በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አሉ የሚባሉ ቅራኔዎች
‹ወደ ፍርድም አስቀድሞ የገባ ፃድቅ ይመስላል፣ ባላጋራው መጥቶ እስኪመረምረው ድረስ› ምሳሌ 18.17
የቅራኔዎች መኖር ውንጀላ
በ Jay Smith, Alex Chowdhry, Toby Jepson, James Schaeffer
[ክፍል አንድ] [ክፍል ሁለት] [ክፍል ሦስት] [ክፍል አራት] [ክፍል አምስት] ክፍል ስድስት
ትርጉምና ቅንብር በአዘጋጁ
ጥያቄ 31 - የኢኮንያን አባት ማን ነበረ?
በማቴዎስ 1.11 መሠረት ኢዮስያስ ወይንስ በ 1ዜና 3.16 መሠረት ኢዮአቄም ነበረ? ይህ ዓይነቱ ቅራኔ መሳይ ሐሳብ የዕብራውያኑን አጠቃቀም ካለማወቅ የሚመጣ የመረዳት ችግር ነው፡፡
ይህ ጥያቄ ከጥያቄ 30 ጋር በጣም ተመሳሳይ ነው የኢኮንያን አባት ኢዮአቄም ነበር እንዲሁም ኢዮስያስ የእርሱ አያት ነበር፡፡ ይህ ደግሞ ተቀባይነት ያለው ውጤትና ከማቴዎስ የትውልድ ሐረግ ዕይታ አንፃር ተቀባይነት ያለው እንጂ ከስህተት ጥቆማ የተነሳ የመጣ አይደለም፡፡
ጥያቄ 32 - የትውልዶች ቁጥር ስንት ነበር?
ከባቢሎን ምርኮ እስከ ክርስቶስ ልደት የነበሩት ትውልዶች በማቴዎስ 1.17 መሠረት አስራ አራት ነበሩ ወይንስ በማቴዎስ 1.12-16 መሠረት አስራ ሦስት ነበሩ?
ይህም የዕብራውያንን የአረፍተ ነገር አወቃቀር አጠቃቀም ካለማወቅ የተነሳ የሚመጣ ችግር ነው፡፡
ማቴዎስ ምዕራፍ 1.17 ላይ በግልፅ እንደተቀመጠው የነበሩት አስራ አራት ትውልዶች ነበሩ፡፡ በመጀመሪያውም ክፍል አስራ አራት ስሞች ነበሩ፣ በሁለተኛው አስራ አምስት እና በሦስተኛው ደግሞ አስራ አራት ይገኛሉ፡፡ ምናልባትም ይህንን ችግር ለመፍታት ቀላሉ የሚሆነው አካሄድ በሁለተኛው መጨረሻ ቁጥር 11 ላይና በሦስተኛው ክፍል ውስጥ ቁጥር 12 መጀመሪያው ላይ አንዱ ሰው ሁለት ጊዜ ስለተጠቀሰ ነው፡፡ በመሆኑም በሁለተኛው ላይ አስራ አምስት ሲያስመስለው በሦስተኛው ላይ ደግሞ አስራ ሦስት አስመስሎታል፡፡ ለማንኛውም የማቴዎስን የትውልድ አቀማመጥ የምንረዳው በስህተትነቱ ሳይሆን ከጽሑፍ ውበትና የትውልድ መያያዝ የአጻጻፍ ልዩ ዘይቤ ጋር ብቻ ነው፡፡ ስለዚህም በእርሱ በኩል ስህተት አለ የሚለው አነጋገር የሚያሳየው ምንምማረጋገጫ የለም፡፡
ጥያቄ 33 - የሳላ አባት ማን ነበር?
የሳላ አባት ማን ነበር በሉቃስ 3.35-36 መሰረት ቃይናን ነበርን ወይንስ በዘፍጥረት 11.12 መሠረት አርፋክስድ ነበር?
