አሁንም ለሁለተኛ ጊዜ እጆቿን በልብሶቿ ላይ አድርጋ ቀደደቻቸው፡፡ ሽማግሌዎችና መሳፍንቱንም ልካ ሰበሰበቻቸው እንዲህም አለቻቸው፡- ‹ንጉሱ ሰለሞን የላከልኝን አታውቁምን?› እነሱም እንዲህ ብለው መለሱ፡ ‹እኛ ንጉሰን ሰለሞንን አናውቀውም፣ ስለመንግስቱም ምንም እውቅናን አንሰጥም› አሉ፡፡ እርሷ ግን አልተረጋጋችም የእነሱንም ቃላት አልሰማችም ነገር ግን የባህሩን መርከቦች ሁሉ ልካ አስጠራችና ስጦታን እጅ መንሻን የከበሩ ድንጋዮችንም ሁሉ ጫነችባቸው፡፡ እርሷም ስድስት ሺ ወንዶችንና ሴቶች ልጆችን ወደ ሰሎምን ላከችበት እነርሱም ሁሉም የተወለዱት በአንድ ዓመት፣ በአንድ ወር በአንድ ቀን በአንድ ሰዓት ውስጥ ነበር እነርሱም ሁሉም እኩል ቁመት እኩል ውፍረት አንድ ዓይነት መልክ እና ሁሉም ሃምራዊ ቀለም ያለውን ልብስ ለብሰው ነበር፡፡ እርሷም ደብዳቤን ጽፋ ለንጉሱ ሰለሞን በእጃቸው ላከችው፡፡ ‹ከኪቶር ግንብም እስከ እስራኤል አገር ድረስም የሚወስደው የጉዞ ጊዜ ሰባት ዓመታት የሚፈጅ ነበር፣ አሁን በፀሎትህና በምልጃህ እኔ እማፀንሃለሁኝ ወደ አንተ እኔ በሦስተኛው ዓመት መጨረሻ ላይ እመጣለሁኝ፡፡

እንዲህም ሆነ በሶስተኛው ዓመት መጨረሻ ላይ ንግስት ሳባ ወደ ንጉስ ሰሎሞን መጣች፡፡ ንጉሱ ሰለሞን ንግስተ ሳባ ወደ እርሱ እንደመጣች በሰማ ጊዜ የጄሆዲያን ልጅ በናያን ወደ እርሷ ላከ፣ እርሱም ልክ ጠዋት ፀሐይ ልትወጣ ስትል እንደምታበራው የሚያበራ ነበረ፣ እንዲሁም በከዋክብቶች መካከል በውበት እንሚያበራውና እንደፀናው እንደ ውቡ ከዋክብት (ቬኑስ) ነበረ፣ እንዲሁም በፈሳሾች ዳር እንዳለው እንደ ሊሊ አበባ ነበር፡፡ ንግስት ሰባ የጄሆዲያን ልጅ በነያን ባየችበት ጊዜ ከሰረገላዋ ላይ ወረደች፡፡ የጄሆዲያ ልጅ በናያም ለእርሷ እንደሚከተለው ተናገራት ‹ከሰረገላሽ ላይ ለምን ወረድሽ?›፡፡ እርሷም መልሳ ‹አንተ ንጉሱ ሰለሞን አይደለህምን?› አለችው፡፡ እርሱም መለሰና ለእርሷ እንዲህ አላት፡ ‹እኔ ንጉሱ ሰለሞን አይደለሁም በፊቱ ከሚቆሙት አገልጋዮቹ አንዱ ነኝ እንጂ› አላት፡፡ ከዚያም ፊቷን ወደ ኋላዋ መልሳ ለመሳፍንቶቿ የሚከተለውን ምሳሌ ተናገረች፣ ‹አንበሳው ሳይታያችሁ ልጁን ካያችሁ፣ እንዲሁም ንጉሱን ሰለሞንን ሳታዩ በፊቱ የሚቆመውን ሰው ውበት ካያችሁ›፡፡ ከዚያም በናያ የጂሆይዲያ ልጅ ወደ ንጉሱ ወሰዳት፡፡ ንጉሱም ወደ እርሱ መምጣቷን ሲሰማ ተነስቶ በሚያብረቀርቀው ቤት ውስጥ ተቀመጠ፡፡ ንግስተ ሰባም ንጉሱን በሚያብረቅር ቤት ውስጥ ተቀምጦ ባየችው ጊዜ በልቧ ያሰበችውና የቆጠረችው ነገር እርሱ በውሃ ላይ እንደተቀመጠ ነበር ከዚያም ወደ እርሱ እንድታልፍ የቀሚሷን ዘርፍ ወደ ላይ ሰበሰበችው እርሱም እርሷ በእግሮቿ ላይ ፀጉር እንዳላት ተመለከተ፡፡ ንጉሱም ለእርሷ እንዲህ አላት፡- ‹ውበትሽ የሴት ውበት ነው፣ ፀጉርሽ ግን የወንድ ፀጉር ነው፣ ፀጉር ደግሞ ለወንድ ውብ ነው፣ ለሴት ግን ክብርን ያሳጣታል› የሳባ ንግስትም ለእርሱ እንዲህ በማለት መለሰችለት፣ ‹ጌታዬ ንጉሱ እኔ ለአንተ ሦስት እንቆቅልሾችን ልናገር፣ እነዚህንም አንተ ከተረጎምክልኝ አንተ ጠቢብ መሆንህን አያለሁኝ ካልተረጎምክ ደግሞ አንተ እንደሌላው ሰው ነህ›፡፡ (ሰሎሞንም ሦስቱንም እንቆቅልሾች በሙሉ መለሳቸው)፣ እርሷም አለች፡ ‹አምላክህ እግዚአብሔር ጌታው አንተን በፍትህና በፅድቅ ዙፋን መንግስት ላይ ያስቀመጠህ የተባረከ ይሁን› እርሷም ለንጉሱ መልካም ወርቅና ብርን ስጦታ ሰጠችው ንጉሱም የፈለገችውን ነገር ሁሉ ሰጣት›፡፡ በዚህ አይሁዳዊ ታሪክ ውስጥ ንግስት ሳባ ሰሎሞን እንዲፈታላት የፈለገችው እንቆቅልሽ ተጠቅሶ እንመለከታለን፡፡ ይህ ነገር በቁርአን ውስጥ ባይጠቀስም እንኳን ነገር ግን በልማዶች መጽሐፍት ሁሉ ውስጥ ተመዝግቧል፡፡ ንግስቲቱ የሚያብረቀርቀውን መተላለፊያ ከጥልቅ ውሃ መስሏት ተሳሳተች ብሎ ቁርአን ስለሚያቀርብ እና ይህም በታርገም ላይ ከቀረበው ታሪክ ጋር ሙሉ ለሙሉ የሌለ በመሆኑ አንዳንድ የመሐመዳውያን ጸሐፊዎች ዝርዝሩን በትክክል ሞልተውታል፡፡ ለምሳሌም ያህል በአራይሱል ማጃሊስ (ገፅ 438) የሚከተለውን እናነባለን፡ ‹በውስጡ ወደ ሰሎሞን እንድታልፍ እግሯን ገለጠች፤ ከዚያም ሰሎምን ያዛት እነሆም እርሷ በቅልጥሟና በእግሯ ከሴቶች ሁሉ ውብ ነበረች ቅልጥሟ ፀጉራም ከመሆኑ በስተቀር፡፡ ስለዚህም ሰሎሞን ይህንን ባየ ጊዜ እንዳትገልጠው ለማድረግ፡ ‹በእውነት ይህ ቤተመንግስት ነው በብርጭቆ (በመስታዎት) የተሰራ›› በማለት ወደ እርሷ ጮኸና ተጣራ፡፡

