የቁርአን የመጀመሪያ ምንጮች

REV. W. ST. CLAIR TISDALL, M.A., D.D

ትርጉምና ቅንብር በአዘጋጁ

ምዕራፍ ሁለት: የጥንታዊ አረቢያን እምነትና ልማዶች ተፅዕኖ

በመሐመድ አዕምሮ ውስጥ የእስልምናን የቀስ በቀስ እድገት ለመረዳት እንዲሁም እርሱ ከምን ዓይነት ምንጮች ነገሮችን እንደተዋሳቸው ለማግኘት፣ በቅድሚያ ባደገበት እና ዘሩ ባለበት በአረብ መካከል የነበረውን የሃይማኖት አመለካከትና የአምልኮ ስርዓቶች ምን ይመስ እንደበረ መመልከት አስፈላጊ ነው፡፡

የአረቢያ ነዋሪዎች ሁሉም የአንድ ጎሳ ሰዎች አልነበሩም፡፡ የአረብ ጸሐፊዎች በአጠቃላይ የከፋፈሏቸው በንፁህ ወይንም የመጀመሪያ አረቦችና ከሌላ አገር የመጡ እና አረብ የሆኑ በማለት ነው፡፡ ሂምያራይትስ እና ሌሎች ጎሳዎች የሚያሳዩን ከኢትዮጵያውያኖች ጋር የቅርርብ ርዝራዥ መኖሩን ነው፡፡ በኩኒፎርሞች ሸክላዎች ላይ ያለው ጽሑፍ በሱመርያኖች ንጉስ በባሊሎን የተደረገው የመጀመሪያ ጦርነት ዘገባ፣ የድሮ የግብፅ ነገስታት ለጊዜውም ቢሆን የሳይናይን ባህረሰላጤ ምናልባትም ሌሎች በሰሜንና በደቡብም ያሉትን ወረዳዎችንም ጨምሮ አጠቃልለው ነበር፡፡ ይህ የመሆኑም እውነታ የጥንት ጊዜ ሐማውያንና ሌሎች የውጭ ዘሮች ሁሉ በሕዝቡ ውስጥ ለመኖራቸው ምንም ጥርጥርን አይተውልንም፡፡ በባቢሎን በነበሩት ታላላቅ የኩሻውያን ገዢዎች ነገስታት ዘመን፣ የአረቢያ ሕዝብ፣ በታላቅ ስልጣኔያቸው፣ በአጠቃላይ በንግዳቸውና በሐሳባቸውም ጭምር ተማርከው ነበር፡፡ ነገር ግን የእነዚያ የባዕድ አገሮች ሃይማኖትም ተፅዕኖ እጅግ ጠንካራ የነበረ ሳይሆን አልቀረም፡፡ ይህንንም የቀደሙት የአረቢያ ጽሑፎች ያረጋግጡታል፣ እነሱም እንደ ሲን (የጨረቃ አምላክ) እና ዓይነት አማልክትን ስም በመያዛቸው አዛዛር (አሽታሮት)  በመጀመሪያ በሱመርያውያን፣ ከዚያም በሴማውያን፤ ባቢሊናውያን፤ አሶራውያን፣ በሶርያ እና በአንዳንድ የአረቢያ ከፍሎችም  የተመለኩት፡፡ የሐማውያን ዘር በሕዝቡ ውስጥ ለመኖሩ ምንም ጥርጥር ባይኖርም ከመጀመሪያው ጀምሮ የነበሩት ብዙዎቹ ሕዝቦች ግን የዝርያ ምንጫቸው እንዲሁም ደግሞ በቋንቋ በባህርይ እና በሃይማኖት ሁልጊዜም የሴማውያን ነበር፡፡

ኢብን ሃሻም ታባሪ እና ሌሎችም የአረቢያን ታሪክ ጸሐፊዎች የአንዳንድ የጥንት የአረብ ጎሳዎችን በተለይም በአገሪቱ ሰሜንና በምዕራብ በኩል ያሉት አገሮች ልማዶች ጠብቀዋል፡፡ እነዚህም የሚስማሙት ከአምስቱ የሙሴ መጻሕፍት አረፍተ ነገሮች ጋር ነው እናም ብዙዎቹ እነዚህ ጎሳዎች ዝርያቸውን ከዮቅጣን (በአረብኛ ካታን) ወይንም ከእስማኤል ወይንም አብርሃም ከኬቱራ ካገኛት ልጆች ጋር ማግኘት እንደሚቻል በማንኛውም መልኩ ማመን ይቻላል፡፡ እንደዚህ ዓይነቱ ዝርያ እንዳላቸው ለመጥቀስ መብት ያልነበራቸው እንኳን በመሐመድ ጊዜ እንዳላቸው አድርገው ይናገሩ ነበር፡፡ የራሱ የመሐመድ ጎሳ ቁራይሾች የሚናገሩት በእስማኤል በኩል ከአብርሃም እንደመጡ ነበር፡፡ ይህንን ማረጋገጥ የማይቻል ቢመስልም እንኳን የመሐመድ ጎሳ እንደዚህ ዓይነትን ጥያቄ የማቅረባቸው እውነታ እራሱ ሊያሳይ የሚችለው፣ የእርሱ ጎሳዎች ዘራችን ነው በማለት የሚመኩበትን የአብርሃምን እምነት እንዲከተሉ እነዚህን ሰዎች ለመጥራት ከእግዚአብሔር የተሾመ መሆኑን ሲናገር ታዋቂ የሆነ የርህራሄ ስሜት በመሐመድ በኩል እንደነበረ ነው፡፡   