ይህም ጥያቄ የመነጨው የዕብራውያንን አጠቃቀም ካለማወቅ የተነሳ ብቻ ነው፡፡ ለዚህም በጣም የቀረበው ምላሽ የሚሆነው በጣም አሳማኙ መልስ በማሶሬቲክ ቴክስት ላይ ያለው የትውልድ ሐረግ ነው ይህም የሚያቀርበው ልክ ማቴዎስ እንዳደረገው ነው፡፡ የሴፕቱጀንቱንም በምንመለከትበት ጊዜ ቃይናን የሚለውን ስም የሴላ አባት ሆኖ ተጨምሮ እናገኛለን ይህም በሉቃስ ላይ የምናገኘውን እውነታ ያሳየናል፡፡ የሉቃስ ጽሑፍ በግሪክ ምናልባትም የሴፕቱጅንቱን እንደ ዋና ምንጭ አድርጎት ተጠቅሞበት ሊሆን ይችላል፡፡
በተመሳሳይም መንገድ የሴፕቱዋጀንቱን የምንጠቅስ ከሆነ የዘፍጥረት 11.12 ስንመለከት አርፋክስድ የ135 ዓመት ዕድሜ የነበረው ሰው ነበር እንጂ የ35 ዓመት ሰው አልነበረም (ይህም እርሱን የሴላ የቅድመ አባት ለመሆን የሚያበቃው ዕድሜ ነበር ማለት ነው) በዚህም መሰረት አርፋክስድ በትውልዱ ሐረግ ውስጥ እንደነበረ ደግሞም በትክክል ቅድመ አባት እንደነበረ ነው፣ በመሆኑም የምንመለከተው ቅራኔ ወይንም ስህተት በዚህም ላይ አይኖርም፡፡
ጥያቄ 34 - መጥምቁ ዮሐንስ ኤልያስ ነበር ወይንስ አልነበረም?
መጥምቁ ዮሐንስ በማቴዎስ 11.14፣ 17.10-13 መሰረት የሚመጣው ኤልያስ ነበር፤ በዮሐንስ 1.19-21 መሰረት ግን አልነበረም፡፡
ይህ ዓይነት ችግር የሚመነጨው የታሪካዊ ዓውዶችን ካለመረዳት ነው፡፡
ማቴዎስ የመዘገበው መጥምቁ ዮሐንስ የሚመጣው ኤልያስ ነው በማለት ነው፡፡ ዮሐንስ ደግሞ የመዘገበው መጥምቁ ዮሐንስ እራሱም እኔ ኤልያስ ነኝ ብሎ አያውቅም ደግሞም ሃሳቡን አልተቀበለውም በማለት ነው፡፡ ለዚህም ምክንያቱ በጣም ግልጥ ነው በዚህ ውስጥ የሚታየው አለመስማማት የሚመስል ነገር በአንባቢዎች ዘንድ ብዙ ጊዜ የሚገኘው አንድ ዓውድን በትክክል ያለመዳት ችግር ነው፡፡
በጊዜው የነበሩት ካህናትና ሌዋውያን ወደ መጥምቁ ዮሐንስ መጥተው እርሱ ኤልያስ መሆን ወይም አለመሆኑን ጠይቀውት ነበር፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ጥያቄ አንድን ሰው ለመጠየቅ በጣም አስገራሚ ጥያቄ ነው ይህም የሚሆነው የአይሁድን ቅዱስ ቃላት የማታውቁ ከሆነ ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር በሚልክያስ ትንቢት ውስጥ የተናገረው ነገር ከተወሰነ ጊዜ በፊት ነቢዩን ኤልያስን እንደሚልክላቸው ተናግሯቸው ነበርና ነው፡፡ ስለዚህም የአይሁድ ሕዝብ ኤልያስን ይጠብቁ ስለነበር ጥያቄያቸው እራሱ ትክክለኛም ሎጂካልም ነበር፡፡
ይህንን ጥያቄ ሲጠየቅ ዮሐንስ 30 ዓመት ይሆነው ነበር፡፡ ወላጆቹ ሞተዋል እርሱም ከሌዊ ነገድ የነበረው የዘካሪያስ ብቸኛ ልጅ ነበር፡፡ ስለዚህም እርሱ ኤልያስ መሆን አለመሆኑን ሲጠየቅ ኤልያስ ከእርሱ 878 ዓመት በፊት ወደሰማይ ተወስዶ ስለነበር፣ መልሱ በትክክል አይደለሁም ነበር ማለትም እኔ ኤልያስ አይደለሁም ነበር፡፡
