ለሙስሊም ተግዳሮት ምላሾች

ምዕራፍ አንድ

  የመጽሐፍ ቅዱስ ተአማኒነት

በጆን ጊልክራይስት (John Gilchrist)

ትርጉምና ቅንብር በአዘጋጁ

 

የመጽሐፍ ቅዱስና «ቅዱስ» ቁርአን ጽሑፎች ተአማኒነት

1.1 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥንታዊሑፎች (manuscripts)

ከብዙ ዓመታት በፊት አንዲት ወጣት ሙስሊም «መጽሐፍ ቅዱስ ተለውጦ ያውቃል?» ብላ ለጠየቀችኝ ጥያቄ በፍፁም አልተለወጠም ብዬ ብመልስላትም «ታዲያ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ያስተምር የለ እንዴ?» ብላ መልሳልኛለች፡፡ እኔም መልሼ፡- አዎ! በእርግጥ ይህን ያስተምራል፤ እንዲያውም በተደጋጋሚ።  ይህንን ስላት «እንግዲያውስ መጽሐፍ ቅዱስ ተለውጧል ማለት ነው፡፡» ብላ መለሰችልኝ፡፡

 ሙስሊም ጸሐፊዎች በክርስትናው ላይ የሚጽፏቸውን ማንኛውም አይነት ጽሑፎች ወይም በዚህ ጽሑፍ መጨረሻ ላይ የተጠቀሱትን የሙስሊም ምሁራን ጽሑፎች የተመለከተ ማንኛውም ሰው፣ ሙግታቸውን ለማስረዳት የሚያቀርቧቸው መረጃዎች ምን ያህል ደካማና አስተዋይ ተማሪን ለማሳመን የማይችሉ መሆናቸውን ይረዳል፡፡ የዚህ ሚስጥር አንድ ይመስለኛል፡- ሙስሊሞች መጽሐፍ ቅዱስ እንደተለወጠ በጠለቀው ሕሊናቸው አያምኑም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ተለውጧል የሚሉት ጠንካራና በቂ መረጃ በመያዛቸው ሳይሆን፣ ቁርአን የአላህ ቃል መሆኑን የሚያሳምኑበት ሌላ መረጃ ስለሌላቸው ነው፡፡ እውነት ነው ሁለት የማይስማሙ  መጽሐፎች በተመሳሳይ ጊዜ የአምላክ ቃሎች ሊሆኑ አይችሉም፡፡ አንዱ ትክክለኛ የአምላክ ቃል እንዳልሆነ የግድ ሊገለጥ ይገባል፡፡ ከእስልምና ውልደት ጀምሮ መጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ አስተምህሮዎችን ማለትም የክርስቶስን መለኮትነትና የመዋጀት ሥራ በግልፅ እንደሚናገር ስለሚገነዘቡት እንዲህ ያሉ አስተምህሮዎቹን የጎሪጥ ማየት የጀመሩት ዛሬ ሳይሆን በለጋነታቸው ነው፡፡ ስለዚህ ብዙዎቹ  መጽሐፍ ቅዱስን በበጎ ህሊና ለመቅረብ አይደፍሩም፡፡ ከጥንት ጀምሮ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ማንኛውንም ግምታዊ ንግግር ወይም ትችት ከማስተላለፍ አልተመለሱም፤ አይመለሱምም፡፡ በግምታቸው መሠረት መጽሐፍ ቅዱስ ተለውጦ መሆን አለበት! በቁርአን ላይ ያላቸው እምነት የግድ ቀጣይ መሆን ካለበት አማራጩ አንድ ብቻ ነው፤ መጽሐፍ ቅዱስ እውነተኛ መለኮታዊ ቃል እንዳይደለ ማመን፡፡

ለመጽሐፍ ቅዱስ ምንባባት እውነተኛነት መረጃዎቹን ማወቅ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ ይህን ለማስረዳት የሚጠቅሙን ከእስልምና ውልደት ጅማሬ እንኳን በመቶ ከሚቆጠሩ ዓመታት ወደ ኋላ ተጉዘን የምናገኛቸው የጥንት የእጅ ጽሑፎች /manuscripts/ የትኞቹ እንደሆኑ ማወቁ ጠቃሚ ነው፡፡ እነዚህ ጥንታዊ ጽሑፎች ዛሬ በእጃችን ይዘን የምንጠቀምበት መጽሐፍ ቅዱስ ጥንት ይኖሩ የነበሩ አይሁዶችና ክርስቲያኖች ይጠቀሙበት የነበረ መጽሐፍ መሆኑን ያረጋግጡልናል፡፡