ስለዚህም የሴም ልጆች የመጀመሪያው ሃይማኖት የእውነተኛው አምላክ አምልኮ እንደነበረ ለማመን የሚያስችል ጥሩ ምክንያት አለ፡፡ በአረቢያ ውስጥ የብዙ አምልኮ ከጥንት ጀምሮ የገባ ቢሆንም፣ በከፊልም በተጠቀሱት የውጭ ተፅዕኖዎች አማካኝነት የገባ መሆኑ ጥርጥር የሌለው ነገር ቢሆንም በእውነተኛው አምላክ የማመን ነገር ከሕዝቡ አዕምሮ ውስጥ በፍፁም ተጠርጎ አልወጣም ነበር፡፡ በጎሳዎች መካከል የነበረው የስምምነት ማሰሪያ ይረጋገጥ የነበረው የእግዚአብሔር ስም ተጠርቶ ሲደረግ ነበር፡፡ እንዲሁም ‹የእግዚአብሔር ጠላት› የሚለውም አገላለጥ በጥቅም ላይ ከዋሉት ውስጥ እጅግ በጣም አስፀያፊው ይመስል ነበር፡፡ በኢዮብ መጽሐፍ ውስጥ ልናይ ከምንችለው ውስጥ በጣም በጥንት ጊዜ የሰማይ ሰራዊትን የማምለክ ነገር በአገሪቱ ውስጥ መግቢያ መንገድን ያገኘ ለመሆኑ ለማየት ይቻላል ኢዮብ 331.26-28፡፡ ሔሮዱቶስ እንደዘገበው (እንደነገረን) (በመጽሐፍ 3 ምዕራፍ 8) ውስጥ በእርሱ ጊዜ ሁለት አማልክት አንድ ወንድና አንዲት ሴት በአረቦች መካከል ይመለኩ እንደነበር ነው እነዚህንም እርሱ ለይቶ የጻፋቸው ‹ዲዮኒሶስ› እና ‹ኦራኒያ› በማለት ነበር፡፡ እርሱም የነገረን ነገር በአረብኛ የእነርሱ ስም ኦሮታል› እና ‹ሃሊላት› እንደነበረ ነው፡፡ ሁለተኛውና ምናልባትም የባቢሎኒያው ‹አላቱ› እንደነበረ ነው፣ ይህም በእርግጥ በቁርአን ውስጥ የተጠቀሰው አል-ላት እንደነበረ ነው፡፡ የኋለኛው ቃል የተወሰደውም የአላህ ‹የሴቴ› ስም መገለጫ ቃል ሆኖ ነው፡፡ ማለትም ሴት እግዚአብሔር ማለት ነው፡፡ አላህ እራሱም የሚታወቀው የአል-ኢላህ አጭር ቃል ሆኖ ነው፤ ይህም በሴማቲክ ቋንቋዎች ውስጥ በመስተፃምር ኖሮት ለእግዚአብሔር በመጠነኛ ልዩነት በአገልግሎት ላይ የዋለ ቃል ነው ስለዚህም አላህ የሚለው ቃል ከግሪኩ ‹ፂዎስ› ጋር ተመሳሳይነት ያለው ነው፡፡ ‹አሊላት› የሚለው ፎርም ግን በሔሮዱቶስ የተሰጠው ያላጠረ የሴቴ ተመሳሳይ ቃል ነው፡፡ ስለዚህም ሔሮዱቶስ የሚተርካቸው አረቦች አንዱን አምላካቸውን ከሴት አጋር ጋር ይጠሩት እንደነበረ ነው፡፡ ይህም ከባቢሎናውያን ሴማውያን ተከትሎ ሲሆን እነርሱም ከሱመርያን ያገኙት ሐሳብ ነው፡፡ ይህም አምላክ ሴቴ ጓደኛ ሊኖረው ይገባል ከሚለው አመለካከታቸው የመጣ ሲሆን አሁንም በሂንዱዎች እንደምናገኘው ማለት ነው፡፡ በሌላ ጎኑ ደግሞ ይህ በሌሎችም አረቦች ሁሉ የነበረ ነው ብለን ሙሉ ለሙሉ ለመናገር አንችልም፡፡ በእርግጠኝነትም በመሐመድ ጊዜ እንደዚያ አልነበረም፣ ምክንያቱም ቁርአንም ሆነ የቀደሙት የጥንታዊ አረብ ግጥም ቅሬቶች ለዚህ ነገር ምንም የሚሰጡት ፍንጭ የለምና፡፡ ይሁን እንጂ አላህ ይታይ የነበረው ብቻውን እንደቆመና ሊታወቅ ወይንም ሊደረስበት እንደማይችል ነበር፡፡ ከዚህም በላይ በሌሎች ጎሳዎች ልዩ (የጎሳ ብቻ) አማልክት ሆነው ይመለኩ የነበሩት አናሳዎቹ አማልክቶች ከእርሱ ጋር ለማማለድ እንደሚያስችሉ ይታመን ነበር፡፡  እነዚህም እጅግ በጣም ብዙ ነበሩ ከእነርሱም ውስጥ በጣም ጠቃሚዎቹ ዉድ፣ ያሁቅ፣ ሁባል፣ አል-ላት፣ ዑዛ፣ እና ማናህ ነበሩበት፡፡ በስተመጨረሻ የተጠቀሱንት የሴት አማልክት ቁርአን ያወግዛቸዋል፣ አረቦች የእግዚአብሔር ሴት ልጆች ናቸው ብለው ስለሚጠሯቸው፡፡ በዚያን ጊዜ ከነበሩት አረቦች የግጥም ይዘት በመነሳት ለመፍረድ ብንነሳ በጣም ሃይማኖተኞች እንዳልነበሩ፣ ይሰጡ የነበረውም አምልኮ ለእነዚህ አነስተኛ አማልክት ብቻ እንደነበር እንገነዘባለን፡፡ ሆኖም በእነርሱ በኩል (እነሱን እንደአማላጅ በመቁጠር) ለአላህ መናገራቸው አጠራጣሪ ነው፡፡ የመጨረሻ ሆኖ ይጠቀስ የነበረውስም  ‹አላህ ታዓ-ላህ› ወይንም ‹ታላቁ እግዚአብሔር› ተብሎ ነበር፣ ስለዚህም የእግዚአብሔር አንድነት በአረቦች መካከል ለመጀመሪያ ጊዜ የተዋወቀው (እንዲተዋወቅ የተደረገው) በመሐመድ ነበር ለማለት አይቻልም፡፡ አላህ የሚለው ቃል መደበኛ መስተፀአምርን ይዞ መገኘቱ ይጠቀሙበት የነበሩት እነሱ በሆነ መንገድ የአምላክን አንድነት ያውቁ የነበሩ መሆንን የሚያስረዳ ነው፡፡ መሐመድ ቃሉን አልፈጠረውም ነገር ግን እንዳልነው ሁሉ እርሱ በአምላክ የተሾምኩኝ ነቢይ ነኝ በማለት እራሱን ባስተዋወቀበት ጊዜ ቃሉን በአገሩ ሰዎች ዘንድ በአገልግሎት ላይ ውሎ አግኝቶታል፡፡ የዚህን ማረጋገጫ ደግሞ በጣም ሩቅ አይደለም፡፡ ልጁ መሐመድ ከመወለዱ በፊት የሞተው፣ የራሱ አባትም ስሙ አብዱ-ላህ ‹የአላህ ባሪያ› ተብሎ ይጠራ ነበር፡፡ ካኣባ ወይንም በመካ የሚገኘው ቤተ መቅደስ ከመሐድ በፊት በጣም ለዘረጅም ዘመናት ‹ባይቱ ኢላህ› ወይንም የአላህ ቤት ተብሎ ይጠራ ነበር፡፡ የአረብ ልማድ እንደሚናገረው በዚያ ቦታ ላይ በአብርሃምና በልጁ በኢስማኤል የመሰዊያ ቦታ ተገንብቶ ነበር ይላል፡፡ የዚህን ዓረፍተ ነገር ታሪካዊ እውነተኝነት በምንም መንገድ ማረጋገጥ ባንችልም እንኳን ልማዱ የሚያሳየው በዚያ ቦታ ላይ አምልኮ የመሰጠቱ ነገር ጥንታዊነት የነበረው መሆኑን ነገር ግን ጅማሬው በተረት ውስጥ ጠፍቶ እንደነበረ ነው፡፡ ካኣባ በሁሉም አማራጭ በኩል በዲዮዶሩስ ሲኩለስ የተጠቀሰው ቦታ ወይንም ነጥብ ነው (60 ዓ.ዓ) በአረቦች ሁሉ በጣም ልዩ የሆነና የተከበረ ማምለኪያ ወይንም ቤተመቅደስ ነበረ፡፡ አል ሙላካት በተባለው ግጥም ውስጥ ከእስልምና ታሪክ በፊት ለእኛ ሲወርድ ሲዋረድ በመጣው አላህ የሚለው ቃል ከግሪኩ ፂዎስ ጋር ብዙ ጊዜ ተጠርቷል፡፡ እንዲሁም ከስራው ውስጥ ምንም ነገር ያልተላለፈልን የቀደመው የመሐመድ ታሪክ ጸሐፊ ኢብን ኢ-ሻቅ፣ በኢብን ሒሻም እንደተጠቀሰው፣ የኪናናህና የቆራይሽ ጎሳ ሆኖ ኢሃላል የተባለውን የሃይማኖት ስርዓት በሚያከናውንበት ጊዜ አምላኩን በሚከተለው ቃል የመጥራት ልማድ እንደነበረው ነው፤ ‹ላባይካ አላሁማ› - ‹እኛ በአንተ አገልግሎት ውስጥ አለን ኦ እግዚአብሔር እኛ በአንተ አገልግሎት ውስጥ አለን አንተም ምንም አጋር የለህም አንተን ከሚፈራህ፣ ደግሞም አንተም ከምትፈራው አጋር በስተቀር እርሱንም ያለውንም ሁሉ አንተ የራስህ አደረግኸው›፡፡ ኢብን ኢሻክ በትክክል የተናገረው በዚህ አጠራር ውስጥ እነሱ የሚገልጡት በአላህ አንድነት ማመናቸውን እንደሆነ ነው፡፡  ሆኖም ‹የምትፈራው አጋር› የሚለውን ሐረግ ትርጉም ግን እልገለጠውም፡፡ ነገር ግን ይህ ከአናሳዎቹ አማልክት ማለትም ከጎሳዎቹ የአንዱ የሆነውን አብሮ መሆንን የሚያመለክት ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ቋንቋው በማንኛውም መንገድ በግልፅ የሚያመለክተው የተጠቀሰው አምላክ ከአላህ ጋር እኩል መሆኑን አይደለም፡፡ ስለዚህም የጥንት አረቦች ሃይማኖት ሊነፃፀር የሚችለው ምናልባትም ከግሪክና ከሮማውያን የቅዱሳን አምልኮ ባህል ጋር ነው፣ ይህም በመሐመድ ጊዜና በእኛም ዘመን እንዳለው ሁሉ ነው፡፡ ከዚህም ጋር ቁርአን አሁን ቢኖርም እንኳን በሙስሊሞች መካከል በብዛት አሁንም እንደሚታየው ነው፡፡ ነገር ግን ለእንደዚህ ዓይነት ቅዱሳን፣ ወይንም ለአናሳ አማልክት የሚሰጠው አምልኮ የእግዚአብሔርን አንድነት ወይንም ታላቅነትን መካድ ይይዛል ተብሎ አይገመትም፣ ምክንያቱም እነዚያ በእግዚአብሔርና በሰው መካከል እንደ አማላጅ ይገባሉ ተብሎ ስለሚታሰብ ነው፡፡

