በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አሉ የሚባሉ ቅራኔዎች
‹ወደ ፍርድም አስቀድሞ የገባ ፃድቅ ይመስላል፣ ባላጋራው መጥቶ እስኪመረምረው ድረስ› ምሳሌ 18.17

የቅራኔዎች መኖር ውንጀላ
በ Jay Smith, Alex Chowdhry, Toby Jepson, James Schaeffer

[ክፍል አንድ] ክፍል ሁለት [ክፍል ሦስት] [ክፍል አራት]

ትርጉምና ቅንብር በአዘጋጁ

መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ ስህተት የሌለበትና እግዚአብሔር ለሰው ልጆች እራሱን እና ዕቅዱን የገለጠበት ቃሉ ነው፡፡ በእግዚብሔር ለሚያምኑ ሁሉ ለሕይወታቸው መመሪያ የሚሆን ሙሉ ትምህርት ያለው ብቁ የሆነ ስጦታ ነው፡፡ ከዚህም በላይ እውነትን ለማወቅ ለሚመጡ ሁሉ ለነፍሳቸው የሚናገር ተናጋሪ መጽሐፍ ነው፡፡

መጽሐፍ ቅዱስን ለማቃለል ዓላማዬ ብለው የተነሱ የተለያዩ የእምነት ተከታዮችና ሙስሊሞች መጽሐፍ ቅዱስ እርስ በእርሱ የሚቃረኑ ሐሳቦች አሉበት በማለት “እርስ በእርስ የሚቃረኑ  የሚመስሉ ጥቅሶችን” ይዘው መቅረብን ይወዳሉ፡፡ ከዚያም መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚብሔር ቃል ሊሆን አይችልም በማለት ሊደመድሙ ይሞክራሉ፡፡ እንደ እርስ በእርስ ቅራኔ የሚታዩትና ሁሌ የሚቀርቡት 101 ጥቅሶች ናቸው፡፡  የእነዚህ ጥቅሶች ትክክለኛ መረዳት ከዚህ በመቀጠል ተራ በተራ አቅርበናቸዋልና አንባቢ በትእግስት እንዲከታተላቸው ጥሪ እናቀርባለን፡፡

አንደኛ፡ የዳዊት ሕዝብ ቆጠራ አነሳሽ ማን ነበር?

ዳዊት የሕዝብ ቆጠራውን እንዲያካሂድ ያነሳሳው ማነው፤ እግዚአብሔር ነበር? (2 ሳሙኤል 4.1) ወይንስ ሰይጣን ነበር? (1ዜና መዋዕል 21.1)፡፡

የዚህ ዓይነቱ ቅራኔ እግዚአብሔር በታሪክ ውስጥ እንዴት እንደሰራ ከመገንዘብ ችግር የመጣ ነው፡፡

እነዚህ አረፍተ ነገሮች ሁለቱም በአንድ ጊዜ ትክክል ካልሆኑ በስተቀር ይህ የሚመስለው ቅራኔ ነው፡፡ ክስተቱ የተከናወነው በዳዊት ግዛት መጨረሻ አካባቢ ላይ ነበር፡፡ ዳዊት ወደነበሩት የቀድሞ ጦርነቶቹ ወደ ኋላ እየተመለከተ ነበር እርሱም ከነዓናውያንን፣ ሶርያውያንን እና ፊኒቂያውያን መንግስታትን ለእስራኤል የሚገብሩ መንግስታት አድርጎ በእስራኤል ላይ እንዲታመኑ አምጥቷቸዋል፡፡ በዚህም ደረጃው ዳዊት ባደረጋቸው በተሳኩለት ነገሮች የትምክህትና እራሱን የማድነቅ አመለካከትን አዳብሯል፡፡ እንዲሁም አሁን ያስብ የነበረው የጦር ሰራዊትን ስለማስታጠቅና ስለ ጦር ብዛት እንጂ ስለ እግዚአብሔር ምህረት አልነበረም፡፡