 

ሦስቱ ታላላቅ የጥንት ቅጂዎች

ከመሐመድ መነሻ በፊት የነበሩና በግሪክ ቋንቋ የተጻፉ ሦስት ታላላቅ ጥንታዊ የእጅ ጽሑፎች /manuscripts/ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ጽሑፎች የሰብአ ሊቃናቱን /Septuagint/ ብሉይ ኪዳንና ዋናውን የግሪክ አዲስ ኪዳን የያዙ ናቸው፡፡ እነርሱም የሚከተሉት ናቸው፡-

1. ከዴክስ አሌክሳንደሪነስ /codex alxndrinus/

ይህ ጥራዝ ከክርስቶስ ልደት በኋላ በአምስትኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተጻፈ ሲሆን ከአዲስ ኪዳን ውስጥ ከጠፉት ጥቂት ገፆች (ማቴ.1፣1-25፣6 ዮሐ.6፣50-8፣52 እና 2ቆሮ.4፣13-12፣6) በስተቀር ሙሉውን የአዲስ ኪዳንን ንባባት የያዘ ጥንታዊ ጽሑፍ ነው፡፡ በዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለ፣ ነገር ግን አሁን በምንጠቀምበት መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሌለ ምንም አይነት ንባብ የለም፡፡ ይህ መጽሐፍ ብሪታኒያ በሚገኘው ሙዚየም ለንደን ውስጥ ይገኛል፡፡

2. ኮዴክስ ሲናቲከስ /codex sinaiticus/

  ይህኛው እላይ ከተጠቀሰው የበለጠ ጥንታዊ ነው፡፡ በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጅማሬ አካባቢ የተጻፈ ሲሆን ሙሉውን አዲስ ኪዳን እና አብዛኛውን የብሉይ ኪዳን መጽሐፍት ያካተተ ነው፡፡ ለበርካታ ምዕተ ዓመታት ያህል ሩሲያ በሚገኘው ቅዱስ ፒተርስበርግ ቤተ መጽሐፍት ተጠብቆ የቆየ ሲሆን በኋላ ግን አንድ መቶ ሺህ ፓውንድ ለእንግሊዝ መንግስት ተሽጦ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት በብሪትሽ ሙዚየም ተጠብቆ ይገኛል፡፡

3. ኮዴክስ ቫቲካነስ /codex vaticanus/

  ሙሉውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ከያዙ ጥንታዊ ጽሑፎች መካከል በእድሜ ያረጀው ይህ እንደሆነ ይገመታል፡፡ በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተጻፈ ሲሆን አሁን ሮም በሚገኘው የቫቲካን ቤተ መጽሐፍት ውሰጥ ይገኛል፡፡ የመጨረሻዎቹ የአዲስ ኪዳን መጽሐፍት ከዕብራውያን 9.14 እስከ ዮሐንስ ራዕይ መጽሐፍ ፍፃሜ ድረስ በሌላ ሰው እጅ ጽሑፍ የተጻፈ ነው (ምናልባት የመጀመሪያው ጸሐፊ በሞት ወይም በሌላ ምክንያት ሳይጨርሰው ቀርቶ ይሆናል።) ሌላ ምንም ተጨማሪ ነገር ሳንል እነዚህ ጥንታዊ ጽሑፎች ብቻቸውን ከመሐመድ ዘመን በሁለት መቶ ዓመታት እንኳን ወደ ኋላ ብንጓዝ የምናገኛቸው ጥንታዊ ቅጂዎች ናቸው፡፡ ማንም ሰው ማረጋገጥ እንደሚችለው በእነዚህ ቅጂዎች መካከልና አሁን በምንጠቀምበት መጽሐፍ ቅዱስ መካከል  ምንም አይነት ልዩነት የለም፡፡

የመጽሐፍ ቅዱስን እውነተኛነት የሚያረጋግጡ ሌሎች ጥንታዊ መረጃዎች

ከእስልምና ጅማሬ በብዙ ምዕተ ዓመታት ወደ ኋላ ርቀው የሚገኙና የመጽሐፍ ቅዱስን ተአማኒነት የሚያረጋግጡ በርካታ ሌሎች መረጃዎች አሉ፡፡ ከሙስሊሞች ጋር በምትወያይበት ወቅት በሚከተሉት ላይ ትኩረት አድርግ፡፡

