የቁርአን እርስ በእርስ ተቃርኖ

ሙስሊሞች ሁሉ ሲኦል ይሄዳሉን?

Sam Shamoun

ትርጉምና ቅንብር በአዘጋጁ

በዚህ ክፍል የተደረገው ውይይት ያተኮረው ሱረቱ 19.71 ላይ መሠረት በማድረግ ነው፡፡ ክፍሉ ሙስሊሞች በሙሉ ሲዖል ይሄዳሉ ስለሚል የሙስሊም አዋቂዎች የሰጡትን መልስ በማስመልከት የተደረገ ውይይት ነው፡፡  ቁርዓን እስላሞች ሁሉ ሲዖል ይሄዳሉ የሚል ትምህርት በእርግጥ ያስተምራልን? በዚህ መሠረት ጆኬን ካዝ ለሰጠው ቁራናዊ ትንተና ሞይዝ አምጃድ ምላሽን አቅርቧል፡፡ የአምጃድ ምላሽ እንደሚያሳየው ከሆነ በጆኬን ካዝ የተሰጠውን ትንተና የሚያጠናክር እንጂ የሚያፈርስ  ሆኖ አልተገኘም፡፡ ክርክሩ እንደሚከተለው ይነበባል፡፡

አምጃድ እንደሚከተለው በመናገር ነው የጀመረው፡-

ከጽሑፎቹ ውስጥ በአንዱ ጆኬን ካዝ በቁርዓን 19.71 መሠረት እስላሞች ሁሉ ሲዖል ይሄዳሉ ሲል ሌሎች የቁርዓን ክፍሎች ደግሞ ማለትም እንደ 3.157-158 እና 9.111 በጂሃድ ላይ ሕይወታቸውን ያጡ በቀጥታ ገነት እንደሚሄዱ ተናግሯል፡፡ እነዚህም በግልፅ የሚታዩ ተቃርኖዎች ለመሆናቸው ማስረጃዎች ናቸው በማለት (ጆኬን ካዝ) ተናግሯል፡፡ ነገር ግን በቁርዓን 19.71 መሠረት እስላሞች በሙሉ ወደ ሲዖል ይሄዳሉ (ቢያንስ ለጥቂት ጊዜም ቢሆን) ነገር ግን ሌሎች ክፍሎች ደግሞ በጂሃድ የሞቱ እስላሞች ወደ ገነት በቀጥታ ይሄዳሉ ይላሉ፡፡

እነዚህ ተቃርኖዎች ተደርገው የቀረቡት ነጥቦች ላይ አስተያየትን ከመስጠቴ በፊት አንባቢዎቼን ማሳሰብ የምፈልገው ነገር ቢኖር ከሲዖል እሳት ሙሉ ለሙሉ ነፃ እንደሚሆኑ ተስፋ የተገባላቸው በእግዚአብሔር መንገድ ያሉት ሰማዕታት ብቻ ሳይሆኑ አማኞች በሙሉ ከማንኛውም ክፉ ነገር እንደሚጠበቁ ቃል ተገብቶላቸዋል 39.60-61፡፡