ስለዚህም ጌታ እግዚአብሔር ዳዊትን የማንበርከኪያው ጊዜ አሁን እንደሆነ ወሰነ እርሱ እንደገና በእግዚአብሔር ምህረት ላይ አንድ ጊዜ እንደገና የሚታመንበት ቦታ ላይ ማንበርከክ ነበረበት፡፡ ስለዚህም በሕዝብ ቆጠራው አላማው ላይ እንዲቀጥል አደረገው ይህም ምን ያህል መልካምን ነገር ለእርሱ እንደሚያደርግለት ለማወቅ ነበር፡፡ ይህም የሕዝብ ቆጠራ የአገር አቀፉን ትምክህት ከፍ የሚያደርግ ብቻ ነበርና (በዚህም የተነሳ የሕዝብ ቆጠራውን በመቃወም የኢዮአብ ማስጠንቀቂያ በዳዊት ላይ መጥቶበት 1ዜና 21.3)፡፡ ቆጠራው እንዳለቀ ወዲያውኑ ብዙ ሕዝብን ሊያጠፋ በሚችል አጥፊ መቅሰፍት ሕዝቡን  እግዚአብሔር  ቀጣ (በእርግጥ በ2 ሳሙኤል 24.15 መሰረት የ70 000 እስራኤላውያን ሕይወት ጠፍቷል)፡፡

ሰይጣንስ? እራሱን በዚህ ጉዳይ ላይ እንዴት አስገባው? (በ1ዜና 21.1 መሠረት) ዳዊትን እንዲህ ዓይነት ሞኝነት በአዕምሮው ውስጥ እንዲያከናውን ያደረገው እግዚአብሔር ከሆነ፤ የሚመስለው የእርሱ አስተሳሰብ ሙሉ ለሙሉ በክፋት የተሞላ የነበረ ነው፡፡ ነገር ግን አይደለም፤ የሕዝቡ ቆጠራ እግዚአብሔርን እንደማያስደስተው የሚያውቀው ሰይጣን (1 ዜና 21.7-8) ዳዊት ቆጠራውን እንዲያከናውነው ቀስቅሶታል፡፡

ነገር ግን ይህ ዓይነት የሰይጣን ጣልቃ ገብነት ሁኔታ ምንም አዲስ የሆነ ነገር አይደለም፡፡ ምክንያቱም ሌሎች ብዙ ክስተቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተከስተዋል፡፡ በእነዚያ ሁለቱም እግዚአብሔርም ሰይጣንም ነፍስን በሚመረምሩ ፈተናዎች እና ውጣ ውረዶችች ውስጥ የተሳተፉባቸው የሚመስሉ ሁኔታዎች ለትምህርታችን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተከስተዋል፡፡ የሚከተሉትን አምስቱን አስተውሉ፡-

ሀ. በኢዮብ መጸሐፍ ውስጥ ምዕራፍ አንድና ሁለት ላይ ለሰይጣን ከእግዚአብሔር ዘንድ የቀረበበትን ሁኔታ እናገኛለን፡፡ በዚህም ሁኔታ ሰይጣን የራሱን ጥፋት እንዲያደርስ ተፈቅዶለታል፡፡ የእግዚአብሔር ዓላማ የኢዮብን እምነት ለማንፃት ነበር እንዲሁም በፈተና ውስጥ ባህርዩን ለማጠናከርም ነበር፣ የሰይጣን ዓላማ ግን ሙሉ ለሙሉ ክፋት የሞላበት ነበር በዚህም በኢዮብ ላይ የተቻለውን ያህል ጉዳትን ለማድረስ በመመኘት ነበር፡፡ ስለዚህም ኢዮብ በእግዚአብሔር ላይ የነበረውን እምነት ተፀፅቶ እንዲተው ነበር፡፡

ለ. በስደት ላይ ባሉት ክርስትያኖች ስቃይ ውስጥ ሁለቱም እግዚአብሔርም ሰይጣንም ይታዩበታል በ1 ጴጥሮስ 4.19 እንዲሁም 5.8 መሠረት የእግዚአብሔር ዓላማ የነበረው በእምነታቸው እንዲጠናከሩና በዚህ ሕይወት ውስጥ እያሉ በክርስቶስ ስቃይ ተካፋዮች እንዲሆኑ ማድረግ ነበር፣ በመሆኑም ከእርሱ ጋር በሰማያዊው ዙፋን ክብር ጋር አብረው እንዲደሰቱ ነው (1ጴጥሮስ 4.13-14) የሰይጣን ዓላማ ግን እነርሱን ለመዋጥ ነው (1ጴጥረ0ስ 5.8) ወይንም ደግሞ እነርሱን ወደ እራስ ዝቅተኝነትና ሐዘን ውስጥ መምራት ነው ከዚያም መራራ ወደ መሆን እና ወደ እርሱ ደረጃ ዝቅ እንዲሉ ማድረግ ነው፡፡