1. የሒብሩው ማሶሬቲክትስ ጽሑፍ /The Hebrew Massoretic Text/

ጥንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎችን በባለቤትነት የሚይዙት ክርስቲያኖች ብቻ ሳይሆኑ አይሁዶችም ጭምር ናቸው፡፡ እንደሚታወቀው አይሁዶች ብሉይ ኪዳንን ብቸኛው ቅዱስ መጽሐፋቸው አድርገው ይይዛሉ፡፡ ይህ ቅጂ በዋናው ዕብራይስጥ ቋንቋ የተጻፈና ብሉይ ኪዳን ለመጀመሪያ ጊዜ የተጻፈበት እንደሆነ የሚታወቅ ከመሆኑም በላይ ቢያንስ የአንድ ሺህ ዓመታት እድሜ እንዳለው ይገመታል፡፡

2. የሙት ባህር ጥቅሎች /The dead sea scrolls/

በሙት ባህር አካባቢ በሚገኝ «ኩምራን» በሚባለው በረሃ በሚገኝ ዋሻ ውስጥ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘ ጥንታዊ ጽሑፍ ነው፡፡ ይህ ጥቅልል በዋናው የዕብራይስጥ ቋንቋ የተጻፉ በርካታ የብሉይ ኪዳን ጽሑፎችን ያካተተ ነው፡፡ ከክርስቶስ ልደት በፊት በሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አካባቢ እንደነበረ ጥናቱ ያስረዳል፡፡ ከሁለት ቅጂ የማያንሱ የትንቢተ ኢሳያስ መጽሐፍ ክፍሎች፡- የኢየሱስ ክርስቶስን ሞትና ትንሳኤ (ኢሳያስ 53.1-12)፣ ከድንግል እንደሚወለድ (ኢሳያስ 7.14) እንዲሁም መለኮታዊነቱን (ኢሳያስ 9.6-7) የሚያስረዱ ክፍሎች በዚህ ጥቅልል ውስጥ ተካተው ተገኝተዋል፡፡

3. የሰብአ ሊቃናት ትርጉም /The Septuagint/

"ሰብቱዋጀንት" ወይም «የሰብአ ሊቃናት ትርጉም» የሚለው መጠሪያ ለመጀመሪያው የብሉይ ኪዳን መጽሐፍት ስብስብ (የግሪክ) ትርጉም የተሰጠ ስያሜ ነው፡፡ ይህ ትርጉም ከክርስቶስ ልደት በፊት በሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አካባቢ እንደተዘጋጀ የሚገመት ሲሆን በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን (መዝሙር 2.7፣ 1ዜና 17.11-14) እንዲሁም ዝርዝር የሆኑ የክርስቶስን መከራዎችና የመዋጀት ሞቱን (መዝሙር 22ና 69ን) ጨምሮ በርካታ አስተምህሮዎችን እናገኝበታል፡፡ የጥንቷ ቤተክርስቲያን ይህን ቅጂ በነፃነት ተጠቅማበታለች፡፡

4. የላቲን ብሉይ ኪዳን /The Latin Vulgate/

የሮም ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ላቲን አስተርጉማለች። ይህ ትርጉም ከክርስቶስ ልደት በኋላ በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተዘጋጀ ሲሆን ከዚህ መጽሐፍ በፊት ክርስቶስ ራሱ የሰብአ ሊቃናትን ትርጉምና ሌሎች ቅጂዎችን ተጠቅሞ እንደነበር ይገመታል፡፡ ይህ ትርጉም ልክ እንደ ሰብአ ሊቃናት ትርጉም ከክርስቶስ ልደት በኋላ በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረና ዛሬ የምንጠቀምባቸውን የብሉይና የሀዲስ ኪዳን መጽሐፍት ያካተተ ነው፡፡ ይህ መጽሐፍ በተለይ ለሮም ካቶሊክ ቤተክርስቲያን እንደ ዋና መለኪያ /standard/ የሚቆጠር ነው፡፡