ጌታ ኢየሱስም እራሱ በተዘዋዋሪ መንገድ ዮሐንስ መጥምቁ ኤልያስ እንዳልነበረ መስክሯል በማቴዎስ 11.11 ላይ ዮሐንስ ከእርሱ በፊት ከተወለዱት ከሁሉም የበለጠ ሰው ነበር በማለት ተናግሮ ነበር፡፡ ሙሴ ከኤልያስ የበለጠ ነበር ነገር ግን መጥምቁ ዮሐንስ ከሁለቱም የበለጠ ነበር፡፡
ስለዚህም ጌታ ኢየሱስ ስለ ዮሐንስ እርሱ የሚመጣው ኤልያስ ነው በማለት ሲናገር ምን ማለቱ ነበር? መልአኩ ገብርኤል ለዘካርያስ ስለ ወንድ ልጁ ሲናገር ዮሐንስ ገና አልተወለደም ነበር የተናገረው ነገር “እርሱ በጌታ ፊት ይሄዳል እርሱም የተዘጋጁትን ሕዝብ ለጌታ እንዲያሰናዳ፥ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች የማይታዘዙትንም ወደ ጻድቃን ጥበብ ይመልስ ዘንድ በኤልያስ መንፈስና ኃይል በፊቱ ይሄዳል።” በማለት ነበር ሉቃስ 1.17፡፡
መልአኩ ወደ ሁለት ትንቢቶች ጠቅሶ ነበር ወደ ኢሳያስ 40.3-5 እና (ሉቃስ 3.4-6 ተመልከቱ ይህ እንደገና ለመጥምቁ ዮሐንስ እንደተጠቀሰ) እንዲሁም ሚልኪያስ 4.5-6 ነበር ከዚህ በላይ የተጠቀሰው እርሱም የሚለው፤ “እነሆ፥ ታላቁና የሚያስፈራው የእግዚአብሔር ቀን ሳይመጣ ነቢዩን ኤልያስን እልክላችኋለሁ። መጥቼም ምድርን በእርግማን እንዳልመታ እርሱ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች፥ የልጆችንም ልብ ወደ አባቶች ይመልሳል።”
ገብርኤል ያለምንም ስህተት የተናገረው ነገር መጥምቁ ዮሐንስ በነቢዩ በሚልክያስ በኩል እግዚአብሔር የተናገረው ፍፃሜ ነው በማለት ነበር፡፡
ስለዚህም መጥምቁ ዮሐንስ ኤልያስ ነበርን? አልነበረም ነው መልሱ፡፡ ነገር ግን ካህናቱና ሌዋውያኑ ጠይቀውት ነበር “አንተ ከነቢያት አንዱ ነህን ሚልኪያስ ስለ ኤልያስ እንደተናገረው?” ተብሎ ቢጠየቅ ኖሮ የዮሐንስ መልስ አዎንታዊ ይሆን ነበር፡፡
በማቴዎስ 17.11-13 ላይ ጌታ ኢየሱስ የሚልኪያስ ትንቢት ትክክል እንደነበረ ነው ያሳየው እርሱም ሲናገር ነገር ግን ኤልያስ መጥቶ ነበር ብሏል፡፡ እርሱም አለ ይህ ኤልያስ ስቃይን ተቀብሏል ልክ እርሱ ጌታ ኢየሱስ እንደሚቀበለው መከራ “ደቀመዛምርቱ የተገነዘቡት እርሱ ስለ መጥምቁ ዮሐንስ ይናገር እንደነበረ ነው” ስለዚህም አንድ ጊዜ አውዱን ከተገነዘብን ነገሩ ሁሉ በጣም ግልጥ ይሆንልናል ዮሐንስ ቃል በቃል ኤልያስ አልነበረም ነገር ግን ስለ ኤልያስ የተነገረው የትንቢት ፍፃሜ ነበር እርሱም ለመሲሁ ቅድሚያ መንገድን የሚያዘጋጀው ሰው ነበር “የዓለምን ሁሉ ኃጢአትን የሚያስገድወድን የእግዚአብሔርን በግ” ዮሐንስ 1.29 የመምጣትን መንገድ የሚያዘጋጀው ሰው እርሱ ነበር፡፡
ጥያቄ 35 - ጌታ ኢየሱስ የዳዊትን ዙፋን ይወርሳል ወይንስ አይወርስም?