እናም በትንሳኤ ቀን እግዚአብሔርን የካዱና የሰደቡትን ፊታቸው ጠቁሮ ታዩአቸዋላችሁ - ምክንያቱም ለደንቆሮዎችና ለማያምኑት ተገቢ የሆነው ቦታ የገሃነም እሳት አይደለምን? እናም እግዚአብሔር ፃድቃንን ያድናቸዋል ምንም ጉዳት አያገኛቸውም እንዲሁም እነሱ በጭራሽ አያዝኑም፡፡ በቁርኣን 29.98-103 መሠረት ሃይማኖተኛው ሰው የሚድነውና የሚጠበቀው ከክፉ ብቻ ሳይሆን ከሚቃጠለው እሳት በሩቅ ሆኖ ነው፡፡ ስለዚህም እነሱ የሚቃጠለውን እሳት አሰቃቂ ድምፅንም እንኳን በፍፁም አይሰሙም፡፡ ጥቅሱም እንደሚከተለው ይነበባል፡- ‹እናንተ ከአላህ ሌላ የምትገዟቸውም (ጣዖታት) የገሃነም ማገዶዎች ናችሁ እናንተ ለርሷ ወራጆች ናችሁ፡፡ እነዚህ (ጣዖታት) አማልክት በነበሩ ኖሮ አይገቡዋትም ነበር ግን ሁሉም በርስዋ ውስጥ ዘውታሪዎች ናቸው፡፡ ለነርሱ በርስዋ ውስጥ መንሰቅሰቅ አላቸው እነርሱም በውስጧ (ምንንም) አይሰሙም፡፡ እነዚያ ከኛ መልካምዋ ቃል ለነርሱ ያለፈችላቸው እነዚያ ከርሷ የተራቁ ናቸው፡፡ ድምጽዋን አይሰሙም እነርሱም ነፍሶቻቸው በሚሹት ነገር ውስጥ ዘውታሪዎች ናቸው፡፡ ታላቁ ድንጋጤ አያስተክዛቸውም መላእክትም ይህ ያ ትቀጠሩበት የነበራችሁት ቀናችሁ ነው እያሉ ይቀበሏቸዋል›፡፡

ስለዚህም ከዚህ በላይ በግልፅ በተጠቀሰው ክፍል ውስጥ እንደምንመለከተው ሃይማኖተኞቹ እግዚአብሔርን የሚፈሩት ፃድቅ ሕዝቦች በፍፁም አይነኩም ወይንም ደግሞ ወደሚያቃጥለው የሲዖል ነበልባል እሳት ጋ በፍፁም አይጠጉም፡፡ ወይንም አይሰጡም፡፡ ስለዚህም ሰማዕታቱን ብቻ ሳይሆን የሚጠቅሰው ወደ ሲዖል የነበልባል እሳት ውስጥ ለመጣል ለማይገባቸው ለሁሉም ነው ስለዚህም እነሱ በሲዖል ውስጥ ከሚኖረው የስቃይ ቅጣት ሙሉ ለሙሉ ነፃ ተደርገዋል፡፡

ከዚህ በላይ ለቀረበው  የተሰጠ መልስ፡-

አምጃድ ከዚህ በላይ የተጠቀሱትን ጥቅሶች በመስጠት ያቀረበው መግለጫ ችግሩን የበለጠ ነው ያሰፋው፡፡ ከዚህ በፊት እንደተናገርነው የጥቅሱ አውድ የሚያሳየው ሲዖል የሚሄዱት የሚለው የሚያጠቃልለው ማንንም ነው ይህም እስላሞችንም ጨምሮ ሁሉም ሲዖል እንደሚገቡ ነው፡፡ ብዙዎቹም የሙስሊም ሊቃውንትና ተንታኞች የሚቀበሉትም ይህንኑ አስተያየት ነው፡፡ ስለዚህም አምጃድ ያቀረባቸው እነዚህ ጥቅሶችም የሚያሳዩት ነገር ቢኖር ጆኬን ካዝ ያቀረበውን እና የቁርዓን ጥቅሶች እርስ በእርስ ይቃረናሉ የሚለውን እውነታ የሚያጠናክር ሆኖ ነው፡፡ ቁርዓን በአንድ ቦታ ‹ሁሉ ሲዖል ይገባሉ› ይላል በሌላ ቦታ ደግሞ አማኞች ከሲዖል ይጠበቃሉ እንዲያውም የስቃዩንም ድምፅ አይሰሙም› ይላል፡፡ ይህ ከፍተኛ እርስ በእርስ መቃረን አይደለምን?