የእብነ መረድ መስታዎት መተላለፊያ መጠቀስ ግን በ1ነገስት 7.23 ላይ ከተጠቀሰው ከቀለጠው ናስ የተሰራው ኩሬ ጋር የተምታታ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ሌሎቹ ሁሉም አስደናቂ ነገሮች የሚመስሉት የአይሁዶች የሐሳብ ፈጠራዎች እንደሆኑ ነው፡፡ የአይሁድ የተረት ጽሑፍ እጅግ በጣም አስደናቂና ማራኪ ነበርና ለመሐመድ እጅግ አስደንቆት ስለነበር እጅግ በጣም እውነት ነው ብሎ ተቀብሎት ነበር፡፡ ነገር ግን ከተጠቀሱት ክስተቶች አንዳንዶቹ ከሌሎቹ ሙሉ ሆነው ሊገለጡ ይቻል ነበር፡፡ ለምሳሌም ያህል (እስከ አሁን ድረስ በምስራቅ በጣም የሚገኘው) ሐሳብ ሰሎሞን በተለያዩ ርኩሳን (ክፉ) መናፍስት ላይ ገዝቷል የሚለው ሐሳብ ከአይሁድ የተወሰደ ነው ይህም በመክብብ 2.8 ላይ በዕብራይስጥ ‹ሺቫ ቨሹኦት› የሚሉት ቃላት የተሳሳተ ግንዛቤ ነው፡፡ እነዚህ ቃላት ምናልባትም ‹የሴትና የሴቶች› የሚሉ ይሆናሉ፡፡ በሌላ በየትኛውም ቦታ ላይ የማይገኙትን እነዚህን ቃላት ተንታኞቹ በስህተት የተገነዘቧቸው ይመስላሉ፡፡ እናም እነሱን የተወሰኑ አጋንንት አድርገው ወሰዷቸው፡፡ ስለዚህም በአይሁድ ልማድ መጽሐፍም በቁራንም ውስጥ ሰለሞን በሰራዊቱ ውስጥ የተወሰኑ ዓይነት መናፍስት ያለው ተደርጎ ተቆጠረ፡፡ በአረቢያን ሌሊት ላይ ያለው የነጋዴውና የጂኒው ታሪክ የዚህ እምነት ሌላው ክስተት ነው፡፡ የቁራኑ ታሪክ ምንጭ ምን (ከየት) እንደሆነ የሚታወቅ ቢሆንም፡፡ የዚያ አስደናቂ መጽሐፍ ጸሐፊ ታሪክ ተራኪ አድርጎ መሐመድን መስራት አስገራሚ ነገር ነው፡፡ ይሁን እንጂ በቀላሉ በማመን መሐመድ ያለምንም ጥርጥር ተቀናቃኙን አጥልቶበታል ምክንያቱም ኋለኛው የራሱን አስደናቂ ታሪኮች እንደሚያምንባቸው ሊገመት አይቻልምና ወይንም ደግሞ ከላይ ተቀብያቸዋለሁ ማለትም አይችልምና፡፡

የዚህ ታሪክ አጠቃላይ ትረካ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሰጠው በ1ነገስት 10.1-10 ላይ ነው (እንዲሁም ደግሞ በ2 ዜና 19.1-9 ላይ ተደግሟል)፣ በእነዚህም ክፍሎች ላይ ስለ ሰሎሞን፣ ስለ ጂኒዎችም እና ስለ ኢፍሪቲዎች እና ስለ አንፀባራቂው ቤተመንግስትም ምንም አስደናቂ ነገር አልተነገረንም፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የቀረበው በጣም ቀላል ትረካ ሲሆን፣ ንግስተ ሳባ ከአረቢያ የታወቀ ክፍል በመምጣት ንጉሱን ሰሎሞንን የመጎብኘቷ ታሪክ ብቻ ነው፡፡

የሳባም ንግሥት በእግዚአብሔር ስም የወጣለትን የሰሎሞንን ዝና በሰማች ጊዜ በእንቆቅልሽ ትፈትነው ዘንድ መጣች። በግመሎችም ላይ ሽቱና እጅግ ብዙ ወርቅ የከበረም ዕንቍ አስጭና ከታላቅ ጓዝ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም ገባች፤ ወደ ሰሎሞንም በመጣች ጊዜ በልብዋ ያለውን ሁሉ አጫወተችው። ሰሎሞንም የጠየቀችውን ሁሉ ፈታላት፤ ሊፈታላት ያልቻለውና ከንጉሡ የተሰወረ ነገር አልነበረም። የሳባም ንግሥት የሰሎሞንን ጥበብ ሁሉ፥ ሠርቶትም የነበረውን ቤት፥ የማዕዱንም መብል፥ የብላቴኖቹንም አቀማመጥ፥ የሎሌዎቹንም አሠራር አለባበሳቸውንም፥ ጠጅ አሳላፊዎቹንም፥ በእግዚአብሔርም ቤት የሚያሳርገውን መሥዋዕት ባየች ጊዜ ነፍስ አልቀረላትም። ንጉሡንም አለችው። ስለ ነገርህና ስለ ጥበብህ በአገሬ ሳለሁ የሰማሁት ዝና እውነት ነው። እኔም መጥቼ በዓይኔ እስካይ ድረስ የነገሩኝን አላመንሁም ነበር፤ እነሆም፥ እኩሌታውን አልነገሩኝም ነበር፤ ጥበብህና ሥራህ ከሰማሁት ዝና ይበልጣል። በፊትህ ሁልጊዜ የሚቆሙ ጥበብህንም የሚሰሙ ሰዎችህና እነዚህ ባሪያዎችህ ምስጉኖች ናቸው። አንተን የወደደ፥ በእስራኤልም ዙፋን ያስቀመጠህ አምላክህ እግዚአብሔር የተባረከ ይሁን፤ እግዚአብሔር እስራኤልን ለዘላለም ወድዶታልና ስለዚህ ጽድቅና ፍርድ ታደርግ ዘንድ ንጉሥ አድርጎ አስነሣህ። ለንጉሡም መቶ ሀያ መክሊት ወርቅ እጅግም ብዙ ሽቱ የከበረም ዕንቍ ሰጠችው፤ የሳባ ንግሥት ለንጉሡ ለሰሎሞን እንደ ሰጠችው ያለ የሽቱ ብዛት ከዚያ ወዲያ አልመጣም ነበር።› 1ነገስት 10.1-10›፡፡

ምንም እንኳን በቁርአን ውስጥ ያሉት ብዙዎቹ ታሪኮች ከአይሁድ ተረቶች የተወሰዱ ቢሆንም አሁን በዚህ ቦታ ላይ ሁሉንም በሙሉ መጥቀስ አስፈላጊ አይደለም፡፡ በሁሉም ሁኔታዎች ውስጥ መሐመድ በብሉይ ኪዳን ላይ ስለተጠቀሱት ነቢያት እውነተኛ ታሪክ በተመለከተ ምንም የማያውቅ ይመስላል፡፡ ይህም ያለምንም ጥርጥር የአረቢያ አይሁዶች ያልተማሩና ከመጽሐፍ ቅዱስ ይልቅ ከታልሙድ ተረት ጋር በጣም የሚተዋወቁ መሆናቸውን ያሳያል፡፡ በጣም ጠቃሚ ወደ ሆኑት ጉዳዮች ከመሸጋገራችን በፊት ግን የሃሩትና የማሩትን ታሪክ መመልከት ይኖርብናል፡፡ እነርሱም በባቢሎን ኃጢአት ያደረጉት ሁለቱ መላእክት ናቸው፡፡ ይህም ተረት በጣም አስደሳች ነው፣ የመጀመሪያ ምንጩንም በመጀመሪያ ከአይሁድ የመጀመሪያ ምንጭ ላይ ስናገኘው፣ ከድብልቅ ምንጭ የመጣ መሆኑን ለማሳየት እንችላለን ማለት ነው፡፡ በቅድሚያም የምንጠቅሰው በቁርአንና በልማድ ውስጥ የተጠቀሰውን እንዳለ ነው፣ በመቀጠልም ከአይሁድና ከሌሎች አፈታሪኮች ውስጥ ያለውንና የመጣበትን እናሳያለን፡፡