በቅድመ እስላም የአረቢያ ጊዜ ስለነበረው የሃይማኖት ሐሳብ እና ልምምድ አሽ ሻሪስታኒ የሚነግረን ነገር ይህንን ሙሉ በሙሉ የሚያረጋግጥ ነው፡፡ እርሱም የአረቢያን ነዋሪዎች በተለያዩ ፓርቲዎችና የእምነት ክፍሎች ከፋፍሏቸዋል፣ እነርሱም በሃይማኖት አመለካከታቸው በጣም የተለያዩ ነበሩ፡፡ እርሱም እንደዘገበው አንዳንዶቹ የፈጣሪን መኖር፣ የነቢያትን ወደ ሰዎች መላክና የመጨረሻውን ፍርድ መኖር የሚክዱ ናቸው፡፡ እነሱም ተፈጥሮን እራሱን ሕይወትን ሰጪ አድርገው ያከብሩ የነበረ ሲሆን፣ ጊዜን ደግሞ አለም አቀፋዊ አጥፊ በማለት ይቆጥሩት ነበር፡፡ ሌሎች ደግሞ በፈጣሪ ያምኑ ነበር ነገር ግን ፈቃዱን የሚናገሩ ነቢያትን በመላክ እራሱን መግለጡን ይክዱ ነበር፡፡ ሌሎች ደግሞ ጣዖታትን ያመልኩ ነበር፣ እያንዳንዱም ጎሳ የየራሱ ጣዖት ነበረው፡፡ ለምሳሌም ያህል የካልብ ጎሳዎች ‹ዉድ› እና ‹ሱዋ› የተባሉትን ያመልኩ ነበር፣ ማዳጅ የተባሉት ደግሞ አንዳንድ የመናውያን እንደሚያደርጉት ‹ያጉዝን› ያከብሩ ነበር፡፡ በሂማር ያሉት ዱልኪላዎች ደግሞ ‹ናስርን›፤ የሐምዳ ጎሳዎች ደግሞ ‹ያዑክን› ያከብሩ ነበር በታይፍ የነበሩት ታኪፎች ደግሞ ‹አል-ላትን› ሲያከብሩ ‹አል-ዑዛ› ደግሞ የባኒ-ኪናና እና የኩራይሾች ጠባቂ ሴት አምላክ ነበረች፡፡ የዑስ እና ካዝጃር ጎሳዎች ደግሞ ‹ማናን› ሲያመልኩ ‹ሁባልን› ግን እንደ ዋነኛ (አለቃ) አምላካቸው ይወስዱ ነበር፡፡ የእርሱም ምስል በጣም ድብቅ በሆነው በመካ ጣሪያ ላይ ይቀመጥ ነበር፡፡ ሌሎችም አምላኮች ‹አሳፍ› እና ‹ናይላ› ነበሩ፡፡ አንዳንዶቹ ጎሳዎች በአቅራቢያቸው በተቀመጡ አይሁዶች ተፅዕኖ ስር ሆነው ነበር እንዲሁም ከሞላ ጎደል የእነርሱን ትምህርት ተቀብለው ነበር፡፡ ሌሎችም ደግሞ ክርስትያኖች ሆነው ነበር፣ ጎረቤቶቻቸውም እምነቱን ለመቀበል ዝንባሌ ነበራቸው፡፡ ሌሎችም ደግሞ በሳባውያን ተፅእኖ ስር ነበሩ፣ ስለዚህም የከዋክብትን ምርምርና ሐሳብ ይከተሉ ነበር፡፡ ለማንኛውም ጠቃሚ እንቅስቃሴዎቻቸው ጥንቆላ የሰማያዊ አካላትን እንቅስቃሴ ይከታተሉ ነበር፡፡ አንዳንዶችም መላእክትን ያመልኩ ነበር አንዳንዶችም ሰይጣንን ጂኒንና ክፉ መናፍስትን ይከተሉ ነበር፡፡ የእግዚአብሔር ሐዋርያ ምክትልና የመጀመሪያው ካሊፍ የነበረው አቡ በከር እራሱም በአንድ ወቅት ሕልምን በመተርጎም ችሎታው ብቃት በጣም ታዋቂ ነበር፡፡