5. የግሪክ አዲስ ኪዳን ክፍሎች /portion of the Greek NT/

ከክርስቶስ ልደት በኋላ ከሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ የነበሩ የግሪኩ አዲስ ኪዳን የተለያዩ ገፆች፣ ክፍልፋዮችና በርካታ ቁርጥራጮች አሁንም በዚህ ዘመን ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ተሰብስበው አንድ ላይ ሲቀናጁ ዛሬ የምናውቀውን አዲስ ኪዳን በትክክል ይሰጡናል፡፡ በነዚህ ስብሰቦችና በዛሬው አዲስ ኪዳን መካከል አንዳችም ልዩነት አናገኝም፡፡ ስብስቦቹን ከሌሎች ጥንታዊ የግሪክና ሮም ቅጂዎች ጋር ማመሳከር ልዩ ስሜት የሚፈጥር ነው፡፡ አብዛኛዎቹ ስብስቦች ከክርስቶስ ልደት በኋላ ከ1000 ዓመታት የማያንስ እድሜ ያስቆጠሩ ናቸው፡፡ በመካከላቸው ያለውን መመሳሰል ስንመለከት ግን የሚያስደንቅ ነው፡፡ በእርግጥም የትኛውም አይነት ጥንታዊ ጽሑፍ ይህን የሚያህል ለቁጥር አዳጋች የሆነ ማስረጃ የለውም፡፡ የግሪክ አዲስ ኪዳን ከበቂ በላይ የሆኑ ማስረጃዎች አሉት፡፡ በዚህ ዘመን የተጻፉ ሌሎች የስነጽሑፍ ውጤቶች እንኳን ይህን ያህል ማስረጃ የላቸውም፡፡

ከሙስሊሞች ጋር በምንወያይበት ወቅት ትኩረት ሊሰጠው የሚገባውና ጠቃሚው ነገር፡- የክርስቶስን ሕይወትና ትምህርቶች ለማወቅ ብቸኛው እና አማራጭ የሌለው መንገድ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ፍፁም እምነትን መጣል ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ በመንፈስ ቅዱስ ምሪት ያልተጻፉት አዋልድ መጽሐፍት ናቸው ተብለው በቤተክርስቲያን የተወገዱት እንኳን የሌሎች ቅዱሳት መጽሐፍትን ዱካ በመጠኑም ቢሆን የተከተሉ ናቸው፡፡ በእርግጠኝነት ልንናገር የምንችለው አንድ ነገር አለን፡- ይኸውም መሐመድ የእስልምና ነብይ መሆኑን የሚያስረዳ በዚያው ዘመን የሚገኝ ታሪካዊም ሆነ ትንቢታዊ ማስረጃ አለመኖሩ ነው፡፡ ሙስሊሞች መጽሐፍ ቅዱስ በትክክል ስለመሐመድ ይተነብያል ይላሉ፡፡ ይህን መሰል ሙግታቸው ግን ውሃ በሚቋጥር መልኩ ተጨባጭ ማስረጃ በማቅረብ ሊያስረዱን አልቻሉም፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ወደፊት በሌላ ንዑስ ርዕስ ሥር የምንለው ስላለን ለአሁን እዚህ ላይ እናብቃ፡፡

ሙስሊሞች መጽሐፍ ቅዱስ እንደተበረዘ ለሚያቀርቡልን ሙግት ዛሬ ያለው መጽሐፍ የተለወጠ መሆኑን ሊያስረዳላቸው የሚችል ታሪካዊ ማስረጃ እንዲያቀርቡ መገዳደሩ አስፈላጊ ነው፡፡ የመጀመሪያው መጽሐፍ ቅዱስ ምን ነበር? ዛሬ በእጃችን ያለው መጽሐፍ ይህን እንዲመስል የተለወጠው ክፍል የቱ ነው? ማነው እነዚህን ለውጦች ያደረገው? መቼ ነው የተለወጡት? ማንኛውንም የተማረም ይሁን ተራውን ሙስሊም መጽሐፍ ቅዱስን ማን እንደለወጠው፣ በየትኛው ዘመን ለውጡ እንደተደረገ፣ በትክክል የትኛው የዋናው መጽሐፍ ቅዱስ ክፍል እንደተለወጠ ማስረጃ እንዲያቀርቡ ብንጠይቃቸው፣ አጥጋቢ ምላሽ የላቸውም፡፡ እንደዚህ አይነት መረጃዎች በፍፁም ሊገኙ አይችሉም፡፡ ሁልጊዜ የሙስሊሞች ጥቃት ምንጩ ምሁራዊ ጥናትና ምርምሮች ሳይሆን «ሊሆን ይችላል» ከሚል ግምት የሚመነጭ መሆኑን አስታውስ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ከቁርአን ጋር የሚጣላ ከሆነ በእነሱ አመለካከት የግድ ስለተለወጠ መሆን አለበት፡፡ አሳዛኙ ነገር ግን፡- አብዛኛው ሙስሊም ማለት ይቻላል የመጽሐፍ ቅዱስ ገፆችን የሚያገላብጠው ስህተት ለመፈለግ እንጂ እውነትን ፍለጋ አለመሆኑ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ብዙዎች ዛሬም መልካም የሚመስል ነገር ግን ወደ ጥፋት በሚመራ ድቅድቅ ጨለማ ተውጠው ይባዝናሉ፡፡