 4. የሐሩትና ማሩት ታሪክ

በቁርአን ውስጥ ሃሩትንና ማሩትን በተመለከተ እንደሚከተለው ተጽፏል፡-

‹ሰይጣናትም በሱለማይን (ሰሎሞን) ዘመነ መንግስት የሚያምኑበትን (ድግምት) ተከተሉ ሱለማይንም አልካደም (ድግምተኛ አልነበረም) ግን ሰይጣናት ሰዎችን ድግምትን የሚያስተምሩ ሲኾኑ ካዱ ያንንም በባቢል በሁለቱ መላእክት በሃሩትና ማሩት ላይ የተወረደውን ነገር (ያስተምሩዋቸዋል)፡- እኛ መፈተኛ ነንና አትካድ እስከሚሉም ድረስ አንድንድም አያስተምሩም ከርሱም በሰውየውና በሚስቱ መካከል በርሱ የሚለዩበትን ነገር ይማራሉ እነርሱም በአላህ ፈቃድ ካልሆነ በርሱ አንድንም ጎጂዎች አይደሉም የሚጎዳቸውንና የማይጠቅማቸውንም ይማራሉ የገዛውም ሰው ለርሱ በመጨረሻይቱ አገር ምንም ዕድል የሌለው መኾኑን በእርግጥ ዐወቁ ነፍሶቻቸውንም በርሱ የሸጡበት ዋጋ ከፋ የሚያውቁ በኾኑ ኖሮ (ባልሠሩት ነበር)፡፡› ቁርአን 2.102፡፡

‹በአራይሱል ማጃሊስ› ደግሞ የሚከተለውን ታሪክ እናገኛለን፣ ይህንን ጥቅስ በማብራራት በኩል በልማድ ስልጣን ላይ የተነገረ ነው፡ ‹ተንታኞቹ ያሉት መላእክቱ የሰዎችን ልጆች ክፉ ስራዎች ባዩ ጊዜ ወደ ሰማይ ያረገውን ስራ በነቢዩ ኢድሪስ ጊዜ ስለዚያ ገስፀዋቸው፣ ነቀፏቸውና እንደሚከተለው ተናገሩ፡- ‹እነዚህ ናቸው አንተ የምድር ገዢዎች አድርገህ የሰራሃቸው እንዲሁም አንተ የመረጥሃቸው ነገር ግን አንተን በደሉህ› ስለዚህም ታላቁ እግዚአብሔር እንዲህ አለ ‹እኔ እናንተን ወደ ምድር ያልላክኋችሁ ቢሆን ኖሮ በናንተም ውስጥ በእነሱ ውስጥ ያስቀመጥኩትን ባላስቀመጥኩ ኖሮ እነሱ እንዳደረጉት ሁሉ እናንተም ታደርጉ ነበር›፡፡ እነሱም ‹ይህን እግዚአብሔር ያርቀው፣ ኦ አንተ አምላካችን ነህ ይህን በአንተ ላይ ማድረግ ለእኛ አይገባንም አሉ፡፡› ታላቁ እግዚአብሔርም እንዲህ አለ፡ ‹ከእናንተም መካከል በጣም ጥሩ የሆኑትን ሁለት መላእክት ምረጡ እኔም ሁለቱንም ወደ ምድር እልካቸዋለሁኝ› ከዚህም የተነሳ ከመላእክት መካከል በጣም ትጉና በጣም ጥሩ የነበሩትን ሃሩትንና ማሩትን መረጡ፡፡› አል-ካሊቢም እንዲህ አለ፣ ‹ታላቁ እግዚአብሔር እንዲህ አለ፡- ‹‹ከእናንተ መካከል ሦስትን ምረጡ›› ስለዚህም እነርሱ ‹አዝንን› ማለትም ሃሩትን እና ‹አዛቢንን› ማሩትንና ‹አዘራልን› መረጡ፡፡ በእርግጥም እነሱ በበደል ውስጥ በተገኙ ጊዜ የእነዚህን የሁለቱን ስም ቀየረው፣ ይህም እግዚአብሔር ‹የኢብሊስን› ስም ‹ከአዛዚል› እንደቀየረው ነው፡፡ እግዚአብሔርም በሰዎች ልጆች ውስጥ ያስቀመጠውን ፍላጎት በእነርሱ ውስጥ አስቀመጠው፡፡ ከዚያም ወደ ምድር ላካቸው እንዲሁም በሰዎች መካከል ትክክለኛ ፍርድን እንዲፈርዱ አዘዛቸው፣ ብዙ አማልክትን እንዳያመልኩ ከለከላቸው፣ ሰዎችንም ያላግባብ እንዳይገድሉ ከርኩሰት እንዲሁም ወይንን ከመጠጣት ሁሉ ከለከላቸው፡፡ አዘራልን በተመለከተ ግን በልቡ ውስጥ ፍላጎት ሲመጣ በእርግጥ ከጌታ ዘንድ ምህረትን ጠየቀና ወደ ሰማይ እንዲወስደው ለመነ፡፡ እርሱንም ይቅር አለውና ወደ ሰማይ ወሰደው፡፡ እርሱም ለአርባ ዓመታት አመለከው ከዚያም እራሱን ቀና አደረገና በእግዚአብሔር ፊት በሐፍረት እራሱን መድፋቱን አቆመ፡፡ ሁለቱን በተመለከተ ግን በእውነት እነሱ በምድር እንደነበሩ ቀሩ፡፡ እነርሱም ቀን በሆነ ጊዜ በሰዎች መካከል ይፈርዱ ነበር በምሽትም ጊዜ ደግሞ የታላቁን እግዚአብሔርን ስም ይደጋግሙ እና ወደ ሰማይ ይወጡ ነበር፡፡ ‹ካታዳ› እንዳለው፡ ‹አንድ ቀን ‹ዙራ› እጅግ በጣም ውብ ከሆኑት ሴቶች መካከል አንዷ ሙግትን ወደ እነርሱ አምጥታ በፈተና ከመውደቃቸው በፊት አንድ ወር እንኳን አልሞላቸውም ነበር፡፡ አሊ እንደተናገረው እርሷ ከፋርስ ሰዎች ነበረች በራሷም አገር ውስጥ ንግስት ነበረች፡፡ እነሱም ባዩአት ጊዜ የሁለቱንም ልብ ማረከችው፡፡ ከዚያም እነርሱ እርሷን ለራሳቸው ጠየቋት፡፡ እርሷም እምቢ ብላ ሄደች፡፡ ከዚያም በሁለተኛው ቀን ተመለሰች እነርሱም እንደበፊቱ አደረጉ፡፡ እርሷም እንዲህ አለች ‹እናንተ እኔ የማመልከውን ካላመለካችሁና ለዚህ ጣዖት ካልፀለያችሁ ካልገደላችሁና ወይንን ካልጠጣችሁ አይሆንም› አለቻቸው፡፡ እነሱ ሁለቱም ‹እኛ እነዚህን ነገሮች እንዳናደርግ እግዚአብሔር ስለከለከለን፣ በፍፁም ልናደርጋቸው አንችልም አሉ›፡፡ ከዚያም በኋላ እርሷ ሄደች፡፡ ከዚያም በሦስተኛው ቀን ተመለሰች፣ ያኔም ከወይን ጠጇ ጋር ነበረች እርሷም ለእነርሱ የምትስብ ሆና እራሷን አቀረበችላቸው፣ እነሱም እራሷን ለእነርሱ ጠየቋት፡፡ እርሷም እምቢ አለችና ባለፈው ቀን የጠየቀችውን እንደገና ጠየቀቻቸው፡፡ ከዚያም እነርሱ እንዲህ አሉ፡ ‹ከእግዚአብሔር ውጪ የሆነውን ነገር ማምለክ በጣም አስፈሪ ነገር ነው፣ መግደልም ደግሞ አስፈሪ ነገር ነው፣ ከእነዚህም ውስጥ ቀላሉ ወይን ጠጅን መጠጣት ነው›፡፡ ከዚያም የወይኑን ጠጅ ጠጡ እነርሱም ሰከሩና በሴትየዋ ላይ በኃጢአት ወደቁ፣ አንድ ሰውም አያቸው እርሱንም ገደሉት›፡፡ ‹ካሊቢ ቢን አናስ› እንደሚከተለው ተናገረ፡ ‹እነርሱም ጣዖትን አመለኩ፡፡ ከዚያም እግዚአብሔር ዙራን ወደ ከዋክብትነት ለወጠው›፡፡ ‹አሊና ሳዲ› ደግሞ ያሉት ነገር እርሷ፡ ‹እናንተ ወደ ሰማይ የወጣችሁበትን ምክንያት ካልነገራችሁኝ በስተቀር እኔን ልታገኙኝ አትችሉም አለቻቸው› እነርሱም፡ ‹እኛ ወደ ሰማይ የወጣነው በታላቁ በእግዚአብሔር ስም ነው አሏት›፡፡ ከዚያም እርሷ ደግሞ፡ ‹ይህንን ለእኔ ካላስተማራችሁኝ በስተቀር እኔን ልታገኙኝ አትችሉም አለች›፡፡ ከሁለቱም አንደኛው ለሌላው እንዲህ አለው ‹አስተምራት›፡፡ እርሱም ‹በእውነት እግዚአብሔርን እፈራለሁኝ አለ› ከዚያም ሌላው እንደሚከተለው ተናገረ ‹የታላቁ እግዚአብሔር ምህረት ታዲያ የት ነው ያለው?› አለው፡፡ ከዚያም እነርሱ ለእርሷ አስተማሯት፡፡ ከዚህም የተነሳ እርሷ ተናገረችውና ወደ ሰማይ ተወሰደች እግዚአብሔርም እርሷን ወደ ከዋክብትነት ቀየራት›፡፡ ዙራህ የሚለው ስም ለፕላኔት ቬነስ የተሰጠ የአረብኛ ስም ነው፡፡ ለዚህ ታሪክ ልዩ ልዩ ሁኔታዎች የሚጠቀሱት ወሳኝ የማገናዘቢያ ጽሑፎች ሁሉ በሙስሊሞች ዘንድ በአጠቃላይ ተቀባይነት ያላቸው ለመሆኑ በትክክል ያረጋግጣል፡፡ በእነሱም ዘንድ ይህ ከነቢያቸው አንደበት እንደመጣ በልማድ ተቀባይነት አለው፡፡ ይሁን እንጂ ምንም ሌላ ተጨማሪ ማስረጃ ባይኖረንም እንኳን ከአይሁድ የመነጨ መሆኑን የሚያሳዩ እጅግ በጣም ብዙ ነጥቦች አሉን፡፡ ከእነዚህም ሐሳቦች ውስጥ አንዱ የእግዚአብሔርን ልዩ ስም ‹ቴትራግራማቶን› ወይንም ‹አራቱ ፊደል ስም› የሚያውቅ ማንም የለም፣ ስሙም ‹ሊነገር የማይቻለው ስም› ነው፣ ሲጠራ ግን ትልቅ ነገርን ያደርጋል የሚለው አባባል ነው፡፡ ይህ አባባልና እምነት በጥንት ጊዜ በነበሩት የአይሁድ ጸሐፊዎች ዘንድ በጣም የታወቀ ነው፡፡ እንደገናም ደግሞ አዝራኤል የሚለው የመልአኩ ስም የአረብኛ ሳይሆን የዕብራውያንን ስም መያዙ ሌላው ማስረጃ ይሆናል፡፡

