መንፈሳዊውን ጨለማ ማብራት

Roland Clarke

ትርጉምና ቅንበር በአዘጋጁ

እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች ሁሉ በመለኮታዊ ብርሃን ያምናሉ፡፡ ‹ከእርሱም የሰማናት ለእናንተም የምናወራላችሁ መልእክት። እግዚአብሔር ብርሃን ነው ጨለማም በእርሱ ዘንድ ከቶ የለም የምትል ይህች ናት።› 1ዮሐንስ 1.5፡፡ እግዚአብሔር ፈቃዱን በአገልጋዮቹ በኩል በመግለጥ በጨለማው ላይ ብርሃኑን ያበራል፡፡ ‹ሕግህ ለእግሬ መብራት፥ ለመንገዴ ብርሃን ነው።› መዝሙር 119.105፡፡ ይህንን በተመለከተ ቁርአን ደግሞ የሚከተለውን ይናገራል፡- ‹አላህ የሰማያትና የምድር አብሪ ነው ..› ቁርአን 25.35፡፡ እንዲሁም ደግሞ ‹በፈለጎቻቸውም (በነቢያቶቹ ፈለግ) ላይ የመርየምን ልጅ ዒሳን ከተውራት በስተፊቱ ያለውን አረጋጋጭ ሲኾን አስከተልን፣ ኢንጂልንም በውስጡ ቀጥታና ብርሃን ያለበት በስተፊቱ ያለችውን ተውራትንም የሚያረጋግጥ ለጥንቁቆችም መሪና ገሣጭ ሲኾን ሰጠነው› ቁርአን 5.44፡፡

ክርስትያኖች ኢየሱስ ክርስቶስ ‹የእግዚአብሔር ቃል› ነው በማለት እንደሚያምኑት ሁሉ ሙስሊሞችም ‹የእግዚአብሔር ቃል› ወይንም በአረብኛ ‹ካሊማቱላህ› በማለት ይጠሩታል ከዚህም የተነሳ እርሱ ጌታ ኢየሱስ እውነተኛ ብርሃንን የሚያመጣ ነው፡፡ በወንጌል ውስጥ የምናነበውም፡- ‹ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን። ... በእርሱ ሕይወት ነበረች፥ ሕይወትም የሰው ብርሃን ነበረች። ብርሃንም በጨለማ ይበራል፥ ጨለማም አላሸነፈውም።› ዮሐንስ 1. 14፣ 4-5 የሚለውንና ስለ እሱ የተገለጠውን እውነታ ነው፡፡ እንዲሁም ደግሞ በቁርአን 5.46 ላይ ‹ኢንጂልንም (ማለትም፣ ወንጌል) በውስጡ ቀጥታና ብርሃን ያለበት በስተፊቱ ያለችውን ተውራትንም የሚያረጋግጥ ለጥንቁቆችም መሪና ገሣጭ ሲኾን ሰጠነው› የሚለውን እናነባለን፡፡

የሚገልጥ ብርሃን

ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሕፃን ልጅ በነበረበት ጊዜ፣ በቤተ መቅደስ መጥቶ ሊገረዝ ሲል እሱን በተመለከተ አስደናቂ የሆነ ትንቢት ተነገረለት፣ ትንቢቱም የሚከተለው ነበር፡- ‹እርሱ ደግሞ ተቀብሎ አቀፈው እግዚአብሔርንም እየባረከ እንዲህ አለ። ጌታ ሆይ፥ አሁን እንደ ቃልህ ባሪያህን በሰላም ታሰናብተዋለህ፤ ዓይኖቼ በሰዎች ሁሉ ፊት ያዘጋጀኸውን ማዳንህን አይተዋልና፤ ይህም ለአሕዛብ ሁሉን የሚገልጥ ብርሃን ለሕዝብህም ለእስራኤል ክብር ነው።›