ሐ. በጌታ በኢየሱስ ሦስት ፈተናዎች ውስጥ እግዚአብሔር ፈተናውን ሲፈቅድ፤ በፈተናውም የነበረው የእርሱ ዓላማ የጌታ የኢየሱስን ሙሉ ለሙሉ አምላክነትና በፈተና ውስጥ በድል ማለፉን ለማረጋገጥና ለማሳየት ነበር፡፡ አዳምና ሔዋንን በኤደን ገነት ውስጥ የጣላቸው ያው አንዱ ፈታኝ በእርሱ ላይ በበረሐ ውስጥ እንኳን ቅንጣትም ስልጣን እንዳነበረው ለማሳየት ነበር፡፡ የሰይጣን ዓላማ ግን አዳኙ ከመጣበት የማዳን ትልቅ አላማውና ትኩረቱ ለማደናቀፍና እንደ እርሱ ዓመፀኛ ለማድረግ ነበር፡፡

መ.  ጴጥሮስ ጌታ ኢየሱስን ለሦስት ጊዜ በካደበት ወቅት በሊቀ ካህኑ አደባባይ ጌታ ኢየሱስ እራሱ ነበር የእነዚህን ሁለት ወገኖች ዓላማ አብሮ መሳተፍ ጠቁሞ የነበረው ይህንንም በሉቃስ ወንጌል 22.31-32  “ጌታም ስምዖን ስምዖን ሆይ፥ እነሆ፥ ሰይጣን እንደ ስንዴ ሊያበጥራችሁ ለመነ፤ እኔ ግን እምነትህ እንዳይጠፋ ስለ አንተ አማለድሁ፤ አንተም በተመለስህ ጊዜ ወንድሞችህን አጽና አለ።”

ሠ. በመጨረሻም ደግሞ የጌታ ስቅለት ሌላ ምሳሌን ሁለቱም እግዚአብሔርም ሰይጣንም የተሳተፉበትን ሁኔታ ለእኛ በማስቀመጥ እራሱ ምስክርነትን ይሰጠናል፡፡ ሰይጣን ዓላማውን ያሳየው በይሁዳ ልብ ውስጥ የመክዳትንና የጥላቻን ነገር ባስቀመጠበት ጊዜ ነበር ዮሐንስ 13.27፣ እርሱም ይሁዳ ጌታ ኢየሱስን እንዲሸጠው አደረገው፡፡ ይሁን እንጂ የጌታ አመለካከት ደግሞ በመስቀሉ ጀርባ ላይ ነበረ፡፡ ጌታ ኢየሱስ ከምድር መፈጠር በፊት የታረደው በግ ሆኖ የራሱን ሕይወት ለብዙዎች ቤዛ አድርጎ እንደሚሰጥ ነበር፡፡ ስለዚህም አንድ ጊዜ እንደገና ኃጢአተኛው ሰው ከመጀመሪያ ጀምሮ በኤደን አትክልት ቦታ ያጣውን ግንኙነት እንደገና እንዲያገኘው ነበር፡፡ እናም በዚያ አማካኝነት ዘላለማዊ በሆነ ግንኙነት ውስጥ አሁን የሰው ልጅ እንዲገባ ነው፡፡

ስለዚህም እግዚአብሔርም ሰይጣንም የተሳተፉበት እነዚህ ሌሎች አምስት ምሳሌዎች አሉን፡፡ ነገር ግን ተሳትፎው ሲመረመር ሙሉ ለሙሉ በተለያየ ዓላማና ፍላጎት ነበር፡፡ የሰይጣን ፍላጎት የነበረው በእነዚህ ምሳሌዎች ውስጥ የዳዊትን የሕዝብ ቆጠራ ጨምሮ የተነሳሳው በክፉ ስሜት ነበር ነገር ግን በእነዚህ ሁሉ ነገሮች የጌታ ፍላጎት የነበረው ሙሉ ለሙሉ የተለየ ነበር፡፡ የጌታ ዓላማ የርህራሄና የደግነት ነበር ከበስተ መጨረሻውም ከሚገኝ ድል ጋር፣ እንዲሁም የተፈታኙን ሰውየ ጠቃሚነት በተመሳሳይ ሁኔታ ከመጨመር ጋር ነበር፡፡ በሁሉም ጉዳይ ላይ የሰይጣን ስኬትና ዓላማው ጊዜያዊ ብቻ ነበር፡፡ አልተሳካለትምም በስተመጨረሻው የእግዚአብሔር ዓላማ ግን በትክክል እና በሚገባ መንገድ ተፈፅሟል፣ የራሱንም ዓላማ በትክክል አራምዷል፡፡

ሁለተኛ፡ የተቆጠሩት 800 000 ወይንስ 1 100 000 የጦር ሰዎች?