በተጨማሪም ደግሞ በመጀመሪያው ክፍል እንደተገለጠው በ21.98 ላይ ያለው ክፍል በ19.71 ላይ ላለው የአረብኛ ቃል ማለትም ‹ውሩድ› ለሚለው ትርጉም ትክክለኛ መረዳትን እንድናገኝ ፍንጭን ይሰጠናል፡፡ ይህም በ19.71 ላይ ለተገለፀው ትክክለኛ ሲኦል ውስጥ መግባትን የሚያሳይ ሆኖ ነው፡፡ ይህንንም እውነታ አምጃድ እራሱም ተቀብሎታል፡፡ ስለዚህም በኋላ በዚህ ላይ የተናገረው ነገር እንደሚከተለው ነው፡-

አምጃድም ቀጥሎ፡-

የተሰጡትን ማብራሪያዎች በአዕምሮአችን ይዘን አሁን አስፈላጊ የሆኑትን ጥቅሶች ከሱረቱ ማርያም ላይ በጥልቅ እንመልከት እነሱም በካዝ የተጠቀሱት ቁጥሮች 71-72 ናቸው፡፡ እነሱም ቀደም ብለው ከተሰጡት ጥቅሶቻቸው ጋር እንደሚከተለው ከዚህ በታች ሰፍረዋል፡- ‹ሰውም በሞትኩ ጊዜ ወደፊት ሕያው ኾኜ (ከመቃብር) እወጣለሁን? ይላል፡፡ ሰው ከአሁን በፊት ምንም ነገር ያልነበረ ሲኾን እኛ የፈጠርነው መኾኑን አያስታውስምን? በጌታህ እንምላለን ሰይጣናት ጋር በእርግጥ እንሰበስባቸዋለን ከዚያም በገሃነም ዙሪያ የተንበረከኩ ኾነው በእርግጥ እናቀርባቸዋለን፡፡ ከዚያም ከየጭፍሮቹ ሁሉ ከነርሱ ያንን (እርሱ) በአልረሕማን ላይ በድፍረት በጣም ብርቱ የኾነውን እናወጣለን፡፡ ከዚያም እኛ እነዚያን እነሱ በርሷ ለመግባት ተገቢ የኾኑትን እናውቃለን፡፡ ከእናንተም ወደ እርሷ ወራጅ እንጂ አንድም የለም (መውረዱም) ጌታህ የፈረደው ግዴታ ነው፡፡ ከዚያም እነዚያን የተጠነቀቁትን እናድናለን አመጠኞቹንም የተንበረከኩ ኾነው በውስጧ እንተዋቸዋለን፡፡› 19.66-72፡፡

በጥቅሱ ዓውድ ውስጥ በጣም ግልጥ የሆነው ቃላቶቹ ‹ከእናንተም ወደ እርሷ ወራጅ እንጂ አንድም የለም ...› የተነገረው የነቢዩን ጥሪ እምቢ አንቀበልም ላሉት (ለእንቢተኞች) ነው፡፡ በእርግጥ እዚህ ጥቅስ ላይ የሚደረሱት ሰዎች ባለፉት ጥቅሶች ውስጥ ማሳሰቢያና ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸውን እነዚያኑ ሰዎች ነው፡፡ ስለዚህም በትክክለኛው አቅጣጫ ሲታይ የተጠቀሰው የማርያም ምዕራፍ ከሞላ ጎደል በ ምዕራፍ አል-አናቢያ ውስጥ ከተጠቀሱት ጥቅሶች ጋር ተመሳሳይ ትርጉም ነው የሚኖረው፡፡ ስለዚሀም አል-ራዚ ደግሞ የተጠቀሰውን ጥቅስ አስመልክቶ የሚከተለውን ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡ እሱ የጻፈውም፡-