ሆኖም ግን ይህ ተረት በቀጥታ አከይሁድ የመነጨ ለመሆኑ እኛ ቀጥተኛ ማስረጃ አለን፡፡ እርሱም ያለው ‹በሚድራሽ ያልኩት› ምዕራፍ 44 በሚገኙትና በሚከተሉት ጥቅሶች ውስጥ ነው፡-

‹ራብ ዮሴፍን ደቀመዛምርቱ እንደሚከተለው ጠየቁት፣ ‹አዛኤል ማነው?› እርሱም ለእነርሱ እንዲህ አላቸው ‹በጥፋት ውሃ ጊዜ የነበሩት ትውልድ ከንቱ አምልኮን ባቀረቡበት ጊዜ ‹የጣዖት አምልኮን›፣ ቅዱሱ፣ ብሩክ ይሁንና! ተቆጥቶ ነበር፡፡ በቅፅበትም ሁለት መልአኮች ተነሱ እነርሱም ‹ሸምሃዛይ› እና ‹አዛኤል› ናቸው፡፡ በፊቱም እንዲህ አሉ፣ ‹‹ኦ የዓለማት ጌታ በፊትህ እንዲህ ብለን አልነበረምን አንተ ዓለምህን ስትፈጥር፣ ‹ታስበው ዘንድ ሰው ምንድነው?› መዝሙር 8.4፡፡ እርሱም እንዲህ አላቸው፣ ‹ዓለምን በተመለከተ ምን ትሆናለች?› እነርሱም እንዲህ አሉት፡ ‹ኦ ጌታ ሆይ ዓለምን እኛ እንገዛታለን› እርሱም ለእነሱ እንዲህ አላቸው ‹ለእኔ የታወቀኝና ግልጥ የሆነው እናንተ ዓለምን ብትገዙ ክፉ ምኞት ይገዛችኋል እናንተም ከሰዎች ልጆች የበለጠ ግትሮች ትሆናላችሁ› ከዚያም ለእርሱ እንዲህ አሉት ‹ፈቃድን ስጠን ከፍጡራን ጋር እንኖራለን እንዲሁም እኛ እንዴት ስምህን እንደምንቀድስ ታያለህ›፡፡ እርሱም ለእነርሱ አላቸው ‹ውረዱና ከእነርሱ ጋር ኑሩ›፡፡ በአንድ ጊዜም ሸምሃዛይ ስሟ አስቴር የተባለች አንዲት ልጃገረድን አየ፡፡ እርሱም ዓይኑን በእርሷ ላይ ጣለ፡ እንዲህም አለ፣ ‹ለእኔ ደስታ ሁኚኝ› አላት፡፡ እርሷም ‹አንተ ደጋግመህ በምትጠራበት ሰዓት እሱን ተጠቅመህ ወደ ሰማይ የምትወጣበትን ልዩ የሆነውን የእግዚአብሔርን ስም ካላስተማርከኝ በስተቀር ጥያቄህን አልሰማህም› አለችው፡፡ እርሱም ለእርሷ የእግዚአብሔርን ልዩ ስም አስተማራት፡፡ እርሷም ደጋገመችው ከዚያም ወደ ሰማይ መውጣትን ቻለች ሆኖም ትሁት አልነበረችም፡፡ ቅዱሱም፣ በረከት በእርሱ ላይ ይሁንና እንዲህ አለ፡- ‹እርሷ እራሷን ከበደለኝነት ስለለየች ሂዱና ከሰባቱ ከዋክብት መካከል አስቀምጧት አለ ያም እርሷን በተመለከተ እናንተ ለዘላለም ንፁሃን እንድትሆኑ ነው› ከዚያም እርሷ በከዋክብቱ ክምችት መካከል ተቀመጠች፡፡ እነርሱም በቅፅበት እራሳቸውን ውብ ከሆኑት ከሰዎች ሴቶች ልጆች ጋር አዋረዱ እንዲሁም ምኞታቸውን ለማርካት አልቻሉም፡፡ እነርሱም ተነሱና ሚስቶችን ለራሳቸው አደረጉ ሂዋንና ሂያን የተባሉትንም ልጆችን ወለዱ፡፡ እንዲሁም ኣዛኤል የተለያዩ ጌጣ ጌጦች እንዲሁም የሴቶች ማጋገጫዎችን የመስራት ሙያ ነበረው ይህም ወንዶች ለበደለኛነት ሐሳብ ጉጉት (ፍላጎት) ያደረባቸው እንዲሆኑ አደረጋቸው፡፡

በዚህ በመጨረሻው አረፍተ ነገር ስለተነገረው በኋላ የምንመለስበት ይሆናል፡፡ የሚድራሹ አዛኤል የመሐመዳውያኑ አፈታሪክ አዝራኤል መሆኑን ግን ግንዛቤ ሊያገኝ ይገባዋል፡፡

የመሐመዳውያን አፈታሪክ ከአይሁድ አፈታሪክ የመጣ መሆኑን ካልተገነዘብን በስተቀር ሁለቱን ለማወዳደር ለማናችንም የማይቻል ይሆንብናል፡፡ አመጣጡም ቃል በቃል ሳይሆን በአፍ የተነገረው በቃል ተዛምዶ ነው፡፡ ይሁን እንጂ አንዳንድ አስደናቂ ነገሮች ከመሐመዳውያን ተረት ውስጥ ይገኛሉ ይህንንም የሚከተለውን ጥያቄ አንስተን ስንመረምር እንገነዘበዋለን፡፡ ጥያቄውም ‹አይሁዶች እራሳቸው ይህንን ታሪክ ከየት ነው የተማሩት?› የሚለው ነው፡፡ ከእነዚህ ነጥቦች አንዱ ሃሩትና ማሩት የሚሉት የመላእክቶቹ ስሞች ምንጭ ነው፡፡