በብዙ የአረብኛ ጸሐፊዎች የተያያዘው ታሪክ በአንዳንድ ታዋቂ የቁርአንም ተንታኞች ጨምሮ የሚያሳየው በመሐመድ ጊዜ የነበሩት አረቦች ታላቁን እግዚአብሔርን (አላህ ታዓላ) የሚሉትን አብረውት ለማምለክ ምን ያህል ዝግጁ እንደነበሩ ነው፡፡ ይህም እርሱ ለጊዜው የእነሱን አናሳ አማልክት መቃወሙን ባቆመበት ሰዓት ነበር (በመካ በመረረ ሁኔታ የተቃወሙትምና የእርሱን ብዙዎቹን ተከታዮች ወደ አቢሲኒያ እንዲኮበልል ያደረጉትንም ጭምር ነው)፡፡ እኛም የተነገረን አንድ ቀን እርሱ ወደ ካዓባ በመካ ወዳለው በታላቁ የአገሪቱ የአምልኮ ቦታ ቤተሰቦቹ በአንድ ወቅት ጠባቂዎች በነበሩበት ሊፀልይ ሄደ፡፡ እዚያም እርሱ የሱራ አል-ነጅምን መድገም ጀመረ ሱራ (ምዕራፍ 53)፡፡ እርሱም አስራ ዘጠነኛውንና ሃያኛውን ቁጥር ማስታዎስ በጀመረ ጊዜ ‹አል-ላትንና፣ አል-ዑዛን አያችሁን? ሦስተኛይቱንም አነስተኛዋን መናትን (አያችሁን የምትዟቸው ኃይል አላቸውን?)› (አያችሁን የምትገዟቸው ኃይል አላቸውን የሚለው በአማርኛ ተርጓሚዎች የተጨመረ ነው)፡፡ ቆይቶ ግን መሐመድ እነዚህን ቃላት ሰይጣን አስገድዶት እንዳስጨመረው ተናግሯ፡፡ ‹አል-ላትንና፣ አል-ዑዛን አያችሁን? ሦስተኛይቱንም አነስተኛዋን መናትን› የሚሉትን እነዚህን ቃላት ሲሰሙ በዚያ የነበሩት አረቦች ሁሉ ከእርሱ ጋር አመለኩና ወዲያውኑ ሁሉም እስልምናን እንደተቀበሉ ዜናው ተስፋፋ፡፡ ይህ ታሪክ በሚገባ የተረጋገጠና በጣምም እውነት ነው፡፡ የታሪኩ መኖር በማንኛውም መንገድ የሚያሳየው ግን የመሐመድ ጠላቶች በአላህ መኖርና ታላቅነት ላይ ያለውን ትምህርቱን ለመቀበል ምንም ችግር እንዳልነበረባቸውና አነስተኛዎቹ አማልክት ሲጠሩ ደግሞ የታላቁ አምላክ አማላጆች ሆነው ከእርሱ ጋር አመለኳቸው፡፡ ነገር ግን መሐመድ የእነዚህን ሴት አማልክት መኖርንና ለስራቸውም ዕውቅና የሰጠውን ቃል ወዲያውኑ ያስወጣው የመሆኑ እውነት እዚህ ላይ መጨመር አስፈላጊ ነው፣ በእነሱም ላይ አሁን በቁርአን ውስጥ የምናገኛቸውን ቃላት ተካው ‹ለእናንተ ወንድ ለእርሱም ሴት (ልጅ) ይኖራልን? ይህቺ ያን ጊዜ አድላዊ ክፍያ ናት፡፡ እነርሱ እናንተና አባቶቻችሁ (አማልክት ብላችሁ) የጠራችኋቸው ስሞች ብቻ እንጅ ምንም አይደሉም፡፡ አላህ በርሷ (መግገዛት) ምንም ማስረጃ አላወረደም ከጌታቸውም መምሪያ የመጣላቸው ሲኾኑ ጥርጣሬንና ነፍሶች የዘነበሉበትን እንጅ ሌላ አይከተለውም፡፡› ቁርአን 58.21፣22፣23፡፡