 

1.2 የተለያዩ ጥንታዊ የቁርአን ቅጂዎች

      ሙስሊሞች ከልጅነታቸው ወራት ጀምሮ መጽሐፍ ቅዱስ እንደተለወጠ ቁርአን ግን በተአምራዊ መንገድ ተጠብቆ ሳይለወጥ እንዳለ በመስማት በታላቅ ስህተት እየተቀረፁ ያድጋሉ፡፡ እውነታው ግን በተቃራኒው ነው፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስን ተአማኒነት የሚያስረዱን መረጃዎች ከቁርአን ይልቅ የበዙና ለቁጥር አዳጋች ናቸው፡፡ በተለይም ወደ ሁለት ሺህ ዓመታት ያህል በፈጁ ረጅም አመታት የተሰባሰቡ ስልሳ ስድስት መጽሐፍት የያዘ ከመሆኑ የተነሳ ከቁርአን ለጋ እድሜ አንፃር ልናነፃረው አንችልም፡፡ እንደሚታወቀው ቁርአን በአንድ ሰው እርሱም በመሐመድ አማካኝነት በአጭር አመታት ማለትም በ23 ዓመታት ውስጥ የተገኘ  ከመሆኑ አንጻር በተአምራዊ መንገድ ተጠብቋል የሚያሰኘው አይደለም፡፡ የአንድ ወጣት እድሜን እንኳ በቅጡ ባላሟላ አጭር እድሜ ውስጥ የተፃፈን መጽሐፍ፣ ሙሉውን ለማግኘት ከአንድ ሺህ አራት መቶ አመት  በላይ ከፈጀው መጽሐፍ ቅዱስ ጋር አነፃፅሮ በተአምራዊ መንገድ ተጠብቋል ማለቱ ብዙ ርቀት የማያስኬድ ቅጥፈት ከመሆን አያልፍም፡፡ በአንድ ሰው ተጽፎ እንኳን በርካታ አለመስማማቶች ያሉበትን ቁርአን ከ40 በላይ በሆኑና በተለያየ ዘመንና ባህል እንዲሁም የኑሮ ደረጃ /status/ ውስጥ የነበሩ ሰዎች ከጻፉት መጽሐፍ ጋር አነፃፅሮ «አላህ በተአምራቱ ጠበቀው» ማለት አንደበትንና ጆሮን የሚያቆሽሽ ውሸት ከመሆን አያልፍም፡፡ እነዚህን ሁሉ ሚዛናዊ ምልከታዎች መሠረት በማድረግ በእርግጥም ተጠብቆ ያለው የአምላክ ቃል መጽሐፍ ቅዱስ እንጂ ሌላ እንዳልሆነ በግልፅ ማየት እንችላለን፡፡ ጥንታዊ የቁርአን ቅጂዎች ላይ የደረሰው ነገር ምንድነው? እስኪ የሚከተሉትን እውነታዎች ለመጽሐፍ ቅዱስ ተአማኒነት ከዘረዘርናቸው ጥንታዊ ቅጂዎች ጋር በማነፃፀር እንመልከት፡-

የመጀመሪያው የቁርአን ንባባት ስብስብ

መሐመድ በሕይወት በነበረበት ዘመን ቁርአን አንድ ወጥ በሆነ መልኩ የተጻፈ አልነበረም፡፡ የመሐመድን ሕይወትና ትምህርቶች በመዘገብ ተአማኒ ከሆኑት ሀዲሶች መካከል በአንዱ ላይ እንደተዘገበው፣ ከመሞቱ ጥቂት ጊዜ በፊት እንኳን የቁርአን ንባባት በብዛት ይወርዱ እንደነበር እናነባለን እንደውም ይህ ወቅት ታላላቅ መገለጦች የተገኙበት ወሳኝ ጊዜ እንደነበር ይናገራል፡- ሳሂሁ አል ቡካሪ ጥራዝ 6 ገጽ 474/Sahih al-Bukhari, Vol.6,P.474/ በዚህ ምክንያት የተለያዩ የቁርአን ሱራዎችን በአንድ ለማሳባሰብ ጥረት አልተደረገም እንዲያውም በሕይወት ባለበት ጊዜ ሁሉ ተጨማሪና በርካታ ሱራዎች ይጠበቁ ነበር፡፡