እነዚህ ሁለቱ መላእክት በመጀመሪያ ሌላ ስም እንዳላቸው ተነግሯል፣ ይጠሩ የነበረውም ‹አዝ› እና ‹አዛቢ› ተብለው ነበር የኋለኞቹ ስሞች የተሰሩት ለዕብራውያንም ለአረቦችም የጋራ ከሆኑት ስሞች ነው፡፡ ‹በሚድራሽ ያልኩት› ጽሑፍ ውስጥ ግን ኃጢአትን የሰሩት መላእክት የተጠሩት ‹ሸምሃዛይ› እና ‹አዛኤል› ተብለው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የአረብኛው ተረት የሚለው ‹አዝራኤል› ወደ መሬት ቢወርድም እንኳን ከሃሩትና ከማሩትን ጋር እንደሦስተኛ የቡድኑ አባል ሆኖ ነው፡፡ እርሱም ከዚያ በኋላ ምንም ኃጢአትን ሳይሰራ ወደሰማይ እንደተመለሰ ነው፡፡ እርሱም አሁን በሙስሊሞች ዘንድ የሚታወቀው እንደ ሞት መልአክ ነው፣ ይህም በአይሁዶች መካከል ‹ሳማኤል› የተባለው መልአክ የሚጫወተውን ሚና ነው፡፡ የአረቦቹ ልማድ ሃሩትና ማሩት የሚለው ስም በኃጢአት እስከወደቁ ድረስ ለመላእክቱ እንዳልተሰጣቸው ይናገራል፡፡ የዚህ ስም ትርጉም ውስጥ ያለው ግልጥ የሚሆነው ስሞቹ የጥንታዊ የአርሜኒያንስ አማልክት ስም መሆኑን ስናገኝ ነው፡፡ አርሜኒያኖች በሦስተኛውና በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ወደ ክርስትና ከመምጣታቸው በፊት እነርሱን ያመልኳቸው ነበር፡፡ በአርሜኒያኖችም ዘንድ እነርሱ ይጠሩ የነበሩት ‹ሆሮት› እና ‹ሞሮት› ተብለው ነበር፡፡ እንዲሁም በዘመናዊ የአርሜኒያን ጸሐፊዎች በጥንታዊው የአገሪቱ የአምልኮ አፈታሪክ ውስጥ የዚያ ታሪክ ክፍል ሚና እንደነበረው ተጠቅሷል ይህም በሚከተሉት ቃላት ውስጥ ይገኛል፡-

‹ከአማልክቶቹ ረዳቶች መካከል ‹ስፓንዳራሚት› ያለምንም ጥርጥር ‹ሖሮት› እና ‹ሞሮት› ነበሩ፣ እነርሱም የማሲስ ተራራ (አራራት) እና አምናቤግ ሰዋዊ አማልክት ነበሩ እንዲሁም ምናልባትም ለእኛ አሁንም ያልታወቁ ሌሎች አማልክትም ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እነርሱም የምድሪቱ ምርታማነት እና አትራፊነት ልዩ አራማጆች ነበሩ፡፡

የአርሜኒያኑ ስፓንዳራሚት የአቨስቲክ ሰፔንታ አርማይቲ ናት፣ የሴት የመላእክት አለቃ በምድር ላይ የምትኖርና የደግ ሴቶች ጠባቂ ናት፡፡ ሆሮት እና ሞሮት በአቬስታ የቀረቡት እንደ ሆርቫት (ወይንም ቦርቫታት) እና አሚርታት ‹መትረፍረፍ› እና ‹ዘላለማዊነት› ሆነውና የአምሻስፓንዶች (አመሸ-ስፒንታዎች፣ ‹የዘላለማዊያን ቆንጆዎች›) ተብለው ነው፡፡ እነርሱም የአሁሮ ማዘዳኦ (ኦረማዝድ) የመልካም ነገሮች ሁሉ ፈጣሪው አጋዦችና አገልጋዮች ናቸው፡፡ በአቨስታ ውስጥ ሆረቫታት እና አመርታት የማይለዩ አጋዦች ናቸው ይህም ሆሮትና ሞሮት በአርሜኒያኑ አፈታሪክ ውስጥ እንዳሉት ነው፡፡ ሁለተኛው በአትክልት ዓለም ሁሉ ላይ ገዥ ሆኗል፡፡ በኋለኛው የፔርሺያን ስም ውስጥ ስሞች ቀስ በቀስ ወደ ኩርዳድ እና ሙርዳድ ተለውጠዋል፣ እዚህም መልካም ጂኒዎች ስሞቻቸውን ለሦስተኛውና ለአራተኛው የዓመቱ ወራት ሰጥተዋል፡፡ ቃላቶቹም ሙሉ ለሙሉ ከአሪያን የመነጩ ናቸው እናም በሳንስክሪት (ሳርቫታ እና አምሪታ የመጀመሪያው በሪግ ቭዳ ውስጥ የሚገኘው በሳረቫታቲ መልክ ነው) ይሁን እንጂ አፈታሪኩ የሚናገረው ስለ ሕልውናዎች አይደለም፡፡ የአሪያኑ አፈታሪክ እነዚህን አማልክት የሚያቀርባቸው ለምድር ምርታማነትን እንደሚሰጡ አድርጎ ሲሆን እንደ ስፐንታ አርማይቲ ስብዕና ሰጥቷቸዋል፣ በማንኛውም ፍሬያማነት ላይ እንዳሉ አድርገውም ያቀርባቸዋል፡፡ በመሐመዳውያን አፈታሪክ መሠረት እነርሱም ቅዱሳን የነበሩና ወደ ምድር የወረዱትም በኦርማዝድ ትዕዛዝ አማካኝነት ነው፡፡ ነገር ግን የእነሱ ተልዕኮ ትግበራ ከምንም የኃጢአት ሐሳብ ጋር ያልተያያዘ ነበር፡፡ መሐመድ ወይንም ታሪኩን ለእርሱ የነገረው ሰው፣ ስማቸውን ከጥንት የአርሜኒያና የፐርሺያ አፈታሪክ ከተበደረ በኋላ እነርሱን ያዛመዳቸው በአይሁድ አፈታሪክ ከተጠቀሱት ከሁለቱ ኃጢአት ካደረጉት መላእክት ጋር ነው፡፡ በጊዜውም እንደምንመለከተው ከፐርሺያና ከአይሁድ ምንጮች ውስጥ መሐመድ የወሰደው ትንሽ ነገርን አይደለም፡፡ በሁለቱም መካከል ብቁ የሆነ መመሳሰል ይገኛል፤ ምንም እንኳን ሁለቱም የተለያየ ምንጭ ቢኖራቸው እርሱ ግን እንደ አንድና ተመሳሳይ አድርጎ አይቷቸዋል፡፡ ስለዚህም በአሪያን አስገራሚ ክስተት ትዕይንት ውስጥ እንደ ዋና ተዋናይነት የተጠቀሱት ሁለት ጂኒዎች ከታልሙድ (ከአይሁዱ) ዋና ሐሳብ ውስጥ የተወሰዱ ናቸው፡፡

ከአይሁድ ታሪክ የተጠቀሰችው ልጅ አስቴር የባቢሎናውያን ሴት አምላክ ‹ኢስታር› ናት፣ በፓለስታይን እና በሶርያ አስታሮት ተብላ ትመለካለች፡፡ ኢስታር የፍቅርና የኃጢአት ፍላጎት ወይንም ስሜት አምላክ ስትሆን በሮማውያንና በግሪኮችም አፍሮዳይት እና ቬነስ በመባል በቅደም ተከተል ትታወቃለች፡፡ እርሷም ዙህራህ ከተባለው ከፕላኔት ቬነስ ጋር በአረቦች ዘንድ ተጠቅሳ ነበር፡፡ በግልፅ እንደሚታየው ሁሉ በአረቢያንና በአይሁዶቹ ተረቶች መካከል ያለው ልዩነት የጊዜ ጉዳይ አይደለም፣ የአፈታሪኩ ሰው ስብዕና ሆኖ የተጠቀሰው ግን አንድና ተመሳሳይ ሰው እውነታ ነው፡፡