‹እነዚህ ክፍሉ የሚናገርላቸውን አንዳንዶቹ የሚመስላቸው በፊት ካሉት ጥቅሶች ውስጥ የተጠቀሱት እምቢተኞችን ነው የሚል አመለካከት አላቸው፡፡ እነሱም በመጀመሪያ በሦስተኛ መደብ ተነገራቸው ቀጥሎም በሁለተኛ መደብ ተነገራቸው፡፡ የዚህ አመለካከት አራማጆች እንደሚሉት ‹አማኞች የሆኑት ሲዖል እሳት ውስጥ ይገባሉ ብሎ መገመት ትክክል አይደለም ይላሉ፡፡ ይህም የተመሠረተው በመጀመሪያ በቁርዓን በአል-አናቢያ 21.101 በግልፅ እንደሚናገረው ‹እነዚያ ከኛ መልካምዋ ቃል ለነርሱ ያለፈችላቸው እነዚያ ከርሷ የተራቁ ናቸው› ከዚያ ‹የተራቁ› ናቸው ከሲዖል እሳት ስለዚህም የተጠበቁት ከሚገቡት ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃም ደግሞ ቁርዓን የሚናገረው ‹ትንሹንም ድምፁን አይሰሙም› በማለት ነው፡፡ እንዲሁም በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ ቁርዓን የሚናገረው ‹እነሱ በዚያን ቀን ከስቃይ ሁሉ ይጠበቃሉ› በማለት ነው፡፡

ከዚህ ገለፃ ግልጥ እንደሆነው ሁሉ ቁርዓን በማንኛውም መንገድ እውነተኛ አማኝ ሲዖል እሳት ውስጥ ይገባል አይልም፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ፍፃሜ የተነገረው እውነቱ ከተነገረና ካወቁት በኋላ ለሚያምፁና በድንቁርና በትዕቢት ለማይቀበሉት ነው፡፡

ለዚህ የተሰጠ መልስ፡-

አምጃድ በ19.71 ላይ ያቀረበው ትርጉም ማለትም ሲዖል የሚሄዱት መሐመድን የተቃወሙት ናቸው የሚለው አባባል በጣም ግልጥ ነው ይሁን እንጂ በጥቅሱ መሠረት ይህ በፍፁም አያስኬድም ምክንያቱም፡-

ሀ. በመጀመሪያ ደረጃ፡

አር-ራዚ ከሱራ 19 ላይ ሁሉም ሰው ሲዖል ለምን እንደማይገባ የሰጠው ምንም ማስረጃ የለም፡፡ ነገር ግን ‹አማኞች በሙሉ ሲዖል ይገባሉ› ለሚለው በቀላሉ የተጠቀሰው አንዳንድ ሙስሊሞች ይህንን የሚክዱት በሌሎች የቁርዓን ጥቅሶች መሠረት ነው በማለት ነው፡፡ ነገር ግን እኛ በትክክል ያነሳነው ችግር በትክክል ይህ ነው፡፡ ማለትም ስለ ሙስሊሞች መጨረሻ ቁርዓን እራሱን በእራሱ ይቃረናል በማለት ነው፡፡ አንድ ሰው በቀላሉ አማኞች ሲዖል ነው የሚሄዱት የሚለውን ጥቅስ በመካድ ይህ አስተያየት ችግሩን ያቃልለዋል ወይንም ለችግሩ መልስ ይሆናል ማለት አይችልም፡፡ ምክንያቱም እነዚህ የተባሉት ጥቅሶች የሚያስረዱት አንድ እውነት ቢኖር በቁርዓን ውስጥ እጅግ መሠረታዊ የሆነ ስህተት የመኖሩን እውነታ ነው፡፡

ለ. በሁለተኛ ደረጃ፡

በአጠቃለይ አውዱ ላይ የሚደረግ ትክክለኛ መረዳት የሚያሳየው ነገር ቢኖር እጅግ ብዙ ቡድኖች በውስጡ እንዳሉበት ነው፡፡ ለምሳሌ የሚከተለውን እንመልከት፡ ‹ሰውም በሞትኩ ጊዜ ወደፊት ሕያው ኾኜ (ከመቃብር) እወጣለሁን? ይላል፡፡ ሰው ከአሁን በፊት ምንም ነገር ያልነበረ ሲኾን እኛ የፈጠርነው መኾኑን አያስታውስምን? በጌታህ እንምላለን ሰይጣናት ጋር በእርግጥ እንሰበስባቸዋለን ከዚያም በገሃነም ዙሪያ የተንበረከኩ ኾነው በእርግጥ እናቀርባቸዋለን፡፡ ከዚያም ከየጭፍሮቹ ሁሉ ከነርሱ ያንን (እርሱ) በአልረሕማን ላይ በድፍረት በጣም ብርቱ የኾነውን እናወጣለን፡፡ ከዚያም እኛ እነዚያን እነሱ በርሷ ለመግባት ተገቢ የኾኑትን እናውቃለን፡፡ ከእናንተም ወደ እርሷ ወራጅ እንጂ አንድም የለም (መውረዱም) ጌታህ የፈረደው ግዴታ ነው፡፡› 19.66-71፡፡