ጌታ ኢየሱስ በሉቃስ 1.32 መሰረት የዳዊትን ዙፋን ይወርሳል ወይንም በማቴዎስ 1.11 1 ዜና 3.16 እና ኤርምያስ 36.30 መሰረት አይወርስም? ይህ መልስ የሚመሳሰለው በቀጥታ ከጥያቄ ቁጥር 26 ጋር ነው፡፡ ማለትም የማቴዎስ የዘር ግንድ የዮሴፍን የዘር ግንድ ከመከተሉ ጋር ተያይዞ ነው፡፡ ከኤርምያስ 36.30 ላይ ብንነሳ በጣም ግልጥ የሆነው ነገር የዮሴፍ የስጋ የዘር ግንድ በዳዊት ዙፋን ላይ ለመቀመጥ ብቁ ይሆን ነበር ምክንያቱም እርሱ እራሱ ከኢኮንያን ዘር የመጣ ነበርና፡፡ ይሁን እንጂ ማቴዎስ ግልፅ እንዳደረገው ሁሉ ጌታ ኢየሱስ የዮሴፍ የስጋ ዝርያ አልነበረውም፡፡ ማቴዎስ የዮሴፍን ዝርያ ከኢኮንያን ዘር የመምጣቱን ችግር ከዘረዘረ በኋላ በመቀጠል ያቀረበው የድንግልን መውለድ ነው፡፡ ስለዚህም እርሱ ያረጋገጠው ጌታ ኢየሱስ የኢኮንያንን ችግር እንዳስወገደውና በዳዊት ዙፋን ላይ ለመቀመጥ የሚችል በመሆኑ እንደቀጠለ ነው፡፡ ሉቃስ በሌላ መንገድ ያሳየው የጌታ ኢየሱስ ትክክለኛ የስጋ ዝርያ ከኢኮንያን ውጭ በሆነ መንገድ ከዳዊት መሆኑን ነው፣ ስለዚህም እርሱ የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ለመውረስ የሚችል ሙሉ ብቃት ያለው መሆኑን ነው፡፡ በሉቃስ 1.32 ላይ ያለው የመልአኩ አዋጅ ይህንን ስዕል ሙሉ ያደርገዋል፡፡ “እርሱ ታላቅ ይሆናል የልዑል ልጅም ይባላል፥ ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤” ይህን የመለኮት ውሳኔ ከስጋ ዝርያው ጋር በአንድ ላይ አስቀምጦ እርሱን በስጋ የዳዊትን ዙፋን ትክክለኛ ወራሽ ያደርገዋል፡፡
ጥያቄ 36 - ጌታ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም የገባው እንዴት ነበር?
ጌታ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም የገባው በማርቆስ 11.7 እና በሉቃስ 19.35 መሰረት በአንድ አህያ ግልገል ላይ ነበር ወይንስ ማቴዎስ 21.7 መሰረት በአንድ የአህያ ግልገልና አህያ ላይ ነበር?
ይህ አይነቱ ስህተት ቃሉን በተሳሳተ መንገድ ከማንበብና ታሪካዊ ዓውዱን ካለመረዳት የሚመነጭ ነው፡፡
እዚህ ላይ ያለው ክስ ጌታ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም በስንት አህያ ላይ እንደገባ ወንጌል የሚያቀርበው ዘገባ እርስ በእርሱ ይቃረናል በማለት ነው፡፡ ይህ ክስ የተመሰረተው የማቴዎስን ወንጌል በትክክል ካለማንበብና ስለዚህ ክስተት የሚናገረውን ሙሉ ነጥብ ከመዝጋት ወይንም በትክክል ካለማየት የተነሳ ነው፡፡
በመጀመሪያ መታወቅ ያለበት ነገር አራቱም ወንጌሎች ስለዚህ ክስተት እንደሚናገሩ ነው፣ ከዚህ በላይ ካለው ነገር ሁሉ ውስጥ የጎደለው ማገናዘቢያ በዮሐንስ 12.14-15 ላይ ያለው ነው፡፡ ማርቆስ ሉቃስ እና ዮሐንስ ሦስቱም የሚስማሙት ጌታ ኢየሱሰ በአህያ ግልገል ላይ እንደተቀመጠ ነው፡፡ እዚህ ላይ ሎጂክ የሚያሳየው ነገር ምንም ቅራኔ እንደሌለ ነው ምክንያቱም ኢየሱስ በአንድ ጊዜ በሁለት አህዮች ላይ ሊቀመጥ አይችልምና ስለዚህም ጥያቄ ሆኖ መነሳት ያለበት ማቴዎስ ስለምንድነው ሁለት እንስሶችን የጠቀሰው? የሚለው ሲሆን ለዚህም ምክንያቱ በጣም ግልጥ ነው፡፡
ማቴዎስን በራሱ ነጥለን እንኳን በማየት ከአረፍተ ነገሩ ልናይ የምችለው ነገር ጌታ ኢየሱስ በሁለት እንስሶች ላይ እንዳልተቀመጠ፤ ነገር ግን በግልገሉ ላይ ብቻ እንደተቀመጠ ነበር፡፡ ስለ ሁለቱ ጥቅሶች ሻቢር አላይ የጠቀሰው እኛ በማቴዎስ ላይ ከብሉይ ኪዳን ሁለት ትንቢቶችን እንደተጠቀሰ ነው በማለት ኢሳያስ 62.11 እና ዘካርያስ 9.9 አንድ ላይ ጠቁሟል፡፡ ማቴዎስም የጻፈው