በባሊኖናውያንና በአሶራውያን አፈታሪክ ውስጥ ኢስታር ምን ጠቃሚ ሚና እንደምትጫወት በጣም የታወቀ ነገር ነው፡፡ ከብዙ ድብቅ ፍቅሮቿ ተረት ውስጥ አንዱ እዚህ ጋ መተርጎም አለበት፣ ምክንያቱም በከፊል የኃጢአተኛ መላእክትን ታሪክ ምንጭ ይናገራልና እንዲሁም ደግሞ ዙህራህ ወይንም አስቴር ወደ ሰማይ ለመውጣት እንድትችል መደረጓንና እንደወጣችም ይገልጥልናልና፡፡

በባሊሎናውያን አፈታሪክ ውስጥ የተነገረን ነገር ኢስታር ጊልጋሜሽ የሚባልን ጀግና እንዳፈቀረችና እርሱም የእርሷን ግስገሳ እንደተቃወመ ነው፡ ‹ጊልጋሜሽ ዘውዱን በራሱ ላይ ጫነ፡፡ ከዚያም ጊልጋሜሽን ወደ ራሷ ለመሳብ እና ተወዳጅነትን ከእርሱ ዘንድ ለማግኘት ብላ ሴቷ አምላክ ኢስታር ለእርሱ እንዲህ አለችው ‹ሳመኝ ጊልጋሜሽ! አንተ የኔ ሙሽራ አይደለህምን ያንተንም ፍሬ እንደ ስጦታ ስጠኝ፡፡ ከዚያም የእኔ ባል ትሆናህ እኔም የአንተ ሚስት እሆናለሁኝ፡፡ ከዚያም አንተ በላፒስ ላዙሊ ሰረገላ ላይ ትነዳለህ በወርቅ ሰረገላ ጎማዎቹ ከወርቅ ከተሰሩት መሽከርከሪያዎቹም ከአልማዝ ከሆኑት፡፡ ከዚያም አንተ በየዕለቱ ታላላቆቹን በቅሎዎች ትጠምዳለህ ከዝግባ እንጨት ሽቶ ጋር ወዳለው ወደ ቤታችን ግባ፡፡›

ነገር ግን ጊልጋሜሽ እርሷን እንደሚስቱ መቀበልን ተቃውሞና እርሷ ብዙ ባሎች እንደነበራትና ፍፃሜያቸውም መጥፎ እንዳደረገች ጠቅሶ እንቢ ባላት ጊዜ ተረቱ እንደሚቀጥለው ቀጥሏል፡-

‹ሴቷ አምላክ ኢስታረ በጣም ተናደደችና ወደ ሰማይ ወጣች ከዚያም አኑ በተባለው አምላክ ፊት ቀረበች፡፡ አኑ በሰማይና የሰማይ አምላክ ነበር በባቢሎናውያን የጥንት አፈታሪክ ኢስታርም የእርሱ ሴት ልጅ ነበረች፡፡ እዚህም የምንመለከተው የእርሷ ወደሰማይ መውጣት፣ በመሐመዳውያኑ እንደተጠቀሰው ሆኖ ቀርቧል፡፡ በኋለኛው ግን እርሷ መልአኩን ኃጢአት እንዲሰራ እንደፈተነችው ተደርጎ ቀርባለች ይህም በባቢሎናውያን ዘንድ እርሷ ጊልጋሜሽን ፈትናለች ተብሎ ተተርኳል፡፡

በሳንስከሪት ጽሑፍ ውስጥ ደግሞ በቁርአንና በልማድ ውስጥ እንዳለው ያለ አስደናቂ ትይዩ የሆነ ታሪክን እናገኛለን፡፡ ይህም ‹በማሃባራታ‹ ያለው ‹የሱንዳና የኡፓሱንዳ› ታሪክ ነው፡፡ በዚያም የተነገረን ነገር ከዕለታት አንድ ቀን ሁለት ወንድማማቾች ሱንዳና ኡፓሱንዳ የተባሉት ለእራሳቸው በመጨረሻ በምድርና በሰማይ ላይ ከሁሉ በላይ ስልጣንን ለማግኘት ያስችላቸው ዘንድ ከፍተኛ ችግርን ይለማመዱ ነበር፡፡ ከዚያም የብራህማ አምላክ በዚህ ሁኔታ ግዛቶቹን እንደሚያጣ መፍራት ጀመረ፡፡ ይህንንም ለማቆም እነዚህን ሁለት ጠላቶቹን ለማጥፋት ወሰነ፡፡ ለዚህም የተጠቀመበት ዘዴ ከገነት ውስጥ ካሉት ሰራተኞች ወደ እነርሱ በመላክ መፈተን ነበር፣ መልእክተኞቹም ‹ሁሪስ› ተብለው ይታወቃሉ በመሐመዳውያንና በጥንታዊ ሒንዱዎች ደግሞ ‹አፕሳራሳስ› ይባላሉ፡፡ ስለዚህም እርሱ እጅግ በጣም ተወዳጅ የሆነን ‹አፕሳራስ ቲሎታማ› የምትባለውን ፈጠረ ይህም እርሱ እንደ ስጦታ ወደ ወንድማማቾቹ ላካት፡፡ እርሷንም በማየት ‹ሱንዳ› የቀኝ እጇን ያዘ ‹ኡፓሱንዳ› ደግሞ የግራ እጇን ያዘ፣ ሁለቱም እርስዋን የራሱ ሚስት ለማድረግ ፈለገ፡፡ ቅናትም በወንድማማቾቹ ልብ ውስጥ ጠላትነትን አፈለቀ ውጤቱም እርስ በእርስ መገዳደላቸውን አመጣ፡፡ ‹ቲሎታማም› ከዚያ በኋላ ወደ ‹ብራማ› ተመለሰች፣ ሁለቱን ተቀናቃኞቹን በማጥፋቷ በእርሷ ደስ በመሰኘት ባረካትና እንደሚከተለው አላት ‹በዓለም ውስጥ ሁሉ ፀሐይ ስታበራ በዙሪያሽ ታበራለች (ታንፀባርቃለች) እንደዚሁም ማንም ሰው አንቺን ትኩር ብሎ ሊመለከትሽ አይችልም ይህም በውበትሽ አስገራሚነትና ከማንም የበለጥሽ ስለሆነ ነው›፡፡

በዚህ ተረት ውስጥ አንዲት ውብ ሴት ወደ ሰማይ መውጣቷ ተጠቅሶ እንገኛለን፣ ምንም እንኳን የሒንዱዎቹ ታሪክ ከባቢሎናውያን ቢስማማና ከመሐመዳውያን ቢለይም፣ አስፓራሳስ በሰማይ ኖሯልና አንደኛው እርሷን ከመጀመሪያው ከላይኛው ዓለም ጋር ግንኙነት እንዳላት አድርጎ አቅርቧታል፣ ሆኖም አስፓራሳስ ብዙ ጊዜ ምድርን ጎብኝቷል ኢስታርም ሴት አምላክ ነበረች፡፡ በሂንዱው ታሪክ ላይ ሁለቱ ወንድማማቾች በመጀመሪያ በምድር ላይ ነበሩ ሆኖም ግን በመጨረሻ በሰማይ ላይ ስልጣንን አግኝተዋል፡፡ በዚህም የተነሳ በአይሁድና በመሐመዳውያን ተረት ውስጥ ካሉትና በቅድሚያ ከሰማይ ወረዱ ከተባሉት መላእክት የተለዩ ናቸው፡፡  ነገር ግን በዚህም ጉዳይ ላይ እንኳን ቢሆን ልዩነቱ በጣም ጥቂት ነው፣ ምክንያቱም የሂንዱው ተረት ወንድማማቾቹን፣ ‹ዲቲ› ከምትባልና ‹የማሩትስ› ወይንም ‹የማዕበል እናት› ከምትባል ከሴት አምላክ እንደመጡ ይናገራልና፡፡ የእነዚህ የተለያዩ አፈታሪኮች መመሳሰል እጅግ አስገራሚ ነገር ነው፡፡   

በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ አገሮች ውስጥ ያለው የታሪኩ የተለያዩ ገለጣዎች ሁሉ ከአንድ ምንጭ የጀመሩ ናቸው ለማለት አንችልም፡፡ ያለምንም ጥርጥር አይሁዶች ተረቱን በከፊል የተዋሱት በተለይም በኢስታር ወይንም በአስቴር ስምና ሌሎችንም አንዳንድ ዝርዝሮችን ጨምሮ ከባቢሎናውያን ነው፣ ባቢሎናውያን ደግሞ የተማሩት ከጥንታዊ አካዲያን ነው፡፡ ከአሕዛብ የመነጨ መሆኑን በመርሳት የአይሁዱ ታልሙድ ተረቱን ተቀብሎታል፣ በአይሁዶች የስልጣን ምንጭነትም መሠረት ላይ በሙስሊሞች ቁርአንና በልማድ ውስጥ ተቀባይነትን አግኝቷል፡፡