በመሲሁም በጌታ በኢየሱስ በኩል ይገለጥ የነበረው ብርሃን የተገለጠው እንደሚከተለው ነበር፡- ‹ይህም ከላይ የመጣ ብርሃን በጐበኘበት በአምላካችን ምሕረትና ርኅራኄ ምክንያት ነው፤ ብርሃኑም በጨለማና በሞት ጥላ ተቀምጠው ላሉት ያበራል እግሮቻችንንም በሰላም መንገድ ያቀናል።› ሉቃስ 1.78፣ ተብሎ ሲሆን ይህም በብሉይ ኪዳን ውስጥ የተነገረው ትንቢት ማለትም ‹ነገር ግን ስሜን ለምትፈሩት ለእናንተ የጽድቅ ፀሐይ ትወጣላችኋለች፥ ፈውስም በክንፎችዋ ውስጥ ይሆናል፤ እናንተም ትወጣላችሁ፥ እንደ ሰባም እምቦሳ ትፈነጫላችሁ።› ሚልክያስ 4.2 ሙሉ ለሙሉ በጌታ በኢየሱስ ወደ ምድር መምጣት የተፈፀመ መሆኑን ያመለክተናል፡፡ በእውነት እግዚአብሔርን የሚፈልጉና የሚፈሩት የፅድቅ ፀሐይ ትወጣላቸዋለችና!  

የሚፈውስ ብርሃን

አንድ አስደናቂ የሆነና ‹የፅድቅ ‹ፀሐይ› በክንፎቿ ‹ፈውስን› ይዛ ትወጣለች የሚል የአረቦች ምሳሌ አለ፣ አባባሉ ትንሽ ግራ የሚያጋባ ቢሆንም ምሳሌው በፈውስና በፀሐይ መካከል ግንኙነት እንዳለ እንደሚከተለው ማለትም፣ ‹ወደ ሐኪም እንደምትሄድ ወደ ፀሐይ ሂድ› በማለት ይናገራል፡፡ በቆዳቸው ላይ ቁስል ላለባቸውን በሽተኞች በማለዳ ፀሐይ ላይ እንዲቀመጡ ዶክተሮች እንደሚያበረታቱ እውነት ነው፣ ምክንያቱም የፀሐይ ሙቀት ቁስል በቶሎ እንዲድን ያደርጋልና፡፡ ከዚህም በላይ የፀሐይ ኃይል ቫይታሚን ዲን እንድናገኝ ያደርግና ለጤናችን ከፍተኛ እገዛ ያደርግልናል፡፡ ከዚህም በላይ በከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ላሉ ሰዎች የፀሐይ ብርሃን እንደማርከሻ ሆኖ ያገለግላል፡፡

እኛ ሁላችንም እንደምናውቀው ጌታ ኢየሱስ እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ ተዓምራታዊ ፈውሶችን አድርጎ ነበር፡፡ በወንጌሎችም ውስጥ እንደሚከተለው ተጽፎ እናገኛለን፡- ‹በነቢዩም በኢሳይያስ፣ የዛብሎን ምድርና የንፍታሌም ምድር፥ የባሕር መንገድ፥ በዮርዳኖስ ማዶ፥ የአሕዛብ ገሊላ፤ በጨለማ የተቀመጠው ሕዝብ ታላቅ ብርሃን አየ፥ በሞት አገርና ጥላ ለተቀመጡትም ብርሃን ወጣላቸው የተባለው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሆነ።› ማቴዎስ 4.14-17፡፡ ደግሞም በዚያው ምዕራፍ በቁጥር 23-24 ላይ የሚከተለውን እናነባለን፡- ‹ኢየሱስም በምኩራቦቻቸው እያስተማረ የመንግሥትንም ወንጌል እየሰበከ በሕዝብም ያለውን ደዌና ሕማም ሁሉ እየፈወሰ በገሊላ ሁሉ ይዞር ነበር። ዝናውም ወደ ሶርያ ሁሉ ወጣ፤ በልዩ ልዩ ደዌና ሥቃይም ተይዘው የታመሙትን ሁሉ አጋንንትም ያደሩባቸውን በጨረቃም የሚነሣባቸውን ሽባዎችንም ወደ እርሱ አመጡ፥ ፈወሳቸውም።›