“ለጽዮን ልጅ። እነሆ፥ ንጉሥሽ የዋህ ሆኖ በአህያ ላይና በአህያይቱ ግልገል በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል በሉአት ተብሎ በነቢይ የተነገረው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሆነ።“ ማቴዎስ 21.5፡፡
አህያን ከዚያም “አህያ ግልገል፣ በአህያ ውርንጫ” በማለት ዘካርያስ የተጠቀመው አስደናቂ የሆነውን የዕብራውያንን የኣረፍተ ነገርን ግጥማዊ አቀማመጥን ነው ይህም በተለምዶ “ትይዩአዊ” በመባል የሚታወቀው ነው፡፡ ይህም አንድን ነገር በቀላሉ በሌላ መንገድ ማለትም ትይዩአዊ በሆነ መንገድ የሚደግም አጻጻፍ ነው፡፡ ይህም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በጣም የተለመደ ነው (ለምሳሌም ያህል መዝሙር 119.105 መመልከት ይቻላል፤ “ሕግህ ለእግሬ መብራት፥ ለመንገዴ ብርሃን ነው።”
ይህም አንዱን ነገር በተከታታይ ተናግሮታል)፡፡ ስለዚህም አንድ እንሰሳ ብቻ ለመቀመጫነት እንደተጠቀሰ በጣም ግልፅ ነው፡፡ ስለዚህም ማቴዎስ በግልጥ የተናገረው ጌታ ኢየሱስ በአንድ የአህያ ግልገል ላይ እንደተቀመጠ ነው ይህም ከሌሎቹ ሦስት ወንጌሎች ጋር ይስማማል፡፡
ስለዚህም ማቴዎስ አህያዋና እናቱ በቁጥር 7 ላይ አብረው ነው የመጡት ያለው ለምንድነው? አሁንም ምክንያቱ በጣም ቀላል ነው፡፡ ከማርቆስና ከሉቃስ ይልቅ የክስተቱ የዓይን ምስክር የነበረው ማቴዎስ ብቻ ነበር፡፡ (ሌሎቹ በቦታው ላይ አልነበሩምና)፡፡ ስለዚህም እርሱ እዚህ ላይ የሚያስገነዝበው የግልገሉን ገና ልጅ መሆን ማለትም ከእናቱ ለመለየት ገና እንደነበረች ነው፡፡ ግልገል አህያ፤ ማለትም ከዚህ በፊት ሰው ያልተቀመጠበት የሚለውም የሚያሳየው ገና ከእናቱ ጋር ያልተለያየ መሆኑን ነበር፡፡ ወደ ኢየሩሳሌም መጓዙንም ቀላል የሚያደርገው ግልገሉ ከእናቱ ጎን ለጎን አብሮ ይጓዝ የነበረ በመሆኑም ጭምር ነው፡፡ ውርንጫው በተለምዶ እናቱን ይከተላልና፤ ምንም እንኳን ከዚህ በፊት ሰው ተቀምጦበት ባያውቅም እንዲሁም በመንገዱ ላይ ሰው አስቀምጦ ለመሄድ ሰልጥኖም ባያውቅ ነበር፡፡
እዚህ ላይ እንደገና የምንመለከተው ነገር በተመሳሳዮቹ ወንጌሎች ውስጥ ምንም ተቃርኖን አንመለከትም ነገር ግን በማቴዎስ በኩል የምናየው ተጨማሪ ዝርዝር ሲጨመር ነው ይህም ክስተቱ ሲከናወን እንደ ዓይን ምስክር ሆኖ ነው፡፡
ይህ ጌታ ኢየሱስ ካሟላቸው ብዙ ትንቢቶች ውስጥ አንዱም ነው፡፡ እርሱም ይህንን በቁጥጥሩ ስር ያለውን ነገር በዚህ ቦታ ላይ እንዲሁም ገና በህፃንነቱም ሊቆጣጠረው በማይችል ሁኔታ ውስጥ ያለውን በተወለደበት ቦታ ላይ (ለምሳሌ ዳንኤል 9.24-26 ሚልክያስ 5.1-2 እና ማቴዎስ 2.1-6 ያሉት ተፈፅመዋል) እንዲሁም ትንሳኤውንም ጭምር (መዝሙር 16.10፣ ሐዋርያት ስራ 2.24-32) እንደ ምዳሌ ሁሉቱን ለመጥቀስ ያህል ብቻ ነው፡፡
አንዳንድ ሙስሊሞች በሙሴ ሕግ (ቶራት) በሚሉት ውስጥ ቁርአን በምዕራፍ 7.157 እና በምዕራፍ 61.6 ላይ ስለ መሐመድ የተናገረውን በተመለከተ የትንቢት ማገናዘቢያ አለ በማለት ይናገራሉ፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ሙስሊሞች ሌላም ማግኘት ይኖርባቸዋል፡፡ ይህም የሚሆንበት ምክንያት ጌታ ኢየሱስን በተመለከተ የተነገሩት ነገሮች እጅግ በጣም ብዙ የነበሩ ሲሆን እነርሱንም ሁሉንም እርሱ በሕይወት ዘመኑ ከሕፃንነቱ ጀምሮ ሁሉንም ፈፅሟቸዋልና፡፡
ጥያቄ 37፡ ጴጥሮስ አግኝቶት የነበረው መገለጥ ከሰማይ ወይንስ ከወንድሙ?