በ2 ሳሙኤል 24.9 “ኢዮአብም የሕዝቡን ቁጥር ድምር ለንጉሡ ሰጠ፤ በእስራኤልም ሰይፍ የሚመዝዙ ስምንት መቶ ሺህ ጽኑዓን ሰዎች ነበሩ፤ የይሁዳም ሰዎች አምስት መቶ ሺህ ነበሩ።”

1ዜና 21.5 “ኢዮአብም የቈጠራቸውን የሕዝቡን ድምር ለዳዊት ሰጠ፤ ከእስራኤልም ሁሉ አንድ ሚሊዮን ከመቶ ሺህ ሰይፍ የሚመዝዙ ሰዎችን አገኘ፤ ከይሁዳም አራት መቶ ሰባ ሺህ ሰይፍ የሚመዝዙ ሰዎችን አገኘ።”

ይህ ቅራኔ የሚመስለው ቁጥር የጸሐፊውን ዓላማ ካለመገንዘብ እና ታሪካዊ አውድንም ካለመረዳት የመነጨ ነው፡፡ ይህንን ለመረዳት የሚያስችሉ እጅግ በጣም ብዙ መንገዶች አሉ፡፡ ይህም በሚከተለው ጥያቄም ላይ የቀረበውን ተግዳሮት ጭምር ይመለካታል፣ ምክንያቱም ሁሉቱም የሚናገሩት ለተመሳሳይ ክፍልና በተመሳሳይ ቆጠራ ላይ ነውና፡፡

የእነዚህ ልዩነቶች የመነጨው ከቆጠራው ያለመሟላት ወይንም በግልጥ ካለመሆን ችግር ጋር ተያይዞ ነው (ይህም ቆየት ብሎ የሚጠቀስ ይሆናል) ወይንም ደግሞ የሳሙኤል መጽሐፍ በተለይም ለይሁዳ ያቀረበው የተቀራረበ (የተጠጋጋ) ቁጥርን ስለነበርም ነው፡፡

ይሁን እንጂ በጣም አሳማኝ የሚመስለው መልስ አንደኛው ቆጠራ የተወሰኑ ወንዶችን ክፍል ሲጨምር ሌላው እነዚያን ቡድኖች አለመጨመሩ ነው፡፡ በ1 ዜና 21.5 ላይ በግልፅ እንደሚታየው ጦርነት ይኑርም ወይንም አይኑር ለጦርነት ዕድሜያቸው የደረሱትን ወንዶች በሙሉ መጨመሩ ግልፅ ነው፡፡ በ2 ሳሙኤል 24.9 ላይ ግን የሚናገረው ነገር ለጦርነት ዝግጁ የሆኑትን (ተዋጊዎች የሆኑትን) እነዚያን ብቻ ነው፡፡ በ2ሳሙኤል 24 ላይ ኢዮአብ ያቀረበው ሪፖርት እንደሚያሳየው የተጠቀመበት ቃል “ኢሽ ሃይል” የሚለውን ሲሆን የሚተረጎመውም “ሃያል ሰዎች” ወይንም ለጦርነት ዝግጁ የሆኑ ወታደሮችን ነው፤ እናም ስለ እነርሱ ሲጠቅስ ቁጥራቸው 800 000 ጦረኞች በማለት ነው፡፡ ስለዚህም ከእነርሱ ተጨማሪ 300 000 መዋጋት የሚችሉና (የመዋጋት ዕድሜ ያላቸው) በተጠባባቂነት የተቀመጡ ሰዎች ለመኖራቸው ግልፅ ነው፡፡ እነርሱም 300 000 በጦር ሜዳ ጦርነት ገና ያልተሳተፉ ናቸው፡፡ ሁለቱም ቡድኖች ስለዚህም በድምሩ የሚሰጡን በ1ዜና 21 ላይ የተጠቀሱትን 1 100 000 ሰዎችን ይሆናል፡፡ እንግዲህ ልዩነቱ እነዚህ 300 000 በዕብራይስጥ “ኢሽ ሃይል” በሚለው ቃል ያልተጠቀሱት ናቸው ማለት ነው፡፡

ሦስተኛ፡ ከይሁዳ የተቆጠሩት ሰዎች 500 000 ወይንስ 470 000 ነበሩ?