ኢብን ኢሻቅ፣ ኢብን ሒሻምና ሌሎችም የአረብ ጸሐፊዎች በአጠቃላይ የተናገሩት በተለይም አረቦች  ከእስማኤል ዘር እንደመጡ የሚናገሩቱ፣ በመጀመሪያ የእግዚአብሔር ብቻ አምላኪዎች እንደበሩ ነው፡፡ ማለትም ከጊዜ በኋላ ወደ ጣዖት አምልኮና ወደ ብዙ አማልክት አምልኮ ውስጥ ቢገቡም እንኳን ነው፡፡ ለእንደዚህ ዓይነት የሃይማኖት ሐሳቦችና ልምምዶች መግለጫ እንደገለጥናቸው ያሉ ቃላትን የምንጠቀም ከሆነ - እነሱ ታላቁ እግዚአብሔር ከኣናሳዎቹ ተመላኪዎች ሁሉ የበለጠ መሆኑን ሁል ጊዜ ያስታውሱ እንደነበረ ነው፡፡

የአይሁድና ክርስትያኑ ቡድን በመሐመድ አዕምሮ ላይ ያመጡትን ተፅዕኖ ለመመልከት የምንመጣ ከሆነ ግን የምናገኘው ነገር እነዚህ ሃይማኖቶች ያለምንም ጥርጥር በአንድ አምላክ የማምለክ እምነቱን እንዳጠናከሩለት ምንም ጥርጥር የለንም፡፡ ነገር ግን በዚያን ጊዜ በነበሩት አረቦች መካከል ይህ አዲስ እምነት አልነበረም፣ እንዳየነው ሁሉ እነሱ ሁልጊዜ ይህንን ተቀብለውት ነበረ፣ ቢያንስ በፅንሰ ሐሳብ ደረጃ፡፡ ነገር ግን የሚያመልኳቸው አናሳዎቹ አማልክት እጅግ በጣም ብዙ ነበሩ ምክንያቱም ከ360 ያላነሱ አማልክት በአገር አቀፍ ማምለኪያ በሆነው በካኣባ ነበሩና፡፡ ከዚህም በላይ እነዚህ የአካባቢው ጎሳዎች አማልክት ስለነበሩ በብዙዎቹ ሕዝቦች መካከል በተግባር የታላቁን አምላክ የእግዚአብሔርን አምልኮ ከልለውት ነበር የሚለው ነገር ከፍተኛ ጥርጥር ላይ ይጥላል ፡፡