የሚያድን ብርሃን

ጌታ ኢየሱስ ከፈወሳቸው እጅግ በጣም ብዙ ሰዎች መካከል አንዳንዶች እጅግ በጣም የታመሙና በአስጊ ሁኔታ ውስጥ ነበሩ፣ ለሞትም በጣም የቀረቡም ነበሩ (ተስፋ የሌላቸው)፡፡ የእሱም ጣልቃ መግባት ከመሞት አድኗቸዋል እሱ የእነሱ ደኅንነት ነበረ ሉቃስ 7.2 እና 8.43፡፡ ሰዎችን ከሞት ማዳን የሚለው ነገር የአዲስ ትርጉም ደረጃን ይይዛል ይህም የመሲሁን የማዳን ብርሃን በኃይል ሲያበራ እና ‹በሞት ጥላና በጨለማ ውስጥ ለተቀመጡት› ሲያበራላቸው ነው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም ጌታ ኢየሱስ ሰዎችን ከሞት አስነስቷቸዋል ይህም በመጽሐፍ ቅዱስም በቁርአንም ውስጥ እንደተገለጠው ነው፡፡ በለምፅ በሽታ ውስጥ ተቀምጠው ለነበሩት ሁሉ ጌታ ኢየሱስ የተስፋቸው ጭላንጭልና ብቸኛው አዳኛቸው ነበር፡፡

ስለ ብርሃን ስናስብ ልናስብበት የሚገባን ሌላም ትንቢት አለ፡፡ በትንቢተ ኢሳያስ 49.6 ውስጥ ‹እርሱም። የያዕቆብን ነገዶች እንድታስነሣ ከእስራኤልም የዳኑትን እንድትመልስ ባሪያዬ ትሆን ዘንድ እጅግ ቀላል ነገር ነውና እስከ ምድር ዳር ድረስ መድኃኒት ትሆን ዘንድ ለአሕዛብ ብርሃን አድርጌ ሰጥቼሃለሁ ይላል።›

ሕይወትን ሰጪ ብርሃን

የእግዚአብሔር ቃል ለሰዎች ሁሉ ብርሃንን የሚሰጥ እንደሆነ ቀደም ሲል ተመልክተናል፡፡ አሁን ደግሞ የክርስቶስን ትምህርት ቀረብ በማለት እንመለከተዋለን በዚህም በብርሃንና በሕይወት መካከል ያለውን ቅርብ ግንኙነት እናስተውላለን፣ ‹ደግሞም ኢየሱስ። እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ በጨለማ አይመላለስም ብሎ ተናገራቸው።›

ከዚያም ከጥቂት ዓመታት በኋላ ወደ ሰማይ አረገ፣ እንደገና ለዮሐንስ በራዕይ ተገልጦለት እንደሚከተለው ተናገረ፡- ‹በቀኝ እጁም ሰባት ከዋክብት ነበሩት፥ ከአፉም በሁለት ወገን የተሳለ ስለታም ሰይፍ ወጣ፤ ፊቱም በኃይል እንደሚበራ እንደ ፀሐይ ነበረ። ባየሁትም ጊዜ እንደ ሞተ ሰው ሆኜ ከእግሩ በታች ወደቅሁ። ቀኝ እጁንም ጫነብኝ እንዲህም አለኝ። አትፍራ፤ ፊተኛውና መጨረሻው ሕያውም እኔ ነኝ፥ ሞቼም ነበርሁ እነሆም፥ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ሕያው ነኝ፥ የሞትና የሲኦልም መክፈቻ አለኝ።› ራዕይ 1.16-18፡፡

ክርስቶስ እንዴት እንደተገለጠለት ዮሐንስ ሲገልጥ የተናገረው፡- ‹ፊቱም በኃይል እንደሚበራ እንደ ፀሐይ ነበረ። ...› በማለት ነው፡፡ የዚህ የክርስቶስ አስደናቂ የፊት ማብራት የሚያስታውሰን አንድ ስም አለ ‹የፅድቅ ፀሐይ› የሚለውን ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት አስደናቂ ብርሃን የሚያመለክተው እሱ ፍፁም ንፁህና ያለ ምንም እንከን የነበረና አሁንም ያለ መሆኑን ነው፡፡ በቁራንም 19.19 ላይም ‹እኔ ንፁሕን ልጅ ነኝ ለአንቺ ልሰጥሽ የጌታሽ መልእክተኛ ነኝ አላት› የሚለውንም ተጽፎ እናገኛለን፡፡