በ2 ሳሙኤል 24.9 ላይ “... የይሁዳም ሰዎች አምስት መቶ ሺህ ነበሩ።”

በ1ዜና 21.5 ላይ ደግሞ “... ከይሁዳም አራት መቶ ሰባ ሺህ ሰይፍ የሚመዝዙ ሰዎችን አገኘ።”

እነዚህ ቅራኔ የሚመስሉት ቁጥሮች አሁንም የታሪካዊ አውድን ካለመገንዘብ የመነጩ እውነታዎች ናቸው፡፡

በ1ዜና 21.6 ላይ ያለውን ስንመለከት የምናገኘው አስደናቂ ነገር ኢዮአብ ቆጠራውን እንዳላጠናቀቀው ነበር ምክንያቱም የብንያምን ነገድና የሌዊን ነገድ ቆጠራ አልጨረሰም ነበርና ይህም ዳዊት ቆጠራን ለማጠናቀቅ ከነበረው እምነት የተነሳ ነበር፡፡  ስለዚህም የቁጥሩ ልዩነት የመጣው ከአገሩ ሕዝብ ውስጥ የተወሰኑ ጎሳዎች ስማቸው ያልተጠቀሰ ቁጥር ከመጨመሩና ካለመጨመሩ የተነሳ እንደሆነ ግልጥ ነው፡፡ ለዚህ ሌላ ማስረጃን የሚሰጠን በ1 ዜና 27.23-24 ላይ እናገኛለን እዚያም የተጠቀሰው ነገር ዳዊት በቆጠራው ውስጥ ሃያ ዓመትና ከሃያ ዓመት በታች ያሉትን አልጨመረም እናም ኢዮአብም ቆጠራውን ጨርሶ ስላልነበረ በዳዊት የቆጠራ መዝገብ ላይ አልተጻፈም የሚል ነገርን እናገኛለን፡፡ (በዳዊት የዜና መዋዕል ላይ)፡፡

በአጠቃላይ የሕዝብ ቆጠራውን ለማከናወን የነበረው ቅደም ተከተል ከዮርዳኖስ ማዶ ካሉት ነገዶች ይጀምርና በ2ሳሙኤል 24.5 ላይ እንዳለው ከዚያም ወደ ሰሜኑ ጫፍ እስከዳን ነገድ ድረስ ሄዶ ወደ ደቡብ ወደ ኢየሩሳሌም ይቀጥል ነበር ይህም በቁጥር 7 ላይ እንደተገለፀው ነው፡፡ የቤንያማውያን ቆጠራ ደግሞ ይመጣ የነበረው በመጨረሻው ደረጃ ላይ ነበር፡፡ ስለዚህም ለእስራኤል ወይንም ለይሁዳ ጠቅላላ ቁጥር የቢንያም ነገድ አልተጨመረም ነበር በሁሉቱም ላይ (በእስራኤልም በይሁዳም)፡፡ በ2 ሳሙኤል 24 በተመለከተ ለይሁዳ የተሰጠው ቁጥር 300 000 በትክክል የታወቁትን ጦረኞች ቢንያማውያንን ጨምሮ ነበር፡፡ ስለዚህም 500 000 የብንያምን ተጠባባቂዎችን የጨመረ ነበር፡፡ (ያካተተ ነበር)