ጴጥሮስ ጌታ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ መሆኑን ያወቀው ከሰማይ በመጣ መገለጥ ነበር በማቴዎስ 16.17 መሰረት ወይንስ በዮሐንስ 1.41 መሰረት በወንድሙ በአንድሩ አማካኝነት ነበር?
ይህ አይነቱ አተረጓጎም እጅግ በጣም ቃል በቃልና አውዶችንና ታሪክን እንዲሁም የድርጊቶችን ጊዜ ያላገናዘበ ነው፡፡
በማቴዎስ 16.17 ላይ ያለው ስምዖን ጴጥሮስ ከሌላ ሰው የሰማውን ነገር ሳይሆን የሚያሳየው እግዚአብሔር እራሱ ለእርሱ ግልጥ እንዳደረገለት ነበር፡፡ ይህም እርሱ በሌሎች ሰዎች የመነገሩን ነገር ከመንገድ ሊያስወጣው አይችልም፡፡ እዚህ ላይ ያለው የጌታ የኢየሱስ ነጥብ አንድ ሌላ ሰው ከዚህ በፊት የተናገረውን ነገር መድገሙ አልነበረም፡፡ እርሱ ማለትም ጴጥሮስ ከጌታ ኢየሱስ ጋር ኖሯል እንዲሁም ሰርቷል ነገር ግን አሁን በአዕምሮው ውስጥ ክርስቶስ እርሱ ክርስቶስ መሲህ መሆኑን የሕያው እግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ልዩ በሆነ መረዳት መገንዘቡን እናያለን፣ ይህንን ያደረገው አሁንም የሚያደርገው ደግሞ እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡
ጌታ ኢየሱስ “እኔ ማን እንደሆንሁ ማን ሲናገር ሰማችሁ?” አላለም ነገር ግን የተናገረው “እናንተ እኔ ማን እንደሆንሁ ትላላችሁ?” ነበር፡፡ በእነዚህ ሁለት ጥቄዎች መካከል ትልቅ ልዩነት አለ፤ ጴጥሮስም በምንም ምክንያት በጥርጥር ውስጥ አልነበረም፡፡
ጥያቄ 38፡ ጌታ ኢየሱስ ጴጥሮስንና ወንድሙን ያገኛቸው የት ነበር?
ጌታ ኢየሱስ ስምዖን ጴጥሮስንና ወንድሙን አንድሩን በመጀመሪያ ያገኛቸው በማቴዎስ 4.18-22 በገሊላ ባህር ነው ወይንስ በዮሐንስ 1.42-43 መሰረት በዮርዳኖስ ወንዝ አጠገብ ነበር?