በዚህ ክፍል ውስጥ በተደራሲዎቹ ላይ ያለውን ለውጥ በጥንቃቄ አስተውሉ፡፡ ክፍሉ የማያምኑትን ሲጠቅስ በጥቅል ስም ‹ሰው› እንዲሁም ‹እነሱ› በሚል ስም ነው፡፡ ከዚያም ሰይጣኖች ቀጥሎም ከሦስተኛ መደብ አጠቃቀስ ወደ ሁለተኛ መደብ ብዙ ቁጥር ወደ እናንተ በመሸጋገር ነው፡፡ በዚህ እንደምናስተውለው የተደራሲዎች አጠቃቀስ ለውጥ፤ ማለትም በአጠቃላይ ተጠቃሾች ላይ ለውጥ መኖሩን በትክክል አያመለክትም፡፡ ነገር ግን አንቀፁ በውይይቱ ውስጥ የተለየ ቡድንን ሲጨምርና ሲጠቅስ ማለትም ሰይጣኖችን ከሚለው የምንረዳው በጉዳዩ ላይ ከአንድ በላይ የሆኑ ሰዎች እየተጠቀሱ እንዳለ ነው፡፡ እዚህም ጋ ሦስት ቡድኖች መኖራቸውን ለመመልከት በጣም ቀላል ነው፡፡ በተለይም የማያምኑት ሰይጣኖች እና አማኞች፣ ስለዚህም ክፍሉ የሚያስረዳው እንዲሁም የሚያመለክተው ነገር፡-

1. የማያምን ሰው ሲዖል ይገባል እዚያም ውስጥ ይቀራል፡፡

2. ሰይጣኖች (ጂኒዎች) ወደ ሲዖል ይወርዳሉ፡፡

3. አማኞችም እንደዚሁ ወደ ሲዖል ይገባሉ (71) ነው፡፡ ነገር ግን በአላህ ምህረት የተነሳ ከዚያ ይወጣሉ (72)፡፡

በመጀመሪያ ሰው፤ በነጠላው የሚለው ወይንም የሚያመለክተው በትንሳኤ የማያምኑትን እና በመካ የነበሩትን አረቦች እንደሆነ ነው፡፡ ያም አማኞችም ይሁኑ የማያምኑትንም ነው፡፡ ከዚያም ክፍሉ የሚሸጋገረው ለማመን በመረጡትና በጥርጥር ለመቆየት በወሰኑት መካከል ነው ይህም ከሞት መነሳት የሚቻል መሆኑን በተመለከተ ነው፡፡ ስለዚህም ክፍሉ የሚከተለውን ለማለት እንደተነሳ መረዳት ይቻላል፡፡

1. ፓጋን አረቦች በአጠቃላይ በአንድ ወቅት ስለ ትንሳኤ ተጠራጥረዋል፡፡

2. አንዳንዶቹ ይህንን ጥርጥር ለማስወገድ መርጠዋል ማለትም እግዚአብሔር ሙታንን ሊያስነሳ እንደሚችል እና ሕይወትን እንደሚሰጥ፡፡