የቀደሙት የአረብ ታሪክ ጸሐፊዎች በትክክል ወይንም በስህተት የተናገሩት ነገር ‹ከእግዚአብሔር ጋር ሸሪክን ማድረግ› የሚለው ሐሳብ እስልምና በአረቢያ በተነሳበት ወቅት ጋር ሲነፃፀር የቅርብ ጊዜ እንደነበረ መታወቅ አለበት፡፡ ልማድ የሚለው በመሐመድ አባባል ላይ መታመን ያስፈልጋል ነው፡፡ ይህም የሚጠቁመን የጣዖት አምልኮ ወደ አረብ አገሮች የገባው ከሶርያ እንደሆነና፣ ይሄ እንዲሆንም ዋና ዋና መሳሪያ የሆኑትን ስሞች እንደሚሰጠን ነው፡፡ ይህም ሆነ ተብሎ የተገለጠው ከመሐመድ በፊት አስራ አምስት ትውልድ ቀደም ብሎ ነው፡፡ ከዚህም ሐሳብ የተለየ ተደርጎ መታየት ያለበት ነገር ለቅዱስ ድንጋዮች ይሰጥ የነበረው ክብር ነበር፡፡ ይህ ደግሞ በአባቶች ዘመን በፓለስታይን ታሪክ፣ እንዲሁም በአረቢያም ውስጥ ያለምንም ጥርጥር ከጥንት ጀምሮ ልማድ የተለመደ ነበር፡፡ ለዚህ ዘገባ ኢብን ኢሻቅ የጣረው መካዎች በጉዞአቸው ላይ እነዚህን ትናንሽ ድንጋዮች ከካኣባ ተሸክመው እንደሚሄዱና እንደሚያከብሯቸው ሐሳብ በመስጠት ነው፡፡ እርሱም እነሱ ከሐራን ወይንም ከቅዱስ ቤተመቅደስ ነበር የመጡት በማለት ጠቁሟል፡፡ ሔሮዱትስ የጠቀሰውም አረቦች በጣም ክቡር የሆነን መሐላ ያደርጉ በነበረበት ጊዜ ሰባት ድንጋዮችን ይጠቀሙ እንደነበረ ነው፡፡ ክብሩም ልክ እንደ አምልኮ እንደሚቆጠር ነበር፣ አሁንም የሙስሊም ተጓዦች ለታዋቂው የበራሪ ኮከብ ቁራጭ ‹ሓጃሩል አስዋድ› ወይንም ለጥቁሩ ድንጋይ የሚሰጡት ዓይነት ክብር ነው፡፡ ይህም ድንጋይ የተገነባው በካኣባ ግድግዳ ላይ ነው፣ እርሱም አንዱ የእስላም ባህል ሲሆን የመጣውም ከመሐመድ በፊት ከነበሩት አረቦች ነው፡፡ በጣም የተሰጡት መሐመዳውያን ተጓዦች የሚያደርጉት የድንጋዩን መሳም ልማድ ከጥንቱ ባህል ሲወርድ የመጣ ነው፡፡ ይህም ልክ እንደ ሌሎች አገሮች በአረቢያም ይደረግ የነበረ አምልኮ አይነት ነው፡፡ ይህንን ድንጋይ በተመለከተ ከመሐመዳውያን ጊዜ በፊት ብዙ ነገሮች  ተነግረዋል እነዚህም አሁንም በጣም በጥብቅ ይታመንባቸዋል፡፡ ከሰማይ ገነት እንደወረደ የሚያዛምደው ልማድ አለ፣ በመጀመሪያም ንፁህ የሆነ ነጭ ድንጋይ እንደነበረ ነገር ግን በሰዎች ልጆች ኃጢአት ምክንያት ጥቁር እንደሆነ፣ በሌላ ዘገባ መሰረት ደግሞ አንድ በስርዓት ንፁህ ካልሆነ ሰው ከንፈር ጋር በመገናኘት ወደ ጥቁርነት እንደተቀየረ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ እንደሚታወቀው ከተወርዋሪ ኮከብ እንደመጣ ነው ይህም የታሪኩ አንዱ ጎን ነው፡፡

እስልምና የተዋሰው አላህ ታኣላህ ማመንንና የካኣባን ጥቁር ድንጋይ አምልኮን ብቻ ሳይሆን ነገር ግን እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ የጥንት አረቦችን ልምዶችንም ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በመሐመዳውያን ዓለም ውስጥ ያሉት አብዛኛዎቹ የሃይማኖት ስርዓቶችና ልምምዶች በጥንት አረቢያ ከሚደረጉት ጋር ተመሳሳይ ናቸው ማለት ማጋነን አይሆንም፡፡ ለምሳሌም ያህል ሔሮዱቱስ የነገረን ነገር በእርሱ ጊዜ (ዘመን) አረቦቹ ፀጉራቸውን በጆሯቸው ትዩይ ባለው ዙሪያ እንደሚላጩና ሌሎቹን አጠር አድረገው የመቁረጥ ልማድ እንደነበራቸው ነግሮናል፡፡ ይህም በመሐመዳውያን በአንዳንድ አገሮች አሁንም ይደረጋል፡፡ ከዚህ የተለየ ልዩነት ቢኖር - እርግጠኛ ልንሆን አንችልበትም፣ ምክንያቱም አንድ አረብ ጭንቅላቱን ሙሉ ለሙሉ ከግንባር እስከ ማጅራት ድረስ ተላጭቶ፣ ፀጉሩም እንዲያድግ ከተደረገ በኋላ በእራስ ጎን በኩል ብቻ አጭር ተደርጎ የተቆረጠ መሆኑን የግሪክ ተጓዦች አለማየታቸውን ነው፡፡ አብዱል ፊዳ በአዲሱ ስርዓት ውስጥ ተጠብቀው ስለዘለቁት የሃይማኖት ልምዶች ቁጥር ያመለክተናል፡፡ እርሱም ‹በድንቁርና ጊዜ የነበሩት አረቦች› አለ፣ ‹ነገሮችን ያደርጉበት የነበረውን ነገር የእስልምና ሃይማኖት ወርሶታል፡፡ እናቶቻቸውን ወይንም ሴት ልጆቻቸውን አያገቡም ነበርና በእነርሱም መካከል ሁለት እህትማማቾችን ማግባት እጅግ በጣም የተጠላ ነገር ነበር፣ እንዲሁም ደግሞ የአባቱን ሚስት ያገባውን ሰው ሙልጭ አድርገው ይሰድቡትና ‹ዳይዛን› በማለት ይጠሩት ነበር፡፡ ከዚህም በላይ ደግሞ ወደ ቤቱ ማለትም ወደ ከኣባ ጉዞን ያደርጉ ነበር፤ የተቀደሱ ቦታዎችን ይጎበኙ ነበር እንዲሁም ደግሞ ኢህራምንም ይለብሱ ነበር፡፡ (ይህም በአሁኑም ጊዜ በካኣባ ዙሪያ በሚዞርበት ጊዜ የሚለበስ ልበስ ነው)፡፡ እንዲሁም ‹ታዋፍ›ን አድርገው ይሮጡ ነበር፡፡ (ይህም በአስ ሳፋና በአል ማርዋ ጉብታዎች መካከል መሮጥን ነበር) እንዲሁም በየመቆሚያ ቦታዎች ላይ ቆመው ድንጋዮችን ይወረውሩ ነበር (በሰይጣን ላይ በሚና ሸለቆ ውስጥ)፡፡ እንዲሁም በየሦስት ዓመቱ አንድ ወርን የመጨመር ልማድ ነበራቸው፡፡ እርሱም እጅግ በጣም ብዙ የሆኑና በአረቢያ ባህል ውስጥ የሚደረጉቱንና ወደ እስልምና እምነት የገቡትን ሌሎችንም ተመሳሳይ ምሳሌዎችን በመጥቀስ ቀጥሏል፡፡ ለምሳሌም ከአንድ የሆነ ዓይነት እርኩሰት በኋላ የሚደረገው የመታጠብ ስርዓት፣ ፀጉርን በመክፈል፣ ጥርስን በማፅዳት፣ ጥፍርን መላጥ የሚደረገው ስርዓት እንዲሁም እንደዚህ ዓይነት ሌሎች ልማዶችን በሙሉ ያደርጉ ነበር፡፡    