የሚከተለውን እንድታስቡበት እስኪ ልጠይቃችሁ? ‹ጌታ ኢየሱስ በእርግጥ ከሞት ተነስቶ ከሆነ እርሱ የሞትና የሲዖል መክፈቻ ያለው መሆኑ ትርጉም የሚሰጥ አይሆንምን?› ለማንኛውም ግን እሱ ወደዚያ ጨለማ ሁኔታ ውስጥ ገብቶ ሁሉን ድል አድርጎ ወጥቷል! ይህንንም ከእሱ በስተቀር ማንም ከቶ አላደረገውም፡፡

አይሁድ ላልሆኑት ብርሃን

በዮሐንስ 4 ላይ ጌታ ኢየሱስ አስደናቂ የሆነን መንፈሳዊ ብርሃን ሰማርያኖች ለተባሉት ሕዝብ እንዳመጣ እናነባለን፡፡ ልክ እንደ ግማሽ የአይሁድ ወንድሞቻቸው ሁሉ እነሱም በሙሴ አማካኝነት ሕግን በሰጠው በፈጣሪው በእግዚአብሔር ያምናሉ፡፡ ይሁን እንጂ ሰማርያኖች ከእውነተኛው መንገድ በብዙ ሁኔታ ርቀዋል፡፡ ጌታ ኢየሱስ የተናገራቸው በእርግጥ እግዚአብሔርን እንደማያውቁ ነው ምክንያቱም ‹መዳን ከአይሁድ ነውና› ዮሐንስ 4.22፡፡

በአሁኑ ዘመናዊ ጊዜ ብዙ ሰዎች ይህን አቀራረብ ጠባብነት ነው በማለት ይተቻሉ፡፡ እግዚአብሔር በአይሁድ ነገድ ውስጥ (ሕዝብ) ውስጥ ነቢያትን፣ ቅዱስ መጽሐፍን እንደዚሁም በመጨረሻ ደኅንነትን ለማምጣት የሚችለውን መሢሁን እንደላከ ይረሳሉ፡፡ የሰማርያ ሰዎች ግን ይህ እንደተነገራቸው የክርስቶስን የፍቅር ነቀፌታ ተቀበሉና የተናገረውን አመኑበት ከዚህም የተነሳ እንደሚከተው ተናገሩ፡- ‹እኛ ራሳችን ሰምተነዋልና፤ እርሱም በእውነት ክርስቶስ የዓለም መድኃኒት እንደ ሆነ እናውቃለን ይሉአት ነበር።› ዮሐንስ 4.42፡፡

ሙስሊሞች ይህንን የጌታ ኢየሱስን መሲህነት ለመቀበል በጣም ያመነታሉ ነገር ግን ቁርአን የጌታ የሲየሱስ ስም እንደተመረጠና በመላእክት በኩል እንደተገለጠ ይናገራል፡፡ ኢየሱስ የሚለውም ስም ‹እግዚአብሔር አዳኝ› ማለት ነው ይህም by Muhammad I. A. Usman in his book 'Islamic Names'. (p. 77) በግልጥ ተቀባይነትን አግኝቶ እንደተተነተነው ማለት ነው፡፡

እናንተ ጌታ ኢየሱስ ከእግዚአብሔር ዘንድ ለእኛ የተሰጠን ብርሃንና ደኅንነት መሆኑን ታምናላችሁን?

የአዘጋጁ ማሳሰቢያ፡-

በቁርአን 5.46 እንደተገለፀው ‹ኢንጂልንም (ማለትም፣ ወንጌል) በውስጡ ቀጥታና ብርሃን ያለበት በስተፊቱ ያለችውን ተውራትንም የሚያረጋግጥ ለጥንቁቆችም መሪና ገሣጭ ሲኾን ሰጠነው›፣ የሚለውን አንብበናል፡፡ ይህም የሚያሳየው የክርስትያኖች ወንጌል ‹ቀጥታና ብርሃን› ያለበት መሆኑን ነው፡፡ ኃጢአተኛ የሆኑ ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር ታርቀው የመንግስተ ሰማይን ሕይወት እንዴት መውረስ እንደሚችሉ በመግለጥ በኩል ለዘመናት ሁሉ ‹ብርሃን› ሆኖ የኖረ መጽሐፍ የክርስትያኖች ወንጌል ነው፡፡ ይህም የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ልክ እንደ ብርሃን በጣም ግልጥና ለሚያነቡት ሁሉ የሚገባ መሆኑን ያሳያል፡፡