አይሁዶች ይህንን አፈታሪክ እንዴት ተቀበሉት በማለት በተጨማሪ ብንጠይቅ መልሱ የሚሆነው እነርሱ ይህንን ያደረጉት በዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ ያለውን አንድ የዕብራይስጥ ቃልን በማሳሳት ነው፡፡ ቃሉም በዘፍጥረት 6.1-4 ላይ ያለውና ‹ኒፍሊም› የሚለው ነው፣ ይህም ናፋል ‹መውደቅ› ከሚለው ግስ እንደመጣ ተገምቶ ነው፡፡ ስለዚህም ‹ዮናታን ቤን ዑዜል› በታርገሙ ውስጥ ‹የወደቁ መላእክት› በማለት ተርጉሞታል፡፡ ይህንንም ለማድረግ የዚያን ጊዜውን የቃሉን ስር ተጠቅሟል፡፡ ስለዚህም ከስረ ቃሉ ጋር እንዲስማማ ለማድረግ ታሪኩ በአይሁዶች በከፊል እንዲፈጠር ተደረገ፡፡ እንዳየነውም ምንም ከማያውቁት አይሁዶችና በከፊል ደግሞ ከባቢሎናውያን ተረት ተወሰደ፡፡ ከዚህ በፊት እንደጠቆምነውና ለዑር የተሳሳተ የቃል ስረ አመጣጥ ተሰጥቶ አብርሃም ‹በከለዳውያን የእሳት እቶን ውስጥ ተጥሎ እንደወጣ› ከሚናገረው ተረት አካሄድ ጋር አንድ ዓይነት ነው፡፡ ስለዚህም ጆናታን በዘፍጥረት 6.4 ትንተናው ላይ  ኔፊሊምን የገለጣቸው እንደሚከተለው፡- ‹ሸምሃዛይ እና ዑዛይል፡ ከሰማይ ወርደው በዚያን ዘመን በምድር ላይ ነበሩ› በማለት ነው፡፡ በመሠረቱ ‹በሚድራሽ ያልኩት› ላይ ያለው ተረት የተገኘው ከዚህ የጅልነት ስህተት ነው፡፡  

ይሁን እንጂ፣ ‹የኔፍሊምን› የግስ አመጣጥ ‹መውደቅ› ነው ብለን ብንቀበል እንኳን የስሙን አመጣጥ በእንደዚህ ዓይነት መንገድ ማብራራት አስፈላጊ አልነበረም፡፡ ይህን ጉዳይ ‹የኦንኪሎስ ታርገም› ያስቀመጠው በጥበብ ነበር፣ ይህም ‹ኔፊሊም› የሚለውን ቃል በደካሞችና እረዳት በሌላቸው ላይ በረብሻ አስገድደው የሚጨቁኑ ሰዎች ነበሩ በማለት ነው፡፡ ስለዚህም ይህ ታርገም ቃሉን የተረጎመው ‹ሽብር ፈጣሪዎች› ወይንም ደግሞ ሌሎችን በማስጨነቅ የሚገዙ በማለት ነበር፡፡ ሌሎች በጣም በቅርብ ጊዜያት ‹ኔፊሊም› የሚለው ቃል ‹ናፋል› ወይንም መውደቅ ከሚለው ግስ መምጣቱን አይቀበሉትም፣ እነሱም ይህንን ከአረብኛውና ‹ናቢል› ከሚለው ቃል ለማዛመድ በመምረጥ ትርጉሙን ‹ኖብል› እንዲሁም ደግሞ ‹በጦር ስራ ባለሙያ የሆነ› ለማለት ፈልገዋል፡፡ ለማንኛውም እንደማንኛውም በዘፍጥረት የመጀመሪያ ምዕራፎች ውስጥ እንዳለው የመጠሪያ ስሞች ሁሉ ሊረጋገጥ የሚችለው ቃሉ የሱመርያውያን ምንጭ እንዳለው ነው፣ ይህም ከሴማውያን ቋንቋዎች ስረ አመጣጥ ጋር ምንም ግንኙነት አይኖረውም፡፡

ብዙዎቹ ምንም የማያውቁት አይሁዶች የአስገራሚ ነገሮች ወዳጆች ናቸው፣ ስለዚህም የወደቁት መላእክት የኃጢአት ታሪክ ዕውቅና በጣም እያደገና አስገራሚ እንዲሁም ድንቅ ነገር ተደርጎ ይቆጠር ጀመር፡፡ በመጀመሪያ ሁለት መላእክት ብቻ እንደወደቁ ይነገር ነበር፣ የባቢሎናውያኑን ጊልጋሜሽን ስለፈተነችው ኢስታር የተነገረው ግን የተጋነነ ነበር፡፡ ነገር ግን ቆይቶ በተረቱ ውስጥ ያላቸው ቁጥር በአሁኑ ጊዜ በአይሁዶች እንደሚገኘው ‹በሔኖክ የአፖክሪፋዊ› መጽሐፍ ውስጥ በመጨረሻ የወደቁት መላእክት ቁጥር 200 ይደርሳል እስከተባለ ድረስ እያደገ ሄደ፣ እንዲሁም ሁሉም የወረዱት ከሴቶች ጋር ኃጢአትን ለማድረግ ነው፡፡ ከዚያ መጽሐፍ የተወሰደው የሚከተለው ማስረጃ ተረቱን በሙሉ ይዘቱ ለማስቀመጥ ከዚህ በፊት ከተጠቀሱት ይልቅ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ አሁን ቀጥሎ በምናየው አንቀፅ ውስጥ በአይሁድ የአፈታሪክ ጽሑፍ ‹በሚድራሽ ያልኩትና› እንዲሁም በቁርአን ውስጥ ከተቀመጡት መደምደሚያዎች ጋርም የሚስማማ አረፍተ ነገርንም ይሰጠናል፡፡ ‹ከእለታት አንድ ቀን እንዲህ ሆነ የሰዎች ልጆች በተባዙበት ቦታ ሁሉ በእነዚያ ጊዜያት የተወለዱት ሴቶች ልጆች ውቦች ነበሩ፡፡ የሰማይ ልጆች፣ መላእክትም አዩአቸውና ለእራሳቸው ተመኟቸው ከዚያም እርስ በእርሳቸው እንዲህ ‹ኑ ከእነሱ ለእኛ ሚስቶችን ከሰዎች እንምረጥ ከዚያም ለእራሳችን ልጆችን እንወልዳለን› ተባባሉ፡፡ ‹ሲሚያዛስ› የእነርሱ አለቃ የነበረው ለእነርሱ እንዲህ አላቸው ‹ይህንን ተግባር እንደምትቃወሙ ይሰማኛል እኔ እራሴ የዚህ ታላቅ ኃጢአት ብቸኛ በደለኛ እሆናለሁኝ›፡፡ ስለዚህም እነርሱ ሁሉም እንዲህ በማለት መለሱለት፡- ‹እኛ ሁላችንም መሃላን እንማል እንዲሁም እኛ ሁላችንም በአንድ ቃል ኪዳን ውስጥ እራሳችንን እናስተሳስር ይህም ይህንን ስሜት ላለመተው ይህንን እስክናደርግና እስክንፈፅመው ድረስ› ከዚያም ሁሉም በአንድ ላይ መሐላን ማሉ ከዚያም እርስ በእርሳቸው በመሐላ  ተሳሰሩ፡፡ የዓመፀኞቹን መላእክት ስም ከሰጠ በኋላ ታሪኩ እንደሚከተለው ይቀጥላል ‹እነርሱም ለእራሳቸው ሚስቶችን ወሰዱ፣ ለእያንዳንዳቸውም ሚስቶችን መረጡ እነርሱም ለእነርሱ ስለ መርዝ ስለ ምትሃት እና ስለ ስራስር ስብሰባ አስተማሯቸው እንዲሁም አትክልቶችን አሳዩአቸው፣ አዛኤልም ሰዎችን ሰይፍና የጦር መሣሪያን፣ ጋሻንና የደረት ቀበቶን እንዲሰሩ አስተማራቸው፣ የመላእክትን ትምህርት እና እርሱም ብረታብረቶችንና የእጅ አንባሮችንና ጌጣ ጌጦችን ቀለሞችን እንዲሁም ሁሉንም ዓይነትን የከበሩ ድንጋዮችን እና ቀለሞችን እንዴት እንደሚሰሩአቸው አሳያቸው፡፡ የዚህ የሴቶች ጌጣ ጌጥ አጀማመር በሚድራሽ ውስጥ ከምናገኘው ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ይህም ትርጉሙን እንድንረዳና ከቁርአን ውስጥ ያሉትን የሚከተሉትን አንቀፆች ምንጮች እንድንለይ ያደርገናል፣ ስለ ማሩትና ሃሩት መሐመድ የተናገረው ሰዎች ‹ከእነርሱ ተምረዋል ሰውን ከሚስቱ በሚለያዩበት› ቀጥሎም የጨመረው ነገር ‹እነርሱም በእግዚአብሔር ፈቃድ ካልሆነ በስተቀር ማንንም አይጎዱም ነበር፣ እንደዚሁም እነርሱ ሰዎችን ምን እንደሚጎዳቸውና ምን እንደማይጠቅማቸው ያስተምሩ ነበር›፡፡ (የመጽሐፈ ሄኖክ የግሪክ እትም በዶ/ር ስዌቲ ምዕራፍ 6-8)፡፡