እርሱም የጠቆመን ሌላው ነገር ልክ እንደ አሁኑ ጊዜ ለስርቆት የነበረው ቅጣት እጅን መቆረጥ እንደነበር፣ እንዲሁም በአሕዛብ አረቦች ዘንድ የመገረዝም ልምምድ እንደነበረ ይህም በቁርአን ውስጥ በየትኛውም ቦታ ላይ ባይገኝም እንኳን አሁንም በሁሉም ሙስሊሞች ዘንድ እንደሚደረግ ነው፡፡ የዚህ የመጨረሻው አረፍተ ነገር እንደሚከተለው በተናገረው በበርናባስ አፖክሪፋል መልክእት ጸሐፊም ተረጋግጧል፡ ‹እያንዳንዱ ሶሪያዊና አረብ እንዲሁም ደግሞ የጣዖታት ካህናት በሙሉ ተገርዘዋል› ይህ ልማድ በጥንታዊ ግብፃውያንም ዘንድ በስፋት ይተገበር እንደነበረ በሚገባ የታወቀ ነገር ነው፡፡ ኢብን ኢሻቅ ልክ እንደ አቡል ፊዳ በጣም ተመሳሳይ የሆኑ ቃላትን ተጠቅሟል እርሱ የጠቀሰውን ልማድም ጨምሯል ይህም ከአብርሃም ጊዜ ጀምሮ የተላለፈው ኢህላል ይገኝበታል፡፡ ይህም ግርዛት ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም፣ ይሁን እንጂ ከሌሎቹ ከተጠቀሱት ነገሮች ጋር አብርሃም ግንኙነት አለው ብሎ መናገር ግን አይቻልም፡፡ እነዚህም መሐመዳውያን አብርሃም መካን ጎብኝቷል እንዲሁም አሁን ካኣባ በቆመበት ቦታ ላይ አምልኳል በማለት የሚናገሩት መጨመር አይቻልም፡፡

ከዚህ በላይ ከተነገረው ነገር ሁሉ ግልፅ እንደሆነው የእስላም የመጀመሪያ ምንጭ የሚገኘው በመሐመድ ጊዜ ከነበሩት አረቦች የሃይማኖት እምነቶች እና ልምምዶች ውስጥ ነው፡፡ ከዚህም አህዛባዊ ምንጭ እስልምና የብዙ ሚስቶችን ጋብቻ እና የባሪያ ስርዓትን ሁለቱንም ወርሷል፡፡ በእነዚህ ክፉ ውጤቶች ላይ በሌላ ጎኑ ምንም የጨመረው ነገር ባይኖርም፣ መሐመድ እነሱን እንዳሉ በመቀበሉ ለሁልጊዜ ተቀባይነት እንዲኖራቸው አድርጎ አፅድቋቸዋል፡፡

ተቀጥላ ምዕራፍ ሁለት

መሐመድ በእስልምና ውስጥ ያካተታቸው የጥንታዊ አረቦችን ልማዶች እና የሃይማኖት ስርዓቶች ብቻ ሳይሆን የኢምራኡል ቃይስን የጥንት የአረቦች ግጥም ጥቅሶች ወስዶ (ተውሶ) በመጨመሩም ያለፈቃድ የሰውን ሐሳብ በመውሰድ 'plagiarism' ወንጀለኛ ነው ተብሎ አሁንም በምስራቅ አንዳንድ ጊዜ ይነገራል፡፡ የሚነገረውም ከእነዚህ ውስጥ አሁንም በቁርአን ሊገኙ ይችላሉ ተብሎ ነው፡፡ እኔም እራሴ የሚከተለውንም ዓይነት ታሪክ ሲነገር ሰምቻለሁ ይህም፣ የመሐመድ ሴት ልጅ ፋጢማ አንድ ቀን ‹ሰዓቲቱ (የትንሳኤው ቀን) ተቃረበች ጨረቃም ተገመሰ› የሚለውን የቁርአን 54.1 ጥቅስን ታስታውስ በነበረበት ጊዜ፣  የግጥሙ ዋና ገጣሚ ሴት ልጅ ቀርባ እንደዚህ ብላታለች ‹ይህ ጥቅስ ከአባቶቼ ግጥሞች አንዱ ነው የአንቺም አባት ሰርቋቸዋል፣ ከእግዚአብሔርም የተቀበላቸው አስመስሏል› ብላ የተናገረቻት መሆኑን፡፡ ይህ ነገር ምናልባትም እውነት ላይሆን ይችል ይሆናል ምክንያቱም ኢምራኡል ቃይስ የሞተው 540ዓ.ም የክርስትኖች ዘመን አቆጣጠር አካባቢ ነውና፣ መሐመድ ደግሞ የተወለደው በ570 ዓ.ም ‹በዝሆኖቹ ዓመት ነበርና›፡፡