ቁርአንን በአንድ ለማሳባሰብ የመጀመሪያ ሙከራ የተደረገው ከመሐመድ ሕልፈት በኋላ ነው፡፡ ከላይ የተጠቀሰው ሐዲስ እንደሚያስረዳን፣ ከመሐመድ በኋላ የመጀመሪያው ከሊፋ በመሆን የመሪነቱን ሥፍራ የያዘው አቡበከር በወቅቱ ቁርአንን በቃሉ በመሸምደድ የሚታወቀውን ዛይድ ኢብን ሳቢት ሱራዎቹን እንዲሰበስብ ኃላፊነት ሰጥቶት ነበር፡፡ ዛይድ ኢብን ሳቢት እንደዘገበው ሱራዎቹን ከተለያዩ ነገሮች ላይ ማለትም ከተምር ዛፍ ቅጠሎች /አገዳ/፣ ጠፍጣፋና ነጭ ድንጋዮችና ከሌሎች በርካታ ነገሮች ላይ እንዳሰባሰባቸው ነው የምንረዳው፡፡ በተለይም የተለያዩ ሱራዎችን በቃላቸው ይወጡ ከነበሩ ሰዎች በማነፃፀር እንደጠረዘው ዘግቧል፡፡ ቢያንስ አንድ የሱራ አንቀጽ እንኳን በአንድ ሰው ዘንድ ማግኘት ይቻል ነበር /sahih al bukhari,vol.6,p.478/ እንግዲህ በዚህ መልክ የተሰባሰቡበትን ነው ፍፁም ስህተት እንደሌለባቸው ሙስሊሞች የቆጠሩት፡፡

በወቅቱ ይህ ስብስብ በመጀመሪያው ካሊፍ ትዕዛ የተፈፀመ ከመሆኑ ውጪ፣ በጊዜው በጥራዙ ላይ የነበረው ፍላጎት ያን ያህል አልነበረም፡፡ በኋላ ላይ ይህ የመጀመሪያ ስብስብ ሐፍሳ በተባለችው የቀድሞ የመሐመድ ሚስት እጅ ላይ ወድቋል፡፡ /Shahih al Bukhari, Vo.6 P.478/ ከዚህ ስብስብ በኋላ ሌሎች ለመሐመድ ቅርብ የነበሩ ሰዎች ሱራዎችን ማሰባሰብ ጀምረው እንደነበር ይታወቃል። የአሰባሰቡ ሂደት በቅጡ ከሚታወቁት ሱራዎች ጋር ተቀራራቢ መሆኑን መርህ ያደረገ መሆን እንዳለበት ትኩረት የሚሰጠው ነበር፡፡

1. አብዱላህ ኢብን ሚስኡድ

እስልምናን ከመነሻው ከተቀበሉት መካከል አንዱ የነበረ ሰው ሲሆን ቁርአንን ለማስተማር ብቁ ናቸው ብሎ መሐመድ ከጠቀሳቸው አራት ሰዎች መካከል አብዱላህ የመጀመሪያና ዋና እንደሆነ ተዘግቧል / Sharih al-Bukhari, Vol.5,P.96/ ይህ ሰው የራሱን የቁርአን ጥራዝ እንዳዘጋጀ በትክክል ይታወቃል፡፡ ጥራዙ በአንድ ወቅትና ቦታ እውቅና የተሰጠው ስብስብ ነበር፡፡ አብዱላህ ብሎታል ተብሎ እንደሚዘገበው መጽሐፉን ከእርሱ ውጪ በቅጡ የሚያውቀው እንደ ሌለ ነው /Sahih al-Bukhari, Vol.6,P,488/