ስለዚህም በቁርአን ላይ የሚገኘውን የሃሩትና ማሩት ታሪክ በተመለከተ ቢያንስ አስፈላጊ በሆኑት ዝርዝሮች ሁሉ ላይ ከአይሁድ የተወሰደ መሆኑን ለማሳየት ከዚህ ሌላ ማስረጃ ማቅረብ አያስፈልግም፡፡ በእነዚህ መላእክቶች ስም ላይ የአርሜኒያንንና የፐርሺያውያንን ጥቃቅን ተፅዕኖዎች የምናይ ቢሆንም ተረቱ ሙሉ ለሙሉ የመጣው ግን ከአይሁዶች ምንጭ ነው፡፡ አይሁዶች ደግሞ የራሳቸውን ተረት የወሰዱት ከባቢሎናውያን ላይ እንደሆነ ተመልክተናል፡፡ የእነርሱም ተረት ተቀባይነት ያገኘው በአብዛኛው በዘፍጥረት ላይ ያለውን የዕብራይስጥን ቃል በተሳሳተ አተረጓጎም በመረዳት ነው፡፡

አንዳንድ ክርስትያኖች ዘፍጥረት 6.1-4 አይሁዶች በሚረዱበት መንገድ ይረዱታል በማለት ክርክር ሊነሳ ይችል ይሆናል፣ ምናልባትም ያ አመለካከት ትክክል ሊሆን ይችል ይሆናል፡፡ እነዚህን ሁሉ ግንዛቤ ውስጥ ስናስገባ የሃሩትና ማሩትን ተረት መሐመድ ከምን ዓይነት የተሳሳተ ምንጭ እንደወሰደው በጣም ግልጥ ይሆንልናል፣ ሆኖም ቁርአንና ባህል ከእዚህ ጋር የሚዛመዱበት መንገድ በምንም ዓይነት ሁኔታ ትክክል ሊሆን አይችልም፡፡

የአዘጋጁ ማሳሰቢያ

በቁርአን ምዕራፍ 27 ውስጥ የሚገኘው የንግስተ ሳባ ታሪክ መጽሐፍ ቅዱስ 1ነገስት 10 ላይ ካለው ታሪክ ጋር እጅግ በጣም ይለያል፡፡ የዚህ ምክንያቱ የቁርአኑን ቃል እንደ መገለጥ ተቀብየዋለሁ ያለው ሰው ታሪኩን የወሰደበት ምንጭ ነው፡፡ ይህም መሐመድ ከአምላክ አገኘሁት የሚለውን መገለጥ ጥያቄ ውስጥ ያስገባዋል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ቁርአን በምንም ዓይነት መንገድ ከእግዚአብሔር የመጣ ላለመሆኑ አስገራሚ ማስረጃ ነው፡፡ 

በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ሰፊ ትንተና የተሰጠው የሁለቱ መላእክት የሃሩትና ማሩት ጉዳይ ነው፡፡ በእርግጥም የሃሩትና ማሩት ተረትም በቁርአን ውስጥ መገኘቱ ሌላው አስገራሚ ነገር ነው፡፡ የተረቱ ምንጭ ማነው እግዚአብሔር ነውን ወይንስ ሌላ? በቁርአን 2.102 የተጠቀሰው ሃሩትና ማሩት በባቢሎን እንደወረዱ ነው፡፡ ይህ አባባል የሚጠቁመው ታሪኩ ከባቢሎናውያን ተረት ላይ የተወሰደ የመሆኑን አስገራሚ እውነታ ነው፡፡ ስለዚህም ቁርአን የያዘው የእግዚአብሔርን መገለጥ ሳይሆን ተረት መሆኑን በግልፅ ያስረዳል፡፡

እነዚህ ሁሉ ምርምሮችና ጥናቶች ለምን ያስፈልጋሉ? መልሱ በጣም ግልጥ ነው፣ እነዚህ የሚያስፈልጉት ሰዎች ስለሚያምኑት ነገር እውነት መሆንና አለመሆን ግንዛቤ እንዲያገኙና ወደ ትክክለኛውና ለአዕምሮ ወደሚመቸው ቅዱስ እምነት እንዲመጡ ለመርዳት ነው፡፡ እውነተኛው እግዚአብሔር የሰማይና የምድር ፈጣሪ ነው፣ እርሱ ከፈጠራ ተረት ጋር ግንኙነት የለውም ሰዎችንም በተረት አይማርክም፡፡ ቅዱስና ሕያው አምላክ ስለሆነ በኃጢት ላይ ይፈርዳል፡፡ እኛ የሰዎች ልጆች ሁላችንም ከፍጥረታችን ኃጢአተኞች በመሆናችን የሲዖል ፍርድ ይገባናል፡፡

በዚህ ምክንያት ነው ይህንን የድረ-ገፅ አገልግሎት እንዲኖር እግዚአብሔር የፈቀደው፡፡ ታላቁና ቅዱሱ እግዚአብሔር የእርሱን ምህረትና ርህራሄውን ለመግለጥና እኛን በራሱ መንገድ ሊታረቀን ፈቀደ በመሆኑም ሞታችንን ሞቶ ከሕያው እምላክ ጋር የሚያስታርቀንን አዳኝ ጌታ ኢየሱስን ከሰማይ ላከልን፡፡ በእርሱም በኩል የምናገኘው ይቅርታ የዘላለም ዋስትና ይኖረው ዘንድ እርሱ የሰውን ስጋ ለብሶ በመምጣት ስለ እኛ ሰው ሆነልን፡፡ ከዚያም ጌታ ኢየሱስ በራሱ ፈቃድ እራሱን በመስቀል ላይ ሰጥቶ በመሞት የዘላለምን ይቅርታ የሚቻል አደረገው፡፡

አንባቢዎች ሆይ የዚህ ገፅ አዘጋጆች የሚጋብዟችሁ ይህንን እውነት ለማየት እንድትችሉ ነው፡፡ ወደ ፀሎት ቤት በመሄድ ቃሉን ስሙ፣ ንስሐ ግቡና ጌታችንን ኢየሱስን ይቅር እንዲላችሁ ለምኑት እርሱም በመለኮታዊ ኃይሉ ይቅር ይላችሁና አዲስን ሕይወት ይሰጣችኋል፣ እናንተም የእግዚብሔር ልጆች እንድትባሉና መንግስተ ሰማይንም እንድትወርሱ መብትን ይሰጣችኋል፣ ጌታ በፀጋውና በኃይሉ ይርዳችሁ አሜን፡፡

የትርጉም ምንጭ: THE ORIGINAL SOURCES OF THE QUR'AN 

ሙሉ መጽሐፉ በአማርኛ:  የቁርአን የመጀመሪያ ምንጮች

ለእስልምና መልስ አማርኛ  ዋናው ገጽ