ሆኖም በፐርሺያ ያገኘሁት በድንጋይ ላይ የተቀረፀው ጽሑፍ፣ በጥራዙ መጨረሻ ላይ በኢምራዑል ቃይስ የተጻፉ የተባሉ አንዳንድ ግጥሞችን አግኝቻለሁ፣ ምንም እንኳን በሌሎቹ ባየኋቸው ግጥሞቹ ውስጥ የእሱ መሆናቸው እውቅና ባይሰጣቸውም ነው፡፡ በእነዚህ ጸሐፊያቸው በሚያጠራጥር ትናንሽ ጽሑፎች ውስጥ ከዚህ በታች የተጠቀሱትን ጥቅሶች አግኝቻለሁኝ፡፡ ምንም እንኳን አንዳንድ ግልፅ የሆኑ ስህተቶች ቢኖሩባቸውም፣ ያለምንም እርማት እነርሱን እንዳሉ ማቅረብ የተሻለ መሆኑን አስባለሁኝ፡፡ በላያቸው ላይ የመስመር ምልክት የተደረገባቸው አንቀፆች በቁርአንም ውስጥ ይገኛሉ፡ (ቁርአን 54፣1፣29፣31፣46 ቁርአን 93.1 ቁርአን 21.96 ቁርአን 37.59 ነው)፡፡ በአንዳንዶቹ ቃላቶች ላይ ጥቂት ልዩነት ቢኖርም፣ ትርጉማቸውም ግን አንድ ነው፡፡ ስለዚህም በእነዚህ መስመሮችና በተመሳሳይ የቁርአን ጥቅሶች መካከል አንድ አይነት ግንኙነት ለመኖሩ ግልጥ ነው ማለት ነው፡፡ ስለዚህም በጥያቄ ውስጥ ያሉትን መስመሮች ኢምራኡል ቃይስ ስለመጻፉ ለመጠርጠር ጥሩ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ እነዚህ ከመሐመድ በፊት በነበረ ጸሐፊ ተጽፈዋል ከማለት ይልቅ ከቁርአን ተወስደው ተጨምረው ሊሆን ይችላል፡፡ በሌላ ጎኑ ደግሞ ከእስልምና መመስረት በኋላ በማንኛውም ጊዜ ማንም ሰው ከቁርአን ላይ አንቀፆችን አስመስሎ ወስዶ በእንደዚህ ዓይነት ግጥሞች ላይ ለማስቀመጥ ይደፍራል ብሎ ለመገመት አስቸጋሪ ነው፡፡ አሁንም በሌላ ጎኑ ደግሞ አሁን ባለንበትም ዘመን እንኳን የቁርአንን ጥቅሶች መጥቀስና ቀጥሎ በመጡት ሃይማኖታዊ ወይንም ፍልስፍናዊ ስራዎች (ቅንብሮች) ላይ መጥቀስ የተለመደ ነው፣ ነገር ግን እነዚህ ግጥሞች በዚህ መደብ ውስጥ አይገቡም፡፡ ይህም እንዲህ ዓይነት ጽሑፍ በማይመለከታቸው ውስጥ እንኳን ነው፡፡ መሐመድ ወደ እንደዚህ ዓይነት የጽሑፍ ስርቆት በጣም ታዋቂ ከሆነው ጸሐፊ ኢምራዑል ቃይስ ይወስዳል ብሎ ለመገመት በጣም አስቸጋሪ ነው (ቆይቶ እንደምንመለከተው ምንም እንኳን በጣም ከማይታወቁት የውጪ ምንጮች ቢያደርግም እንኳን)፣ ሆኖም ይሄ በከፊል የተገኘው ያንን እውነታ በመገመት ነው፣ እነዚህ ግጥሞች የሙላካትን ምንም ክፍል ያልሰሩ ቢሆንም፣ በአጠቃላይ በኋለኛው ጊዜ እንደተሰበሰቡት ግጥሞች አልነበሩም፡፡ ለሙላካት ግጥሞች በአጠቃላይ የተሰጠው ዘገባ፣ አንድ ሰው በጣም የተለየ ውብ የሆነን ግጥም በገጠመበት ጊዜ ሁሉ በካኣባ ግድግዳ ላይ ይሰቀል ነበር (ይቀመጥ ነበር)፡፡ እናም በእንደዚህ ዓይነት የከበረ ስብስብ መንገድ ግጥሞቹ የራሳቸውን ስያሜ ያገኙ ነበር፣ ማለትም ‹የተሰቀሉት ግጥሞች› ተብለው በዚህ ባህል በመጠራት፡፡ ታማኝ የሆኑት ዘገባዎች ይሁን እንጂ የስያሜዎች ጅምራ ይህ የነበረ መሆኑን ይክዳሉ ምናልባትም ያ ጠቀሜታው ትንሽ ይሆናል፡፡ ከጠቀስኩት የምስራቃውያን ታሪክ ባሻገር ግን፣ መሐመድ የተከሰሰበት ጽሑፎችን የራሱ አድርጎ በድፍረት የመናገር ግምት የሚያመዝነው እርሱ ምናልባትነትም እንዳልወሰደ ነው፡፡

የአዘጋጁ ማሳሰቢያ፡

ከዚህ በላይ ያየነው የቁርአን ምንጮች ምዕራፍ ሁለት፣ አስገራሚ ነገሮችን እንድናስተውል ይረዳናል፡፡ እስልምና የመጣበት ዓለም በሃይማኖታዊ ልዩ ልዩ ልምምድ የተሞላ ዓለም ነበረ፡፡ በአረቢያ ውስጥ ከመሐመድ በፊት ምን ዓይነት ሃይማኖታዊ ልምምድ እንደነበረ እና ከመሐመድ በኋላ ደግሞ ምን እንደሆነ ተመልከተናል፡፡

እነዚህን ነገሮች ማወቅና የምንከተለው ሃይማኖት ምን ያህል ትክክል እና ለዘላለም ሕይወት ጠቃሚ መሆኑን እንድናስብ ይረዳናል፡፡ የዚህ ገፅ አዘጋጆች ይህንን ጠቃሚ የሆነ ታሪካዊ እውነታ አንባቢዎች ተከታትለው እንዲጨርሱ እየጋበዙ ተከታዩ ምዕራፍ ሦስት እስኪመጣ ድረስ ሌሎች ርዕሶችን እንድትቃኙና መጽሐፍ ቅዱስን እንድታነቡ እንጋብዛችኋለን፡፡

ፍፁም እውነተኛ የሆነው ጌታ እግዚአብሔር ወደ እራሱ እውነት እንዲያመጣችሁ የማያቋርጥ ፀሎታችን ነው፡፡

የትርጉም ምንጭ: THE ORIGINAL SOURCES OF THE QUR'AN 

ሙሉ መጽሐፉ በአማርኛ:  የቁርአን የመጀመሪያ ምንጮች

ለእስልምና መልስ አማርኛ  ዋናው ገጽ