2. ሳሊም፡- ነፃ የወጣው የአቡ ሁድሐይፋ ባርያ

መሐመድ በግልጽ ከዘረዘራቸው አራት የቁርአን አዋቂዎች መካከል ሁለተኛው ነው፡፡ ምንም እንኳን በያማማ ጦርነት ላይ ብዙም ከመሐመድ ሳይርቅ የተገደለ ቢሆንም ቁርአንን በአንድ ጥራዝ ለማሰባሰብ የመጀመሪያው እንደሆነ ይነገርለታል። ሙሻፍ ማለት በእጀ ጽሑፍ የተዘጋጀ ጥራዝ ማለት ነው፡፡ /As suyuti, Al-Itqan fii ‘ulum al-qur’an, vol.1,p.135/

3. ኡባይ ኢብን ካአብ

ይህም ሰው ከተጠቀሱት አራት መካከል አንዱ ሲሆን በአንድ ወቅት መሐመድ እንኳን በአላህ አማካይነት ኡባይ ቁርአንን ሲቀራ እንዲያዳምጥ ታዞ እንደነበር ተዘግቧል፡፡ ኡባይ «ሳይድ አል ቁርአን» በሚል መጠሪያ ይታወቅ የነበረ ሰው ነው፡፡ ይህም ምን ያህል ውብና ከሌሎች በተሻለ መልኩ ቁርአንን ይቀራ እንደነበር ለማመልከት ነው፡፡ ይህ ሰው የራሱ የቁርአን ስብስብ የነበረው ሲሆን ስብስቡ በሶሪያ ፍፁም ተመራጭ ነበር፡፡

ከነዚህ በተጨማሪ ሌሎች በርካታ ስብስቦች ነበሩ፡፡ በወቅቱ በተመሳሳይ ወቅት ተሰባስበው ከነበሩት መካከል አሊ፣ ኢብን አባስ፣ አቡ ሙሳ፣ አናስ ኢብን ማሊክ እና ኢብን አል ዙቤር ያሰባሰቧቸው በጣም ታዋቂዎቹ ናቸው፡፡

 

የተቀሩት የቁርአን ስብስቦች እንዲቃጠሉ በኡስማን መታዘዙ

ሦስተኛው የእስልምና ካሊፍ ኡስማን በነገሠበት ወቅት በተለያዩ ክፍለ ግዛቶች የሚገኙ ሙስሊሞች በቁርአን አነባበብ ላይ እንደሚለያዩ ተነገረው፡፡ በዚህ ወቅት ኡስማን የእስልምናውን ማህበረሰብ /ኡማ/ ወጥና ልዩነት በሌለው ቁርአን /ሙሻፍ ዋሂድ/ አንድ ማድረግ እንዳለበት ከውሳኔ ላይ ደረሰ፡፡ በዚህም መሠረት ከላይ የጠቀስነውን እና በዛይድ ኢብን ሳቢት አማካይነት የተሰባሰበውን የቁርአን ጥራዝ ከሀፍሳ ዘንድ በማስመጣት ዛይድ  ከሌሎች አራት ሰዎች ጋር በመቀናጀት በሰባት ተመሳሳይ ግልባጭ እንዲያዘጋጁት ትዕዛዝ ሰጠ፡፡ በመቀጠልም ለእያንዳንዱ ክፍለ ግዛት አንድ አንድ እንዲላክና በእጃቸው የሚገኘውን ከዚህ ቅጂ ጋር የማይመሳሰለውን ስብሰባው እንዲያቃጥሉት አዘዘ፡፡ /Sahih al-Bukhari, Vol.6 P479/ በተለይም የአብዱላህ ኢብን ማስኡድ እና የኡባይ ኢብን ካአብ ስብስቦች ተለይተው ወጥተው እንዲወድሙ ተደረገ፡፡

የካሊፋውን ትዕዛዝ በጽኑ ከተቃወሙት መካከል የመጀመሪያው አብዱላህ ኢብን ማስኡድ ዋነኛው ነበር፡፡ የዛይድ ቅጂ እውቅና ሳይሰጠው ለረጅም ጊዜ የቆየ ከመሆኑ ባሻገር  እንዲሁ በወቅቱ የተከሰተውን ችግር ለመፍታት አመቺ እንዲሆን የታሰበ ነበር፡፡ በተለይ የሙስሊም ቡድን ዘንድም የሚገኝ አልነበረም፡፡ አብዱላህ የካሊፋውን ትዕዛዝ ሲቃወም ያቀረበው መረጃ ሰባ የሚያህሉ ሱራዎችን በቀጥታ ከመሐመድ እንዳገኛቸው በመናገር ነበር፡፡ እነዚህን ሱራዎች ሲያሰባስብ ዛይድ ገና ልጅ እንደነበር ተሟግቷል፡፡ ለምንድነው ታዲያ በዚህ መንገድ ያገኛቸውን ሱራዎች ቸል እንዲል የሚገደደው? /Ibn Abi Dawud kitab al-Masahif, P.15/ ይህ ሰው ተቃውሞውን በግልፅ ሲያስቀምጥ ቁርአን በዛይድ ሳይሆን በመሐመድ ሲቀራ ማድመጥ እንደሚመረጥ ተናግሯል፡፡ በተለይም ዛይድ ያሰባሰበው የቁርአን ጥራዝ ጎዶሎ እንደሆነና ሊታመን እንደማይችል በፅናት ሲያስረዳ «ሕዝቡ ትክክለኛ ያልሆነ ቁርአን በማንበባቸው ተታለዋል በዚህም ወንጀለኞች ሆነዋል፡፡» ብሏል። /Ibn said,kitab al-Ta baqat al-kabis, Vol.2 P144/