እዚህ ላይ ማስተዋል የሚያስፈልገፈው ሰለሞን ከሞተና አንዱ መንግስት ለሰሜንና ለደቡብ ለሁለት ከተከፈ በኋላ በ930 ዓ.ዓ ብዙዎቹ ቢንያማውያን ለዳዊት ዘር መንግስት ታማኝ ሆነው ቀርተው እንደነበር (በደቡብ በኩል ከነበረው ስምዖን ጋር) አንድ ላይ ሆነው የይሁዳ መንግስትን ሰጥተው ነበር፡፡ ስለዚህም በከፊል አጠቃላይ ቁጥሩ ላይ ቤንያማውያንንና ስምዖናውያንን በይሁዳ ላይ መጨመር እና 500 000 ማምጣት የሚያስኬድ ነገር ነበር፡፡ ምንም እንኳን ኢዮአብ ለዳዊት ባቀረበው በመጀመሪያው ሪፖርቱ በ1ዜና 21.5 ላይ ይህንን በሚገባ ባያቀርበውም እንኳን ነበር፡፡ ስለዚህም የአጠቃላይ የተዋጊዎች ኃይል ሙሉ ቁጥር ለዳዊት የነበሩት 1 600 000 (1 1000 000 ከእስራል እና 470 000 ከይሁዳና ስምዖን እና 300 000 ቢንያም ነበሩ)፡፡

አራተኛ፡ ከቀረቡት የቅጣት ምርጫዎች ረሃቡ ለሰባት ዓመታት ወይንስ ለሦስት ዓመታት ነበር?

በ2 ሳሙኤል 24.13 ላይ “ጋድም ወደ ዳዊት መጥቶ። የሦስት ዓመት ራብ በአገርህ ላይ ይምጣብህን? ወይስ ጠላቶችህ እያሳደዱህ ሦስት ወር ከእነርሱ ትሸሽን? ወይስ የሦስት ቀን ቸነፈር በአገርህ ላይ ይሁን? አሁንም ለላከኝ ምን መልስ እንደምሰጥ አስብና መርምር ብሎ ነገረው።” (በ2 ሳሙኤል 24.13 ላይ ያለው የረሃቡ ዘመን ቁጥር በእንግሊዝኛው ሰባት ዓመት ነው፤ በ1879 የአማርኛው የጥንቱም ትርጉም ሰባት ዓመት ተብሎ በትክክል ተተርጉሟል)፡፡

በ1ዜና 21.12 ላይ ደግሞ፡ “የሦስት ዓመት ራብ፥ ወይም ሦስት ወር የጠላቶችህ ሰይፍ እንዲያገኝህ ከጠላቶችህ መሰደድን፥ ወይም ሦስት ቀን የእግዚአብሔር ሰይፍ ቸነፈርም በምድር ላይ መሆንን፥ የእግዚአብሔርም መልአክ በእስራኤል ምድር ሁሉ ማጥፋትን ምረጥ፤ አሁንም ለላከኝ ምን እንድመልስ ተመልከት አለው።”

ይህንን ቅራኔ የሚመስል ሐሳብ የምንመለከትበት ሁለት መንገዶች አሉ፡፡ የመጀመሪያው የሚሆነው የዜና መዋዕል ጸሐፊ ያተኮረው በሦስት ዓመታት ጠንካራ ረሃብ ላይ ሲሆን የ2 ሳሙኤል ጸሐፊ ግን ከሦስት ዓመታቱ ረሃብ በኋላና በፊት የሚኖሩትን ሁለት፣ ሁለት ዓመታት ማለትም አራት አመታትንም ጨምሮ ነው፣ ይህም ረሃቡ በጣም የሚከፋበትንና ቀለል እያለ የሚሄድበትን ጊዜያት ጨምሮ ነው፡፡