ይህ ዓይነቱ ጥያቄ አረፍተ ነገሮችን አዛብቶ ከማንበብ የመጣ ነው፡፡
እዚህ ላይ ያለው ክስ የቀረበው አንድ ወንጌል ጌታ ኢየሱስ ስምዖንንና ወንድሙን ያገኛቸው በገሊላ ባህር ነው ሲል ሌላው በዮርዳኖስ ወንዝ ነው በማለቱ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ይህም ውንጀላ በፊት ለፊቱ የሚደፋ ነው ምክንያቱም የተለያዩ ጸሐፊዎች የተለያዩ ሁኔታዎችን በተለያዩ ቦታዎች ላይ መጻፋቸውን ስንረዳና ስንገነዘብ ነው፡፡ በዚህ ላይ ያሉት ክስተቶች ሁለቱም እውነቶች ናቸው እንጂ ልዩነቶች አይደሉም፡፡
ዮሐንስ 1.35 የሚናገረው ጌታ ኢየሱሰ በዮርዳኖስ ወንዝ አጠገብ እንዳገኛቸውና ከእነርሱም ጋር በዚያ ቦታ ጊዜን እንደወሰደ ይናገራል፡፡ አንድሩ (ምናልባትም ጴጥሮስ) የመጥምቁ ዮሐንስ ደቀመዛምርት ነበሩ፡፡ ይህንን አካባቢም ትተው ወደ ገሊላ ሄዱ በዚያም የቃና መንደር የነበረችበትና ጌታ ኢየሱስ የመጀመሪያውን ተዓምራትን በሰርጉ ላይ ያደረገበት ቦታ ነበር፡፡ “ኢየሱስ ይህን የምልክቶች መጀመሪያ በገሊላ ቃና አደረገ፤ ክብሩንም ገለጠ፥ ደቀ መዛሙርቱም በእርሱ አመኑ።” ዮሐንስ 2.11፡፡
ጴጥሮስና አንድሩ አመጣጣቸው በመጀመሪያ ቢታንያ ከሚባል ከተማ ነበር (ዮሐንስ 2.44) ነገር ግን አሁን የሚኖሩት በቅፍርናሆም ነው (ማቴዎስ 8.14-15 እና ማርቆስ 1.30-31 እንዲሁም ሉቃስ 4.38-39) ይህም ከቤተሳይዳ ትንሽ ኪሎ ሜትር ራቅ ያለ ቦታ ነበር፡፡ እነርሱም በስራቸው አሳ አጥማጆች ነበሩ፡፡ ስለዚህም ለእነርሱ አሳን ማጥመድ የተለመደ ነገር ነበር በቤት ውስጥ በእነዚህ ጊዜያት በነበሩበት ሰዓት (በዚህም ወቅት ጌታ ኢየሱስ የአደባባይ አገልግሎቱን ገና መጀመሩ ብቻ ነበር)፡፡
ማቴዎስ ታሪኩን ከዚህ ላይ ነበር የጀመረው ወይንም ያነሳው፡፡ ጴጥሮስና አንድሩ በገሊላ ባህር አሳ እያጠመዱ እያለ ጌታ ኢየሱስ እንዲከተሉት እነርሱን ጠራቸው ከኋላቸው ያለውን ማንኛውንም ነገር ወደ ኋላ ጥለው የእርሱ ቋሚ ተከታዮች (ደቀመዛምርት) እንዲሆኑ ጠራቸው፡፡ ይህ ከመሆኑ በፊት እርሱ አልጠየቃቸውም ነበር ነገር ግን እነርሱ በዮሐንስ ምስክርነት የተነሳ ተከትለውት ነበር (ዮሐንስ 1.35-36)፡፡ አሁን በዚህ ምስክርነት የተነሳ እንደዚሁም በቃና ገሊላ በሆነው ተዓምር እንዲሁም እራሱ ጌታ ኢየሱስ በተናገረው ነገር መሰረት እንዲሁም ደግሞ በዓለም ላይ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ እጅግ በጣም ብልህ ከሆነውና ፍፁም ከሆነው ሰው ጋር ጊዜን በማሳለፋቸው የተነሳ ሁሉን ነገር ወደ ኋላ ትተው እርሱን ለመከተል ምንም ሊያግዳቸው የሚችል ነገር አለመኖሩ በጣም ግልፅ የሆነ ነገር ነበር፡፡ በድንገት የተገለጠን ሰው በድንገት ተነስተው ለመከተልና ሁሉን ትቶ ለመውጣት ለእነርሱ የማይቻል ነገር ነበር፡፡ ቢያደርጉት ኖሮ ይሆን የነበረው ልክ እንደልጆች ነበር፤ ጌታ ኢየሱስም ማንንም ሰው እንደ አስማት አላታለለም ወይንም አስተሳሰባቸውን አልወሰደም፡፡ እነርሱ እርሱን የተከተሉት ማን እንደሆነ በትክክል ካወቁ በኋላ ነበር፣ ነቢያት ሁሉ የተናገሩለትን እርሱን መሲሁን እንዲሁም የእግዚአብሔር ልጅ የሆነውን በትክክል ካወቁ በኋላ ነበር፡፡
ጥያቄ 39፡ የኢያኢሮስ ልጅ ሞታ ነበር ወይንስ በሞት ጫፍ ላይ ነበረች?