3. ሌሎቹ ደግሞ ባለማመን ለመቆየት መርጠዋል፡፡

4. አላህ የሚያምኑትን ከማያምኑት ይለያል፤ የሚያምኑትን መርጦ የማያምኑትን እዚያ እንዲሰቃዩ ይተዋል፡፡

ሐ. በሦተኛ ደረጃ፡-

ከዚህ በፊት እንደጠቀስነው ብዙዎቹ ሙስሊሞች የ19.71 ‹ሲዖል የሚገቡት ሰዎች› ትርጉም መሐመድን ባልተከተሉት ላይ ብቻ የተወሰነ እንዳልሆነ እንደሚያምኑ ነው፡፡ ማለትም እነሱ የሚያምኑት ማንኛውም ሰው ሲዖል እንደሚገባ ነው፡፡ ይህም የሚያምን ይሁን የማያምን፤ ፃድቅም ይሁን ፃድቅ ያልሆነም ማለት ነው፡፡ እንዲያውም እነዚህ ሙስሊሞች የሚያምኑት ሲዖል መግባት የሚባለው የመሐመድ ጥሪ ለማያምኑት የተወሰነ ብቻ እንዳልሆነ ነው፡፡ ስለዚህም በዓውዱ ውስጥ ሲዖል መግባት ለማያምኑት ብቻ የተወሰነ ለመሆኑ ምንም ማስረጃ የሚሆንን ነገር መመልከት እንዳልቻሉ ነው፡፡

የአምጃድ የራሱ ምንጭም እንኳን ማለትም የአር-ራዚ እምነት የሚያመለክተው ብዙ ሙስሊሞች እንደተስማሙበት የ19.71 የሚያስረዳው ማንኛውም ሰው ሲዖል እንደሚገባ ነው፡፡ የሚከተለውን የአር-ራዚን ትንተና በጥንቃቄ ተመልከቱ፡-

‹አንዳንዶች እንደሚያስቡት በክፍሉ ውስጥ የተደረሱት ተቃዋሚዎች ናቸው፡፡ የሚቀጥለው ጥቅስ እንደሚያመለክተው ... › የአር-ራዚ አንዳንዶች የሚያመለክተው ሁሉም አንድ ዓይነት አመለካከት እንደሌላቸው ነው ማለትም አምጃድ ከሰነዘረው ሐሳብ የተለየ ሐሳብ ያላቸው ሌሎች ሙስሊሞች አሉ ማለት ነው፡፡ የአር-ራዚ አጠቃላይ ትንተና እየተተረጎመ በመሆኑ ሲያልቅ እንዳለ በድረ ገፅ ላይ ለአንባቢዎች እንዲቀርብ ይደረጋል፡፡

መ. በአራተኛ ደረጃ፡

የአምጃድ ጥቅሶች ከሌሎቹ ጥቅሶች ጋር ለማያያዝና የሚያመለክቱትም ጥሪውን የተቃወሙትን ነው ለማለት የተደረገው ሙከራ ሌሎች ችግሮችን አስከትሏል፡፡ ነገር ግን ከቁጥር 71 ቀጥሎ ያለው ጥቅስ የሚለው ‹ከዚያም እነዚያን የተጠነቀቁትን እናድናለን አመጠኞቹንም የተንበረከኩ ኾነው እንተዋቸዋለን› ይላል፡፡ ስለዚህም በዚህ በቁጥር 72 መሠረት አላህ ፃድቅ የነበሩትን እነዚያን ከሲዖል ውስጥ ያወጣቸዋል ማለትም የአምጃድ መረዳት ትክክለኛ ከሆነ፡

1. መሐመድን የተቃወሙት አንዳንዶቹ ፃድቃን ነበሩ ማለት ነው፡፡

2. ወይንም መሐመድን የተቃወሙት ክፉ አድራጊዎቹ ከሲዖል ውስጥ ለመውጣት ዕድል አላቸው ማለት ነው፡፡

3. ይህም ክፉ አድራጊዎቹ ሲዖል ውስጥ እያሉ ልብን የማግኘት ዕድል ያላቸውና ፃድቃን እንደሚሆኑ የሚያመለክት ነው አለበለዚያም እነሱ እንደፃድቃን ሊቆጠሩ አይችሉም ማለት ነው፡፡