ምንም እንኳን የዛይድ ስብስብ ከሌሎች በርካታ ስብስቦች መካከል አንዱ እንደነበረ ቢታወቅም በተጨማሪም ብቸኛውና ትክክለኛው ቅጂ ለመሆኑ ምንም ማስረጃ ባይኖርም በካሊፋው ትዕዛዝ መሠረት እውቅና ሊያገኝ ችሎአል፤ እንደዋና ቅጂም ተቀባይነት ተሰጥቶታል፡፡ እስከዚህም ዘመን ድረስ ሊቆይ ችሏል፡፡ በኋላ ላይ በዚህ ምዕራፍ የተለያዩና እርስ በእርስ የማይጣጣሙ ንባባትን እያነፃፀርን እንመለከታለን፡፡ በዚሁ መልኩ ጎን ለጎን መጽሐፍ ቅዱስንም እንመለከታለን፡፡ በዚህ ንኡስ ክፍል ላይ ግን ዋናው ትኩረታችን በአሳዛኝ ሁኔታ በኡስማን አማካይነት ለእሳት ማገዶ ስለተደረጉት ጥንታዊ የቁርአን ቅጂዎች ነው፡፡ የበለጠ አሳዛኙ ነገር ግን የቅጂዎቹ መቃጠል ብቻ ሳይሆን መሐመድ ራሱ ቁርአንን በሚገባ ያውቃሉ እንዲያውም ለማስተማር ብቁ ናቸው ብሎ ከጠቀሳቸው አራት ሰዎች መካከል በሁለቱ የተሰባሰበውን ስብስብ እንኳን ለማቃጠል አለመታፈሩ ነው፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ የተቃጠለው በጠላቶቹ እንጂ በክርስቲያኖች ወይም በአይሁዶች አይደለም፡፡ ኡስማን ግን ሃፍሳ ከመኝታዋ በታች ደብቃ ላስቀመጠችው አንድ ቅጂ ሲል በርካታ ስብስቦች በእሳት ውስጥ እንዲወድሙ አድርጓል፡፡ በእጁ ላይ ለነበረ ቅጂ ብሎ ሕዝቡ ይጠቀምባቸው የነበሩት እሳት እንዲበላቸው ተፈረደ፡፡ እንግዲህ ይህን ሁሉ አሻጥር ስንመለከት ዛሬ ሙስሊሙ አለም የሚጠቀምበት ቁርአን ምን ያህል ብቸኛና በርካታ ጓደኞቹን ያጣ ምስኪን ስብስብ እንደሆነ ማስተዋል ይቻላል፡፡ በእሳት እንኳን ከጠራ በኋላ ዛሬም አስቀያሚ ጥላሸቱ በላዩ ላይ በጉልህ ስለሚታይ፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚነፃፀር አቅም የለውም፡፡ ምንም እንኳን መጽሐፍ ቅዱስ ስለቁርአን የሚሰጠው ምስክርነት ባይኖርም በስምም ባያውቀውም ቁርአን ግን በተቃራኒው ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የሚመሰክራቸው አንዳንድ እውነታዎች አሉት፤ በሌላ ቦታ መልሶ ቢያጣጥላቸውም!!

 

የትርጉም ምንጭ: Facing the Muslim Challenge  A Handbook of Christian-Muslim Apologetics

ሙሉ መጽሐፉ በአማርኛ: ለሙስሊም ተግዳሮት ምላሾች

ለእስልምና መልስ አማርኛ  ዋናው ገጽ