ጌታ ኢየሱስ ኢያኢሮስን ሲገናኘው የ12 ዓመት ሴት ልጁ በማቴዎስ 9.18 “ያን ጊዜ ነበርን የሞተችው” ወይንስ በማርቆስ 5.23 መሰረት “በሞት ጫፍ ላይ ነበረች”?
ኢያኢሮስ ቤቱን በተወበት ጊዜ ሴት ልጁ በጣም ታማ ነበር እንዲሁም በሞት ጫፍ ላይ ነበረች እንደዚያ ባይሆን ኖሮ እርሱ ጌታ ኢየሱስን ለመፈለግ አይሄድም ነበር፡፡ ኢያኢሮስም ጌታ ኢየሱስን እንዳገኘው ልጁ በእርግጥ ሞታ እንደነበርና እንዳልነበር እርግጠኛ አልነበረም፡፡ ስለዚህም ሁለቱንም ዓረፍተ ነገሮች ተናግሮ ሊሆን ይችላል፡፡ ማቴዎስ የልጅቷን ሞት መጥቀሱ እንዲሁም ማርቆስ ላይ ስለ ሕመሟ ተናገሮ ቆይቶ ሞቷ መጠቀሱ ወሳኙን ነጥብ ከማየት አያግደንም፡፡ ስለዚህም መታየት ያለባቸው በጣም ጠቃሚ የሆኑ ዝርዝሮች እነዚህ ሳይሆኑ የሚከተሉትና ግልፅ ነገሮች ናቸው፡
የኢያኢሮስ ሴት ልጅ ሊገድል የሚችል ሕመም ነበረባት
ለእርሷም ሊደረግ የሚቻለው ነገር ሁሉ ተደርጎላት ነበር፤ ነገር ግን እርሷ ልክ እንደሞተች ያህል ነበረች በአሁኑ ወቅት ካልሞተች በስተቀር፤
ኢያኢሮስ ያወቀው ነገር ጌታ ኢየሱስ ሊፈውሳትም ወይንም ከሞትም ሊያስነሳትም ሁለቱንም እንደሚችል ነበር፡፡ እርሱንም በተመለከተ የትኛውም ምክንያት ይሁን ለጌታ ኢየሱስ ምንም ችግርን የሚያመጣ አልነበረም፡፡ ለእርሱ ከሞትም ማስነሳትም ከበሽታ መፈወስም ቀላል ናቸውና፡፡
ስለዚህም ኢያኢሮስ ጌታ ኢየሱስ ዘንድ በደረሰበት ጊዜ ልጅቷ ሞታ የነበረች መሆኗ ወይንም ገና በሞት አፋፍ ላይ የነበረች መሆኗ ምንም ለውጥን የሚያመጣ ነገር አይደለም ወይንም የሚያነጋገርም ነገር አይደለም፡፡ እንዲሁም ትልቅ የሆነና እምነትን የሚያናጋ የትርጉም ልዩነት የሚያስከትል አይደለም፡፡
የአዘጋጁ ማሳሰቢያ፡
በተከታታይ እንደተመለከትነው ሁሉ ቅራኔ ናቸው ተብለው የተጠቀሱት አንቀፆችና ቁጥሮች ሁሉ በትክክለኛ አዕምሮ ሲመረመሩ፣ ከአውዳቸውና ከታሪክ ጋር ሲታዩ ቅራኔዎች ተብለው ሊቆጠሩ በፍፁም አይችሉም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የሕያው እግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ በትክክለኛው አውዱና በትክክለኛው ታሪካዊ አቀማመጡ ሲነበብ የሚሰጠው ትምህርት አገራሚና ዘለቄታዊ ጠቀሜታ ያለው ሕይወትንም የሚነካ ነው፡፡ በምድር ላይ ከተጻፉት መጽሐፍት ሁሉ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ያለ ለሕይወት እውነት የሆነ መጽሐፍ የለም፡፡
አንባቢዎች ሁሉ ይህንን መጽሐፍ፣ መጽሐፍ ቅዱስን አግኝታችሁ ማንበብና በውስጡ ነነፍሳችሁ ያለውን መልእክት በጥንቃቄ እንድትገነዘቡ በጌታ ፍቅር እንጋብዛችኋለን፡፡ ጌታ እግዚአብሔር በፀጋው ይርዳችሁ፡፡
የትርጉም ምንጭ: "101 Cleared-up Contradictions in the Bible"
ለእስልምና መልስ አማርኛ ዋናው ገጽ