4. ይህም ቀጥሎ የሚያሳየው አላህ በሲኦል ውስጥ ለሚኖሩትም እንኳን የንስሐን ዕድል እንደሚሰጣቸው ነው፡፡ ማለትም በምድር በነበሩ ጊዜ መሐመድን ይቃወሙ ለነበሩት ነው፤ ይህም ፃድቃን እንዲሆኑ ዕድል በመስጠት ነው ማለት ነው፡፡

ነገር ግን ይህ የመጨረሻው ሐሳብ የሚከተለውን አንቀፅ ይቃወመዋል ‹ጸጸትንም መቀበል ለነዚያ ኃጢአቶችን ለሚሠሩ አንዳቸውንም ሞት በመጣበት ጊዜ አሁን ተጸጸትኩ ለሚልና ለነዚያም እነርሱ ከሐዲዎች ኾነው ለሚሞቱ አይደለችም፡፡ እነዚያ ለነሱ አሳማሚን ቅጣት አዘጋጅተናል፡፡› 4.18፡፡

አምጃድ ከዚህ በላይ ያሉትን ማጠቃለያ ሐሳቦችን አልቀበልም ማለት አይችልም ምክንያቱም የክፍሉና እሱ የመረጣቸው ትርጉሞች መሠረታዊ ውጤቶች ናቸውና፡፡ አቶ አምጃድ ክፍሉን እንዴት እንተጠቀመበት አስተውሉ፡፡ ‹ከዚያም እኛ ፃድቃንን ከስቃያቸው ሁሉ እናድናቸዋለን ከዚያም ክፉ አድራጊዎቹን ደግሞ እዚያ እንተዋቸዋለን› እንዲሰቃዩ፡፡

የአምጃድ የራሱ ትርጉም አማኞች ሲኦል አይገቡም በማለት ሊያስረዳ አልቻለም ነገር ግን ያረጋገጠው አማኞች ሲዖል ይወርዳሉ ብለን በትክክል የተጠቀሰውን የገለፅነውን የእኛን ሐሳብ ነው፡፡ የራሱም ትርጉም ያረጋገጠው ቁርዓን አማኞች ሲዖል ይወርዳሉ ብሎ ያለውን ነው፡፡ ይህም አምጃድ እዚያ ውስጥ እያሉ ከስቃይ ይድናሉ ብሎ የጠቀሰውም እንኳን ይህንንኑ ነው የሚያስረዳው፡፡ ይህንንም በሌላ መንገድ ለማስቀመጥ ፃድቃንን ወይንም ክፉን ከማድረግ እራሳቸውን የቆጠቡቱ እነዚያ በሲዖል ውስጥ እያሉ ምንም ስቃይ አያጋጥማቸውም የሚለው ሐሳብ ከንቱ ነው ምክንያቱም እነሱ አሁን ያሉት በሲዖል ውስጥ ነውና፡፡ ይህም ያለፉት ሙስሊሞች ሁሉ የሚያምኑት እውነታ ነው፡፡ ስለዚህም አማኞች ይሰቃያሉ ወይንም አይሰቃዩም ከሚለው አመለካከት ውጪ አማኞቹ ሲኦል ውስጥ ለመግባታቸው ምንም ጥርጥር የሌለው ነገር ነው፡፡ የአቶ አምጃድም የትርጉም ሐሳብ እራሱ የሚያመለክተው እውነታ ወይንም የሚመራው መረዳት ሙስሊሞች እራሳቸው በትክክል ሲኦል እንደሚገቡ ነው፡፡ የአምጃድ ምርጥ ትርጉም ‹የአረብኛውም ቃል› እንዲያውም በእርግጥ ወደዚህ ይመጣሉ ‹ዋሪዳሁ ከ ዉሩድ› የሚያመለክተው በትክክል ሲዖል ውሰጥ መግባትን ነው፡፡ አሁንም በ19.71 እንዴት እንተጠቀሙበት አስተውሉ፡፡ ‹እያንዳንዳችሁ በእርግጥ ወደዚህ (እሳት) ትመጣላችሁ ... ...›፡፡