ሌላው መፍትሄ ሊታይ የሚችለው በእያንዳንዱ አንቀፅ ውስጥ አገልግሎት ላይ የዋሉትን ቃላት በማስተዋል ላይ ነው፡፡ በሁለቱ መጽሐፍት ውስጥ ያሉትን ሁለቱን አንቀፆች በምታወዳድሩበት ጊዜ የምታስተውሉት ነገር ቢኖር የቃላት አጠቃቀሙ በ1ዜና 21 ላይ ያለው ከ2 ሳሙኤል 24 ላይ ካለው ጋር በጣም የተለያየ ነው፡፡ በ2 ሳሙኤል 24.13 ላይ የሚገኘው ቃል “የሰባት ዓመታት ረሃብ ይምጣብህን?” የሚል ሲሆን በ1ዜና 21.12 ላይ ግን የምናገኘው ነገር ከብዙ ምርጫዎች ውስጥ “ለራስህም የሦት ዓመታትን ረሃብ ምረጥ” የሚልና ጥያቄው በተለየ መልኩ ቀርቦ ነው፡፡ ከዚህም እኛ በማስተዋል ልናጠናቅቅ የምንችለው ነገር በ2 ሳሙኤል ላይ ያለው ሐሳብ ነቢዩ ጋድ በመጀመሪያ ዳዊትን በቀረበበት ጊዜ የተነገረ ነገር መሆኑን ነው፡፡ በዚያም የነበረው የረሃብ አማራጭ ሰባት ዓመታት ሆኖ እንደቀረበ ነበር፣ ነገር ግን በዜና ዘገባ ውስጥ ግን የምናገኘው የሁለተኛውንና የመጨረሻውን አማራጭ ነው ይህም የተደረገው በነቢዩ በጋድ ለንጉሱ የቀረበው ነው በዚህም ጌታ (በዳዊት የቅንነት ልመና በግል ፀሎቱ) ያንን አስጨናቂ ሁኔታ አማራጭ ወደ ከሰባት ዓመታት አጠቃላይ ሙሉ ጊዜ ወደ ሦስት ዓመታት ለውጦት ነው፡፡ ነገር ግን ከታሪኩ እንደምናየው ዳዊት እግዚአብሔር ካስቀመጣቸው ምርጫዎች ውስጥ የመረጠው ሦተኛውን ምርጫ ነው፣ እናም የሦስት ቀናት ክፉ መቅሰፍትን ተቀበለ በዚህም በ70 000 የእስራኤላውያን ወንዶችን ሞት አስከተለ፡፡

አምስተኛ፡ አካዝያስ ሲነገስ ዕድሜው 22 ወይንስ 42 ነበር?

በ2 ነገስት 8.26 ላይ አካዝያስ፣ “መንገሥ በጀመረ ጊዜ አካዝያስ የሀያ ሁለት ዓመት ጎልማሳ ነበረ በኢየሩሳሌምም አንድ ዓመት ነገሠ። እናቱም ጎቶልያ የተባለች የእስራኤል ንጉሥ የዘንበሪ ልጅ ነበረች።” የነገሰው በሃያ ሁለት ዓመቱ ነው ሲል

በ2ዜና 22.2 ደግሞ፡ “አካዝያስም መንገሥ በጀመረ ጊዜ ዕድሜው አርባ ሁለት ዓመት ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም አንድ ዓመት ነገሠ እናቱም ጎቶሊያ የተባለች የዘንበሪ ልጅ ነበረች።” በእርባ ሁለት ዓመቱ ነው ይላል፡፡
   
የዚህ ዓይነቱ ችግር ከጸሐፍት የቅጂ ስህተት የሚመደብ ነው፡፡ አሁን የምንመለከተው ከብዙ ሺ ዓመታት በፊት የተጻፈ ታሪካዊ ዘገባን ሲሆን በአሁኑ ጊዜ የመጀመሪያው ጽሑፍ “ኦቶግራፍ” በእጃችን እንዲገኝ አንጠብቅም፡፡ ምክንያቱም “ኦቶግራፎቹ” ማለትም የመጀመሪያዎቹ ጽሑፎች የተጻፉባቸው ከብዙ ዓመታት በፊት ተበላስተዋልና፡፡ ስለዚህም እኛ የምንደገፈው የመጀመሪያዎቹ ከተገለበጡባቸው ቅጅዎች ላይ ነው፣ እነርሱም ደግሞ በተከታታይ ለዘመናት እየተቀዱ ቀጥለው ነበር፡፡ ጽሑፎቹን ይቀዱ የነበሩት እነዚያ ሰዎች ሁለት ዓይነት ስህተቶችን ለማድረግ ይችሉ የነበሩ ሰዎች ናቸው፡፡ አንዱ የግል ስሞችን ፊደላት መሳት ሲሆን ሌላው ደግሞ የቁጥር ስህተቶችን ማድረጎች ነበሩ፡፡