በእውነትና በትክክል እግዚአብሔርን ለማወቅ ለሚጠሩት የወንጌል መልእክት ታላቅ ‹የምስራች ወይንም የደስታ ዜና› ነው፡፡ ምክንያቱም በኃጢአቱ የተነሳ ከቅዱስና ከፍፁሙ እግዚአብሔር የራቀው የሰው ልጅ ሁሉ፣ የእግዚአብሔር ታላቅ ቁጣና ፍርድ የዘላለምም የገሃነመ እሳት ቅጣት የሚጠብቀው እንደሆነ በግልጥ ይናገራል፡፡ ይሁን እንጂ ከሚመጣው የእግዚአብሔር ታላቅ ቁጣና ፍርድ ኃጢአተኛው ሰው መዳን ይችል ዘንድ እግዚአብሔር ያዘጋጀውን እውነተኛ የብርሃንና የእውነትን መንገድ - ‹የደስታ ዜና› ወይንም ‹የምስራች› አድርጎ ያቀርበዋል፡፡ አንድ ሰው እራሱን፣ እራሱ በሚሰራው ስራ በፍፁም ማዳን ስለማይችል፣ ደኅንነት በእግዚአብሔር ተዘጋጅቶ ለሰው መምጣቱ ታላቅ የምስራችና ግልፅ መልእክት አይደለምን! ነው እንጂ!

በመሆኑም እግዚአብሔር ሰውን ለማዳን ካለው መልካም ፈቃድና እቅድ የተነሳ ብርሃን የሆነውን እና የሰዎችን ሁሉ ጨለማ ማብራት የሚችለውን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ወደ ምድር በመላክ፡-

ሀ. የብርሃን መልእክቱ ምን እንደሆነ፡፡

ለ. በዚህ በብርሃን መልእክት በኩል ወደ እግዚአብሔር መምጣት እንዴት እንደሚቻል ግልጥ አደረገ፡፡

በጌታ በኢየሱስ በኩልም የመጣው ብርሃኑ ለሰዎች እንዲበራ እራሱ ጌታ ኢየሱስ አስፈላጊ የሆነውን የማዳንን መስዋዕትነት በመስቀል ላይ ከፈለ፡፡ ስለዚህ ኃጢአታቸውን በእውነት ተናዝዘው በእሱ በኩል ወደ እግዚአብሔር የሚመጡት ሙሉ ለሙሉ እንዲድኑ እና የመንግስተ ሰማይ ወራሾች እንዲሆኑ ተደረገ፡፡

የዚህ ገፅ አዘጋጆች ለአንባቢዎች የሚያስተላልፉት መልእክት ይህ ነው፣ እናንተም ወደዚህ የሕይወት ብርሃን፣ ወደ ጌታ ኢየሱስ ብትመጡ እውነተኛና ፍፁም ተስፋ ያላችሁ ትሆናላችሁ፡፡ እኛ እራሳችን ከእግዚአብሔር ዘንድ እርግጠኛ መታረቅን እና እውነተኛ ሰላምንና መንፈሳዊ እረፍትን ያገኘነው በዚህ በጌታ በኢየሱስ ስራ አምነን ነው፡፡ ወደ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በእምነት ቀርባችሁ ኃጢአታችሁን ይቅር በማለት ከእግዚአብሔር ጋር እንዲያስታርቃችሁ በትህትና ጠይቁት እርሱ ብቻ ነው ሊረዳችሁ የሚችለው! ሙሉ ለሙሉ ሊረዳችሁም እሱ ፈቃደኛ ነው፣ ጌታ በፀጋውና በምህረቱ ይርዳችሁ! አሜን፡፡

 

የትርጉም ምንጭ: Lighting Up The Darkness

ለእስልምና መልስ አማርኛ  ዋናው ገጽ