አምጃድ ከክፍሉ እንደተረዳው ሰዎች ወደ እሳቱ ይመጣሉ ከሚለው እኛ የምንለውን (ቁርዓን ሰዎች ሁሉ ሙስሊሞችን ጨምሮ) ወደ ሲዖል ይወርዳሉ የሚለውን ትርጓሜ ነው ያረጋገጠው፡፡ ይህንንም ከተረዳ በኋላ አምጃድ የተገደደው ከዚያ ውስጥ የሚወጡት እና የሚገቡትን ከፃድቃን ለመለየት ነው፡፡ ስለዚህም በእሱ ትርጉም መሠረት ሁለት ቡድኖች አሉ ማለት ነው እንጂ አንድ ቡድን አይደለም፡፡ ይህም ዓይነት ክፍሉን በራሱ ሐሳብ ለማስታረቅ አለመቻሉ ተጨማሪ ችግርን እንደሳበ ወይንም እንደፈጠረ ነው እንጂ ያመጣው ምንም መፍትሄ የለም፡፡

ስለዚህም እንዳለ ነገሩን ስናየው አምጃድ የተቀበለው ነገር ክፍሉ ሰዎች በትክክል ሲዖል ይወርዳሉ ብሎ አንደሚናገር ነው እንጂ አንዳንዶች እንደሚመስላቸው ወይንም እንደሚያስቡት ዝም ብሎ በውስጡ በቀላሉ ያልፋሉ ማለት አይደለም፡፡ ስለዚህም የእሱ የእራሱ አተረጓጎም እንኳን እኛ የምንለውን ወይንም እያልን ያለውን እውነታ ነው የሚያስረዳው፡፡ ይህም የሚያስረዳው የክፍሉ ቀጥታ መረዳት የሚጠቁመው ማንኛውም ሰው ወደ ሲዖል መውረድ እንዳለበት ነው፡፡ ማለትም ማንኛውም ሙስሊም እዚያ ውስጥ የሆነ ጊዜ የግድ ማሳለፍ እንዳለበት ነው፡፡ አቶ አምጃድ ይህንን ግልጥ የሆነውን እውነታ ለመካድ ከፍተኛ ጥረት አድርጓል ነገር ግን ከንቱ ልፋት ነው፡፡

የአዘጋጁ ማሳሰቢያ፡-

አንባቢዎች ሆይ ከዚህ በላይ በቁርዓን 19.71 ላይ የተመሠረተውን ውይይት አስተውላችኋል፡፡ በውይይቱ የሙስሊም ተንታኞች ጥቅሱ የሚለውን እውነታ ለመቀየር ከንቱ ጥረትን እንዳደረጉም ተገንዝባችኋል፡፡ አዎ ቁርዓን ሲዖል ከመግባት ማንም (ሙስሊም) አያመልጥም ነው የሚለው፡፡ ታዲያ የእናንተ ተስፋ ምንድነው? መጽሐፍ ቅዱስ ግን እውነተኛና የተረጋገጠ ተስፋን ይሰጣል፡፡ የአዲስ ኪዳን ወንጌሎች በሙሉ ይህንን የምስራች ነው የሚያሳዩት፡፡ ኃጢአተኛውና ሲዖል የሚገባው ሰው በክርስቶስ የመስዋዕትነት ሞት አምኖ ንስሐ በመግባት እሱን ክርስቶስን ቢታመን መንግስተ ሰማይ የመግባትን እውነተኛ ተስፋ ያገኛል በግል ሕይወቱም እግዚአብሔር በመንፈስ ቅዱስ ይህንን ያረጋግጥለታል፡፡ ይህ እውነት በብዙዎች ሕይወት ውስጥ ታይቷል፡፡ ስለዚህም ዛሬ መጽሐፍ ቅዱስን በማግኘት ከምስራቹ ቃል በመጀመር እንድታነቡ እንጋብዛችኋለን፡፡ እግዚአብሔር ይርዳችሁ አሜን፡፡

 
የትርጉም ምንጭ: Qur'an Contradiction: Will all Muslims go to Hell?

ለእስልምና መልስ አማርኛ  ዋናው ገጽ