ሁለቱ የቁጥር ልዩነት ምሳሌዎች በተሰጡት ቁጥሮች ውስጥ በመካከላቸው የሃያ ዓመታት ልዩነት አላቸው፡፡ በ2 ነገስት 8.22 አካዝያስ የነገሰው 22 ዓመቱ ሲባል በ2 ዜና 22.2 ደግሞ 42 ዓመቱ እንደሆነ ቀርቧል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ትክክለኛው የትኛው እንደሆነ ለመወሰን የሚያስችል አጥጋቢ የሆነ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃ አለን ትክክለኛውም ዕድሜ 22 ዓመት የሚለው ነው፡፡ ቀደም ብሎ በ2 ነገስት 8 ውስጥ ቁጥር 17 የአካዝያስ አባት ኢዮራም የአክአብ ልጅ 32 ዓመቱ ነበር ንጉስ ሲሆን፤ ከስምንት ዓመትም ንጉስነቱ በኋላ በአርባ ዓመቱ ሞቷል፡፡ ስለዚህም አካዝያስ አባቱ  በ40 ዓመቱ ሞቶ ስልጣን ሲይዝ 42 ዓመት ሊሆነው አይችልም ነበር ማለት ነው፡፡

እንደዚህ ዓይነቱ የጸሐፍት ስህተት ደግሞ የአይሁዶችንም ሆነ የክርስትያኖችን እምነት ወይንም ስለመጽሐፍ ቅዱስ ያላቸውን መረዳት በምንም መንገድና ቅንጣትም ያክል አይቀይረውም፡፡ በእንደዚህ ዓይነት ጉዳዮች ሁሉ ላይ የሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል እርማትን ይሰጣል በዚህ ጉዳይ ላይ 2 ነገስት 8.26 እርማትን ሰጪ አድርገን እናቀርበዋለን ማለት ነው፡፡ ሌላው ማስታዎስ የሚገባን ነገር ደግሞ እነዚያን ቅጂዎች ያደርጉ የነበሩት ጸሐፍት እራሳቸው እጅግ በጣም ትጉዎች እና ለእግዚአብሔርም ቃል እውነተኞችና ከፍተኛ ክብር የሚሰጡ የነበሩ መሆናቸውን ነበር፡፡ የእግዚአብሔርን ቃላት እንደተቀበሏቸው አስተላልፈዋቸው ነበር ያለምንም ለውጥ፤ በእርግጥ ሰዎች በመሆናቸው እነዚህን የመሳሰሉ ነገር ግን መሰረታዊ ትርጉም የማይለውጡ ስህተቶችን አድርገዋል ማለት እንችላለን፡፡

የሚቀጥለው ጥያቄ ስድስት ምላሽ ጸሐፍት እንዴት ስተተቶችን ያደርጉ እንደነበረ ጠለቅ ያለ ማብራሪያ ይሰጣል እና ተከታተሉ፡፡

የአዘጋጁ ማሳሰቢያ፡

ከዚህ በላይ በታዩት ቅራኔ በሚመስሉ ነገር ግን ባልሆኑት ጥቅሶች ውስጥ የተመለከትነው መጽሐፍ ቅዱሰ ለሚነሱ ጥያቄዎች ሁሉ ትክክለኛ መልስ እንዳለው ነው፡፡ ይህም ደገግሞ ደጋግሞ የሚሰጠን ሐሳብ መጽሐፍ ቅዱስ ከእግዚአብሔር የመነጨ፤ የራሱን ማንነት እንድናውቅ የተሰጠን መጽሐፍ ሲሆን እኛ የሰው ልጆች ደግሞ ምን እንደሆንን፣ ምን እንደሚያስፈልገን እንድንገነዘብም የሚናገረን የእግዚአብሔር የራሱ ቃል ነው፡፡

አንባቢዎች መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ የሚገባቸው ስህተትን ለመፈለግ ሳይሆን ለሕወታቸው የሚጠቅም ትምህርትን ለመውሰድ መሆን ይገባል፡፡ ስለዚህም የዚህ ድረ-ገፅ አዘጋጆች አንባቢዎችን የ፣ሚመክሩት መጽሐፍ ቅዱስን በተከፈተ አዕምሮ ለማንበብ እንዲጀመሩ፣ እግዚአብሔር በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ሲናገራቸው እንዲሰሙና ለመልእክቱ ምላሽን እንዲሰጡ ነው፡፡

የምናቀርባቸውን የ101 ቅራኔ የሚመስሉ ጥቅሶችን ማብራሪያ በትዕግስት ተከታተሉ እግዚአብሔርም ጥበብንና ማስተዋልን ይስጣችሁ፣ አሜን፡፡

የትርጉም ምንጭ: "101 Cleared-up Contradictions in the Bible"

ለእስልምና መልስ አማርኛ  ዋናው ገጽ